ኢትዮጵያን ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ሲያወዛግብ የቆየው የሕዳሴ ግድብ ቁልፍ ክስተቶች

ሕዳሴ ግድብ

ኢትዮጵያ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን አስታውቃ ለማስመረቅ የናይል ተፋሰስ አገራት መሪዎችን እንዲሁም ሌሎች እንግዶችን ጠርታለች።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግንባታን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከሱዳን እና ግብፅ ጋር አለመግባበት ውስጥ ቆይታለች።

ግብፅ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ላለፉት አስራ አራት ዓመታት በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።

በ2003 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው ይህ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ 233 ቢሊየን ብር ለግንባታ እንደወጣበት ተገልጿል።

ኢትዮጵያ የተናጠል እርምጃ ወስዳ የግድቡን ሙሌት ያጠናቀቀች ሲሆን፣ ይህም ሁልጊዜም በታችኛው ተፋሰስ አገራት ዘንድ ስጋትን ሲያጭር ቆይቷል።

የሕዳሴ ግድብ ከተጀመረ ወዲህ ባሉት ዓመታት ግብፅ እና ሱዳን ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ የመጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የማያወላውል አቋም ለመገዳደር ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ እስከ መስማማት ደርሰዋል።

ግብፅ ዘወትር የውሃ ድረሻዋን በማንኛውም መንገድ እንደምትከላከል ስትናገር የቆየች ሲሆን፣ ናይል "የኅልውና ጉዳይ ነው" ስትል ትደመጣለች።

በሱዳን እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት፣ ከዚያ ቀደም ብሎ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተቀሰቀሰው የድንበር አለመግባባት በሕዳሴ ግድብ ንግግር ላይ ቀላል የማይባሉ ተጽዕኖዎችን አሳርፈዋል።

ሱዳን አንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን መሆኗን ስታሳይ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከአዲስ አበባ በተቃራኒው ቆማ ከግብፅ ጋር ስታብር ታይታለች።

የሕዳሴ ግድብ መገኛ በሆነው ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልም የታጠቁ አማፂያን ግንባታው እየተካሄደ በነበረባቸው ዓመታት ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ሶማሊያ እና ኤርትራ ጋር የነበራት ወዳጅነት መቀዛቀዝ ግብፅ በሕዳሴ ግድቡ ላይ ላላት ቅሬታ መጠቀሚያ አድርጋዋለች።

ባለፉት 14 ዓመታት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ጋር በተያያዘ የነበሩ ዋነኛ ክስተቶች የሚከተሉት ነበሩ።

የመለስ ዜናዊ ንግግር

ከ2003 - 2005 ዓ.ም.

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መጋቢት 2003፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በአባይ ወንዝ ላይ ሊገነባው ያቀደውን በአፍሪካ ትልቁ የውሃ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን ይፋ አደረገ። ሚያዝያ ላይ የግድቡ ግንባታ ተጀመረ።

ግንቦት ወር ላይ ግብፅ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅረው ጥናት ማካሄድ ጀመሩ።

መስከረም 2004፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ግድቡ የግብፅን የውሃ ድርሻ የሚጎዳ አይደለም አለ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በግብፅ ጉብኝት ለማድረግ ካይሮ በገቡበት ወቅት ደግሞ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡ ሁለቱንም አገራት ሊጠቅም እንደሚችል ተናገሩ።

2004 ግንቦት፡ ከሦስቱ አገራት የተወጣጡ አባላትን ጨምሮ ሌሎች አራት የውጭ አካላትን ያካተተው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የግድቡን ተጽእኖ መገምገም ጀመረ። በጥቅምት 2005 ዓ.ም. ላይ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ግድቡ የሚገነባበትን ቦታ ሄዶ ጎበኘ። ከዚያ በኋላም ስፍራውን አራት ጊዜ ሄደው ጎብኝተዋል።

2005 ግንቦት፡ ኢትዮጵያ ለግድቡ ግንባታ አመቺነት የአባይን ወንዝ አቅጣጫን ቀየረች። ሰኔ ላይ ደግሞ የባለሙያዎቹ ቡድን የመጨረሻ ሪፖርቱን አቀረበ። ኢትዮጵያ እና ግብፅም በሪፖርቱ አተረጓጎም ላይ መስማማት አልቻሉም።

የግብፁ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሙርሲ በግድቡ ዙሪያ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን ማራመድ ጀመሩ። በተለያዩ አጋጣሚዎችም በቴሌቪዥን በሚያደርጓቸው ንግግሮች እና ውይይቶች ላይ ኃይል መጠቀም የሚለውን ሀሳብ በተደጋጋሚ ያነሱ ነበር።

ግብፅ በተደጋጋሚ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደምትወስደው ብትናገርም ብዙም ሳይቆይ አገራቱ የባለሙያዎቹ ቡድን ያቀረበውን ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ፖለቲካዊ እና የቴክኒክ ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስማሙ።

የሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, GRAND ETHIOPIAN RENAISSANCE DAM

የምስሉ መግለጫ, በ2003 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው ግድቡ 233 ቢሊየን ብር ወጥቶበታል

ከ2006- 2008 ዓ.ም.

2006 መስከረም፡ የተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ስብሰባ በኒውዮርክ ሲካሄድ ሁለቱ አገራት ባደረጉት የጎንዮሽ ስብሰባ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ድርድሩን ለመቀጠል ተስማሙ።

በኅዳር እና በታኅሣሥ ወር ላይ የኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ካርቱም ላይ ተሰባስበው ባለሙያዎቹ ያቀረቡት ሀሳብን ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት አካሄዱ። ነገር ግን ስብሰባው ያለስምምነት ተጠናቀቀ።

2006 ጥር፡ የኢትዮጵያ፣ የግብፅ እና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ለሦስተኛ ጊዜ በካርቱም ተሰበሰቡ። በስብሰባውም በቀሪ ጉዳዮች ላይ መስማማት ስላልቻሉ ከዚህ በኋላ ስብሰባ ላለማድረግ ተስማሙ።

የካቲት ወር ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ እና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች ብቻ በአዲስ አበባ ቢሰበሰቡም ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ግብፅ በግድቡ ዙሪያ የጀመረቸውን ዘመቻ እንድታቆምና ወደ ሦስትዮሽ ድርድር እንድትመለስ ጥያቄዋን አቀረበች።

ሰኔ ወር ላይ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር በኢኳቶሪያል ጊኒ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ላይ ውይይት በማድረግ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በድጋሚ ሥራውን እንዲጀምር ተስማሙ።

በነሐሴ ወር ላይ ደግሞ የሦስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች በካርቱም ድርድራቸውን በድጋሚ ጀመሩ። በዚያውም በባለሙያዎቹ ቡድን ምክረ ሀሳብ መሠረት አገራቱ በገልተኛ ዓለም አቀፍ ድርጅት የሚመራ እና ከሦስቱ አገራት የተወጣጡ አባላት ያሉት ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማሙ።

2007 መስከረም ፡ የግብፅ እና የሱዳን ውሃ ሚኒስትሮች የግድቡን የግንባታ ሂደት ከጎበኙ በኋላ የሦስትዮሽ ኮሚቴው አባላት በአዲስ አበባ ውይይት አደረጉ። ጥቅምት ወር ላይ ደግሞ የግድቡን አጠቃላይ ጥናት የሚያካሂድ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅትን ለመምረጥ በካይሮ ስብሰባ አደረጉ።

2007 ጥር፡ ግብፅ የግድቡን 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም እና የግድቡን ከፍታ አልቀበለውም አለች። መጋቢት ላይ ደግሞ ሦስተኛው ዙር የሦስትዮሽ ኮሚቴ ስብሰባ በካርቱም ተካሄደ።

በዚያውም ሦስቱ አገራት በመርኅ ደረጃ በሚያስማሟቸው ጉዳዮች ላይ ተፈራረሙ። በዚያው ወርም የግብፁ ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ንግግር አደረጉ።

2007 ሚያዝያ፡ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በአዲስ አበባ በመገናኘት የግድቡን አጠቃላይ ጥናት የሚያከናውኑ ሁለት የአውሮፓ አማካሪዎችን መረጡ። ሐምሌ ወር ላይ ደግሞ የኮሚቴው አባላት በካይሮ ባደረጉት ስብሰባ የሁለቱ አማካሪዎች የመጀመሪያ ዙር ምክረ ሀሳብን ገመገሙ።

2008 ኅዳር፡ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በካይሮ ተሰበሰበ። በዚህ ስብሰባ ላይም ሁለቱ የአውሮፓ አማካሪ ተቋማት መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ተገለጸ። በታኅሣሥ ወር ደግሞ ኮሚቴው ካርቱም ላይ ተሰብስቦ የካርቱሙን ስምምነት ተፈራረመ። በስምምነቱ መሠረትም የግድቡን አጠቃላይ የጥናት ሥራ በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅና ከማማከሩ እራሱን ባገለለው ድርጅት ፈንታ አዲስ አማካሪ ለመምረጥ ተግባቡ።

2008 ጥር፡ የግብፁ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አዲስ አበባ ውስጥ በመገናኘት የካርቱሙን ስምምነት ለማክበር እና ከመግባባት ላይ ለመድረስ ተስማሙ።

የካቲት ወር ላይ ደግሞ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በካርቱም በመሰብሰብ ግድቡ በግብፅ እና በሱዳን ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ በፈረንሳይ አማካሪ ድርጅት በተሠራው ጥናት ላይ በመወያየት ግምገማ አካሄደ።

የኃይለማሪያም ንግግር
ካርታ

ከ2009-2011 ዓ.ም.

2009 መስከረም፡ ሦስቱም አገራት በዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን የቀረበውን ምክረ ሀሳብ ለማስፈጸም 'ቢአርኤልአይ' ከተባለው የፈረንሳይ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራረሙ።

2009 የካቲት፡ ሁለቱ የፈረንሳይ አማካሪ ድርጅቶች የመጀመሪያ ዙር ሪፖርታቸውን በግድቡ ዙሪያ አቀረቡ። ሪፖርቱን ግብፅ ስትቀበለው ኢትዮጵያ እና ሱዳን ውድቅ አደረጉት።

ሚያዝያ ላይ ደግሞ የግብፁ ፕሬዝዳንት እና ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካይሮ ውስጥ ተገናኙ። በዚያውም የግብፁ ፕሬዝዳንት ካርቱም ላይ የተፈረመውን ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ የግድቡ ሙሌት ላይ ከስምምነት መድረስ እንደሚገባ ገለጹ።

2010 ጥቅምት፡ የሦስትዮሽ ኮሚቴው ካይሮ ውስጥ በመሰብሰብ በሁለቱ የፈረንሳይ አማካሪ ድርጅቶች በቀረበው ምክረ ሀሳብ ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ዙሪያ ምክክር አደረገ።

ኅዳር ወር ላይ ደግሞ በድጋሚ ኮሚቴው በካይሮ ቢሰበሰብም ምንም ስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ቀረ። በዚያው ው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብፅ ችግር እየፈጠረች ነው በማለት ከሰሰ።

2010 ጥር፡ የግብፁ ፕሬዝዳንት ድርድሩ ተስፋ ሰጪ ነገር እየታየበት አለመሆኑ እንዳሳባቸው በመግለጽ የዓለም ባንክን በጉዳዩ ለማስገባት ሀሳብ አቀረቡ። ነገር ግን ኢትዮጵያ የግብፅን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አደረገችው።

በዚያው ወር ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ዓመታዊ የሦስትዮሽ ስብሰባ ለማካሄድ እና በአንድ ወር ውስጥ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የመሠረተ ልማት ፈንድ በማቋቋም የሦስቱንም አገራት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶችን ያካተተ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማሙ።

ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውሃ ሚኒስትሮች እና የደኅንንት ኃላፊዎች በካርቱም ተሰበሰቡ። ነገር ግን ስብሰባው ውጤት ሳያስገኝ ተበተነ።

ግንቦት ወር ላይ የኢትዮጵያ፣ የግብፅ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ፣ የደኅንነት እና የውሃ ሚኒስትሮች በድጋሚ ስብሰባቸውን በአዲስ አበባ አደረጉ። ግብፅም ስብሰባው ስኬታማ እንደነበረ ገለጸች።

ሰኔ ወር ላይ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብፅን ሲጎበኙ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ የግብፅን የውሃ ድርሻ እንደማይጎዳ ተናገሩ።

2011 መስከረም ፡ ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ ግብፅ ስምምነቱን አልፈርምም አለች።

2011 ጥር፡ በሱዳን እየተካሄደ በነበረው ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት የግድቡ ድርድር መቋረጡን ግብፅ አስታወቀች።

ሐምሌ ወር ላይ የግብፁ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካይሮ ውስጥ ተገናኙ። በዚያውም የሦስትዮሽ ድርድሩን ለማስቀጠል ተስማሙ።

የግድቡ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ማመንጫ
የምስሉ መግለጫ, ግድቡ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ግንባታው ከመጠናቀቁ ከዓመታት በኋላ ነው
የኢንጂነር ስመኘው ንግግር በጽሁፍ እና ፎቷቸው

2012 ዓ.ም.

2012 መስከረም፡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድርድሩ መጓተት እንዳላስደሰተው አስታወቀ። ኢትዮጵያ ደግሞ ግብፅ ከግድቡ አሞላል ጋር በተያያዘ ያቀረበችውን ሀሳብ በድጋሚ ውድቅ አደረገችው። ግብፅ በበኩሏ ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት እንዳትጀምር አስጠነቀቀች።

ጥቅምት ወር ላይ ደግሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ መግለጫ አወጣ። ግብፅም በግድቡ ድርድር ላይ አሜሪካ እጇን እንድታስገባ ጥያቄዋን አቀረበች። ኢትዮጵያ ደግሞ የግብፅን ጥሪ ተቃወመች።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለአገራቸው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የትኛውም ኃይል ኢትዮጵያን ግድቡን ከመገንባት እንደማያስቆማት ተናገሩ። ግብፅ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በመተቸት በአሜሪካ ዋሽንግተን ለመነጋገር የቀረበውን ሀሳብ እንደምትቀበለው ተናገረች።

ኅዳር ላይ ደግሞ በአሜሪካ አደራዳሪነት አዲስ ውይይት ተጀመረ። የሦስቱ አገራት የውሃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዋሽንግተን ድርድራቸውን ካደረጉ በኋላ በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሁለተኛ ድርድራቸውን በአዲስ አበባ አካሄዱ።

ታኅሣሥ ወር ላይ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በካይሮ፣ በዋሽንግተን እና በካርቱም በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሦስት ስብሰባዎችን አካሄደ። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ስብሰባው ውጤታማ እንደነበረ እና ግብፅም ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ ያቀረበችውን ሀሳብ እንደተወችው አስታወቀ። ነገር ግን ግብፅ አልተውኩትም በማለት አስተባበለች።

2012 ጥር፡ የአገራቱ የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች ዋሽንግተን ሁለት ጊዜ ሲገናኙ የውሃ ሚኒስትሮች ብቻ ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ተገናኝተዋል።

ሕጋዊ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የሚሠራው ቡድን ደግሞ ካርቱም ውስጥ ተገናኘ። በዚህ ወቅት በተደረሱ ስምምነቶች ዙሪያ ግብጽ እና ኢትዮጵያ እርስ በርስ የሚቃረኑ መግለጫዎችን አወጡ።

ሕጋዊ እና ቴክኒካዊ ቡድኑ እንዲሁም የውሃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በአሜሪካ በተደጋጋሚ ተወያዩ። ነገር ግን የመጨረሻዎቹን ሁለት ስብሰባዎች ኢትዮጵያ አልተካፈለችም። ግብፅ ደግሞ ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ አሸማጋይነት የቀረበውን ሀሳብ ተቀብላ ስምምነቱን ፈረመች።

መጋቢት ወር ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃላፊዎች በግድቡ ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ዓይነት ጥቃትን ለመመከት ዝግጁ መሆናቸው አስታወቁ። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አሜሪካ በድርድሩ ላይ ወደ አንድ ቡድን ያጋደለ አቋም እንዳረመደች በመግለጽ ቅሬታውን አሰማ።

ግብፅ በበኩሏ ወደ አረብ አገራት በመሄድ አቋሟን እንዲረዱ እና እንዲደግፏት ዘመቻ አደረገች። ኢትዮጵያም በአረብ ሊግ የቀረበውን ሀሳብ አልቀበለውም አለች።

ግንቦት ላይ ደግሞ የግድቡን ሙሌት የተመለከተውን በኢትዮጵያ የቀረበውን ሀሳብ ግብፅ እንደማትቀበለው አሳወቀች። ኢትዮጵያ ደግሞ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ እና የውሃ ሙሌት ሥራውን በተገቢው መንገድ ለማከናወን የግብፅን ይሁንታ እንደማትፈል በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ጻፈች።

ግብፅ ደግሞ ቀደም ብላ ሁለቱ አገራት ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ ግድቡን የመሙላት ሥራ እንዳትጀምር ለፀጥታ ምክር ቤት ደብዳቤ አስገብታ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ ሁለቱ አገራት አለመግባባታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱት ሀሳብ አቀረበ።

ሰኔ ወር ላይ ሱዳን ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ሁለቱ አገራት ውይይት ሳይካሄድ ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳያስተላልፉ ስትል ጠየቀች።

በጉዳዩ ላይ ለማሸማገል ሩሲያ ሀሳብ አቅርባ ነበር። ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን አምስት ተከታታይ ድርድሮችን አካሄዱ። ግብፅ ድርድሩ ተስፋ ሰጪ አይደለም ስትል ኢትዮጵያ በበኩሏ ድርድሩ ውጤታማ የማይሆነው በግብፅ ምክንያት ነው ስትል ከስሳለች።

ሰኔ 26 ላይ ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ሲሪል ራማፎሳ ከሦስቱ አገራት መሪዎች ጋር በቨዲዮ ኮንፈረንስ ተወያዩ።

በሁለት ሳምንታት ውስጥም ስምምነት ላይ ለመድረስ የተስማሙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት በተከታይነት በነበሩት ሳምንታት እንደምትጀምር በመግለጽ የግድቡን ሥራ ለማከናወን የሌሎችን ፈቃድ እንደማትጠይቅ አስታወቀች።

ሐምሌ ላይ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ወታደራዊ አማራጭን እንደማይከተሉ ገለጸ። በአፍሪካ ኅብረት አስተባባሪነት ሦስቱንም አገራት በማሳተፍ የተካሄደውም ድርድር ያለምንም ስምምነት ተጠናቀቀ።

ተከትሎም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የግድቡ ሙሌት መጀመሩን ይፋ ማድረግ ጀመሩ። የአረብ አገራት ሚዲያዎችም ዜናውን ተቀባበሉት። ግብፅ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣት የኢትዮጵያን መንግሥት ጠየቀች። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ መረጃውን ቀድሞ ይፋ ያደረገው የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዜናውን ከገጹ ላይ አነሳ።

ሱዳን በበኩሏ የውሃ ሙሌቱ ተጀመረ ከተባለ በኋላ የ90 ኪዩቢክ ሜትር ቅናሽ ማየቷን አስታወቀች።

የሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, PM Office

የምስሉ መግለጫ, የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለመጠናቀቅ 14 ዓመት ፈጅቶበታል
የኢንጂነር ስለሺ ፎቶ እና ንግግር

2013 -2014 ዓ.ም

ጥር 2013፡ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በበይነ መረብ በሚካሄደው ስብሰባ ሁለተኛ ቀን ላይ ሱዳን ሳትገኝ ቀረች። ከዚያ በኋላ በተደረገ ስብሰባም ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ሲያደርጉት በነበረው ውይይት ድርድሩን ለማስቀጠል በቀረበ ሀሳብ ላይ ሱዳን ሳትስማማ ቀርታለች። ድርድሩን ለማስቀጠል እንዲያግዝ አገራቱ ከአፍረካ ኅብረት ባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ ካካሄዱ በኋላ ውጤቱ ለኅብረቱ ምክር ቤት ሊቀመንበር እንዲቀርብ በሚለው ሀሳብ ላይ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ሲስማሙ ሱዳን እንዳልተቀበለችው የሚኒስትሮቹ የሦስትዮሽ ስብሰባ መግለጫ አመልክቷል።

መጋቢት፡ በትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ይገባኛል የምትለውን ግዛት በኃይል የያዘችው ሱዳን ግንኙነቷን ከግብፅ ጋር ማጠናከሯን ቀጠለች። ከግድቡ አንጻር ተመሳሳይ አቋም በመያዝ አብረው ከመቆማቸው ባሻገር ሁለቱ አገራት ይፋዊ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመሩ። በዚህ ወቅት ሁለቱ አገራት የተቋረጠው ድርድር እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

ሚያዝያ- ግብፅ የአፍሪካ ኅብረት በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚያካሄደው ድርድር ያለውጤት መበተኑን አስታወቀች። ይህ ንግግር ሳይሳካ ከቀረ በኋላ ኢትዮጵያ ስለሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሱዳን እና ግብፅ መረጃ ለመለዋወጥ እንዲያመች ባለሙያዎቻቸውን እንዲያሳውቁ ጠይቃለች። በዚሁ ወር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር ግብፅ እና ሱዳን እንዲመለሱ ግፊት እንዲያደርግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትን ጠይቃለች።

ግንቦት፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ በታላቁ በግድቡ ዙሪያ መወያየታቸውን ከፕሬዝዳንት ባይደን ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ አመልክቷል። በዚህም በስልክ በተደረገው ውይይት "ፕሬዝዳንት ባይደን የአባይን ውሃ በተመለከተ ግብፅ ያላትን ስጋት እንደሚረዱ ገልጸዋል" ብሏል።

ሐምሌ፡ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መጀመሯን ተከትሎ ግብፅ የቀጠናውን መረጋጋት አደጋ የሚጥል ነው በማለት እርምጃውን ተቃውማ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ደብዳቤ መፃፏን አስታውቃለች።

መስከረም 2014፡ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የሦስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ስር ቀጥሎ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ስምምነት ላይ በአስቸኳይ እንዲደርሱ መግለጫ አወጣ። ኢትዮጵያም ሁኔታው እንዳሳዘናት ገልጻለች።

ጥቅምት፡ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ከውሃ ሙሌቱ እንዲሁም በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስለ ግድቡ ከተካሄዱ ውይይቶች ጋር በተያያዘ ገናና ስም ያተረፉት ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በሚኒስትር ማዕረግ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የሕዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪና አማካሪ ሆነው ተሾሙ።

ኅዳር፡ ኢትዮጵያ ከግድቡ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደምትጀምር አስታወቀች። አንድ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው ግድቡ በመጀመሪያ ደረጃው 700 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሏል። ይህም አገሪቱ እያመነጨች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል በ14 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው ተነግሯል።

የካቲት፡ ግድቡ የካቲት 13/2014 ዓ.ም. የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀመረ፤ ይህም የፕሮጀክቱ ዋነኛ ምዕራፍ ነበር። ይህም ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች አንዱ ከተሳካ ተከላ እና ሙከራ በኋላ ያመነጨው ኃይል ነው።

መጋቢት፡ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ከኮንጎው ድርድር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ የተመራ ምሥጢራዊ ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል።

ሐምሌ፡ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ለጉብኝት ወደ ካይሮ ከተጓዙት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ጋር በኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ተዘገበ። ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የግብፁ ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት ከሶማሊያው አቻቸው ጋር በዓለም አቀፍ ወንዞች ላይ በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ዙሪያ "አደገኛ የተናጠል ፖሊሲዎች" ባሏቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል። የግብፁ ፕሬዝዳንት ከሶማሊያው አቻቸው ጋር በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ "የተናጠል እርምጃ መውሰዷ አሉታዊ ውጤት ይኖረዋል" ማለታቸውን አናዶሉ ዘግቧል።

ነሐሴ - የግድቡ ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተርባይን ኃይል የማመንጨት ሥራን የጀመረ ሲሆን ግንባታውም ወደ 83.3 በመቶ መድረሱን የግድቡ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናግረዋል።

ግድቡ

2015-2016 ዓ.ም

መስከረም 2015፡ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ እና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በካይሮ ተገናኝተው በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ተወያይተዋል።

ጥቅምት፡ የሱዳን እና የኢትዮጵያ መሪዎች በአዲስ አበባ ተገናኝተው በግድቡ ባልተፈቱ ጉዳዮች ዙሪያ በመነጋገር ለመፍታት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ታኅሣሥ፡ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው ግድብ ዙሪያ በቅን ልቦና በሚካሄድ ንግግር ከስምምነት እንዲደረስ የግብፁ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጥሪ አቅርበዋል። ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት ሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ውስጥ በተካሄደው የቻይና-አረብ አገራት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ሚያዝያ፡ ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ያለውን ውዝግብ ግድቡን ለመሙላት እንደ "ጊዜ መግዣ እየተጠቀመችበት ነው" ስትል ግብፅ ከሰሰች። የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ ግዙፉን ግድብ በውሃ መሙላቷን ቀጥላለች ብለዋል።

ሚያዝያ፡ ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር የሚደረገውን የሦስትዮሽ ድርድርን መልሳ ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን ገለጸች። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋው የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ከሆኑት ማይክ ሐመር ጋር በተወያዩበት ጊዜ ነው የአገራቸውን ፍላጎት የገለጹት።

ግንቦት፡ የአረብ ሊግ አገራት ምክር ቤት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም እና በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ እየወሰደች ካለችው "የተናጥል እርምጃ እንድትቆጠብ" ውሳኔ አሳልፏል። ሊጉ "የግብፅ እና የሱዳን የውሃ ደኅንነት የአረብ ውሃ ደኅንነት አካል" መሆኑን በመግለጽ አገራቱ በአባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን መብት የሚነካ ማንኛውንም እርምጃ ውድቅ አድርጓል። ኢትዮጵያም ሊጉ ያስተለላፈውን ውሳኔ በመቃወም "ፀብ አጫሪ ትርክትን አስተጋብቷል" ብላለች።

ነሐሴ፡ ለሁለት ዓመት ያህል ተቋርጦ የቆየው በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ መካከል ሲደረግ የነበረው ድርድር ካይሮ ላይ ተጀመረ። የሦስቱ አገራት ተወካዮች ኢትዮጵያ ወደማጠናቀቁ በተቃረበችው ግድብ ላይ የሚያደርጉትን ድርድር ከረጅም ጊዜ በኋላ መጀመራቸውን የአገራቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

መስከረም 2016፡ ኢትዮጵያ አራተኛ ዙር ግድብ ሙሌትን አከናውኛለሁ ማለቷን ተከትሎ ግብፅ ከወንዙ የማገኘው የውሃ መጠን ላይ አደጋ የጋረጠ ነው ስትል ከሰሰች።

ታኅሣሥ፡ አራተኛው ዙር በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና በሱዳን መካከል የሚደረገው የሦትዮሽ ድርድር በአዲስ አበባ ተካሄደ።

ጥር፡ ፕሬዝዳንት ሲሲ የሶማሊያ እና ኤርትራ ፕሬዝዳንቶችን በካይሮ በመጋበዝ ኢትዮጵያ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የባሕር በር ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር ስለተፈራረመችው ስምምነት ትኩረት አድርገው ተወያዩ።

የካቲት፡ የግብፁ ፕሬዝዳንት ከኤርትራው አቻቸው ጋር በካይሮ ተገናኝተው ከኢትዮጵያ ጋር ፖለቲካዊ ፍጥጫ ውስጥ ገብታ የነበረችውን የሶማሊያ ሉዓላዊነት ማክበር አንደሚያስፈልግ ተናጋገሩ።

ሚያዚያ፡ ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ መሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 13ኛ ዓመት አከበረች።

ነሐሴ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሕዳሴውን ግድብ ጎብኝተው የሦስተኛው እና አራተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመራቸውን ይፋ አደረጉ።

የዐቢይ ንግግር እና ፎቶ

2017 ዓ.ም.

መስከረም፡ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕዳሴ ግድብን በሚመለከት የኢትዮጵያን "የተናጠል ፖሊሲ" ውድቅ በማድረግ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ጻፈ። ይህንን ውንጀላ የኢትዮጵያ መንግሥት ውድቅ አደረገ።

ጥቅምት፡ ፕሬዝዳንት ሲሲ የናይልን ወንዝ መጠበቅ "የኅልውና ጉዳይ ነው" በማለት የውሃ ጉዳይ የአገራቸው ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ተናገሩ።

ታኅሣሥ፡ ኢትዮጵያ የኤሌትሪክ ኃይል ለጎረቤት አገራት እንዳልሸጥ ግብፅ ዲፕሎማሲ ዘመቻ ከፍታብኛለች ስትል ከሰሰች።

መጋቢት፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በ2017 ሙሉ በሙሉ አንደሚጠናቀቅ ተናገሩ።

ሚያዝያ፡ ኢትዮጵያ ግድቡ 98̂.6 በመቶ መጠናቀቁን እና ስድስቱ ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸውን ይፋ አደረገች።

ግንቦት፡ ኢትዮጵያ የሕዳሴን ግድብ የሚጠብቅ የባሕር ኃይል ፖሊስ አቋቋመች።

ሐምሌ፡ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በመጠናቀቁ የናይል ተፋሰስ አባል አገራት በሙሉ ምረቃው ላይ አንዲገኙ ጥሪ አቀረበች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግብፅ እና ሱዳን በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚሁ ወር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለግድቡ ግንባታ አሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረገች በተደጋጋሚ በይፋ ሲናገሩ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ግንባታው የተካሄደው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የገንዘብ መሆኑን አስታውቋል።

ነሐሴ፡ ግብፅ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የገነባችው እና ሊመረቅ ቀናት የቀሩት ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በምሥራቅ የናይል ተፋሰስ አገራት ላይ ዘላቂ ስጋት ደቅኗል አሉ።

ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ አጠናቅቃ ለምረቃ እየተዘጋጀች ባለችብት ጊዜ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሮች በካይሮ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ባወጡት መግለጫ ነው ስጋታቸውን የገለጹት።

ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የተለያዩ አገራት መሪዎች በተገኙበት በይፋ ተመረቀ።