የሲያድ ባሬ አስከሬን በድብቅ ከናይጄሪያ ወደ ሶማሊያ የተወሰደበት ምሥጢራዊ በረራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ልክ ከ31 ዓመታት በፊት ነው። ሁለት የኬንያዊያን አብራሪዎች ሁሴን መሐመድ አንሹር እና መሐመድ አዳን በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በሚገኘው ዊልሰን አየር ማረፊያ ቢሯቸው ያልጠበቁት እንግዳ ጎበኛቸው።
እንግዳቸው የናይጄሪያ ዲፕሎማት ነበሩ። በ80 ዓመታቸው ያረፉትን የቀድሞውን የሶማሊያ መሪ ሲያድ ባሬን አስከሬን ተሰደው ከኖሩበት ናይጄሪያ ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ከባድ እና ምሥጢራዊ ተልዕኮ ሰጧቸው።
አንሹር ቀደም ሲል በኬንያ አየር ኃይል ውስጥ በአብራሪነት አገልግለዋል። በኋላም ከአዳን ጋር በመሆን ብሉበርድ አቪዬሽንን ኬንያ ውስጥ አቋቁመዋል።
አንሹር በጉዳዩ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየት ሲሰጡ ይህ ከቢቢሲ ጋር ያደረጉት ቆይታ የመጀመሪያቸው ነው።
የናይጄሪያው ዲፕሎማት "በቀጥታ ወደ ጉዳዩ ገቡ" ይላሉ። እሳቸው እና ሁሴን "በኪራይ አውሮፕላን አስከሬኑን በድብቅ ከናይጄሪያ ዋና ከተማ ሌጎስ እንዲያጓጉዙ" ጠየቋቸው።
ጉዞው በደቡብ ሶማሊያ ወደምትገኘው የባሬ የትውልድ ከተማ ወደ ገርባሃሬይ ነው። በሁለቱ ከተሞች መካከል ወደ 4,300 ኪሎ ሜትር ርቀት አለ።
አንሹር በጥያቄው እንደተገረሙ አልደበቁም። "ይህ የተለመደ ሥራ እንዳልሆነ ወዲያውኑ አውቀናል" ብለዋል።
ሲያድ ባሬ ታላቋን ሶማሊያ ለመመሥረት በነበራቸው ህልም ምክንያት ከጎረቤቶቻቸው በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ያደረጉት ጦርነት መንግሥታቸውን አዳክሞታል።
በተለያዩ የሶማሊያ ክፍሎች ሲካሄዱ የነበሩ የአማጺያን እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው በአውሮፓውያኑ ጥር 28 ቀን 1991 ወደ ዋና ከተማዋ ሲደርሱ አገሪቱ ውስጥ ሌላ ዙርት የእርስ በርስ ጦርነት ተቀስቅሷል።
ሲያድ ባሬም ሥልጣናቸውን ብቻ ሳይሆን አገራቸውን ለቅቀው በውጪ አገር በስደት ከቆዩ በኋላ በህመም ምክንያት ሕይወታቸው ሲያልፍ አስከሬናቸውን ወደ ሶማሊያ ለመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረ።
ነገር ግን አስከሬናቸውን ወደ ትውልድ አገራቸው መመለሱ ፖለቲካዊ ውጥረት የበዛበት ነበር። የበርካታ ባለሥልጣናትን፣ የደካማ የክልል ግንኙነት መረብን እና የዲፕሎማሲያዊ ውድቀትን ሊያስከትል ይችላል።
በረራው ከተለመደው አሠራር ውጭ እንዲከናወን ዲፕሎማቱ መጠየቃቸው አንሹር ስጋት እንዲገባቸው አድርጎ ነበር።
"የኬንያ ባለሥልጣናት ቢያውቁ ከባድ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችሉ ነበር" ብለዋል አንሹር።
አብራሪዎቹ ጥያቄውን እንቀበል ወይስ አንቀበል በሚለው ላይ ለመወሰን ቀኑን ሙሉ ሲወያዩ ዋሉ። በወቅቱ በፕሬዝዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ የሚመራው የኬንያ መንግሥት ጉዳዩን ቢደርስበት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲያወጡ እና ሲያወርዱ ቆዩ።
በ1969 ባሬ በመፈንቅለ መንግሥትነበር የሶማሊያን የመሪነት ሥልጣን ተረከቡት። ደጋፊያቸው ፓን-አፍሪካኒስት ናቸው ሲሉ ያሞካሿቸዋል። የደቡብ አፍሪካ የዘረኛ ሥርዓትን መቃወማቸውን ደግሞ በምክንያትነት ያሳሉ።
ተቺዎቻቸው ደግሞ ከሥልጣን እስኪባረር ድረስ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ አምባገነን ናቸው ይሏቸዋል።
ባሬ መጀመሪያ ላይ ወደ ኬንያ ሸሹ። የሞይ አስተዳደር ከአገሪቱ ፓርላማ እና ከሰብዓዊ መብት ቡድኖች ከፍተኛ ጫና ደረሰበት። ባሬ ወደ ናይጄሪያ አቀኑ፣ የፖለቲካ ጥገኝነት ተሰጣቸው። ወታደራዊው መሪ ጄነራል ኢብራሂም ባንዳባጊዳ ዘመን ወደ ሌጎስ አቅንተው በስኳር በሽታ ምክንያት እስከሞቱበት ድረስ በናይጄሪያ ኖረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Corbis/Getty Images
የተልዕኮውን አደገኛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት አብራሪዎቹ አንድ ተጨማሪ ቀን እንዲሰጣቸው የናይጄሪያውን ዲፕሎማት ጠየቁ። የሚያገኙት ገንዘብ ትልቅ ነበር። ትክክለኛውን መጠን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። አብረውት የነበሩት አደጋዎቹም ግን ከፍተኛ ነበሩ።
"የናይጄሪያ የአየር ኃይል አውሮፕላንን ለመጠቀም ምክረ ሃሳብ አቀረብን። ፈቃደኛ ግን አልሆኑም" ሲሉ አንሹር ያስታውሳሉ። "ሥራው በጣም ምሥጢራዊ በመሆኑ የኬንያ መንግሥት ምንም መረጃ ሊሰጠው እንደማይገባ ነገሩን።"
ስለጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመገናኛ ብዙኃን የተናገሩት የቀድሞው የሶማሊያ መሪ ልጅ አያንሌ መሐመድ ዚያድ ባሬ "ምሥጢራዊ የተደረገው ሕገወጥ የሆነ ነገርን ለመደበቅ በሚል አልነበረም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በእስልምና እምነት የቀብር ሥነ ሥርዓት በፍጥነት መፈጸም እንዳለበት አስረድተዋል። አንዳንድ መንግሥታት ዕቅዱን ቢያውቁትም መደበኛ ሂደቶች ተጥሰዋል።
"ጊዜ አልነበረንም። መደበኛውን አካሄድ ብንከተል የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ያዘገየው ነበር።"
የናይጄሪያ ባለሥልጣናት የጋርባሃሬይ የአውሮፕላን ማረፊያ ማኮብኮቢያ ለወታደራዊ አውሮፕላን "በጣም ትንሽ" እንደሆነ ነግረውኛል ብለዋል።
"ለዚህም ነው የብሉበርድ አቪዬሽንን ማነጋገር ያስፈለገው" ሲሉ የባሬ ልጅ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በወቅቱ አብራሪዎቹ ከባሬ ቤተሰብ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም። በኋላም ውሳኔያቸውን ለናይጄሪያዊው ዲፕሎማት ጥር 10 ቀን 1995 (እአአ) መንገራቸውን አንሹር ያስታወሳሉ።
"ቀላል ምርጫ አልነበረም። ጉዞውን ለማከናወን ኃላፊነት እንዳለብን ግን ተሰምቶናል" ሲሉ አንሹር ተናግረዋል።
ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ጋር በሥራ ምክንያት ሲገናኙ ግን ይህ የመጀመሪያቸው አልነበረም።
የሲያድ ባሬ ቤተሰባቸው ዋና ከተማዋን ሞቃዲሾን ሸሽተው ጋርባሃሬይ ክልል ውስጥ ወደምትገኘው ቡርዱቦ አቀኑ።
በወቅቱ አብራሪዎቹ ለባሬ ቤተሰብ ምግብ፣ መድኃኒት እና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን ወደ ቡርዱቦ አድርሰዋል።
የባሬን አስከሬን ይዘው ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ግን የናይጄሪያ መንግሥት ዋስትና እንዲሰጣቸው አብራሪዎቹ ጠየቁ።
"በፖለቲካዊ መንገድ የሆነ ስህተት ከተፈጸመ ናይጄሪያ ኃላፊነቱን መውሰድ ነበረባት" ብለዋል አንሹር። "ለዚህም ደግሞ ሁለት የኤምባሲ ሠራተኞች አብረው እንዲበሩ ተደረገ።"
ናይጄሪያ ተስማማች። አብራሪዎቹ ተልዕኳቸው ምሥጢራዊ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ የነደፉት ዕቅድ ተሳካላቸው።
ጥር 11 ቀን ከቀኑ 9፡00 ሰዓት በኋላ ቢችክራፍት ኪንግ ኤር ቢ200 የተሰኘ አነስተኛ አውሮፕላናቸው ከናይሮቢ ዊልሰን አየር ማረፊያ ተነሳች።

አብራሪዎቹ መዳረሻቸው በምዕራብ ኬንያ የምትገኘው ኪሱሙ እንደሆነች ተናግረው ጉዞ ጀመሩ።
"ዕቅዱ በወረቀት ላይ ብቻ የሰፈረ ነበር። ወደ ኪሱሙ ስንቃረብ ራዳር አጥፍተን ወደ ኡጋንዳ ኢንቴቤ አመራን" ብለዋል አንሹር።
በወቅቱ አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የራዳር ሽፋኑ የተገደበ ነበር። አብራሪዎቹ ይህንን ከፍተት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አውቀውታል።
ኢንቴቤ ደረሱ፤ አብራሪዎቹ ለአየር ማረፊያው ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ ከኪሱሙ እንደመጣ ገለጹ። ሁለቱ የናይጄሪያ ባለሥልጣናት ምንም እንዳይነጋሩ እና ከአውሮፕላን እንዳይወርዱ ታዘዋል።
አውሮፕላኑ ነዳጅ ሞልቶ ቀጣዩ መዳረሻው ያውንዴ ካሜሩን ሆነ። ያውንዴ ላይ የናይጄሪያ ዲፕሎማቶች ሥራውን ለማስተባበር እየጠበቋቸው እንደነበር አንሹር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ያውንዴ ላይ አጭር ቆይታ አድርገው አውሮፕላኑ ጉዞውን ወደ ሌጎስ አደረገ። አውሮፕላኑ ወደ ናይጄሪያ የአየር ክልል ከመግባቱ በፊት የናይጄሪያ ባለሥልጣናት አብራሪዎቹ ጥርጣሬ እንዳይፈጠር "ደብሊውቲ 001" የሚል የናይጄሪያ አየር ኃይል ስም እንዲጠቀሙ ትዕዛዝ ደረሳቸው።
"ዝርዝር ጉዳይ አስፈላጊ ነበር። ያ ባይሆን ጥያቄ ሊቀርብብን ይችል ነበር" ብለዋል አንሹር።
ጥር 11 ከሰዓት 7 ሰዓት ገደማ ሌጎስ ደረሱ። የባሬ ቤተሰብ አባላት እየጠበቋቸው ነበር።
ቀኑን ሙሉ እረፍት ካደረጉ በኋላ አብራሪዎቹ የባሬን አስከሬን ወደ ሶማሊያ ጋራባሃሬይ ይዘው ስለሚመለሱበት ጉዞ የመጨረሻ ዝግጅት አደረጉ።
ጥር 12 ቀን 1995 የአስከሬኑ የእንጨት ሳጥን አውሮፕላኑ ላይ ተጫነ። ሁለቱ የናይጄሪያ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ተሳፍረዋል። ልጃቸው አያንሌ መሐመድ ሲያድ ባሬን ጨምሮ ስድስት የቤተሰቡ አባላት የጉዞው አካል ተደርገዋል።
አብራሪዎቹ የመልስ ጉዞውም ምሥጢራዊነቱ እንዲጠበቅ ፈልገዋል።
"በካሜሩን፣ በኡጋንዳ ወይም በኬንያ ለሚገኙ የአየር ማረፊያ ባለሥልጣናት አስከሬን እንደጫንን አልነገርናቸውም። ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ ነበር" ብለዋል ሁሴን"
አውሮፕላኑ ሲመለስ ወደ ኢንቴቤ ከመብረሩ በፊት ለአጭር ጊዜ በያውንዴ ቆሞ ነዳጅ ሞላ። የኡጋንዳ ባለሥልጣናት የአውሮፕላኑ መዳረሻ ምዕራብ ኬንያ ኪሱሙ እንደሆነ ተነግሯቸዋል።
በድጋሚ ወደ ኪሱሙ ሲቃረቡ አብራሪዎቹ አቅጣጫቸውን ቀይሩ። በረራቸውን በቀጥታ ወደ ጋራባሃሬይ አደረጉ።
አስከሬኑ ወርዶ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሲፈጸም የተገኙት አንሹር እና ባልደረባው ጉዟቸውን ወደ ዊልሰን መመለስ ጀመሩ። ወደ ኬንያ ባደረጉት በረራ ሁለቱ የናይጄሪያ ባለሥልጣናት አብረዋቸው ተሳፍረው ነበር።
ይህ ከጉዟቸው "በጣም አስጨናቂው" ክፍል ሆኖ እንዳገኙት አንሹር ተናግረዋል።
"'እዚህ ነው ልንያዝ የምንችለው' ብለህ ታስባለህ።"
አብራሪዎቹ እንዳይያዙ በመፍራት ለዊልሰን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ ከምትገኘው ማንዴራ እየመጡ መሆኑን ተናገሩ። ይህም የአገር ውስጥ በረራ እንደሆነ እንዲሰማቸው ለማድርግ ነበር።
ማንም ጥያቄ አላነሳምም። "ያኔ ነው ምንም እንደማንሆን ያወቅነው" ብለዋል አንሹር።
አሁን ተልዕኮዋቸው ተጠናቀቀ።
"በኋላ ላይ ነበር ያደረግነው ነገር ምን እንደሆነ በትክክል የገባን" ሲል አንሹር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አሁንም ተመሳሳይ ተልዕኮ ይፈጽም እንደሆን ሲጠየቅ "አሁን 65 ዓመቴ በመሆኑ አልሞክረውም። ደግሞ ተመሳሳይ ተልዕኮ ላይ አልሳተፈም፤ ምክንያቱም የአቪዬሽን ቴክኖሎጂው በጣም ስለተሻሻለ አፍሪካ ውስጥ በቂ የአየር ትራፊክ ራዳር ሽፋን አለ።"
"አሁን በ1995 የነበረውን ዓይነት የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ክፍተቶችን መጠቀም ፈጽሞ የማይቻል ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Hussein Mohamed Anshuur















