ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ላይፈጽሙ እንደሚችሉ ከተናገሩ በኋላ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ቀነሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ላይፈጽሙ እንደሚችሉ ከተናገሩ በኋላ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ቅናሽ አሳየ።
የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ 64 ዶላር ዝቅ በማለት የአራት በመቶ ቅናሽ አስመዝግቧል።
ባለፉት ቀናት የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 67 ዶላር ነበር።
በሌላ በኩል ረቡዕ ዕለት የወርቅ ዋጋ ወደ 4ሺህ 600 ዶላር ከፍ ያለ ሲሆን፣ ይህም ማክሰኞ ከነበረው በ0.4 በመቶ ከፍ ያለ ሆኗል።
ትራምፕ በጽህፈት ቤታቸው ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች "ኢራን ዜጎቿን በሞት መቅጣት ማቆሟን ሰምተናል። . . . .በሞት የመቅጣት ዕቅድ የለም” ብለው ነበር።
ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደም የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ላይ “በጣም ጠንከር ያለ እርምጃ” እንደሚወስዱ ዝተው ነበር።
የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከ1 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም የትራምፕን አስተያየት ተከትሎ ወዲያውኑ ቅናሽ ተመዝግቧል።
ትራምፕ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዳቸውን ትተውት እንደሆን ሲጠየቁ ያለውን ሁኔታ እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል።



















