አሉታዊ አስተያየቶች በጥልቀት የሚጎዱን ለምንድን ነው? አእምሯችንስ ለምን አብዝቶ ያሰላስላቸዋል?

ልቧ የተሰበረ እና የምታለቅስ በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለአሉታዊ ሃሳቦች ማድላት (ኔጋቲቭ ባያዝ) በአእምሮ እና አካላዊ ጤና ላይ እክል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ

ማዕዶት አሁን ባለትዳር እና የሦስት ልጆች እናት ብትሆንም በልጅነቷ ከእንጀራ አባቷ ይሰነዘሩባት የነበሩ አሉታዊ ቃላትን እስካሁን አትረሳቸው።

ምንም እንኳን በሕይወቷ ብዙ መልካም ነገሮች ቢያልፉም ማዕዶት [ስሟ የተለወጠ] አዕምሮዋ ወደ እነዚያ አሉታዊ ቃላት ያጋድላል።

ነገሩ ዱላ አጥንት ቢሰብርም ቃላት ከዱላ በላይ አቅም አላቸው እንደሚባለው ነው።

ከአካላዊ ጉዳቶች መፈወስ ሳምንታት ሊወስድ ይችላል። አሉታዊ አስተያየቶች ግን በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ይከተሉናል፤ የማይሽር ጠባሳም ጥለውብን ያልፋሉ።

እነዚህ አሉታዊ አስተያየቶች ልክ በማዕዶት ላይ እንደደረሰው ከቤተሰብ፣ ከአስተማሪ፣ ከጓደኛ አሊያም ከፍቅረኛ እንደቀልድ የተወረወሩ ሊሆኑ ይችላሉ። የከፋ የሚያደርጋቸውም የሚሰነዘሩት ከቅርብ ሰው መሆናቸው ነው።

ለመሆኑ አሉታዊ አስተያየቶች ለምንድን ነው ውስጣችንን ሰርስረው የሚገቡት? በይበልጥስ ለምን እናስታውሳቸዋለን?

አዎንታዊ ከሆኑት ይልቅ አሉታዊ ነገሮችን ለምን በአዕምሯችን ተከትበው ይቀራሉ?

ጥናቶች እና ባለሙያዎች በዚህ ላይ ብዙ ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አእምሯችን አዎንታዊ ወይም ምንም ካልሆኑ አስተያየቶች ይበልጥ አሉታዊ ሃሳቦችን መዝግቦ የመያዝ አድልዎ (ኔጋቲቭ ባያዝ) አለው።

በዚህም ምክንያት ከጥሩው ይልቅ መጥፎውን፣ ከብርሃኑ ይልቅ ጨለማን፣ ከሙገሳ ይልቅ ትችቶችን ያስታውሳል።

እንዲህ መሆኑ ከአእምሮ ብቃት ባሕርይ ጋር የሚገናኝ እንደሆነ የሥነ ልቦና ባለሙያው አቶ ቴዎድሮስ ድልነሳው ያስረዳሉ።

አቶ ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሳይኮሎጂ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በማማከር አገልግሎት ከአዲስ አበባ አግኝተዋል።

በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይም በተለይ የአእምሮ ቁስለትን (ትራውማ) በተመለከተ ሙያዊ ሃሳባቸውን በማጋራት ይታወቃሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት በሥነ ልቦና ሳይንስ የአእምሮ ባሕርይ ውስጥ የተዛቡ ሃሳቦች አሊያም ግንዛቤዎች አሉ።

እነዚህ ሃሳቦች 'ሁሉም ወይም ምንም' በሚል አስተሳሰብ የተደመደሙ ናቸው። በሌላ አገላለጽ ጭፍን አሉታዊ ድምዳሜ ሊባል ይችላል።

ታዲያ እነዚህ ግንዛቤዎች ለረጅም ጊዜ ሲቆዩ ወደዚያ አስተሳሰብ ማድላትን (አድልዎን) ይፈጥራሉ። ይህም በሁለት መንገዶች ይገለጣል ይላሉ ባለሙያው።

አንደኛው ጥሩውን አጥልሎ በማስቀረት ወይም በጎ ነገርን ባለመቀበል ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ አሉታዊ ነገሮችን በጣም በማጉላት ወይም በማጋነን ነው።

ወደዚህ የሚገፉን ምክንያቶች በራሳችን ላይ አሊያም በሌሎች ላይ ሲደርስ ያየናቸው የሕይወት አጋጣሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

በኪዊንስላንድ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሥነ ልቦና አማካሪ እና 'ዘ ፖዎር ኦፍ ባድ' መጽሐፍ ደራሲዎች አንዱ የሆኑት ሮይ ባውሜስተር እንደሚሉትም ያሳለፍናቸው ውስብስብ የሕይወት መንገዶችም በዚህ አድልዎ ይገለጣሉ።

ይህም ከአዎንታዊ በበለጠ እኛን ለሚነኩ አሉታዊ ስሜቶች የተለየ ትኩረት እንድንሰጥ እና አደጋዎችን እንድናጋንን ያደርገናል።

በእርግጥ ከብርሃኑ ይልቅ ጨለማው ላይ ማተኮር ተስፋ አስቆራጭ ሊመስል ይችላል።

ነገር ግን የሰው ልጆች የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን፣ መቅሰፍቶችን እና ጦርነቶችን ለመቋቋም በተሻለ ሁኔታ ቀድሞ በመዘጋጀት ሁሉንም እንዲያሸንፉ ረድቷል።

የማኅበረሰብ ሥነ ልቦና ባለሙያው ባውሜስተር እንደሚሉት "በአሉታዊ አድልዎ ምክንያት ቅድመ አያቶቻችን ነገሮችን በተሻለ መቋቋም ይችሉ ነበር።"

ችግር ላይ በቅድሚያ ትኩረት ማድረግም ጥሩ ዘዴ መሆኑን ባውሜስተር ይናገራሉ።

"መጀመሪያ ላይ አሉታዊ ነጥቦችን አስወግዶ ችግሩን መፍታት፤ ጉዳቱን ከማከም በፊት ደሙን ማቆም ያስፈልጋል" ይላሉ።

ይህ ማለት ግን አዎንታዊ አመለካከት አያስፈልግም ማለት አይደለም።

አዎንታዊ መሆንም በእንደዚያ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለጭንቀት እንዳንዳረግ እንደሚያደርግ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

ለአሉታዊ ማድላት ተፈጥሯዊ ወይስ የምንማረው?

የሰው ልጅ አእምሮ የተፈጠረው ሰውነታችንን ለመጠበቅ እና በሕይወት ለማቆየት ሲሆን፣ የተፈጠረውም እንግዳ የሆኑ አደገኛ ሁኔታዎችን ለመጋፈጥ ከሚረዱ ሦስት የማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ጋር ነው።

አንደኛው ባሳል ጋንግሊያ ሲሆን፣ ትግላችንን ወይም ለሚገጥመን ፈተና የምንሰጠውን ምላሽ የሚቆጣጠር ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ሊምቢክ ሥርዓት ሲባል፣ ለሚኖረን ስጋት ምላሽ ለመስጠት አደገኛ ሁኔታዎችን እንድንረዳ ስሜት ይቀሰቅሳል።

ሌላኛው እና ሦስተኛው ደግሞ ፕሪ ፍሮንታል ኮርቴክስ ይባላል። ይህ ሥርዓት የገጠመንን ፈተና በምክንያታዊነት እና በአመክንዮ ተረድተን ውሳኔ እንድንሰጥ እና እንድናቅድ ያስችላል።

የሰው ልጅ ስጋቶችን መለየት የሚጀምረው ከስምንት ወሩ ጀምሮ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። ሕጻናት በዚህ ዕድሜያቸው ከምታጫውታቸው ድመት ምሥል ይልቅ ፊታቸውን በፍጥነት የሚያዞሩት ወደ እባብ ምሥል ነው።

በአምስት ዓመታቸው ደግሞ ከደስተኛ ፊት ይልቅ የተቆጣን ፊት ቅድሚያ ሰጥተው ይረዳሉ።

አቶ ቴዎድሮስም የሰው ልጅ አሉታዊ የምንላቸውን ነገሮች የመታዘብ አቅሙ ተፈጥሯዊ ነው ይላሉ።

ሕጻናት ስንስቅላቸው ምላሽ እንደሚሰጡ፤ ነገር ግን በአንድ ዓመታቸው አካባቢ አሉታዊ የሆኑ ስሜቶችን ይበልጥ መለየት ይችላሉ ተብሎ እንደሚታመን በሕጻናት ላይ የተሠሩ ጥናቶችን በማጣቀስ ይናገራሉ።

የሰው ልጅ ሕይወቱን ለማስቀጠል እና ራሱን ከአደጋ ለመጠበቅ አሉታዊ ናቸው ብሎ በአእምሮው ከመዘገባቸው ነገሮች መጠበቅ አለበት።

አእምሯችንም የሚሠራው በዚሁ መሠረት ነው።

እዚህ ላይ በካናዳ የሚገኘው ማክጊል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ያካሄዱትን ጥናት ማንሳት ይቻላል።

ተመራማሪዎቹ ለጥናታቸው ፈቃደኛ የሆኑ በጎ ፈቃደኞች ለየትኛው ዜና ወይም ጽሑፍ ትኩረት እንደሚሰጡ ለማወቅ የዐይንን እንቅስቃሴ የሚከታተል ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ነበር።

በጥናቱም አብዛኞቹ ሰዎች ከአዎንታዊ አሊያም ምንም ካልሆኑ ዜናዎች ይልቅ ስለ ሙስና፣ ስለ አምባገነንነት፣ ስለ ኪሳራ እና ሌሎች መጥፎ ዜናዎች ላይ ትኩረት ሲያደርጉ አግኝተዋቸዋል።

ለወቅታዊ ጉዳዮች እና ለፖለቲካ ፍላጎት የነበራቸው ሰዎችም የመረጡት ዜና መጥፎውን ነበር፤ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ሲጠየቁ የሚወዱት ጥሩ ዜና እንደሆነ ነበር የተናገሩት።

ጭንቅላቱን በእጆቹ ደግፎ አቀርቅሮ ጋዜጣ የሚያነብ አረጋዊ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የሥነ ልቦና ባለሙያው አቶ ቴዎድሮስ አሉታዊ ሃሳቦች ላይ ትኩረት ማድረጋችን በሥነ ልቦና ሳይንስ ውድቀትን ከመፍራት (ፊር ኦፍ ፌሊየር) ጋር የሚተሳሰር እንደሆነ ያስረዳሉ።

ይህ ግን ባለን አስተሳሰብ ላይ የሚመሠረት ሲሆን፣ ጥቅም እና ጉዳቱ የሚወሰነውም በዚሁ አስተሳሰባችን ላይ ነው።

"ምንም የማይለወጥ (ፊክስድ ማይንድሴት) ያለው እና የሚያድግ (ግሮውዝ ማይንድሴት) አስተሳሰብ ያለው ሰው እነዚህን አሉታዊ አስተሳሰቦች የሚያስተናግድበት መንገድ ይለያያል" ይላሉ።

የማይለወጥ አስተሳሰብ ያለው ሰው ተግዳሮቶችን እንደ ፈተና የማየት፣ መሰናክል እና ትችትን ያለመፈለግ አስተሳሰብ ካለው አሉታዊ መድልዎው ይጨምራል።

በሌላ በኩል የሚያድግ አስተሳሰብ ያለው ሰው ደግሞ ተግዳሮትን እንደ ዕድል፣ ዳገት ውስጥ ዕድገት እንዳለ፣ ከትችት ለመማር እና ራስን ለመገምገም ይረዳኛል ብሎ ስለሚያስብ አሉታዊ አድልዎውን (ኔጋቲቭ ባያዙን) እንዲያሸንፍ ያደርገዋል።

የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምንድን ነው?

ባውሜስተር እንደሚሉት ያልተመጣጠነ አሉታዊ አድልዎ ለዓለም ያለን ዕይታ እና ለዚያ የምንሰጠው ምላሽ ላይ እክል ይፈጥራል።

ለምሳሌ ጋዜጣ ስናነብ ሕይወት በጠቅላላው ጨለማ ይመስለናል።

ጋዜጠኞችም ጋዜጦቻቸውን ለመሸጥ እና ዕይታን ለማግኘት ሲሉ በብዛት መጥፎ ዜናዎችን በመከታተል ይወቀሳሉ። በእርግጥ ይህ በከፊልም ቢሆን እውነትነት አለው።

ሆኖም አጥኚዎች እንደሚሉት አንባቢዎች በተፈጥሮ አስከፊ በሆኑ ታሪኮች የመመሰጥ እና ለሌሎች የማጋራት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

የመከሰት ዕድላቸው ዝቅተኛ ቢሆንም እንኳን አደገኛ ክስተቶችን በሚመለከት የሚሰሙ ጭምጭምታዎች ጠቃሚ ከሚሆኑ ወሬዎች ይልቅ ብዙ ርቀው ይጓዛሉ ወይም ብዙ ይናፈሳሉ። ጋዜጠኞችም ይህንን የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ይዘቶቻቸውን የሚያቀርቡት።

ነገር ግን ስለ መላምት ወይም ስለ አስከፊ ሁኔታ አብዝቶ መጨነቅ ፈሪ እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል።

አንድ ትንሽ መጥፎ አጋጣሚ በውሏችን ላይ ያልተመጣጠነ ተፅዕኖ ሊያሳድርብን እንደሚችል ባውሜስተር ይናገራሉ።

በሴንት ልዊ በሚገኘው ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና እና አእምሮ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ራንዲይ ላርሰን እንደሚሉት አሉታዊ ስሜቶች ከደስታ ስሜቶች በላይ ለረዥም ጊዜ የመቆየት ዕድል አላቸው።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ብዙ ጊዜ የምናጠፋው ስለመጥፎ አጋጣሚዎች በማሰብ ነው። ይህ ምን አልባትም የሚያናድዱ አጋጣሚዎች ወይም ትችቶች ለዓመታት ለምን እንደሚያሳድዱን ለማስረዳት በቂ ምሳሌ ናቸው ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

በተለይ ከምንወዳቸው ሰዎች የሚሰነዘሩ ጎጂ አስተያየቶችን አለማስታወስ አይቻለንም።

ከቤተሰብ፣ ከሚቀርቡን፣ ከጓደኛ የሚሰነዘሩብን ትችቶች እንግዳ ከሆነ ሰው ከሚሰነዘርብን የበለጠ ተፅዕኖ አላቸው።

አንዳንዴ ከምንወዳቸው ሰዎች የሚሰነዘሩብን አስተያየቶች ለረዥም ጊዜ አብረውን ይዘልቃሉ። ግንኙነት እንዲፈርስም ያደርጋሉ።

ለዚህ አንደኛው ምክንያት ጓደኞቻችን አሊያም ቤተሰቦቻችን ስለእኛ በጎ አመለካከት አላቸው ብለን ስለምንጠብቅ ነው።

በአንዳንድ ሁኔታዎች ከምንወዳቸው ሰዎች የሚሰጡ አሉታዊ አስተያየቶች ለረዥም ጊዜ ወደሚቆይ ጠባሳ ሊያመሩ ይችላሉ።

ከፊቷ የቆመ ሰው እግር እና ፊቷን በእጇ ሸፍና መሬት ላይ ተቀምጣ የምታለቅስ የምትመስል ወጣት ተማሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማዕዶትም ከእንጀራ አባቷ ሲዘነሩባት የነበሩ መጥፎ ቃላት በቤተሰባዊ እርቅም ሆነ ስጦታዎች መጥፋት ያልቻሉ እንደሆኑ ትናገራለች።

"እነዚያን ቃላት የሚያስታውሰኝ አንድ አጋጣሚ ከተፈጠረ፣ ቀኑን ሙሉ የተሰነዘሩብኝን ቃላት ጥቀሽ የተባልኩ ይመስል ስዘረዝር እና ስትመነዝር የዋልኩባቸው ቀናት ጥቂት አይደሉም" ትላለች።

በአሜሪካ ኬንተኪ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጤናማ ሕይወት መምራት የሚቻለው እና ግንኙነቶች የሚሰምሩት እነዚህን ችግሮች አሸንፎ ማለፍ ሲቻል እንደሆነ ይናገራሉ።

ተመራማሪዎቹ ግንኙነቶች የሚሰምሩት ጥንዶች በግንኙነታቸው ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችን ማለፍ ሲችሉ እንደሆነም ያስረዳሉ።

ለ10 ዓመታት ጥንዶችን ሲከታተል የነበረ አንድ ጥናት፣ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ጥንዶቹ እርስ በርሳቸው አሉታዊ ስሜቶችን የሚለዋወጡበት መጠን (አሉታዊው ላይ ትኩረት ማድረጋቸው) ሊለያዩ እንደሚችሉ ለመተንበይ እንደሚያስችል አመልክቷል።

በተፋቱ ጥንዶች መካከልም ያሉ አሉታዊ ነገሮች ከፍተኛ ናቸው።

የምናያቸውና የምናነባቸው አሉታዊ ዜናዎችም ችግሩን ከፍ ያደርጉታል።

"በርካቶቻችን የፍቅር ግንኙነታችን በጥሩ ሁኔታ ሲሄድ የትም የማያመልጠን የሚመስለን እና ቶሎ ብለን ጉድፎችን ነቅሰን የምናወጣው እንዲሁም በጣም ኢምንት የሆኑ ጉዳዮችን የምናጋንነው በአሉታዊ አድልዎ ምክንያት ነው" ይላሉ።

ትችትም በብዛት ሲሰነዘር ይጎላል።ለዚህም ነው ማኅበራዊ ሚዲያዎች የአሉታዊ ሃሳቦች ማስተጋቢያ የሚሆኑት።

ድምጻዊቷ ቢሌ ኤሊሽ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ምንም እንኳን በ2019 ያወጣችው አልበም በጥሩ ሁኔታ ቢሸጥም አስተያየቶችን ከማየት ተቆጥባ ነበር።

"አስተያየቶች ሕይወቴን ያበላሹታል" የምትለው ኤሊሽ፣ የተረጋጋ ነገር ብታደርጉም በርካታ ሰዎች ይጠሏችኋል።በጣም የሚገርም ነው" ብላለች።

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰነዘሩ አሉታዊ እና ገንቢ ያልሆኑ ሃሳቦች ምክንያት ለድብርት የተዳረጉ ጥቂት አይደሉም።

የእነዚህ አሉታዊ አስተያየቶች ማየል በሚሰነዘርበት ሰው ላይ ጉዳት ከማስከተላቸው ባሻገር አስተያየቱን የሚሰነዝረውን ሰው አሉታዊ አድልዎም ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አሉታዊ ባሕርያችንን የሚያጎላ ወይም ያ ባሕርያችን እንዲወጣ የማድረግ ባሕርይ አላቸው የሚሉት ቴዎድሮስ፣ አንድ ሰው እየተፈተነ ያለበት ጉዳይ ካለ እና በውስጡ ቁጣ ካለው የሚያናድዱ ጉዳዮችን ፈልጎ የማየት እና አዎንታዊ በሆኑ ንግግሮች እና ሃሳቦች ላይ አሉታዊ ሃሳቦችን ሲሰነዝር እንደሚስተዋል ያስረዳሉ።

ሚዲያውም የፈለገውን አብዝቶ ይሰጠዋል።

ይህንን መቆጣጠር የሚችለው ኃላፊነት የሚሰማው ጋዜጠኛ እና የሚዲያ ይዘት ፈጣሪ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተጠቃሚው እንደሆነ የሥነ ልቦና ባለሙያው ይገልጻሉ።

አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት እነዚህ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተሳሰቦች እንደ ወረርሽኝ የሚዛመቱ ናቸው።

በመሆኑም በራሱ የማያስብ፣ የማይወስን፣ የማይተማመን ፣ ነገሮችን በጥልቀት የማያገናዝብ እና የማያሰላስል ሰው ከሆነ በሚሰነዘሩበት አሉታዊ አስተያየቶች ተጠልፎ ሊወድቅ ይችላል።

ቁጭ ብላ የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን የምታይ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተደጋጋሚ አሉታዊ አስተያየቶችን የሚሰነዝሩ እና የሚያስተጋቡ ሰዎች ለአሉታዊ የሚያደላ አስተሳሰብ ተጠቂ መሆናቸውን ሊያመልክት ይችላል

አሉታዊ አድልዎ ችግር የሚሆነው መቼ ነው? መፍትሔውስ?

ባውሜስተር እንደሚሉት አሉታዊ ነገሮችን ለመቆጣጠር እና ለመፍታት የሚያስችል አቅም የለንም።

ምክንያቱም አእምሯችን የተፈጠረው በመቶዎች እና በሺዎች ከሚቆጠሩ የማናውቃቸው ሰዎች ይልቅ ቅርብ ከሆኑ ሰዎች ለሚመጡ ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት ለመስጠት ነው። በመሆኑም ከብዙ ሰዎች አሉታዊ ነገሮችን መስማት በጣም አስከፊ ነው።

በኦንላይን በጓደኛ መተቸት የሚያመጣው ተፅዕኖ እንደየሰዉ ቢለያይም አሉታዊ አስተያየቶችን መቀበል፣ ወደ ውስጥ ማስገባት እና መሸከም፤ ውጥረት፣ ድብርት፣ ስጋት እና ጭንቀት እንደሚያስከትል የሥነ ባሕርይ ተመራማሪ እና በለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት ተጋባዥ መምህር የሆኑት ሉሲያ ማሺያ ይናገራሉ።

"እነዚህ አሉታዊ ሃሳቦችን ማስተናገድ በሰውነታችን እና በአዕምሯችን ላይ ከባድ ተፅዕኖ የሚያደርሱ ሲሆን፣ ከተባባሱም አካላዊ ህመምን ያስከትላሉ" ይላሉ።

ይህም በታዳጊዎች እና በወጣቶች ዘንድ ጎልቶ ይታያል።

በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች ዕድሜያቸው በጨመረ ቁጥር ብርሃናማ ነገር የመመልከት ዕድላቸው ሰፊ ነው።

ተመራማሪዎች ይህንን አዎንታዊ አድልዎ (ፖዘቲቪቲ ባያዝ) ሲሉ ይገልጹታል። በመካከለኛ ዕድሜ ክልል ውስጥ ስንሆን ከአሉታዊ መረጃዎች ይልቅ አዎንታዊ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ማስታወስ እንጀምራለን።

ባውሜስተር እንደሚሉት የዚህ ምክንያቱ ወጣት በነበርንበት ወቅት ከውድቀት እና ከተሰነዘሩብን ትችቶች ለመማር ስለምንፈልግ አሉታዊዎቹ ላይ ትኩረት የምናደርግ ሲሆን፤ ሆኖም ይህ ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ እየቀነሰ ይመጣል።

ሆኖም አንዳንዶች ከሌሎች ሰዎች በበለጠ በአሉታዊ ሃሳቦች ይገዛሉ የሚለው አከራካሪ እንደሆነ ማሺያ ይናገራሉ።

አንድ ጥናትም በሰዎች ስብዕና አሊያም ፖለቲካዊ አቋም እና በአሉታዊ አድልዎ መካከል ግንኙነት እንዳለ የሚያሳይ ወጥ የሆነ ማስረጃ እንደሌለ አረጋግጧል።

"ሁላችንም ለአሉታዊ አስተያየቶች ስስ ነን። ለእንደዚህ ዓይነት ነገሮች ጠንካራ የሚባል ስብዕና የለም"

ነገር ግን ማንኛውም ሰው የሚቀበላቸው አሉታዊ አስተያየቶች ችግሮቹን እንዲፈታ እና የአእምሮ ጤናውን ለመጠበቅ ጥሩ ዘዴ ሊሆን ይችላል ሲሉም ማሺያ ያክላሉ።

አሉታዊ አስተያየቶቹ ከአስተያየት ሰጪው ጋር እንጂ ከእኛ ከተቀባዮቹ ጋር የበለጠ ግንኙነት እንደሌላቸው ማሰብም ጠቃሚ እንደሆነ ይመክራሉ።

ይህም የሚያስከትሉትን አሉታዊ ጉዳት በመረዳት የማያስፈልግ ምላሽ ከመስጠት ለመቆጠብ እና ወደ ጠቀሜታው ለማዘንበል ይረዳል።

በካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ሼሊይ ቴይለር እንደሚሉት አሉታዊ አድልዎ ለገጠመን ችግር በተለምዶ የምንሰጠው ምላሽ ላይም ተስፋ የሚሰጥ ነገር አሳይቷል።

ይህም ቅነሳ (ሚኒማይዜሽን) ይባላል። የገጠመንን ሁኔታ ተፅዕኖ መተው፣ መቀነስ እና ማጥፋት የምንችልበት ችሎታ ነው - 'የባሰ አለ' ብሎ ክፉ ነገሮችን እንደማሰብ።

ለምሳሌ በጡት ካንሰር የተያዙ ሴቶች የማይጨበጡ አሉታዊ እምነቶችን መፍጠራቸው ችግሩን ለማለፍ ረድቷቸዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

እነዚህ ቅዠቶች ከአእምሮም ሆነ ከአካላዊ የጤና ጥቅሞች ጋር ይገናኛሉ። በጉዳዩ ላይ ከሚያስፈልገው በላይ ብዙ ትኩረት እንዳንሰጠው በማድረግም ያግዛሉ።

በቴይለር ጥናት የተካተቱ የካንሰር ህሙማን ራሳቸውን ከእነርሱ በበለጠ ከሚሰቃዩ ሌሎች ሰዎች ጋር ያወዳድራሉ። ይህን የሚያደርጉት የእነርሱን ህመም ለማቅለል ነው።

ሆኖም ይህ ስልት የማይሠራበት ዕድል አለ። ለምሳሌ ለስካይዳይቨሮች (ከአየር ወደ ምድር ለሚዘሉ) ይህ አይሠራም። ስጋታቸውን ለመቀነስ ቅነሳ የሚለውን ሳይንስ መጠቀም አይችሉም።

አንዳንዶቻችን ደግሞ አሉታዊ ሃሳቦችን በማስወገድ አዎንታዊዎቹን በማጠናከር ህልሞቻችንን ለማሳካት ጠንካራ ሆነን ልንቆም እንችላለን።

ሆኖም አሉታዊ አስተያየቶች በማንኛውም የዕድሜ ክልል ሊገጥሙን እና ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። በተለይ ተጋላጭ በሆንባቸው የዕድሜ ክልሎች።

አንድ ጊዜ በዚያ ሃሳብ ተፅዕኖ ከደረሰብን ለመመለስ ከባድ ነው። በዚያ ሁኔታ ውስጥ እያለንም አሉታዊ አስተያየቶችን መቀበል የበለጠ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

አዎንታዊ አድልዎ (ሁሉም በጎ ነው፤ ጥሩ ነው) ብቻ ብሎ ማሰብም ትክክል አይደለም የሚሉት ቴዎድሮስም ሚዛናዊ መሆንን ይመክራሉ።

"አዕምሯችን አሉታዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር የተደረገበት ምክንያት አለው፤ ነገር ግን ሚዛኑ ሲያጋድል ማስተዋል እና ማመጣጠን ያስፈልጋል። ሕይወትን ከነህጸጿ፣ ከነድክመቷ እንዲሁም ከነውበቷ ማየት አለብን" ብለዋል።

ሆኖም ሰዎች ይህ አሉታዊ አድልዎ በሕይታቸው ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድር፣ ሥራቸውን እና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ሲያውክ፤ ለራሳቸው ያላቸውን ግንዛቤ ተፅዕኖ ሥር ሲከተው የባለሙያ እገዛ መጠየቅ አለባቸው ብለዋል።

ማዕዶትም ለአስርተ ዓመታት አዕምሮዋን ተቆጣጥሮት ከነበረው አሉታዊ ሃሳብን በማመጣጠን የተወሰነም ቢሆን እፎይ ያለችው የባለሙያ እገዛ ካገኘች በኋላ ነበር።

አሁን ላይ እርሷም ከአፏ ለምታወጣቸው ቃላቶች ትጠነቀቃለች።

"መጥፎ ቃላት ምን ያህል ከአእምሮ እንደማይወጡ እና እንደሚሰብሩ አውቃለሁ" ብላለች።