ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ልታስመርቅ ነው

ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. የአፍሪካ መሪዎች እና ሌሎች የተጋበዙ እንግዶች በሚገኙበት እንደሚመረቅ በኬንያ የኢትዮጵያ ምክትል አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ተናገሩ።
ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት በአፍሪካ ግዙፉ እንደሆነ የተነገረለት ሕዳሴ ግድብ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው ሲካሄድ ቆይቷል።
አምባሳደር ደመቀ ሐሙስ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም. ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ የሕዳሴ ግድብ ሴፕቴምበር 9 [ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም.] በይፋ ምረቃው እንደሚካሄድ አመልክተዋል።
በአምስት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ከአስር ዓመታት በላይ ፈጅቶ የኢትዮጵያ መንግሥት በመጪው አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ በይፋ እንደሚመረቅ አስታውቆ ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረው መጋቢት 24/2003 ዓ.ም. ሲሆን አጠቃላይ ግንባታው 14 ዓመታትን ወስዷል።
ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን "በጨለማ ነው የሚኖሩት" ያሉት አምባሳደሩ እነዚህ ሕዝቦች የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታልሞ ግድቡ መገንባቱን ተናግረዋል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ገንዘብ ማዋጣቱን ያመለከቱት አምባሳደሩ "የነበሩ በርካታ መሰናክሎች" ታልፈው ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ምረቃው እንሚካሄድ ገልጸዋል።
ከ14 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ ተጠቃሽ የሆነ ግዙፍ ግድብ መገንባት መጀመሯን በማብሰር በይፋ የመሠረት ድንጋዩን በማስቀመጥ ግንባታውን ያስጀመሩት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው።
ግንባታው ከተጀመረው በኋላ ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቶች ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ገብታ የቆየችው ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ሙሉ ወጪ የሸፈነችው ከሕዝብ ከተሰበሰበ ገንዘብ ነው።
የግድቡ ግንባታ ሲጀመር በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ሲሆን "ኢትዮጵያውያን ራሳቸው መሃንዲስም የፋይናንስ ምንጭም ሆነው ይገነቡታል" በማለት ነበር የተገለፀው።
አምባሳደር ደመቀ ኢትዮጵያ ትርፍ የኤሌትሪክ ኃይል ማምረት በመጀመሯ ለጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ መሸጥ መጀመሯንም አስታውሰዋል።
በዚህም የተነሳ ከጎረቤት አገራት ጋር በኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት መተሳሰር ተችሏል ያሉት በማለት፣ ይህም ወደ በፖለቲካዊ ትስስር አንደሚያመራም ተናግረዋል።
የሕዳሴውን ግድብ ተጠናቅቆ ሲመረቅ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የምታከብረው "የአባይ ተፋሰስ አገራት እንዲሁም ቀሪው የአፍሪካ አገራት በጋራ የሚያከብሩት ይሆናል" ሲሉም አክለዋል።
በቅርቡ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ይመረቃል መባሉን ተከትሎ ግብፅ "የዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ መልኩ በምሥራቃዊ ናይል ተፋሰስ የሚደረግ የተናጠል እርምጃን" እንደማትቀበል ለበርካታ አፍሪካ አገራት አሳውቃለች።
14 ዓመታትን የፈጀው እና አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪን የጠየቀው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አምስተኛ ዙር ሙሌት ተጠናቆ ምረቃው ጳጉሜ 4 /2017 ዓ.ም. ጥሪ የተደረገላቸው አገራት መሪዎች በተገኙበት እንደሚካሄድ ምክትል አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ አረጋግጠዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጅምሩ እንዲሁም የተካሄዱ አምስት ውሃ ሙሌቶችን በጽኑ ያወገዙት የግብፅ ፕሬዝዳንት፣ ከላይኛው የናይል ተፋሰስ አገራት አንዷ ከሆነችው የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር።
ፕሬዝዳንት ሲሲ "በድጋሚ ለግብፃውያን ማረጋገጥ የምፈልገው 105 ሚሊዮን ዜጎቻችን እና 10 ሚሊዮን የሚሆኑ በአገራችን ያሉ እንግዶቻችን በሕይወት የሚያቆየው ውሃ እንዲነካ ፈጽሞ እንደማንፈቅድ ነው" ብለዋል።
አምባሳደር ደመቀ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ "በአሁኑ ወቅት ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም" ያሉ ሲሆን፣ ግብፅ ታሪካዊ መብት የምትለው "አክትሞለታል" ካሉ በኋላ "ያለው አማራጭ ወደ ትብብር መምጣት ብቻ ነው" ብለዋል።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው እና የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት መሠረት አድርጋ ታሪካዊ ተጠቃሚነቷን በማስጠበቅ የወንዙን ውሃ በበላይነት የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት በመጥቀስ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስትቃወም ቆይታለች።
ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድታገኝ እና 86 በመቶ የአባይ ወንዝ ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይ እና ኢፍትሃዊ እንደሆነም ይጠቀሳል።
ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የግብፅ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተናቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው በግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስታስታውቅ ቆይታለች።
አምባሳደር ደመቀ ኢትዮጵያ ከውኃ ኃይል ለማመንጨት ያላትን አቅም በሙሉ እየተጠቀመች ነው ያሉ ሲሆን፣ ከሕዳሴ ግድብ በመቀጠል ትልቁ በኮይሻ ወንዝ ላይ የሚሠራው 1800 ሜጋ ዋት የኃይል የሚያመነጨው ግንባታ 70 በመቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ኬንያ ከላከችው የኤሌትሪክ ኃይል ብቻ 86 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷን የተናገሩት አምባሳደሩ፣ ተጨማሪ 200 ሜጋ ዋት ጥያቄ ቀርቦ ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ታንዛኒያ 100 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ኃይል እንደምትልክ እንዲሁም ፍላጎት ያላቸው ብዙ አገራት መኖራቸውንም አመልክተዋል።
የሕዳሴ ግድብ 13 ተርባይኖች የሚኖሩት ሲሆን አጠቃላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅሙ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት እንደሚደርስ ተገልጿል።
ይህም በአፍሪካ ትልቁ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ አመንጪ ያደርገዋል።
ግድቡ 145 ሜትር ከፍታና ወደ ጎን ደግሞ 1780 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሙሉ በሙሉ ሲይዝም ውሃው የሚተኛበት ስፍራ ርዝመት 246 ኪሎ ሜትር እንደሚደርስ ተገልጿል።















