ብዙ ወጣት ወንዶች ከአእምሮ ጤና ችግር ጋር እየታገሉ እርዳታ የማይጠይቁት ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓለም እያደገ የመጣውን የወጣቶች የአእምሮ ጤና ችግር አስተውሏል። በተለይ ደግሞ ወንዶች፣ ወጣት ወንዶች የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን ጥናቶች አሳይተዋል።
ለበርካታ አስርት ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች ወንዶች ለአእምሮ ጤንነታቸው እርዳታ የመጠየቅ ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው። ይህም ከሴቶች ጋር ሲነጻጸር በ40 በመቶ ያነሰ መሆኑን በአሜሪካ የተደረገ ጥናት አረጋግጧል።
አሁንም ግን አፍላ ጎረምሳ ወንዶች ወይንም ወጣቶች እንዴት ወይም መቼ ለአእምሮ ጤናቸው የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንደሚጠይቁ የሚያውቁ ጥቂቶች ነው።
በ2024 በአውሮፓ ቻይልድ ኤንድ አዶለሰንት ሳይኪያትሪ ጆርናል ላይ የወጣው ጥናት "ይህ አሳሳቢ ነው፤ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች እና ወጣቶች በከፍተኛ ቁጥር ራሳቸውን የሚያጠፉ ቢሆንም ድጋፍ ፈልገው የሚመጡት ግን ጥቂት ናቸው" ብሏል።
ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ትምህርት ቤቶች፣ ወላጆች እና ፖሊሲ አውጪዎች ምን ማድረግ ይችላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዝምታ መማቀቅ
የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ባካሄደው ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 19 ዓመት ውስጥ ከሚገኙ ሰባት ወንዶች መካከል አንዱ የአእምሮ ጤና መታወክ ያጋጥመዋል።
በእነዚህ ታዳጊዎች ላይ ድብርት፣ ጭንቀት እና የባህሪ ለውጦች በጣም የተለመዱ የአእምሮ ጤና መታወኮች እንደሆኑ ተረጋግጧል።
ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 በሆኑት መካከል ደግሞ ራስን ማጥፋት ሦስተኛው የሞት መንስኤ ሆኖ ተገኝቷል።
ዘ ላንሴት ሳይካትሪ ኮሚሽን ይፋ እንዳደረገው ከሆነ 75 በመቶ የሚሆኑት የአእምሮ ጤና መታወኮች የሚጀምሩት 25 ዓመት ሳይሞላ ነው።
በ15 ዓመት ዕድሜ ላይ ደግሞ ከፍ ብሎ ይታያል።
ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአካል ጤነኞች ሆነው ቢታዩም በአእምሮ ጤናቸው ግን ከባድ ትግል እየገጠማቸው ነው።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ደግሞ ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣቱ የወጣቶች የአእምሮ ጤና ጉዳይ "አደገኛ ምዕራፍ" ላይ ደርሷል።
ምንም እንኳ ክትትል እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፣ ብዙ ወንዶች እና ወጣቶች ያሉትን የአእምሮ ጤና አገልግሎቶች አይጠቀሙም።
"ባለፉት 15 እና 20 ዓመታት ውስጥ በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ የአእምሮ ጤና ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አይተናል። ነገር ግን እርዳታ መፈለግ በወጣት ወንዶች ዘንድ በጣም አናሳ ነው" ሲሉ የሥነ አእምሮ ሐኪም እና የኦሪጅን ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ፓትሪክ ማክጎሪ ተናግረዋል።
እምቢተኛነታቸው የሚያሳየው ብዙውን ጊዜ ወጣት ወንዶች የሚመጡት ችግሩ ከተባባሰ በኋላ እንደሆነ ነው።
በማኅበረሰቡ ውስጥ ወንድ ልጅ ጠንካራ እና በራስ መተማመን ያለው መሆን አንዳለበት ተደርጎ መቀረፁ አብዛኛውን ጊዜ እርዳታ ፈልገው ወደ ጤና ተቋማት እንዳይሄዱ እንደሚያደርግ ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለውም ጥናቶች በተከታታይ እንደሚያሳዩት እርዳታ መፈለግ የድክመት ምልክት ነው የሚለውን መልዕክት ወንዶች ውስጥ ዘልቆ ገብቷል።
በካናዳ የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ አእምሮ ፕሮፌሰር እና የወንዶች የአእምሮ ጤና አገልግሎት የሚሰጠው ሄድስአፕጋይስ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ጆን ኦግሮድኒችዙክ ብዙ ወንዶች ልጆች አሁንም እርዳታ መጠየቅን ከውድቀት ጋር እንደሚያመሳስሉት ያስረዳሉ።
"ስለ ወንድነት ማኅበራዊነት ከተነጋገርን፣ ወንዶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ወይም እንደሌለባቸው ብዙ የሚጠቀሱ አሉ። ብርቱ ሁን፤ ጠንካራ ሁን፤ ነገሮችን ተቆጣጠር፤ ምንም ዓይነት ድክመት ወይም ገበናህን አታሳይ፤ ነገሮችን በራስህ ተወጣ" ሲሉ ይዘረዝራሉ።
"እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከስሜታዊ የሕይወት ክፍል ጋር የሚኖርህን ግንኙነት እና ሲያስፈልግህ እርዳታ ለመጠየቅ እንዴት እንቅፋት ሆነው እንደሚያገለግሉ ማየት ትችላለህ።"
ዶ/ር ኦግሮድኒዙክ ድጋፎች ለወንዶች ሲዘጋጁ በድምፅ፣ በቋንቋ እና በአቀራረብ መሆን አንዳለበት እና ይህም ተሳትፎን እንደሚጨምር ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መደበኛ ያልሆነ አቀራረብ
የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ወንዶች ልጆች የአእምሮ ጤና ድጋፍን እንዳይፈልጉ ከሚያደርጉት ማኅበራዊ አመለካከቶች እና ድክመትን ማሳየት አለመፈለግ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ጭብጦችን ለይተዋል።
ብዙ ወንዶች የሕመማቸውን ምልክት አይረዱትም፤ እርዳታ እንዴት እንደሚጠይቁም አያውቁም። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ መደበኛ የሕክምና ተቋማት ሁኔታ ብዙ ጊዜ ምቾት አይሰጣቸውም።
አፍላ ጎረምሶች እና ወጣት ወንዶች ብዙ ጊዜ መደበኛ ያልሆነ እርዳታን ይመርጣሉ። ለምሳሌ ከጓደኞቻቸው ጋር መወያየት፣ ወይም ማንነቱ በማይታወቅ ግለሰብ የሚሰጥ ድጋፍ፣ በኦንላይን የሚሰጥ እርዳታ እና ከወንድ ልጅ ጥንካሬ ጋር በቀላሉ የሚተሳሰር የመልዕክት መላላኪያን መጠቀም፣ ኃላፊነት እና ተግባር የበለጠ ተጽዕኖ አላቸው።
ይህ አንዳንድ የወጣቶች አገልግሎቶች ተለምዷዊውን የሕክምና ተቋማት እንዲተዉ አድርጓል። ለምሳሌ በአውስትራሊያ ውስጥ፣ የወጣቶች የአእምሮ ጤና አገልግሎት የሚሰጠው ኦሪጀን ከወጣቶች ጋር በመሆን "ቀለል ያለ የመግቢያ" ንግግሮችን አዘጋጀ።
የኦሪጀን ዋና ዳይሬክተር ፓትሪክ ማክጎሪ "ወጣት ወንዶች ለመጀመሪያ ጊዜ በሚመጡበት ወቅት በአማካሪ ክፍል ውስጥ ለመቀመጥ ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ።ለቃለ መጠይቅ መቀመጥ ላይፈልጉ ይችላሉ።"
"ምናልባት ሌላ ዘና ያለ ነገር እያደረጉ፤ እንደ የእግር ጉዞ ወይም ምናልባት ፑል ወይም የጠረጴዛ ቴኒስ እየተጫወቱ ውይይት ቢያደርጉ ይመርጡ ይሆናል።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማኅበራዊ ሚዲያ፦ ወዳጅ ወይስ ጠላት?
ማኅበራዊ ሚዲያ በሁለት በኩል የተሳለ ቢላዋ ማለት ነው።
ራሳቸውን ነጥለው ለተቀመጡ ወጣቶች ከሚያስፈልጋቸው መረጃ ጋር ሊያገናኝ አልያም ለጎጂ እና መርዛማ ወንድነት ሃሳቦች ሊያጋልጣቸው ይችላል።
የሥነ ልቡና ባለሙያው ዶ/ር ሲሞን ራይስ "አብዛኞቹ ወጣት ወንዶች አሁን ከወንዶች እና ወንዳ ወንድነት ከሚሰብኩ ተጽእኖ ፈጣሪ ይዘቶች ጋር የተገናኙ ናቸው" ይላሉ።
ዶ/ር ራይስ የሠሩት ጥናት እንደሚያሳየው በርካታ ወንዶች "ወንዳ ወንድነትን ለሚሰብኩ እና ሴቶችን ለሚያንቋሽሹ" ይዘቶች የተጋለጡ ሲሆኑ፣ ይህ ደግሞ ከጓደኞቻቸው ይልቅ የአእምሮ ጤናቸውን የበለጠ ይጎዳል።
ነገር ግን ዶ/ር ራይስ ሁሉም ይዘቶች አሉታዊ እንዳልሆኑ እና ማኅበራዊ ሚዲያ የአእምሮ ጤናን ለማሻሻል ጠቃሚ መሳሪያ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።
"የማኅበራዊ ሚዲያ አዎንታዊ ገጽታዎች ማኅበረሰቦችን አንድ ላይ በማሰባሰብ፣ ጥሩ የጤና እና የአዕምሮ ጤና መረጃን በማቅረብ ጉዳቱን እየቀነስን መጠቀም እንደምንችል ማረጋገጥ ያስፈልጋል።"
ነገር ግን የማኅበራዊ ሚዲያ ቀመሮች በተፈጥሯቸው በርካታ ሰው ጋር ሊደርሱ የሚችሉ ይዘቶችን ለማሠራጨት የተነደፉ በመሆናቸው አዎንታዊ እና ጤና ላይ ያተኮሩ ይዘቶች "ቀመሩን (አልጎሪዝምን) ለማሸነፍ" ከባድ ፈተና እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚና ፋዝል ታዳጊዎችን እና ወላጆችን የማኅበራዊ ሚዲያ ቀመር እንዴት እንደሚሠራ ማስተማር ወሳኝ መሆኑን ይስማማሉ።
በቅርቡ የሚታተመውን ጥናታቸውን ጠቅሰው አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ወጣቶች በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ራስን ከመጉዳት ጋር የተያያዘ ይዘትን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አይተዋል።
ፕሮፌሰር ፋዝል አያይዘውም ማኅበራዊ ሚዲያ ብቻ ተጠያቂ እንዳልሆነ እና በሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ሰፊ ለውጦችም ግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ያስረዳሉ።
"የቤተሰብ እና የማኅበረሰብ አወቃቀሮች በከፍተኛ ሁኔታ እየተለወጡ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ለብዙ ወጣቶች በጎ አስተዋጽኦ ሊጫወት ይችላል" ብለዋል።
ብቸኝነት እና መዘዙ
ወንዶች ልጆች ከሚያጋጥማቸው ፈተና መካከል በጣም በስፋት የሚታይ እና እምብዛም ትኩረት ያልተሰጠው ብቸኝነት ነው።
በግንቦት ወር የታተመው የጋሉፕ ጥናት እንደሚያመለክተው ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 34 ዓመት የሆናቸው በአሜሪካ የሚኖሩ 25 በመቶ ወንዶች ከአንድ ቀን በፊት በጣም ብቸኝነት ተሰምቷቸው ነበር።
ይህ ደግሞ በአገር ደረጃ በአማካይ 18 በመቶ እና አጠቃላይ ከወጣት ሴቶች ደግሞ 18 በመቶ ከፍ ያለ ነው።
ዶ/ር ኦግሮድኒዙክ በሄድስአፕጋይስ የሰበሰቡት መረጃ እንደሚያሳየው ብቸኝነት እና የዓላማ ማጣት በወጣት ወንዶች መካከል በጣም የተለመዱ የጭንቀት ምንጮች ናቸው።
ወንዶች ልጆች በዕለት ተዕለት ግንኙነታቸው ውስጥ ጓደኝነትን የሚመሠርቱበት እና በግልጽ የሚነጋገሩበት ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የትምህርት ቤቶች ሚና
ፕሮፌሰር ሚና ፋዘል "ወጣት ወንዶች ድጋፍ ሲፈልጉ ብዙውን ጊዜ ጠቃሚ ሆኖ ያገኙታል የሚል አዎንታዊ አዝማሚያ አለ" ብለዋል።
"ያ እርዳታ የትም ቢሰጥ ችግር የለውም፤ በትምህርት ቤት ሊሆን ይችላል፣ በማኅበራዊ ተቋማት ወይም በማኅበረሰብ ውስጥ ሊሆን ይችላል።"
ትምህርት ቤት በወንዶች ደኅንነት ላይ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት የሚያረጋግጡ መረጃዎች አሉ።
የትምህርት ጫና፣ በተለይም ወንዶች ከሴቶች ወደ ኋላ ቀርተው በሚገኙበት አውድ፣ ጭንቀትን፣ ብስጭትን እና መነጠልን ያመጣል።
ፕሮፌሰር ፋዝል ትምህርት ቤቶች ወንዶችን በተሻለ ሁኔታ እንዲያግዙ ሆነው በአዲስ መልክ መስተካከል አለባቸው ብለው ያምናሉ።
"አብዛኞቹ የዓለም ሕጻናት ትምህርት ቤት የመሄድ ዕድል አላቸው" የሚሉት ፕሮፌሰሯ፣ "ስለዚህ ምናልባት ይህ ቦታ ሕጻናትን ለማስተማር ብቻ ሳይሆን በጉርምስና ወቅት ምን ማድረግ እንዳለባቸው፣ በተለይ ለወንዶች ሰፋ ያለ ትምህርት ለመስጠት መታሰብ አለበት" ብለዋል።















