ቻይናዊቷ 'አሳማ የሚያርድልኝ' ብላ በማኅበራዊ ሚዲያ ያቀረበችውን ጥያቄ ተከትሎ ሺህዎች ወደ መንደሯ ጎረፉ

ዳይዳይ

የፎቶው ባለመብት, Jimu News

ዳይዳይ አባቷ በእርጅና ምክንያት ለቻይና አዲስ ዓመት ዝግጅት እንደማኅበረሰቡ ወግ ሁለት አሳማዎችን ለማረድ አቅም እንደሌላቸው ስትገነዘብ ፊቷን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ዞረች።

አባቷ መጥፎ ስሜት እንዲሰማቸው አልፈለገችም።

"ማንም ሊረዳኝ ይችላል?" ስትል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ዱዪን በተሰኘው የቻይና ቲክቶክ ጥያቄዋን አቀረበች። "አባቴ አርጅቷል። እነዚህን አሳማዎች መቋቋም እንደማይችል አስባለሁ" ስትል አከለች።

በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው ዳይዳይ ሊረዷቸው ወደ መንደራቸው ኪንግፉ የሚመጡ ሰዎች የአሳማ ስጋ ጥብስ እንደሚጋበዙ ቃል ገብታለች።

በገጠርማ ሲቹዋን እና ቾንግኪንግ ምግብ የማኅበረሰቡ የባህል ትልቅ አካል ነው። ሁለት ጊዜ የበሰለ የአሳማ ሥጋ፣ የተጠበሰ የጎድን አጥንት፣ ሾርባ እና በቤት ውስጥ የተሰራ መጠጥ መቅረብ ይኖርበታል።

"በመንደራችን አንገቴን ቀና አድርጌ ልሂድ" ስትልም አከለች።

የእርዳታ ጥሪዋ ከአንድ ሚሊዮን በላይ 'ላይክ' ሲያገኝ፤ ድጋፋቸውን ለመግለጽ ወደ መንደሯ በሺህዎች የሚቆጠሩ መኪኖች ጎርፈዋል።

ብዙዎችም በደቡብ ምዕራብ ቻይና በምትገኘዋ ቾንግኪንግ የትራፊክ መጨናነቅ መከሰቱን ጠቁመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የድሮን ምስሎች ወደ ኪንግፉ ለመግባት የሚጓዙ እና በግራና እና በቀኝ የሩዝ እርሻ መሀል ባለው መንገድ የሚጓዙ መኪናዎችን አሳይተዋል። አንዳንዶች የትራፍፊክ መጨናነቁን ለማለፍ ረዥም መንገድ በእግር ለመጓዝ መርጠዋል።

ዳይዳይ ወደ አካባቢው የሚመጡ አሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ በተለይም ከከተማ የሚመጡት በገጠር ያለውን ሁኔታ ስለማያውቁ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጻለች።

"ድባቡ በጣም ጥሩ ነበር። ቤተሰቤ አሳማዎችን የሚያረቡበትን የልጅነት ጊዜዬን አስታውሶኛኝ። እንደዚህ ዓይነት ነገር ከተሰማኝ ዓመታት አልፈዋል" ሲል ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ መኪና ነድቶ የደረሰ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከመላው አገሪቱ የመጡ የመኪና ሰሌዳዎችን መመልከቱንም አስታውቋል።

የአሳማ እርዱ እና ቀጥሎ የነበረውን ግብዣ ከ100 ሺህ በላይ ተመልካቾች በቀጥታ የተከታተሉት ሲሆን 20 ሚሊዮን ላይኮችን አግኝቷል። የአካባቢው ባላሥልጠናትም አጋጣሚውን የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ ተጠቅመውበታል።

የመጡትን እንግዶች ለማስተናገድ ሁለት አሳማዎች በቂ ባለመሆናቸው የቱሪዝም ባለሥልጣናት ተጨማሪ አሳማዎችን ለግሰዋል። አነስተኛ ምግብ ቤቶች ከቤት ውጭ የመቀመጫ ቦታዎች በማዘጋጀት ለብዙ ጎብኚዎች አገልግሎት ሲሰጡ ታይተዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን አንድ ትንሽ ነገር ምን ያህል በፍጥነት ግዙፍ ነገር ሊሆን እንደሚችል ያሳየ አጋጣሚ ሆኗል።

ዳይዳይ ለቻይና መገናኛ ብዙኃን "ምናልባትም አስራ ሁለት ገደማ ሰዎች ይመጣሉ ብዬ አስቤ ነበር። ነገር ግን ለመቁጠር በጣም ብዙ ነበሩ" ብላለች።

የቻይናውያን ከማኅበረሰቡ የባህል ዝግጅቶች ጋር እንደገና ለመገናኘት ባላቸው ፍላጎት እና ሕይወት ከባድ በሚሆንበት አጋጣሚ አዎንታዊ ተሞክሮዎችን የማግኘት ፍላጎት የፈጠረው ምላሽ እንደሆነ ተነግሯል።

ዳይዳይ ነገሮች በምን ያህል በፍጥነት እንደተቀየሩ ማመን አልቻለችም። ባለፈው አርብ ጥያቄዋን ለጠፈች። ምላሹ በጣም ትልቅ ስለነበር በመንደሩ ብዙ ሰው ሊኖር እንደሚችል ለማስጠንቀቅ ቅዳሜ ወደ ፖሊስ ሄዳ ሁኔታውን በማስረዳት ተጨማሪ ፖሊሶች እንዲመደቡ አደረገች።

ድግሱ ለሁለት ቀናት ተከናውኗል። በመጀመሪያው ቀን አንድ ሺህ በሁለተኛው ቀን ደግሞ ሁለት ሺህ ሰዎች ተስተናግደዋል። ምሽት ድረስ በቀጠለው ድግስ የእሳት ዳር ጨዋታ እና ባንድ ሙዚቃም ነበር።

በመጨረሻም ዳይዳይ ክብረ በዓሉ ማብቃቱን ገልጻ ተጨማሪ ጎብኚዎች መንደሩን አንዲጎበኙ ነገር ግን ወደ ቤቷ እንዳይመጡ ጠይቃለች። በሁለት ቀናት ውስት ለአራት ሰዓታት ብቻ ከተኛች በኋላ ደክሟት እንደነበር ተናግራለች።

ሆኖም አጋጣሚው ለእሷ እና ለመንደሯ አስደናቂ ጊዜ ነበር።

ጥሪዋን ለተቀበሉት እንግዶች "ያልናንተ ተሳትፎ እንዲህ አይነት ድግስ አይኖርም ነበር" ስትል ተናግራለች።

"ለመጡ ሁሉ፣ ስሜቱ እንደ ትልቅ ቤተሰብ ነበር። በጣም ሞቅ ያለ፣ በእውነት የሚያድን እና በጣም ትርጉም ያለው ነበር።"

እንዲህ ያለ ድንገተኛ ክብረ በዓል እንዲካሄድ ለተባበሩት የመንግስት ባለሥልጣናት እና ለፖሊስ ምስጋናዋን አቅርባለች።

በዚህ አጋጣሚ ለዕውቅና በቃው የሄቹዋን ክልል አጋጣሚውን ወደ መደበኛ ዝግጅት ለመቀየር እንደሚሞክር እየተገለጸ ይገኛል።

አንድ የመንደሩ ነዋሪ "እዚህ ጎረቤቶች እርስ በርስ ይረዳዳሉ። ዛሬ የእናንተን አሳማ ለማረድ ልረዳችሁ እችላለሁ፣ ነገ ደግሞ የእኔን ለማረድ ትመጣላችሁ" ሲሉ ለፒፕልስ ዴይሊ ተናግረዋል።

"አባቴ በጣም ደስተኛ ነው። ይህን ብዙ ሰዎች ሲመጡ ሲያይ ከሌሎች የመንደሩ ነዋሪዎች ጠረጴዛዎችን እና ወንበሮችን መበደር ነበረበት። እንደዚህ አይነት ነገር አጋጥሞን አያውቅም" ስትል ዳይዳይ አባቷን በተመለከተ ተናግራለች።