የኤርትራን "የግዛት አንድነት ጥሰቶች" በተመለከተ መንግሥት የያዘው "የመታቀብ" አቋም "ሁሌም እንደማይቀጥል" ዶ/ር ጌዲዮን አሳሰቡ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ

የፎቶው ባለመብት, House of Peoples Representatives

ኤርትራ በኢትዮጵያ "ሉዐላዊነት እና የግዛት አንድነት" ላይ የምትፈጽማቸው "ጥሰቶችን" በተመለከተ የፌደራል መንግሥት የያዘው እርምጃ ከመውሰድ "የመታቀብ" አካሄድ "ሁሌም የሚቀጥል እና ገደብ የለሽ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት" የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ተናገሩ።

ዶ/ር ጌዲዮን፤ ኢትዮጵያ "ከኤርትራ መገንጠል በፊት እና በኋላ" በአሰብ ወደብ ላይ "ባፈሰሰችው ከፍተኛ ሀብት ምክንያት"፤ አሰብ በፌደራል መንግሥት "በዋነኛነት ቅድሚያ የሚሰጠው" ጉዳይ እንደሆነ መግለጻቸውም ተዘግቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ይህንን የተናገሩት ትናንት ሐሙስ ኅዳር 4/2018 ዓ.ም. "ሆርን ሪቪው" የተባለው ቲንክ ታንክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ባካሄደው የፖሊሲ ፎረም ላይ ነው።

ዶ/ር ጌዲዮን፤ አምባሳደሮችን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች በታደሙበት በዚህ መድረክ ላይ በአፍሪካ ቀንድ የታዩ ሰሞነኛ ሁኔታዎች በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥትን ፖሊሲ እና ምልከታ አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለጻ በተለይም ያተኮረው በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ላይ ነው። በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለዘመናት የዘለቀው ግጭት መነሻ ከድንበር ውዝግብ ወይም ከባህር በር ፍላጎት የተሻገረ መሆኑን እንዳብራሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ ገጹ ባወጣው የዶ/ር ጌዲዮን ሙሉ ንግግር ላይ ሰፍሯል።

ለግጭቶች ዋነኛ ምክንያት አድርገው ከጠቀሷቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ እንደሚፈጽም ያመለከቱት ጣልቃ ገብነት ነው። "የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አቋም መያዝ፣ ሀሳብ ማቅረብ እና በንቃት የመሳተፍ ጭምር መብት እንዳለው ይሰማዋል" ሲሉ ሙግታቸውን በማሳያ አስደግፈዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የኤርትራ መንግሥት አመራር "ኢትዮጵያ ላይ ጠበኛ ፍላጎት ላላቸው ሁሉም ኃይሎች ራሱን መገልገያ አድርጎ የማቅረብ ዝንባሌ" እንዳለው በማንሳት ወቅሰዋል።

የአገሪቱ አመራር "ለሦስተኛ ወገኖች ቀጠናዊ ተቀጽላ ሆኖ ለመንቀሳቀስ ያለውን ብርቱ ፍላጎት" በመጥቀስም ወንጅለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኤትርትራ ጋር በተያያዘ ያነሱት ሌላኛው ሀሳብ "የኢሳያስ ዶክትሪን" በማለት የጠሩትን ጉዳይ ነው። "ይህ ዶክትሪን፤ የኤርትራ ራሷን በራሷ የምታስተዳድር አገር ሆኖ የመቀጠል ጉዳይ በኢትዮጵያ የፀጥታ መደፍረስ፣ መከፋፈል እና አለመረጋጋት ላይ እንደሚመሰረት ያስባል" ብለዋል።

በዶ/ር ጌዲዮን ገለጻ መሠረት፤ ይህ ዶክትሪን ኤርትራን በኢትዮጵያ ላይ "ተቀጽላ አድርጎ ለመጠቀም" ከሚፈልጉ አካላት "የመነጨ" ነው።

ኤርትራ በኢትዮጵያ "ሉዐላዊነት እና የግዛት አንድነት ላይ ከፍተኛ ትንኮሳ እና ጥሰት" መፈጸሟን ለታዳሚዎች ተናግረዋል።

"በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ የአካባቢ አስተዳደር ክፍሎችን ተቆጣጥረው ይገኛሉ" ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህም ቦታዎች "ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ሉዐላዊ ግዛት ውስጥ የሚወድቁ" መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመድረኩ ታዳሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, በፖሊሲ ፎረሙ ላይ የውጭ አገራት ዲፕሎማቶች፣ ምሁራን እና የፖሊሲ ባለሙያዎች እንደተገኙ ተገልጿል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተጨማሪም የኤርትራ መንግሥት "በመንግሥት ላይ መሳሪያ ላነሱ ቡድኖች የቁሳ ቁስ ድጋፍ በማቅረብ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ" መሆኑን በማንሳት ወንጅለዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን፤ እነዚህ የአሥመራ መንግሥት እንቅስቃሴዎች "ኢትዮጵያ ራሷን የመከላከል ሕጋዊ መብቷን ለማስከበር በቂ መሠረት" እንደሆኑ ተናግረዋል።

ይህም ቢሆን ግን መንግሥት በጉዳዩ ላይ እርምጃ ከመውሰድ "እንደታቀበ" አክለዋል። "ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷና በግዛት አንድነቷ ላይ ከፍተኛ ትንኮሳ እና ጥሰት እየተፈጸመባት ቢሆንም ራሷን የመከላከል ሕጋዊ መብቷን ተግባራዊ ከማድረግ በመታቀብ ላይ ነች" ሲሉ መንግሥት ወስዶታል ያሉትን አቋም አብራርተዋል።

ይህን የአጸፋ ምላሽ ከመስጠት የመታቀብ አቋም "ሁሌም የሚቀጥል እና ገደብ የለሽ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት" አሳስበዋል። ኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ፖሊሲው የሚጸናው "እስከሚችለው ድረስ" ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።

"የቀጠለው የኤርትራ ጠብ ጫሪነት እና ትንኮሳ ከዚህ በላይ መታቀብን ይበልጥ አስቸጋሪ እያደረገው ነው" ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትናንቱ መድረክ ላይ ስለ ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት እንዳነሱም የመስሪያ ቤታቸው መረጃ ያሳያል። ዶ/ር ጌዲዮን፤ የባህር በር "ለኢትዮጵያ የኅልውና ጉዳይ" መሆኑን እንዲሁም "ከ130 ሚሊዮን በላይ" የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ "ዘላቂ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ ባሕር እንደሚያስፈልገው" በመጥቀስ ከዚህ ቀደም በመንግሥት ባለስልጣናት የተነሱ ሀሳቦችን በድጋሚ አንጸባርቀዋል።

በተጨማሪም ዶ/ር ጌድዮን አሰብ ወደብ በኢትዮጵያ መንግሥት "በዋነኛነት ቅድሚያ የሚሰጠው" ጉዳይ መሆኑን እንደተናገሩ መድረኩን ባዘጋጀው 'ሆርን ሪቪው' ድረ ገጽ በወጣው የውይይቱ ጭምቅ ሃሳብ ላይ ሰፍሯል። መንግሥት ይህንን አቋም የያዘው የአሰብ ወደብን በተመለከተ የተፈጸሙ "ታሪካዊ እና ሕጋዊ" ስህተቶችን "ለማረም" ካለፈው ፍላጎት የመነጨ ብቻ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በመድረኩ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

ኢትዮጵያ "ከኤርትራ መገንጠል በፊት እና በኋላ [በወደቡ ላይ] በከፍተኛ መጠን ሀብት ማፍሰሷ" የአሰብ ወደብን "ቅድሚያ የሚሰጠው" ጉዳይ ለማድረጓ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል ተብሏል። ከኢትዮጵያ "አስገዳጅ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ ዴሞግራፊያዊ እውነታዎች እና ታሪካዊ ሁኔታዎች" የተነሳ መንግሥት የሚያነሳው የባህር በር ፍላጎት "ፍትሐዊ፣ ምክንያታዊ እና ቅቡልነት ያለው" እንደሆነ አስምረውበታል።

ዶ/ር ጌዲዮን፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው "ውጥረት ሊፈታ የሚችለው" በሁለቱ አገራት መካከል በሚደረግ "ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት" በመፍጠር ነው የሚል አቋማቸውን በገለጻቸው አቅርበዋል። የኢትዮጵያ "ዘላቂ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ" የባህር በር የማግኘት ፍላጎትም በዚህ አካሄድ መፍትሔ እንደሚያገኝ አስረድተዋል።

"ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን በዘላቂነት እና ደህንነቱ በተጠበቀ" መልኬ ለማግኘት የሚያስችላትን "ሌሎች አማራጭ መንገዶችን ለመመልከት ዝግጁ" መሆኗን ተናግረዋል። ይህ አይነቱ አማራጭ "የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ ፍላጎት የሚያሟላ እና ለኤርትራም ጠቃሚ" እንደሚሆን አክለዋል።

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የሚታየውን መካረር ለመፍታት የሚደረግ የዲፕሎማሲ ስራ የሚከሽፍ ከሆነ ቀጣዩ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እንደቀረበላቸው የሆርን ሪቪው መረጃ አመልክቷል። ዶ/ር ጌዲዮን ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት "በማንኛውም መንገድ ጦርነትን ለማስወገድ ቁርጠኛ መሆኑን" በአጽንኦት እንዳነሱ ተጠቅሷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማብራሪያቸውን ባቀረቡበት ጊዜም፤ "መላው [የአፍሪካ ቀንድ] ቀጣና ካለበት ደካማ ሁኔታ አንጻር ሌላ ዙር ጦርነት አውዳሚ ይሆናል" ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለኤርትራ የአጸፋ ምላሽ ከመስጠት "የተቆጠበውም" ከዚህ የተነሳ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሁለቱን አገራት የወደፊት እጣ ፋንታ ለመቀየር ለሚደረግ "ንግግር ዝግጁ" መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ጌዲዮን፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በኤርትራ ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

"የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የሚፈፅመውን ትንኮሳ እና ጥሰት አቁሞ በቅን ልቦና ውይይት እንዲያደርግ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ እና እንዲያበረታታ ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።