ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ የሚያካሂዱትን ጦርነት ለመገደብ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢራን በሚያካሄደው ጦርነት ላይ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣንን ለመገደብ ያለመ በሁለቱ ፓርቲዎች የቀረበው የውሳኔ ሃሰብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ።
ይህ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአገራቸውን ምክር ቤት ፈቃድ ሳያገኙ ወታደራዊ እርምጃ እንዳይወስዱ ለመከልከል የታሰበው የውሳኔ ሃሳብ በ53 ተቃውሞ ውደቅ ሲሆን የደገፉት 47 ናቸው።
ዴሞክራቶች ትራምፕ የአሜሪካ ምክር ቤትን ሥልጣን ወደ ጎን ገፍተዋል በሚል ተችተዋል። በምክር ቤቱ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ የትራምፕ ፓርቲ አባላት የውሳኔ ሃሳቡን የተቃወሙት ሲሆን፣ ነገር ግን ጦርነቱ በሚመጡት ሳምንታት እየሰፋ የሚሄድ ከሆነ ሀሳባቸውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የተጀመረው ይህ ጦርነት እስከ ስምንት ሳምንታት ሊቆይ እንደሚችል የመከላከያ ሚኒስትሩ ፔት ሄግሴት ተናግረዋል፤ ይህ ትራምፕ ከሰጡት ጊዜ በእጥፍ የሚበልጥ ነው።
የምክር ቤት አባላቱ በፓርቲ ደረጃ ድጋፍ እና ተቃውሟቸውን በተመሳሳይ የገለጹ ሲሆን፣ አንዲት የሪፐብሊካን ፓርቲ የምክር ቤት አባል ውሳኔውን መደገፍ "ለኢራን እና ለአሜሪካ ወታደሮች የተሳሳተ መልዕክት ማስተላለፍ ነው" ብለዋል።
የዲሞክራቶች መሪው ቻክ ሹመር ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት ባደረጉት ንግግር "በመካከለኛው ምሥራቅ በሚካሄደው ያልተቋረጠ ጦርነት ከተሰላቸው የአሜሪካ ሕዝብ ጋር ትቆማለችሁ ወይስ ወደ ሌላ ጦርነት እያስገቡን ካሉት ዶናልድ ትራምፕ እና ፔት ሄግሴት ጋር ትቆማለችሁ?" ሲሉ ጠይቀው ነበር።
ይህ የውሳኔ ሐሳብ በምክር ቤቱ አባላት ውድቅ ቢደረግም ዛሬ ደግሞ ወደ ሌላኛው ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል፤ ነገር ግን ተቀባይነት የማግኘቱ ነገር አጠያያቂ ነው።
በአሜሪካ ሕግ መሠረት ፕሬዝዳንቱ በይፋ ሳያውጅ በራሱ ውሳኔ ጦርነት ማካሄድ የሚችል ሲሆን፣ ነገር ግን በ48 ሰዓት ውስጥ ለኮንግረሱ ማሳወቅ ይጠበቅበታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ እንደተናገሩት የትራምፕ አስተዳደር በሕግ የሚጠበቅበትን ሂደት አክብሮ እየሠራ መሆኑን በመጥቀስ ፕሬዝዳንቱን ተከላክለዋል።።
በኢራን ላይ ጦርነቱ ከመከፈቱ በፊት ከፍተኛ የምክር ቤት አባላት እንዲያውቁ መደረጋቸውን እና ምንም እንኳን አስፈላጊ አልነበረም ቢሉም ሰኞ ዕለት ደግሞ ትራምፕ ለምክር ቤቱ እርምጃቸውን በደብዳቤ ገልጸዋል።
ትራምፕ ከዚህ በፊት በኢራን ላይ የአየር እና የሚሳዔል ድብደባ ሲፈጸም እና የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንትን በያዙበት ጊዜ ከአገራቸው ምክር ቤት ምንም ዓይነት ፈቃድ አልጠየቁም ነበር።
የአሜሪካ ምክር ቤት ፕሬዝዳንቶች የምክር ቤቱን ፈቃድ ሳያገኙ ወደ ጦርነት እንዳይገቡ የሚከለክለውን ሕግ ያሳለፈው በአውሮፓውያኑ 1973 ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን በቬትናም የሚያደርጉትን ጦርነት ከመገደብ ነበር።
ሕጉ ፕሬዝዳንቶች ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቁ እና ምክር ቤቱ ደግሞ ጦርነቱ በጀመረ በ60 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል።
ከዚህ ቀደም ከ25 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ላይ የተፈጸመውን ከባድ የሽብር ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካ ምክር ቤት በመካከለኛው ምሥራቅ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ፈቃድ ሰጥቶ ነበር።
በተለያዩ ጊዜያት የአሜሪካ መሪዎች ወታደራዊ እርምጃ ሲወስዱ ከምክር ቤቱ ፈቃድ እንዲጠይቁ የሚያስገድደው ሕግ እንዲሰረዝ ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም ሳይሳኩ ቀርተዋል።















