"ራሴን ለማጥፋት ጫፍ ላይ ደርሼ ነበር፤ አሁን ግን ሌሎችን እረዳለሁ"

አንዳንድ አባቶች ቀይ ሽንኩርት እየጠበሱ እንቁላል እየመቱ በጠረጴዛ ዙሪያ አትክልቶችን ሲቆርጡ ሌሎች ደግሞ አዲስ የተወለዱ ሕፃናትን ይንከባከባሉ። ልጆች በአሻንጉሊት ይጫወታሉ፤ እናቶቻቸው ይመለከቷቸዋል።
በኢንዶኔዢያ ዋና ከተማ ጃካርታ የምግብ ዝግጅት ክፍለ ጊዜዎች በበዛበት ወቅት ጥንዶች ስለ ግንኙነታቸው ያወጋሉ።
ብዙዎቹ ሴቶች ከድባቴ፣ ከጭንቀት ወይም ከሌሎች የአእምሮ ጤና ሁኔታዎች ጋር እየታገሉ ነው።
ይህንን ለእናቶች የሚሰጠውን ድጋፍ የሚያካሂደው የ'ማዘር ሆፕ ኢንዶኔዢያ' መሥራች የሆነችው ኑር ያናይራህ ይህን ትግል እንደ ጦርነት ትገልጸዋለች።
ኑር ከ12 ዓመታት በፊት ራሷን ለማጥፋት አፋፍ ላይ ደርሳ ነበር። ነገር ግን፣ የዘጠኝ ወር ሴት ልጇን ዓይን ስትመለከት የሆነ ነገር ተለወጠ።
"ቆዳዋን ከዳሰስኩ ጠረኗን ካሸተትኩ [በኋላ].…ለዚህች ልጅ ስል መሻሻል እንዳለብኝ ተሰማኝ" ትላለች።

ሕይወቱ ያለፈ የ28 ሳምንታት ልጅ ከወለደች ከሦስት ወራት በኋላ ድጋሚ ፀነሰች ። የስሜት ቀውስ፣ ከፍተኛ ስጋት ያለው እርግዝና እና ፍፁም እናት የመሆን ማኅበራዊ ጫና ተደምረው የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲሰማት፣ ለእንቅልፍ ማጣት እና ልጇን መንከባከብ እንድትቸገር አድርጓታል።
ከዚያ ቅጽበት በኋላ፣ የሥነ ልቦና ሐኪም ድጋፍ አስፈልጓት ነበር፤ ከዚያም የድኅረ ወሊድ ድባቴ እንዳለባት አወቀች።
በዓለም የጤና ድርጅት መሠረት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ከአምስት ሴቶች አንዷ ከወሊድ በኋላ የአእምሮ ጤና መታወክ፤ በዋነኛነት የመንፈስ ጭንቀት ያጋጥማታል።
የሆርሞን ለውጦች እንዲሁም ስቃይ የበረታበት ወሊድ፣ ድህነት ወይም ሐዘን የመሳሰሉ ጭንቀቶች በእርግዝና ወቅት እና ከእርግዝና በኋላ በአእምሮ ጤና ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።
ኑር ለዘጠኝ ወራት ብቻዋን ተሠቃይታለች። "ማንም የተረዳኝ አልነበረም ማንም መረጃ አልሰጠኝም" ትላለች። "ካገገምኩኝ በኋላ...የሌለኝን ድጋፍ ለመስጠት ሞከርኩ" ስትል ታክላለች።

ማዘር ሆፕ ኢንዶኔዢያ አሁን ሁለት መቶ የሠለጠኑ በጎ ፈቃደኞች አሉት፣ የድጋፍ ቡድኖችን እና ለአባቶች የምግብ ዝግጅትን ሥልጣና ያዘጋጃል፣ በተጨማሪም 58,000 ጠንካራ የፌስቡክ ማኅበረሰብን ገንብቷል።
ናድያ የመጀመሪያ ልጇ ከተወለደች በኋላ ድብርት እና ጭንቀት ገጥሟት ታሪኳን ለማካፈል በምግብ ዝግጅት ክፍለ-ጊዜ ላይ ትገኛለች።
"ሐዘኑ ማለቂያ የሌለው ነበር። እንቅልፍ ባይኔ፣ ምግብ ባፌ አይዞርም ነበር፤ በጣም መጥፎ ነበር" ትላለች።
"ያለ ግልጽ ምክንያት ማልቀስ ትጀምራለች ወይም ትበሳጫለች" የሚለው ባለቤቷ ራኬን፤ "ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም ነበር" ሲል ያስታውሳል።
ነገር ግን በምግብ ዝግጅት ክፍለ-ጊዜዎቹ ላይ ሲገኝ እንዴት እንደሚደግፋት - ማጽዳት፣ የሽንት ጨርቅ መቀየር እና ልጃቸውን መንከባከብ እንደተማረ ተናግሯል።
"አሁን ባለቤቴ ስታለቅስ ወይም የደከመች መስሎ ከታየኝ ምን ማድረግ እንዳለብኝ የተሻለ ግንዛቤ አለኝ" ይላል።
ናድያ መድኃኒት እና ምክር አግኝታለች ሌሎች እናቶችም ማገገም እንደሚቻል እንዲያውቁ ትፈልጋለች።
ጥንዶቹ አንዲት የአምስት ዓመት ሴት እና የሦስት ዓመት ወንድ ልጆች አሏቸው። ራኬን ነገሮች አስቸጋሪ ሲሆኑ ማረጋገጫ ይሰጣል። "'ጥሩ እናት መሆን አልችልም' ስትል…መሆን እንደምትልችል መናገር አለብኝ" ሲል አክሎ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Nur Yanayirah
ቢቢሲ በሦስት ሀገራት ከራሳቸው ልምድ በመነሳት የእናቶችን የአእምሮ ጤና የሚደግፉ መሠረታዊ ውጥኖችን ሰምቷል።
በዓለም ጤና ድርጅት የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ኔርጃ ቻውድሃሪ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት የሕይወት ተሞክሮ "መተማመንን እና ተዛማጅነትን እንደሚያሳድግ"፣ የአቻ ደጋፊዎቸ የአእምሮ ጤና ድጋፍ በመስጠት "ውጤታማ ወኪሎች" ያደርጋቸዋል።
ማኅበረሰቡን መሠረት ባደረገ ዝቅተኛ ወጪ የሚደረግ ድጋፍ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የእናቶችን የአእምሮ ጤንነት በእጅጉ እንደሚያሻሽል ተናግረዋል። በቂ ሥልጠና እና የአቻ ለአቻ ድጋፍ ክትትል "አስፈላጊ" መሆኑንም ያክላሉ።
አንጊ ማኮርንጎ የምትኖረው ከኢንዶኒዢያ ከ8,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ በዚምባብዌ ነው። የራሷ የአእምሮ ጤና ትግል አንድን ነገር እንድታደርግ አነሳሳት።
ከ27 ዓመታት በፊት ሴት ልጇን ከወለደች በኋላ በሚያስደነግጡ ሃሳቦች ራሷን ተውጣ አገኘችው።
"ይህን ትራስ ይዤ 'ልጄን ባፍናትስ' ብዬ ሳስብ ትዝ ይለኛል" ስትል ታስታውሳለች። "ሌላ ጊዜ፣ ምን ላደርግ እንደምችል በመፍራት ጩቤ ይዤ ወጥ ቤት ውስጥ እቆም ነበር።"

የፎቶው ባለመብት, OCD Trust
ከጊዜ በኋላ በእርግዝና ወቅት ወይም ልጅ ከወለዱ በኋላ በአንድ ዓመት ውስጥ ሊፈጠር በሚችል እና በፕሪናታል ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር (POCD) በተሰኘው የጭንቀት ሁኔታ እየተሰቃየች እንደሆነች ተረዳች።
ስለ ቤተሰቧ ለመናገር ስለ ፈራች ካህናትን አማከረች። ነገር ግን ካህናቱ በአእምሯዋ የሚመላለሱትን አስደንጋጭ ሃሳቦች እንደ ኃጢያት ነበር የሚመለከቱት ትላለች። ይህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲሰማት እና ብቸኛ እንድትሆን አድርጓታል።
ሴት ልጇ በአሥራዎቹ ዕድሜ ስትደርስ አንጊ 'ኦሲዲ' እንዳለባት ካወቀች በኋላ መድኃኒት ታዘዘላት። "እንደገና የተወለድኩ ያህል ተሰማኝ" ትላለች።
ከዚህ በኋላ 'ኦሲዲ' ትረስት የተባለ ድርጅት መሠረተች። አሁን በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በራዲዮ ንግግሮች እና በወርክሾፖች ግንዛቤን ታስጨብጣለች፤ የቤተሰቧንም ቤት የድጋፍ ወደ ድጋፍ ማዕከልነት ቀይራዋለች።
የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ታፋዝዋ ሙጋዛምቢ-መኪ በዚምባብዌ በእናቶች የአእምሮ ጤና ድጋፍ ላይ ለረጅም ጊዜ "ትልቅ ክፍተት" ነበር ይላሉ።
ሦስት ልጆች አሏት፣ ነገር ግን የፅንስ መጨንገፍ እና በሕክምና ድጋፍ ፅንስ ለመያዝ ሳትችል ቀርታ አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሟታል። በሀገሯ ውስጥ የአእምሮ ጤና "በአፈ ታሪክ እና በመገለል የተከበበ" መሆኑን እንደተገነዘበች የምትናገረው ባለሙያዋ 'ሳልት አፍሪካ' የተሰኘ ድርጅት አቋቋመች።
የስሙ ትርጓሜ "Someone Always Listens To You" ["አንድ ሰው ሁልጊዜ ያዳምጥሻል"] የሚል ሲሆን፣ በዋና ከተማዋ ሃራሬ በሚገኘው ምቡያ ነሀንዳ የእናቶች ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎት ይሰጣል።

የፎቶው ባለመብት, SALT Africa
በመጀመሪያው ፎቅ ላይ የሚገኝ አንድ የግል ክፍል ግድግዳ በጽጌሬዳ አበቦች ተውቧል። በክፍሉ ማዕዘን ላይ አንድ የሕጻናት አልጋ አለ።
እዚህ ክፍል ውስጥ፣ ልጆቻቸው የሞቱባቸው ቤተሰቦች የልጆቻቸውን አስከሬን ማየት እና መያዝ ይችላሉ፣ ይህም የተከሰተውን ለመቀበል እና ለመረዳት ያግዛቸዋል። 'ሳልት አፍሪካ' ይህን ክፍል ያዘጋጀቸው ስምነተኛ ልጃቸው ከወሊድ በፊት ያጣ ቤተሰብን ካገዘ በኋላ ነው።
በሕንጻው የምድር ክልፍ ላይ ደግሞ በወሊድ ጊዜ ልጅ ላጡ እናቶች ልዩ ክፍል አቋቁሟል።
'ሳልት አፍሪካ' በተጨማሪም ያለ ጊዜያቸው የተወለዱ ሕጻናት ያሏቸውን እናቶችን ይደግፋል፣ ወ/ሮ ሙጋዛምቢ-መኪ "ብዙ የመሳለቂያ እና የሴሰኝነት ውንጀላዎች" ሊገጥማቸው ይችላል ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, CHIME Project
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት በእርግዝና ወቅት ሴቶችን ስለ አእምሮ ጤና ቀደም ብሎ ማስተማር አስፈላጊ ነው። ይህ በጋምቢያ ውስጥ የሚገኝ አንድ ፕሮግራም ትኩረት ነው።
በደማቅ ቀለም ያሸበረቀ ልብስ የለበሱ የሴቶች ቡድን በእጆቻቸው እያጨበጨቡ በሚፈጥሩት የከበሮ ምት ይወዛወዛሉ።
አንዷ ዘፋኝ ድምጿን ከፍ አድርጋ ታንጎራጉላቸው፤ ሌሎቹም መልሰው ይዘፍናሉ። አንዳንድ ነፍሰ ጡር ሴቶች ለመደነስ ተነሱ።
ዘፈኑ አስደሳች ነው፥ ነገር ግን ለወደፊት እናቶች ስለ አካላዊ እና አእምሮአዊ ጤንነት ከባድ መልዕክቶችን ያስተላልፋል - መድኃኒቶችን ከመውሰድ እስከ ጭንቀትን ማስወገድ።
የማኅበረሰብ ጤና ድጋፍ በሙዚቃ ተሳትፎ ፕሮጄክት ጭንቀትን ለመቀነስ፣ መነቃቃትን ለመፍጠር እና ሰዎችን በማኅበራዊ ግንኙነት ለማስተሳሰር እነዚህን የሙዚቃ ስብስቦች የመጠቀም ዓላማ አለው።

የፎቶው ባለመብት, CHIME Project
የሙዚቃ ተጫዋቾቹ ካንዬሌንግ የሚባሉት በሙዚቃ እና በጨዋታ አዋቂነታቸው ሚታወቁ የባህል አስተላላፊዎች ናቸው።
እንደ ሰርግ ባሉ ዝግጅቶች ላይ በብዛት ይታያሉ። በተፈጥሮ በመካንነታቸው ልጅ መውለድ ያልቻሉ ወይም የልጅ መጥፋት ያጋጠማቸው ሴቶች ናቸው።
የጋምቢያ ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ጃራራ ማሬጋ እንደተናገሩት ከችግር ያገገሙ እና አሁን ሌሎችን በመርዳት ላይ ያሉ "ቁስለኛ ፈዋሾች" ተደርገው ይታያሉ።
ሥራቸው "ከጠንካራ ባህል እና አፈታሪክ ጋር ይጣጣማል" ይላሉ። "ሙዚቃ በተፈጥሮው መሰናክሎችን ያፈርሳል።"
በዩናይትድ ኪንግደም እና በደቡብ አፍሪካ ተመራማሪዎች የተመራው ጥናት እንዳመለከተው በእንደዚህ ዓይነት ክፍለ ጊዜዎች ላይ በሚሳተፉ ነፍሰ ጡር እናቶች ላይ የድብርት ምልክቶች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ተናግረዋል።
ከዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና ምርምር ተቋም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በደቡብ አፍሪካ እና በሌሱቶ ተመሳሳይ ሥራዎች እየተሞከሩ ነው።
እንደ ኢንዶኔዢያ እና ዚምባብዌ ያሉ መገለሎች እና አለመግባባቶች እዚህም ችግሮች ናቸው። ይሁን እንጂ እንደ አንጊ እና ኑር ላሉ ሴቶች የራሳቸውን ታሪክ መናገር ለውጥ አምጥቷል።
"በተናገርኩ ቁጥር፣ በማገገም ላይ የበለጠ እጠነክራለሁ" ትላለች አንጊ።















