በዋግ ኽምራ ዞን ካምፕ ውስጥ በነበሩ ሚሊሻዎች ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ 36 ሰዎች ተገደሉ

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር የሚገኘው ጻግብጂ ወረዳ ሚሊሻዎች

የፎቶው ባለመብት, Sehala Woreda Communication

የምስሉ መግለጫ, በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር የሚገኘው ጻግብጂ ወረዳ ሚሊሻዎች

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስብሰባ ላይ በነበሩ የሚሊሻ አባላት ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸውን አንድ የሰሃላ ሰየምት ወረዳ አመራር፣ የጤና ባለሙያ እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በጥቃቱ 16 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም ካምፑ እና በውስጡ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች እንደወደሙ የወረዳ አመራሩ አስታውቀዋል።

በአካባቢው የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አዛዦች ጥቃቱ የተፈጸመው "በስህተት" እንደሆነ መናገራቸውን የወረዳ አመራሩ እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ሐሙስ ጥር 7/2018 ዓ.ም. ጠዋት ላይ የድሮን ጥቃት የተፈጸመው በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፤ ሰሃላ ሰየምት ወረዳ በሚገኝ የሚሊሻዎች ካምፕ ላይ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት ምንጮች ተናግረዋል።

የወረዳው ማዕከል ከሆነችው 'መሻሃ' ንዑስ ከተማ ወጣ ብሎ 'ሰፋ ድልድይ' በተባለ አካባቢ የሚገኘው ይህ ካምፕ፤ ከትግራይ ጦርነት አንስቶ የሚሊሻዎች ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱን ነዋሪዎች አስረድተዋል።

ካምፑ የትጥቅ ማከማቻ እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎች ማረፊያ እና መመገቢያ እንደሆነም አክለዋል። ነዋሪዎች እንደሚናገሩት፤ ካምፑን ማዕከላቸው ያደረጉት የሚሊሻ አባላት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ኃይሎች "ወደ ወረዳው እንዳይገቡ ጥበቃ" ያደርጋሉ።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰዓት የሚሊሻ አባላቱ ከካምፑ ፊት ለፊት ከሚገኝ ሜዳ ላይ በአዛዣቸው "ስምሪት እየተሰጣቸው እና ቁርስ እየተመገቡ" እንደነበር የወረዳ አመራሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል። ሦስት የወረዳው ነዋሪዎችም ሚሊሻዎቹ ቁርስ እና ስብሰባ ላይ እንደነበሩ አረጋግጠዋል።

በዕለቱ የፋኖ ኃይሎች "በአካባቢው ሚሊሻ ላይ ጥቃት ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ" ነበር የሚሉት እኚህ የወረዳው አመራር፤ የሚሊሻ አባላቱም ታጣቂዎቹ ላይ ለሚወሰድ እርምጃ "እየተዘጋጁ" እንደነበር ገልጸዋል። "ሁኔታዎች እየተጫጫኑ ሲመጡ መከላከያ እንዲመጣ" ተጠይቆ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

ነዋሪዎቹ እና አመራሩ እንደሚናገሩት አስቀድሞ ባሉት ቀናት የድሮን ቅኝት ሲደረግ ነበር። ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊትም አንድ ጊዜ በአካባቢው ድሮን ሲዞር ታይቷል።

የድሮኑ መታየት በሚሊሻዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም "በወገን ላይ ጥቃት አይፈጽምም" የሚል መተማመን እንደነበረ ነዋሪዎቹ አስረድተዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የወረዳው አመራርም ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል።

አመራሩ "ስምሪት ለመስጠት፣ ወደላይ ካለው ኃይል ጋር ለማስተሳሰር እየተነጋገርን ባለንበት ሰዓት 'ድሮን መጣ' ተባለ። 'ምንድነው ድሮን?' ስንል፤ 'ድሮን እየዞረች ነው' ተባለ። 'እየቃኘች ይሆናል' አልን። ምንም ባልጠበቅነው ሰዓት፤ 30 ደቂቃ አይሞላም ተመልሶ [መጥቶ] መታ" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ አብራርተዋል።

እንደ አመራሩ ገለጻ፤ በዚህ የድሮን ጥቃት "36 ሰዎች" መገደላቸው ተረጋግጧል። "16 ሰዎች" ላይ ጉዳት እንደደረሰ እና አራት ሰዎች "ሁኔታቸው እንዳልታወቀ" አስረድተዋል።

"[ካምፑ] በአጠቃላይ በሙሉ ወድሟል። ብዙ መሳሪያዎች ተቃጥለዋል። አጠቃላይ የሎጂስቲክስ ሥራዎች፣ ተተኳሽ እዚያው ነበረ። ሩቅ ስለሆነ እዚያ ስለማናደርስ ጥቅል ተተኳሽ የሚባል፣ ለግንባር የሚሆን ተተኳሽ የሚባል፣ የቡድን መሳሪያዎች ብዙ ቦታ ተቃጥሎ ነው የቀረው" ሲሉ በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ዘርዝረዋል።

ድሮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁለት የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው "38 ሰዎች" መሞታቸውን እና በጥቃቱ የተገደሉት "በሙሉ የሚሊሻ አባላት" እንደሆኑ ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አምቡላንስ ይዘው ተጎጂዎች መጀመሪያ ወደተወሰዱበት ጤና ጣቢያ ያመሩ አንድ የጤና ባለሙያ ደግሞ፤ 10 ሕይወታቸው ያለፈ እንዲሁም ዘጠኝ የቆሰሉ ሰዎችን ወደ የሚሠሩበት የጤና ተቋም ይዘው መምጣታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያው "[አስሩ] ከሞቱ በኋላ ነው እኛ ጋር የመጡት። እኛ ደርሶ የሞተው አንድ ነው። እዚያ ድልድይ ሄደን ነበር። ከድልድይ ይዘን እየመጣን አንዱ አረፈ። አንዱ ደግሞ እኛ ጋር ገብቶ [ሪፈር] ከላክን በኋላ መንገድ ላይ አረፈ" ብለዋል።

የጤና ባለሙያው እንደሚያስረዱት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ወደ ጤና ተቋሙ የተወሰዱት "ከሞት በኋላ የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት (postmortem care)" እንዲያገኙ እና "ሰው እስከሚረጋጋ" ድረስ ነው።

ወደ ጤና ተቋሙ እየተወሰዱ ሳለ ሕይወታቸው ያለፈው "ለሚሊሻዎቹ ስምሪት ሲሰጡ የነበሩት የግንባር መሪው አቶ ደሳለኝ ልብስነው" መሆናቸውም ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ደግሞ በካምፑ ምግብ የሚያበስሉ ሁለት ሴቶች እና አንድ ሕጻን እንደሚገኙበትም ገልጸዋል። የጤና ባለሙያው በበኩላቸው በሁለቱ ሴቶች እና ሕጻን ልጅ ላይ ደረሰው ጉዳት "ቀላል" የሚባል እንደሆነ አክለዋል።

ከሞቱት በተጨማሪ ሌሎች ሚሊሻዎች "ከባድ ጉዳት" እንደደረሰባቸው የሚናገሩት የጤና ባለሙያው፤ ሦስት ሰዎች ለተሻለ ሕክምና ወደ ሰቆጣ እና ደሴ ከተሞች መላካቸውን ጠቅሰዋል።

ጤና ባለሙያው የሞቱ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ሲያስረዱ፤ "አብዛኞቹ እዚያው እንደተቀበሩ ነው የሰማነው። እኛ ጋር የመጡት ብዙዎቹ በጣም የተጎዱ ናቸው" ብለዋል።

ሦስት የወረዳው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ "አስከሬናቸውን መለየት ያልተቻለ ከ20 በላይ ሰዎች" የቀብር ሥነ ሥርዓት የተከናወነው ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ነው።

"ከ10 በላይ" ዘመድ የሆኑ እና የሚያውቃቸው ሰዎች መገደላቸውን የሚናገር አንድ ነዋሪ፤ "[ማንነታቸው] የተለዩት ቀብራቸው ተፈጽሟል። ያልተለየው አንድ ላይ ተለቅሞ ነው የተቀበረው" ብሏል።

ሰሃላ ሰየምት ወረዳ

የፎቶው ባለመብት, Sehala Woreda Communication

በዚህ ጥቃት ቢያንስ "አራት የአክስ፣ አጎት ልጅ" እንደተገደሉበት የሚገልጽ ሌላ ነዋሪ ደግሞ "አስከሬኑ የተቃጠለው ባለበት እዚያው ግንባር ላይ 20 ገደማ ሰው ነው የተቀበረው። [ማንነት መለየት] አይቻልም፤ ክሰል ነው አብዛኛው። ጋንታው ላይ የነበሩ ሰዎች ስለሚታወቁ ነው እንጂ አብዛኛው አይለይም" ሲል የደረሰውን የጉዳት ሁኔታ አስረድቷል።

ሌሎች አስከሬኖች ሚሊሻዎቹ ወደመጡባቸው የወረዳው ቀበሌዎች መወሰዳቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። አርብ ጥር 08/2018 ዓ.ም. በወረዳው ዋና ከተማ መሻሃ የተከናወነ የቀብር ሥነ ሥርዓት መኖሩንም አስረድተዋል።

በዚህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የመከላከያ ሠራዊት አዛዥ እና የዞኑ አመራሮች እንደተገኙ አንድ ቀብሩ ላይ የተገኘ አንድ ነዋሪ አስረድቷል።

የመከላከያ ሠራዊት አዛዡ "ይቅርታ፤ ስህተት ተፈጥሯል። የሟች ቤተሰቦችንም፣ የሟች ልጆችንም፣ ዞኑንም እናግዛለን። ለተፈጠረው ነገር ይቅርታ" ማለታቸውን ተናግሯል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የወረዳ አመራርም፤ የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው "በስህተት" ስለመሆኑ የመከላከያ ሠራዊት አዛዦች ለወረዳው ኃላፊዎች መግለጻቸውን አረጋግጠዋል።

"ማብራሪያ ተሰጥቷል። እነሱ እያሉት ያለው 'ስህተት' የሚል ነው። […] እዚህ ያለ ጄነራል መጥቶ ነበር። ዛሬ የተሰጠው ማብራሪያ በስህተት የመጣ መሆኑን ነው የሚያስረዳው" ሲሉ በአካባቢው በሚገኙ መከላከያ ሠራዊት አዛዥ የተሰጠውን ገለጻ ጠቅሰዋል።

የወረዳ አመራሩ ግን 'በምን ዓይነት መልኩ ስህተት ተፈጸመ?' የሚለው ላይ ጥያቄዎች እንዳሏቸው አልሸገጉም።

"ስህተት ዝም ብሎ ስህተት አይደለም" የሚሉት አመራሩ፤ "ቦታው ሳይጠና፣ ሳይታወቅ 'ማን [ጥቃቱን] አዘዘው?' የሚለው ለእኛ ጥያቄ ነው" ብለዋል።

"[ድሮኑን] የላከው ሰው መጠየቅ መቻል አለበት። ግለሰቡ መለየት አለበት። ነገም ለመንግሥት ታማኝነት ይህንን ነው የምንፈልገው። ከዚያ ውጪ 'በስህተት ነው' የሚል ማስተባበያ የእኛ ግምገማ አይደለም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ቢቢሲ በአካባቢው ስለደረሰው ጥቃት የመከላከያ ሠራዊትን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ስለተፈጸመው ጥቃት "መረጃ እንደሌላቸው" የገለጹት የመከላከያ ሠራዊት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ኮሎኔል ቢረሳው ሽፈራው፤ "ከሚመለከታቸው የበላይ አካላት" መረጃ አሰባስበው ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።