"ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ህወሓት የፈጸማቸው ትንኮሳዎች ወደ ጦርነት ለመግባት ከበቂ በላይ ናቸው" ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force

የምስሉ መግለጫ, ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የፈፀማቸው ድርጊቶች ወደ ጦርነት ለመግባት ከበቂ በላይ ምክንያቶች እንደሆኑ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

ኤታማዦር ሹሙ ከአምስት ዓመት በፊት በትግራይ ውስጥ በነበረው የአገሪቱ ጦር ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለመዘከር ሰኞ ጥቅምት 24/1018 ዓ.ም. በተካሄደ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር በህወሓት ላይ ክሶችን ሰንዝረዋል።

"ህወሓት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የሠራቸው ትንኮሳዎች፣ ሥራዎች እና ሴራዎች ወደ ጦርነት ለመግባት በቂ ናቸው፤ ከበቂም በላይ" ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ።

ለዚህም 'ጽምዶ' የተባለ ቡድን ማቋቋምን፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ አለመፍቀድን፣ ሠራዊት ማሠልጠንን እንዲሁም በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን [ፋኖ] ድጋፍ ማድረግን በምሳሌነት ዘርዝረዋል።

"ከሻዕቢያ ጋር ጽምዶ ብሎ ድንበር ሰብሮ መሄድ፤ እኔን ተሸክሞ ካልገባ ተፈናቃይ አለቅም ማለት፣ ኃይል ማሠልጠን ፣ ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የተደረጉ የትግራይ ተዋጊዎችን [ዲዲአር] መመለስ፣ ለፋኖ ዕቅድ እና ጥይት ሰጥቶ ኢትዮጵያን እንዲበጠብጥ፣ አማራ ክልልን እንዲበጠበጥ መላክ ፀረ ሕገ መንግሥትም፤ ፀረ ፕሪቶሪያም ነው" ብለዋል።

"ህወሓት ጉዳት እያደረሰ ቢሆንም ጦርነት ቢመጣ የበለጠ ጉዳት ይመጣል፤ በጊዜ ሒደት ቀልብ የሚገዛ ሰው ይፈጠራል" በሚል መንግሥት ዝምታን መምረጡንም አስረድተዋል።

ከአምስት ዓመታት በፊት የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀሙት ድንገተኛ ጥቃት ለሁለት ዓመታት ለተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት መቀስቀስ እንደዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል።

ጦርነቱ በትግራይ ክልል ውስጥ በጀመርም ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ ከባድ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከሦስት ዓመታት በፊት የተደረሰው የፕሪቶሪያው ስምምነት ይህንን ደም አፋሳሽ ጦርነት ማስቆም የቻለ ቢሆንም በአፈፃፀሙ ላይ የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት እርስ በእርስ ይካሰሳሉ።

ሕጋዊነቱ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሓት እሑድ ጥቅምት 23/2018 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት "ሌላ ዙር ጦርነት ለማካሄድ ግልጽ እንቅስቃሴ" እያደረገ ነው ሲል ከስሶ፤ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን እንቅስቃሴ እንዲያስቆም አሳስቧል።

ህወሓት የዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነቱ አንዱ ፈራሚ ሲሆን በፕሪቶሪያ ስምምነት አካማኝነት መፈጸም የነበረባቸው ተግባራት ተፈጻሚ አለመሆናቸውን በመግለጫው አንስቷል።

ከባድ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ያስከተለውን ጦርነት ለማስቆም ከሦስት ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተፈረመው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሳይሆን በዚህ ሳምንት ሦስት ዓመት ሆኗታል።

ህወሓት ባወጣው መግለጫ ጦርነቱ በስምምነቱ አማካኝነት ይቁም እንጂ "በዝምታ [ከሚካሄድ] ዘር ማጥፋት ጋር ቀጥሎ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል" ብሏል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለመዘከር በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ለዘመናት የትግራይ ሕዝብን ለመጠበቅ ሰፍሮ በነበረው ሠራዊት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት "አሳፋሪ ክህደት እና የታሪክ ጠባሳ" ሲሉ ገልጸውታል።

አክለውም ህወሓት በጦርነቱ ወቅት "የዘር ጭፍጨፋ ፈፅሞብኛል" በማለት ሲከሰው ከነበረው አካል [ሻዕቢያ] ጋር ጥምረት ፈጥሮ መሥራቱ የክህደቱ ሌላ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

"ሰሜን ዕዝ ትግራይ የገባው ባድመ ፣ ዛላምበሳ እና ጾረና ላይ ሆኖ የትግራይን ሕዝብ ከሻዕቢያ ለመከላከል ነው" ሲሉ በማስታወስም በራሱ ወገን መከዳቱን ገልጸዋል።

"ይህ ኃይል ክህደቱን ከጀመረ 50 ዓመቱ ነው። ግብፆች ሻዕቢያን ቀጥረው፣ ሻዕቢያ ደግሞ እርሱን ቀጥሮ ኢትዮጵያን ወግቶ የባሕር በር ያሳጣን እና አገር ያስገነጠለ ከሃዲ ነው" ብለውታል።

ኤታማሾር ሹሙ ንግግራቸው "የተወሰኑ ቡድኖች" እንጂ የትግራይ ሕዝብን እና አጠቃላይ የህወሓት አባላትን እንደማይመለከትም አፅንኦት ሰጥተዋል።

"ካሁን በኋላም የትግራይን እናት እናስለቅሳለን በሚል እየሠሩ ስለሆነ የትግራይ ሕዝብ ራሱን ነጻ ማውጣት አለበት። 'የህወሓት ጉጅሌ' የትግራይን ሕዝብ ዕጣ ፈንታ መወሰን የለበትም" ብለዋል ኢታማዦር ሹሙ።

በአንድ ወገን ብቻ ጦርነትን ማስቀረት እንደማይቻል የገለጹት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ "በብሔራዊ ጥቅማችን፣ በሰላማችን ከመጣ እና ድንበራችንን ካለፈ መዋጋት አለብን፤ የተደራጀነውም የታጠቅነውም ለዚያ ነው" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

መስከረም ወር መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤርትራ መንግሥት እና ህወሓት "ጽምዶ" በሚል ጥምረት ኢትዮጵያ ላይ "ጦርነት ለመክፈት" እየሠሩ ነው ሲል ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ከስሷል።

ህወሓት በበኩሉ በህወሓት እና በትግራይ ሕዝብ ላይ የተሳሳተ እና ፖለቲካ ዓላማ ያዘለ ከስ ተሰንዝሮብኛል ሲል በጻፈው ደብዳቤ የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀልም ኢትዮጵያ የላከችውን ደብዳቤ "ድፍረት የተሞላውና እጅግ አሳሳች" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ተችተዋል።

ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ ነው በሚል በተደጋጋሚ ማንሳቷ ከኤርትራ ጋር ያለውን ውጥረት ያባባሰው ሲሆን፣ በትግራይ የህወሓት ኃይሎች ክፍፍል እና አንደኛው የህወሓት ቡድን ከኤርትራ ኃይሎች ትብብር እንዳለው ከተገለጸ ወዲህ ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።