ትራምፕ ግብፅ እና ኢትዮጵያን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ዳግም ለማደራደር ደብዳቤ ጻፉ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የገባችበትን ውዝግብ ለመፍታት ዳግም ለማደራደር ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ።
ዶናልድ ትራምፕ ለግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ በጻፉት ደብዳቤ ላይ አገራቸው በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የጀመረችውን የማሸማገል ጥረት መቀጠል እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ አርብ ጥር 8/2018 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ላይ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረስ ለሰጡት "ውጤታማ አመራር" አድንቀዋቸዋል።
ግብፅ ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. በኋላ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የቀጠናው ደኅንነት እና ሰብዓዊ ቀውስ በመፍታት በኩል ለነበራት ሚና ምሥጋናቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ "ባለን የግል ወዳጅነት መንፈስ እና አሜሪካ ለግብፅ ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ባላት ቁርጠኝነት፣ በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን 'የአባይን ውሃ መጋራት' ጥያቄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በኃላፊነት መንፈስ ለመፍታት አደራዳሪነቷን ዳግም ለመጀመር ዝግጁ ነኝ " ሲሉ ትራምፕ በደብዳቤው ላይ አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግንባታን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከሱዳን እና ግብፅ ጋር አለመግባበት ውስጥ ቆይታለች።
ግብፅ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ላለፉት አስራ አራት ዓመታት በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ አጠናቅቃ ያስመረቀችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከ5000 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌትሪክ ኃይል ያመነጫል።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሦስቱን አገራት ማደራደር ጀምረው ተከታታይ ውይይት የተደረገ ቢሆንም በወሳኝ ነጥቦች ላይ ከስምምነት ሳይደረስ መቅረቱ ይታወሳል።
ግብፅ እና ሱዳን በተደጋጋሚ በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የገነባችው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በምሥራቅ የናይልተፋሰስ አገራት ላይ ዘላቂ ስጋት ደቅኗል ሲሉ ይናገራሉ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሁን በጻፉት ደብዳቤ ላይ አገራቸው በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለበርካታ ዓመታት ባለመግባባት ውስጥ የቆዩትን አገራት ጉዳይ ለመፍታት ያላትን ፍላጎት በመግለጽ "በዚህ ቀጠና የትኛውም አገር የአባይን ውድ ሃብት በተናጠል መቆጣጠር እና በሂደቱ ጎረቤቶቹን መበደል የለበትም" ሲሉ አስፍረዋል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባጋሩት በዚህ ደብዳቤ ላይ "ቡድኔ እና እኔ የአባይ ወንዝ ለግብፅ እና ለሕዝቧ ያለውን ጥቅም እንረዳለን" ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በተደጋጋሞ ስምንት የዓለም ጦርነቶችን ማስቆማቸውን እና ከእነዚህም መካከል አንዱ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ሊካሄድ የነበረው አንዱ መሆኑን ይናገራሉ።
ትራምፕ በደብዳቤያቸው ላይ "ትክክለኛ በሆነ ቴክኒካዊ ዕውቀት፣ ፍትሃዊ እና ግልጽ ድርድር እንዲሁም አሜሪካ በሚኖራት ጠንካራ የቁጥጥር እና የማስተባበር ሚና ከሁሉም የአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር ዘላቂ ስምምነት ላይ መድረስ እንደምንችል አምናለሁ" ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
አክለውም ". . .በድርቅ እና ለረጅም ጊዜ በተራዘመ ደረቅ ዓመታት ወቅት ለግብፅ እና ለሱዳን ሊገመት የሚችል ውሃ እንዲለቀቅ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እንድታመነጭ ያስችላል፣ የተወሰነውም ለግብፅ እና ለሱዳን ሊቀርብ ወይም ሊሸጥ ይችላሉ" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የሕዳሴው ግድብ አለመግባባት ዘላቂ ከሆነ ቀጠናዊ መረጋጋት ጋር በተያያዘ "ከፍተኛ ትኩረት" የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል።
"ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላም ስሠራ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት ቁልፍ አጀንዳዬ ነው" ብለዋል።
ለፕሬዚዳንት አልሲሲ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ ለኢትዮጵያው ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ ለሱዳኑ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እንዲሁም በቀጠናው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ላላቸው የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን እና የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ቢን ዛይድ ተልኳል።
አሜሪካ ሁለቱን አገራት ማደራደር መቼ እንደምትጀምር ደብዳቤው ላይ የተገለጸ ነገር የለም።
ደብዳቤውን በተመለከተ የግብፅም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥታት እስካሁን ድረስ ምንም ያሉት ነገር የለም።
የአባይ ውሃን በተናጠል ስለመቆጣጠር እና በድርቅ ወቅት ከግድቡ ስለሚለቀቀ ውሃ በፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ ላይ የሰፈረው ሃሳብ የግብፅን አቋም የሚደገፍ በመሆኑ ወደ ዋሺንግተን እንደሚሄዱ ሲጠበቁ የነበሩት ፕሬዝዳንት አል ሲሲየድርድር ጥሪውን በደስታ እንደሚቀበሉት ይጠበቃል።
መንግሥታዊው አል አህራም ጋዜጣ በፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ ላይ የሰፈረው የቋንቋ አጠቃቀም የግብፅን አቋም የሚደግፍ እንደሆነ ተደርጎ ሊተረጎም ይችላል ሲል ጽፏል።
ኢትዮጵያ በግድቡ ምክንያት በተፋሰሱ አገራት ላይ የሚደርስ ጉዳት እንደሌላ በመግለጽ በተፈጥሮ ሀብቷ በፍትሐዊነት የመጠቀም ሕጋዊ መብቷን እንደምትጠቀም በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
ግብፅ ግን በግድቡ የውሃ ይዘት እና የሚለቀቅበት ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ሕጋዊ ስምምነት እንድትፈርም ስትጠይቅ መቆየቷ ይታወቃል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ዋሺንግተን የግድቡን ግንባታ በገንዘብ ደግፋለች ብለው የተናገሩ ቢሆንም አዲስ አበባ ግን ከኢትዮጵያውያን ውጭ የማንም ሰባራ ሳንቲም በግድቡ ላይ አልዋለም ስትል አስተባብላለች።
ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበት ግንባታው የተካሄደው የሕዳሴ ግድብ 1.78 ኪሎ ሜትር የተዘረጋ ሲሆን 145 ሜትር ከፍታ አለው።
በዓለማችን በርዝመቱ የሚታወቀው የዓባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ ውሃውን የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ነው።
የወንዙን አብዛኛውን ውሃ የምትጠቀመው ግብፅ፤ በኢትዮጵያ ግድብ መገንባቱ የውሃ መጠን ይቀንስብኛል ስትል በተደጋጋሚ ከስሳለች። ኢትዮጵያ ይሄንን ውንጀላ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው እና አብዛኛውን የወንዙን ውሃ ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት በመጥቀስ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት አላት በማለት ኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳላበት ስትከራከር ቆይታለች።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ የሚጥል አይደለም ስትል በተደጋጋሚ ገልጻለች።















