በሕዳሴ ግድብ ግንባታ "15 ሺህ ሰዎች ሞተዋል" ስለመባሉ የግድቡ የሠራተኞች ደኅንነት ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

የህዳሴ ግድብ ሰራተኛ እንጨት ተሸክሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተካሄደባቸው 14 ዓመታት ውስጥ "እስከ 15 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ሞተዋል" በሚል የተጠቀሰውን ቁጥር ለረጅም ዓመታት በሂደቱ የተሳተፉ ሁለት የግድቡ ሠራተኞች የደኅንነት ባለሙያዎች ውድቅ አደረጉ።

ይህንን ቁጥር አረጋግጠዋል የተባሉት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው "ጥያቄው በተሳሳተ መልኩ ተተርጉሟል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ፤ ከቀናት በኋላ እንደሚመረቅ የሚጠበቀው ግዙፉ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ 15 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በግድቡ ግንባታ ሕይወታቸው ስለማለፉ እውነታነት እንዲያረጋግጡ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

ሪፖርተር የእንግሊዝኛ መጽሔት በጽሁፍ ባወጣው ቃለ መጠየቅ ላይ ሚኒስትሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ "አዎ፤ እውነት ነው" የሚል ምላሽ እንደሰጡ ሰፍሯል።

በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይ የተጠቀሰው ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር የተያያዘ ሞት ቁጥር ባለፉት ቀናት በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው፤ የቀድሞው "ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ" የደኅንነት አስተባባሪ እና መሃንዲስ ከግንባታ ሥራ ጋር በተያያዘ ይህንን ያህል ሰው ሞቷል መባሉን ውድቅ አድርገዋል።

"ዊ ቢውልድ" በሚል ስያሜውን የቀየረው ይህ የሕዳሴ ግድብ ዋና ተቋራጭ፤ በግንባታው ሂደት የሲቪል ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቷል።

የተቋራጩ የ"ኸልዝ ኤንድ ሴፍቲ ኢንቫይሮመንት" መሃንዲስ የሆኑት ኢንጂነር ሞገስ የሺዋስ ከመጋቢት 2004 ዓ.ም. እስከ ባለፈው ግንቦት 2017 ዓ.ም. ድረስ በግንባታው ላይ ሰርተዋል።

"ኸልዝ ኤንድ ሴፍቲ ኢንቫይሮመንት" ክፍል አስተባባሪ የነበሩት ሌላኛው ባለሙያ ምንተስኖት አየለ በበኩላቸው ከ2004 ዓ.ም. አንስቶ ለአስር ዓመታት ገደማ ግንባታው ላይ ቆይተዋል።

አብዛኛውን የሰው ኃይል የሚያሰማራው "ዊ ቢውልድ" ሠራተኞችን የሥራ ላይ ደኅንነት የመከታተል እና የመመዝገብ ኃላፊነት ያላቸው እነዚህ ባለሙያዎች፤ በግንባታው ሂደት ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ።

እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ኸልዝ ኤንድ ሴፍቲ ኢንቫይሮመንት ኮርዲኔተር ሆነው የሠሩት ምንተስኖት "በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች የሞቱበት መንገድ አለ" ይላሉ።

"ከሥራ ጋር በተገናኘ በአደጋ የሚሞቱበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። የግድቡን ኅልውና በማስጠበቅ፣ ከተለያዩ ቦታዎች ላይ ቁሳቁሶችን በማመላለስ፣ ጥቃት ሲደርስ ስለነበር በዚያ ሰዓት የተሰዉ ወገኖችም፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትም ሊኖሩ ይችላሉ" ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ እና የተፈጠረውን ሰው ሰራሽ ሚያሳይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, ላለፉት 14 ዓመታት በግንባታ ላይ ቆየው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመጪው ሳምንት ጷግሜ 4/2017 ዓ.ም. ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን በትክክል መናገር የሚችሉት ከግድቡ ግንባታ ሥራ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን በተመለከተ እንደሆነ አስረድተዋል። "ከዚህ ጋር በተያያዘ የነበረው ሞት በጣም ጥቂት ነው። 15 ሺህ ከሚለው አንጻር ጋር ሲታይ በጣም ጥቂት ነው የነበረው" ብለዋል።

"እኛ ሳሊኒ ጋር የነበረው ከሥራ ጋር የተያያዘ የሞተ ሰው ከ100 የሚያልፍ አይመስለኝም። 100ም የሚደርስ አይመስለኝም" ሲሉም አክለዋል።

እስከ ግንቦት ድረስ የኮንትራክተሩ የኸልዝ ኤንድ ሴፍቲ ኢንቫይሮመንት ኢንጂነር የነበሩት ሞገስም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።

ኢንጂነሩ፤ "ሥራውም ይመለከተኝ ስለነበር፤ እንመዘገበውም ስለነበረ ዳታው [መረጃ] ነበረኝ። ባለኝ ዳታ መሠረት እስከ ነበርኩበት ጊዜ ድረስ እኔ የማውቀው ቁጥር [የሞቱ ሠራተኞች ብዛት] 25 አካባቢ ነው፤ ድርጅቱ የሚያውቀውም ይህንን ነው" በማለት የሞቱ ሠራተኞች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ከእነዚህ የዊ ቢውልድ ሠራተኞች ውስጥ አብዛኞቹ ሕይወታቸው ያለፈው "በትራፊክ አደጋ" እንደሆነ ተናግረዋል። "ከከፍታ ቦታ ላይ መውደቅ" እና "ከኤሌክትሪክሲቲ ጋር የተገናኙ" አደጋዎችም ሠራተኞችን ለሞት ከዳረጉ ምክንያቶች መካከል እንደሚጠቀሱ አስረድተዋል።

ምንተስኖትም በተመሳሳይ "ግቢ ውስጥ የሚከሰት የከባባድ የኮንስትራክሽን መኪናዎች የመገልበጥ እና መውደቅ"፣ "ከከፍታ ላይ መውደቅ" እንዲሁም "ኤሌክትሪክ አደጋዎችን" ጠቅሰዋል። ከሥራ ጋር በተያያዙ አደጋዎች ከሞት በተጨማሪ አካል ጉዳቶች መድረሳቸውንም ሁለቱ ባለሙያዎች አክለዋል።

የኸልዝ ኤንድ ሴፍቲ ኢንቫይሮመንት ኢንጂነሩ ሞገስ፤ በተለይም በግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታ ላይ የሚሳተፉ ሌሎች ተቋራጮች መኖራቸውን አንስተዋል። ይሁን እንጂ "በይበልጥ ለአደጋ የመጋለጥ ዕድል ያለው" የዊ ቢውልድ ሠራተኞች በሚያከናኑት የሲቪል ግንባታ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"[የሲቪል ሥራ] እንቅስቃሴው በይበልጥ ወሳኝ ነው። በተለይም ከከፍታ ቦታ ላይ መሥራት በብዛት አለ። ከእርሱ ጋር ተያይዞ አደጋ የመድረስ ዕድሉ ሰፊ ነው" በማለት አስረድተዋል።

ከሥራ እስከለቀቁበት ግንቦት ወር 2017 ዓ.ም. ድረስ "ለሰባት ገደማ ዓመታት የሠራተኞች ተወካይ" ሆነው እንዳገለገሉ የሚናገሩት ሞገስ፤ በዚህ ምክንያት የሌሎች ተቋራጮች ሠራተኞች ሕይወት ካለፈ ሊያውቁ የሚችሉበት ዕድል እንደነበርም አንስተዋል።

የህዳሴ ግድብ ሰራተኛ ግዙፍ ቁመት ካለው የግድቡ ግንባታ ፊት ለፊት ቆሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሰራተኞች ብዛት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ 10 ሺህ ገደማ በሚሆንባቸው ጊዜያት "ከሰባት ሺህ በላይ የሚሆኑት" የሚሰሩት በዋናው ተቋራጭ ዊ ቢውልድ ስር እንደሚሆን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

አክለውም፤ "አንድ ሰብ ስቴሽን ላይ የሚሠራ የቻይና ኮንትራክተር ሠራተኛ ከከፍታ ቦታ ወድቆ ሕይወቱ እንዳለፈ ሰምቻለሁ። ከዚያ የዘለለ የሰማሁት የለም" ብለዋል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ "የሁሉም ሰው አሻራ ያረፈበት" መሆኑን ባስረዱበት የቃለ መጠየቅ ክፍል ላይ "ሕይወታቸውን የሰዉ የፀጥታ ኃይሎች" እና "የተገደሉ አሽከርካሪዎች" መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የተለያዩ ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የተለያዩ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የፌደራል መንግሥት በተደጋጋሚ ሲናገር ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኞ ዕለት በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈ የአንድ ሰዓት ገደማ ቆይታ ላይም ይህንን ጉዳይ ጠቅሰውት ነበር።

ዐቢይ፤ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በነበሩ ዓመታት "ግጭት እና ውጊያ" በዝቶ እንደነበር እንዲሁም "ተፋላሚዎች ወጥተው ከሀገር፣ ሠልጥነው [ሲያስቸግሩ]" እንደነበር አንስተዋል።

ቢቢሲ ያነጋራቸው ሁለት ባለሙያዎችም በግድቡ ግንባታ ሂደት ወቅት በተለያየ መልኩ ጥቃት ሲፈጸም እደነበር ገልጸዋል።

የሠራተኞች ደኅንነት አስተባባሪ የነበሩት ምንተስኖት፤ "በጣም ብዙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል። በአንድ ቀን መምጣት የሚቻለው መንገድ ሰባት ቀን በመኪና ታጅቦ ነው ይመጣ የነበረው። እቃ ወደ ግድቡ የሚመጣው፣ ሠራተኛውም ወደ ቤተሰቡ ሄዶ ሲመለስ አብሮ ታጅቦ ነው የሚመለሰው" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል።

ምን ያህል ወይም ምን ዓይነት ጥቃት ተፈጽሟል የሚለውን በተመለከተ ግን መናገር እንደማይችሉ አስረድተዋል። በተፈጸሙ ጥቃቶች የሞቱ ሰዎችን ብዛት፤ "ከእኛ በላይ የነበሩ ሰዎች ያንን ቁጥር ሊያውቁት ይችላሉ" ብለዋል።

የኸልዝ ኤንድ ሴፍቲ ኢንቫይሮመንት ኢንጂነሩ ሞገስ በበኩላቸው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት "ከሁለት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ" ተሽከርካሪዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩት በፀጥታ ኃይሎች እጀባ እንደነበረ ገልጸዋል። ይህ እጀባ ያስፈለገውም "ታጣቂዎች ጫካው ጋር ይሆኑና መኪና አልፎ ሲሄድ ጥይት ስለሚተኩሱ እና ጉዳት ስለሚያደርሱ" እንደነበር ተናግረዋል።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት ግድቡ አካባቢ ተሰብስበው

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force

የምስሉ መግለጫ, "ህዳሴ ኮር" የተባለ በግድቡ አካባቢ የሚንቀሳቀስ የጦር ክፍል በምዕራብ ዕዝ ስር ያቋቋመው ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ ለግንባታ ሥራው እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ጥበቃ ሲያደርግ ቆይቷል

"በ2015 ዓ.ም." አካባቢ በተፈጸመ "የሽብር ጥቃት አንድ የዊ ቢውልድ አሽከርካሪ" ሕይወቱ ማለፉን አስረድተዋል። ሠራተኛው ይዞት የነበረው ተሽከርካሪው በእጀባ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ያስታወሱት ሞገስ፤ "መንገድ ላይ የተጠመደ ፈንጂ ነው ጉዳት ያደረሰበት። እጀባ ቢኖርም እጀባ ሊያድነው የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም" ብለዋል።

በዚህ ጥቃት ከተገደለው አሽከርካሪ በተጨማሪ "ሠራተኛ ያልነበረች አንዲት ተሳፋሪ" ጉዳት ደርሶባት እንደነበርም ጠቅሰዋል። ሞገስ ጥቃቶች ሲደርሱ እንደነበር እንደሚያውቁ ቢናገሩም፤ ከእነዚህ ጥቃቶች ጋር በተያያዘም ቢሆን የተጠቀሰው ቁጥር እንደማያሳምናቸው ተናግረዋል።

ሪፖርተር መጽሔት ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 29 ከሰዓት በድረ ገጹ ላይ በወጣው ቃለ መጠይቅ ላይ ባደረገው ማስተካከያ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በቀረበው ጥያቄ የተጠቀሰው ቁጥር "ከኮንስትራክሽን ደኅንነት ጉዳዮች ጋር" ብቻ በተያያዘ እንዳልሆነ የሚያመለክት መልዕክት አስፍሯል።

መጽሔቱ ይህንን ማስተካከያ ያደረገው "አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን እና ግለሰቦች ትክክለኛውን ገለጻ ከአውድ ውጪ ወስደው ስለተረጎሙት" እንደሆነ ገልጿል።

ቢቢሲ ይህንን ቁጥር በተመለከተ ጥያቄ ያቀረበላቸው ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ፤ የቀረበላቸው ጥያቄ "በተሳሳተ መንገድ መተርጎሙን" ተናግረዋል። ሚኒስትሩ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም ጥያቄው የቀረበላቸው "የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በመውሰድ" እንደነበረ አክለዋል።

ዶ/ር ሀብታሙ፤ "15 ሺህ" በሚል የተጠቀሰው ቁጥር ትክክለኛ ስለመሆኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ "ልክ ሆነም አልሆነም፤ የተጻፈበት አተረጓጎም ልክ አልነበረም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። "ጥያቄው እንደዚያ አልነበረም" ሲሉም ተናግረዋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከመከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማብራሪያ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።