ቀጥታ, አሜሪካ እያደነችው የነበረውን በሩሲያ ባንዲራ የሚንቀሳቀስ የነዳጅ መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች

በአውሮፓ የአሜሪካ ዕዝ ከቬንዙዌላ ነዳጅ ጋር ግንኙነት ያለው እና በአሜሪካ ሲታደን የነበረው ነዳጅ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታወቀ። ዕዙ የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር እና የሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤትን ዋቢ አድርጎ “ኤም/ቪ ቤላ 1 የአሜሪካን ማዕቀብ በመጣሱ” በቁጥጥር ሥር ውሏል ብሏል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዩኬ ለአሜሪካ ድጋፍ ማድረጓን ስትገልፅ ሩሲያ የአሜሪካን ተግባር ኮንናለች

    በአውሮፓው የአሜሪካ ዕዝ ያጋራው ምስል

    የፎቶው ባለመብት, US EUROPEAN COMMAND

    የሩሲያ ትራንስፖርት ሚኒስትር “የትኛውም ሀገር በአንድ ሀገር የተመዘገበ መርከብን በኃይል የመያዝ መብት የለውም” የሚል መግለጫ አውጥቷል።

    በቀድሞ ስሙ ቤላ 1 ተብሎ የሚታወቀው የነዳጅ መርከብ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር መዋሉን ተክተሎ ነው ሩሲያ መግለጫ ያወጣችው።

    አሜሪካ ከቬንዙዌላ ነዳጅ ጋር ግንኙነት ያለው መርከብ ማዕቀብ ጥሷል በማለት አድና በቁጥጥር ሥር ማዋሏን አስታውቃለች።

    ማሪኔራ ተብሎ የሚጠራው መርከብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሩሲያ ባንዲራ ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን ሞስኮው መርከቡን ለማጀብ የባሕር ኃይሏን አሰማርታ ነበር።

    የሩሲያ መግለጫ እንደሚጠቁመው በሞስኮው ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 9 ሰዓት የአሜሪካ ኃይሎች መርከቧን በቁጥጥራቸው ስር ካዋሉ በኋላ ከመርከቡ ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋርጧል ብሏል።

    ሚኒስቴሩ አክሎ እንደገለፀው ማሪኔራ ከአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ጀምሮ “በጊዜያዊ ፈቃድ” በሩሲያ ባንዲራ ሲንቀሳቀስ ነበር።

    በተያያዘ ዜና ዩናይትድ ኪንግደም አሜሪካ መርከቡን በቁጥጥር ሥር እንድታውል ድጋፍ ማድረጓን አስታውቃለች።

    የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ መርከቡ በሰሜን አትላንቲክ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ድጋፍ ማድረጉን አስታውቆ “መርከቡ ሩሲያ እና ኢራን ማዕቀብ ጥሰው ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ዩክሬን ሽብርን፣ ግጭት እና መከራን የሚያስፋፉበት ነው” ብሏል።

    አሜሪካ ከዚህ መርከብ በተጨማሪ ሌላ ቬንዙዌላ ላይ የተጣለ ማዕቀብ የጣሰ ነው ያለችውን መርከብ ካሬቢያን ላይ በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታውቃለች።

  2. አሜሪካ እያደነችው የነበረውን የነዳጅ መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች

    በአውሮፓ የአሜሪካ ዕዝ

    የፎቶው ባለመብት, US EUROPEAN COMMAND

    በአውሮፓ የአሜሪካ ዕዝ ከቬንዙዌላ ነዳጅ ጋር ግንኙነት ያለው እና በአሜሪካ ሲታደን የነበረው ነዳጅ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታወቀ።

    ዕዙ የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር እና የሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤትን ዋቢ አድርጎ “ኤም/ቪ ቤላ 1 የአሜሪካን ማዕቀብ በመጣሱ” በቁጥጥር ሥር ውሏል ብሏል።

    “መርከቡ በአሜሪካ ፌዴራል ፍርድ ቤት በወጣበት ማዘዣ መሠረት በሰሜን አትላንቲክ በቁጥጥር ሥር ውሏል” ይላል ዕዙ በኤክስ ገፁ ያጋራው መግለጫ።

    ዩኤስሲጂሲ ሙንሮ የተባለው የአሜሪካ የጦር መርከብ ነዳጅ ጫኝ ታንከሩን ተከታትሎ እንደያዘውም አክሏል።

    በአውሮፓውያኑ 2024 ሕጋዊ ያልሆነ ነዳጅ በማመላለስ ማዕቀብ የተጣለበት መርከብ ባንዲራውንና ባለቤትነቱን ወደ ሩሲያ ቀይሮ ሲንቀሳቀስ ነበር።

    ሩሲያ ነዳጅ ጫኝ መርከቡን ለማጀብ ሰርጓጅ መርከብ ጨምሮ የባሕር ኃይሏን ብታሰማራም አሜሪካ መርከቡን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ብሏለች።

    ባለፈው ቅዳሜ የቬንዙዌላውን ፕሬዝደንት በቁጥጥር ስር ያዋለው የትራምፕ አስተዳደር ከቬንዙዌላ የሚወጡና የሚገቡ መርከቦች ላይ ማዕቀብ የጣለው ባለፈው ወር ነበር።

    መርከቡ ከዚህ ቀደም የቬንዙዌላን ነዳጅ ያመላልስ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ምንም ዓይነት ነዳጅ እንዳልጫነ ተዘግቧል።

  3. ማሪናራ የተባለው ነዳጅ ጫኝ መርከብ በአሜሪካ እየታደነ ያለው ለምንድነው?

    ማሪናራ የተሰኘው ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ከዚህ ቀደም ቤላ 1 በተባለ ስሙ የሚታወቀው ነዳጅ ጫኝ መርከብ ባለፈው ወር ወደ ቬንዙዌላ እየሄደ እንደሆነ ተዘግቦ ካሪቢያን ላይ ታይቶ ነበር።

    የአሜሪካ ባሕር ጠረፍ ጠባቂ ኃይል አባላት (ኮስት ጋርድ) መርከቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ማዘዣ አውጥተው ሲጠባበቁት ነበር። መርከቡ የአሜሪካን ማዕቀብ ጥሷል፤ የኢራንን ነዳጅ ጭኗል ስትል ዩናይትድ ስቴትስ ትወቅሳለች።

    ነዳጅ ጫኙ መርከብ ይሄኔ ነው ስሙን ብቻ ሳይሆን ሰንደቅ ዓላማውን ወደ ሩሲያ ቀይሮ የሚመጣበትን መንገድ ትቶ በሌላ አቅጣጫ መጓዝ የጀመረው።

    ከዚህ ቀደም በሐሰተኛ መንገድ በጉያና ሰንደቅ ዓላማ ይንቀሳቀስ ነበር። የቬንዙዌላን ነዳጅ በማመላለስ የሚታወቀው መርከብ አሁን ምንም ነገር እንዳልጫነ ተነግሯል።

    የአሜሪካ ኃይሎች መርከቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በሰሜን አትላንቲክ የተሰማሩ ሲሆን፣ ሩሲያ ደግሞ መርከቡን ከአሜሪካ ኃይሎች ለመጠበቅ በሰርጓጅ መርከብ ታግዛ ለማጀብ ተንቀሳቅሳለች።

    መርከቡ በድንገት አቅጣጫውን ወደ ደቡብ ቀይሮ በአሁኑ ወቅት ከአይስላንድ ጠረፍ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ቢቢሲ ያረጋገጠው መረጃ ያሳያል።

  4. “በሕገ-ወጥ ደላሎች ተታለው ከሀገር ሊወጡ የነበሩ” 7900 ሰዎች መያዙን የአፋር ክልል ፖሊስ አስታወቀ

    የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ቢል አህመድ

    የፎቶው ባለመብት, Afar Police/FB

    የአፋር ክልል ፖሊስ በሕገ-ወጥ ደላሎች ተታለው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሀገር ሊወጡ የነበሩ 8 ሺህ ገደማ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።

    ባለፉት 6 ወራት ብቻ 7900 ሰዎች በሕገ-ወጥ መንገድ በአፋር በኩል ከሀገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ያወጣው መግለጫ ያሳያል።

    የፖሊስ ኮሚሽነር ቢልኤ አህመድ “በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ሰዎች መነሻቸው እና መድረሻቸው አፋር ክልል አለመሆኑ ሁኔታዎች አስቸጋሪ አድርጎብናል” ማለታቸውን የክልሉ ፖሊስ በፌስቡክ ገፁ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    ቢሆንም የክልሉ ፖሊስ የዝውውር መስመር ናቸው ባላቸው ቦታዎች ላይ ቁጥጥር እና ፍተሻ በማድረግ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ነበር የተባሉ ሰዎችን መያዙን ገልጿል።

    በፖሊስ የተያዙት ሰዎች “አስፈላጊው እንክብካቤ ተደርጎላቸው በአፋር ክልል ወጪ ወደመጡባቸው ከተማዎች ተመልሰዋል” ይላል መግለጫው።

    ኮሚሽነሩ በአብዛኛው የሕገ-ወጥ ዝውውር መነሻዎች ከአማራ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ከአማራ ክልል ጋር ሁኔታውን ለመቆጣጠር እየሠራን ነው ብለዋል።

    ማክሰኞ ዕለት ከሀገር ሊውጡ የነበሩ 85 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የጭነት መኪና ተገልብጦ 22 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

    የግለሰቦቹ የመጨረሻ መዳረሻ በግለፅ ባይታወቅም መስመሩ በጂቡቲ አድርገው፤ በቀይ ባሕር በኩል ወደ የመን ቀጥሎም ወደ ሳዑዲ አራቢያና ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሚጓዙ ስደተኞች የሚጠቀሙበት ነው።

  5. የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከ40 ዓመት ገደማ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶማሊያን ሊጎበኙ ነው

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋንግ ዪ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፤ ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት ለሚቆይ ይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ እና ሌሶቶ ሊጓዙ መሆኑን መሥሪያ ቤታቸው አስታወቀ።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመጨረሻ ጊዜ በሶማሊያ ጉብኝት ያደረጉት በአውሮፓውያኑ በ1980ዎቹ እንደሆነ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

    ከዛሬ ታኅሣሥ 29 እስከ የሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ጥር 4/2018 ዓ.ም. የሚቆየው ጉዞ፤ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲሱ አውሮፓውያን ዓመት የሚያደርጉት የመጀመሪያው ጉብኝት እንደሚሆን መግለጫው ያስረዳል።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላለፉት 36 ተከታታይ ዓመታት፤ የዓመቱ የመጀመሪያ የውጭ ጉዞ መዳረሻቸውን ወደ አፍሪካ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሷል። ዋንግ ዪ ወደ አራቱ አገራት የሚጓዙት በቀረበላቸው ግብዣ አማካኝነት ነው ተብሏል።

    ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አፍሪካ መዳረሻዎች መካከል በቀዳሚነት የተጠቀሰችው ኢትዮጵያ ናት። በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ “በአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት በሚካሄደው የቻይና-አፍሪካ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት” እንደሚገኙ ተገልጿል።

    መግለጫው ሶማሊያን በሁለተኛነት ጠቅሷል። እንደ ሬውተርስ ዘገባ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ሶማሊያ የተጓዘው በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ሲሆን የአሁኑ ጉብኝት ከ40 ዓመታት ገደማ በኋላ የመጀመሪያው ይሆናል።

    እስራኤል ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻነቷን ላወጀችው ሶማሊላንድ የመጀመሪያውን የአገርነት እውቅና ከሰጠች በኋላ የሚደረገው ይህ ጉብኝት፤ ለሞቃዲሾ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ሊሰጥ እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል።

    የእስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና ከሰጠች በኋላ ለሶማሊያ ያላትን ድጋፍ በድጋሚ ያረጋገጠችው ቤይጂንግ፣ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ዙሪያ ተፅዕኖዋን ለማጠናከር ትሻለች። ይህ ቀጣና ወደ ቀይ ባሕር መግቢያ ከመሆኑም በላይ በስዊዝ ካናል በኩል ወደ አውሮፓ ገበያ ለሚጓዘው የቻይና ንግድ ወሳኝ መተላለፊያ መስመር ነው።

  6. ሩሲያ በአሜሪካ እየታደነ ያለውን ነዳጅ ጫኝ ታንከር ለማጀብ ሰርጓጅ መርከብ አሰማራች

    በአሜሪካ ኃይሎች እየታደነ ያለው መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Hakon Rimmereid via Reuters

    ሩሲያ የአሜሪካ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እያደረጉበት ላለው በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚጓጉዝ የነዳጅ ጫኝ መርከብን ለማጀብ ሰርጓጅ መርከብን ጨምሮ የባሕር ኃይሏን ማሰማራቷን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘገበ።

    በአሁኑ ሰዓት ምንም ዓይነት ጭነት ያልያዘው ይህ መርከብ፤ ከዚህ ቀደም የቬንዙዌላን ድፍድፍ ነዳጅ ሲያጓጉዝ ቆይቷል። ማክሰኞ ዕለት በስኮትላንድ እና በአይስላንድ መካከል እየተጓዘ እንደነበረም ተገምቷል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማዕቀብ ተጥሎባቸው ነገር ግን ወደ ቬንዙዌላ በሚገቡ እና በሚወጡ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ "እገዳ" እንዲጣል ባለፈው ወር ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር። የቬንዙዌላ መንግሥት የትራምፕን ትዕዛዝ "ዘረፋ" ሲል ገልጾታል።

    ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በአሜሪካ ኃይሎች ተያዙት የአገሪቱ የቀድሞ መሪ ኒኮላስ ማዱሮ፤ የቬንዙዌላ መንግሥት መርከቦችን በመጠቀም ወደ አሜሪካ ዕፅ ያስገባሉ የሚል ተደጋጋሚ ክስ ከትራምፕ ሲቀርብባቸው ነበር።

    የአሜሪካ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እያደረጉበት ያለው "ማሪኔራ" የተሰኘው ይህ መርከብ ከዚህ ቀደም "ቤላ 1" በሚል ስም ይንቀሳቀስ ነበር።

    ባለፈው ወር ላይ የአሜሪካ የባሕር ጥበቃ ዘብ ባለፈው በካሪቢያን ባሕር ላይ እየተጓዘ በነበረውን "ቤላ 1" መርከብ ላይ ለመውጣት ሞክሮ ነበር። ባሕር ጥበቃ ኃይሉ ይህንን ያደረገው መርከቡ ወደ ቬንዙዌላ እያመራ ነው በሚል ጥርጣሬ እንደሆነ ተገልጿል።

    የአሜሪካን ማዕቀብ በመጣስ የኢራንን ነዳጅ ጭኗል የሚል ውንጀላ የቀረበበት ይህ መርከብ፤ በቁጥጥር ሥር እንዲውል የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶበት ነበር።

    ይሁን እንጂ መርከቡ በድንገት አቅጣጫውን የለወጠ ሲሆን ስሙንም "ማሪኔራ" በሚል ቀይሯል። ሲጓዝበት የነበረውን የጉያና ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ የሩሲያን እንደሰቀለም ተዘግቧል።

    የአሁኑ መርከቡ ወደ አውሮፓ የተቃረበበት እንዲሁም ወደ 10 የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደራዊ ትራንስፖርት አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች ወደ ቀጣናው የደረሱበት ጊዜ ተገጣጥሟል።

    ሩሲያ በበኩሏ በመርከቧ ዙሪያ ያለውን ሁኔታ "በስጋት እየተከታተልኩ ነው" ብላለች።

    ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ማክሰኞ ዕለት ለሲቢኤስ ኒውስ እንደገለጹት ከሆነ፤ የአሜሪካ ኃይሎች መርከቡ ላይ የመውጣት ዕቅድ አላቸው። የአሜሪካ መንግሥት መርከቡን ከማስጠም ይልቅ በቁጥጥር ስር ማዋልን እንደሚመርጥም ምንጮቹ ገልጸዋል።

  7. በዩክሬን የሰላም ስምምነት ከተደረሰ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ ጦራቸውን ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን ገለፁ

    የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ፣ የፈረንሳዩ ማክሮን እና የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ፤ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የሰላም ስምምነት የምትደርስ ከሆነ ወታደሮቻቸውን ለማሰማራት ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ ስምምነት ተፈራረሙ።

    በፓሪስ ከዩክሬን አጋሮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ዩኬ እና ፈረንሳይ ወደፊት ሊኖር የሚችል ወረራን ለመከላከል "በዩክሬን ዙሪያ ወታደራዊ ማዕከላትን እንደሚመሰርቱ" ተናግረዋል።

    በኋላ ላይ ደግሞ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ሊሰማሩ እንደሚችሉ ይፋ አድርገዋል።

    በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአውሮፓ አገራት፤ ለዩክሬን ጠንካራ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጥ ተስማምተው፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመከታተል ረገድ አሜሪካ ግንባር ቀደም እንድትሆን ሐሳብ አቅርበዋል።

    ነገር ግን ለሰላም ስምምነቱ እንቅፋት የሆነው ዋናው የግዛት ጉዳይ አሁንም በውይይት ላይ ነው።

    ሩሲያ፤ ዩክሬን ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም የውጭ አገር ጦር "ሕጋዊ ዒላማ" እንደሚሆን በተደጋጋሚ አስጠንቅቃለች።

    ሞስኮ በፈረንሳይ ዋና ከተማ ስለተፈረመው ስምምነት እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

    የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እአአ በየካቲት 2022 ዩክሬንን ላይ በከፈቱት ሙሉ ወረራ፤ በአሁን ሰዓት 20 በመቶ የአገሪቱን ግዛት በቁጥጥራቸው ሥር አስገብተዋል።

    ማክሰኞ ዕለት በፓሪስ በተካሄደው ውይይት ላይ ከ"በጎ ፈቃደኞች ጥምረት" የተውጣጡ መሪዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት ተሳትፈዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ከስብሰባው በኋላ በነበረ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ “የሰላም ስምምነት የሚደረስ ከሆነ ወደ ዩክሬን የሚላኩ ኃይሎችን ለማሰማራት ስምምነት ፈርመናል። ይህ ከዩክሬን ጎን ለረዥም ጊዜ ለመቆም ያለን ቁርጠኝነት ወሳኝ አካል ነው" ብለዋል።

    የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ከአሜሪካ ጋር በመሆን ክትትል ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

  8. በኢራን በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን አስታወቀ

    የኢራን ፖሊስ የግራንድ ባዛር የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅሟል
    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፖሊስ የግራንድ ባዛር የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅሟል

    ባለፉት 10 ቀናት በኢራን በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን አስታወቀ።

    መቀመጫውን ከኢራን ውጭ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች የዜና ኤጀንሲ (ሂራና) እንደዘገበው ከተገደሉት መካከል 34ቱ ተቃዋሚዎች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው።

    የኢራን ባለሥልጣናት በይፋ የሟቾችን ቁጥር ባያሳውቁም ሦስት የደህንነት ሠራተኞች መገደላቸውን ተናግረዋል። ቢቢሲ ፐርሺያን እስካሁን የ20 ሰዎችን ሞት እና ማንነት አረጋግጧል።

    በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በተቀሰቀሰው እና 27ቱ የኢራን ከተሞች ተስፋፍቶ በቀጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከ60 በላይ ሰልፈኞች መቁሰላቸውን እና 2,076 ሰዎች መታሰራቸውን ሂራና ገልጿል።

  9. ትራምፕ፤ ቬንዙዌላ እስከ 50 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ነዳጅ ለአሜሪካ “ታስረክባለች” አሉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ከሥልጣን ያስወገደው ወታደራዊ ዘመቻ እንዲካሄድ ትዕዛዝ የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ቬንዙዌላ እስከ 50 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ነዳጅ ለአሜሪካ “ታስረክባለች” አሉ።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ነዳጁ በገበያ ዋጋ እንደሚሸጥ እና ከሽያጩ የሚገኘውንም ገንዘብ ራሳቸው እንደሚቆጣጠሩ ተናግረዋል። ከነዳጁ የሚገኘው ገቢ ለቬንዙዌላ እና ለአሜሪካ ሕዝብ ጥቅም እንደሚውልም አክለዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት፤ አንድ ዓመት ከመንፈቅ በሚሆን ጊዜ ውስጥ የአሜሪካ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ቬንዙዌላ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ከገለጹ በኋላ ነው። አሜሪካ ኩባንያዎች በቬንዙዌላ በሚኖራቸው እንቅስቃሴ ወደ ለአገሪቱ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ያገኛሉ ብለዋል።

    ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተንታኞች፤ የቬንዙዌላን የነዳጅ ምርት ከዚህ ቀደም ወደነበረው ለመመለስ በአስር ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እና ምናልባትም አስር ዓመታትን ሊወስድ እንደሚችል አስረድተዋል።

    ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ልጥፍ፤ “የቬንዙዌላ የሽግግር ባለሥልጣን ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ጥራት ያለው እና ማዕቀብ የተጣለበት ነዳጅ ለአሜሪካ እንደሚያስረክቡ ሳበስር ደስታ ይሰማኛል” ብለዋል።

    “ይህ ነዳጅ በገበያ ዋጋ ይሸጣል። እኔም እንደ የአሜሪካ ፕሬዝዳንትነቴ፤ ገንዘቡም ለቬንዙዌላ እና ለአሜሪካ ሕዝቦች ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ እቆጣጠረዋለሁ!” ሲሉ ጽፈዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያስታወቁት፤ የቬንዙዌላ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ዴልሲ ሮድሪጌዝ የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። በሌሊት በዋሽንግተን የጸጥታ ኃይሎች ከአገራቸው ተይዘው የተወሰዱት ኒኮላ ማዱሮ በአንጻሩ፤ በተመሰረተባቸውን የእፅ ዝውውር እና የጦር መሳሪያ ወንጀል ክስ የተነሳ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

    ሰኞ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከኤንቢሲ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ነዳጅ አምራች የሆነችው ቬንዙዌላ መኖሯ ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ ያደርጋል” ብለዋል።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ የዋነኞቹን የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች ተወካዮች በዚህ ሳምንት ከትራምፕ አስተዳደር ጋር የመገናኘት እቅድ ይዘዋል።

  10. ቬንዙዌላን የሚመራት ማን ነው?. . . ፕሬዝዳን ትራምፕ መልስ. . .

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    • ከኤንቢሲ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ፕሬዝዳንቱ በአሁኑ ጊዜ ቬንዙዌላን እየመራት ያለው ማን ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እኔ” የሚል መልስ ሰጥተዋል
    • ትራምፕ አሜሪካ ከቬንዙዌላ ጋር ጦርነት ውስጥ አይደለችም በማለት "ጦርነት ላይ ያለነው ዕጽ ከሚሸጡት. . . እስረኞችን እየለቀቁ ወደ አገራችን ከሚልኩት ጋር ነው”

    የቬንዙዌላ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ማሪና ኮሪና ማቻዶ

    • ማቻዶ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት ትራምፕ በማዱሮ ላይ ለወሰዱት እርምጃ ምሥጋና አቅርበዋል
    • ለወራት ተደብቀው የቆዩት ተቃዋሚዋ በቶሎ ወደ ቬንዙዌላ መመለስ እንደንሚፈልጉ ገልጸዋል
    • ጨምረውም ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቷ ዴልሲ ሮዴሪጌዝ “ሊታመኑ የሚችሉ አይደሉም” ብለዋል

    የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ማይክ ጆንሰን

    • ለመገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ “ቬንዙዌላ ውስጥ ጦር ሠራዊት የለንም፤ ያንንም አገር በወረራ አልያዝንም” በማለት አሜሪካ ጦርነት ውስጥ እንዳልሆነች ተናግረዋል
    • አክለውም "ይህ የሥርዓት ለውጥ አይደለም" ከዚያ ይልቅ "የአንድ ሥርዓትን ባህሪ መለወጥ አስፈላጊ የሆነበት ነው”
  11. የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሶማሊያ የተቃወመችውን ጉብኝት በሶማሊላንድ አደረጉ

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን እና ፕሬዝዳንት አብዲራህማን

    የፎቶው ባለመብት, @gidonsaar

    የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን እና ፕሬዝዳንት አብዲራህማን

    ለሶማሊላንድ የመጀመሪያውን የአገርነት ዕውቅና የሰጠችው የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳአር በሐርጌሳ ጉብኝት አደረጉ።

    ሶማሊላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትመለከታት ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጉብኝት "ሕገወጥ እና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው" ስትል ጉብኝቱን ተቃውማለች።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እራሷን ከሶማሊያ በመነጠል ነጻ አገርነቷን ወዳጀችው ሶማሊላንድ ለጉብኝት ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ዕውቅናውን ከሰጡ ከአስር ቀናት በኋላ ነው።

    ጊዲዮን ሳር በሐርጌሳ ባደረጉት ጉብኝት ከሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ እና ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልናት ጋር ውይይት ያደርጋሉ የተባለ ሲሆን አስካሁን በይፋ የተነገ ነገር የለም።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ያናገራቸው ምንጭ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሶማሊላንድ ጉብኝት ማድረጋቸውን አረጋግጠው ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ከጉብኝቱ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን በኤክስ ገጻቸው ላይ ጉብኝታቸውን የሚገልጹ ፎቶግራፎች አጋርተው ከፕሬዝዳንቱ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    በተጨማሪም እስራኤል ለማን ዕውቅና እንደምትሰጥ እና ከየትኛው መንግሥት ጋር ግንኙነት እንደሚኖራት የምትወስነው ራሷ ብቻ ናት በማለት ለሶማሊላንድ ለሰጠችው ዕውቅና ያላትን አቋም አሳውቀዋል።

    በቀጣይም የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ በእስራኤል ጉብኝት እንዲያደርጉ የቀረባለቸውን ግብዣ እንደተቀበሉ ገልጸዋል።

    የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በጉብኝቱ ወቅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና በሶማሊላንድ ባለሥልጣናት መካከል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን እና ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸው መገለጹን አመልክቷል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጉብኝት "ሕገወጥ" በማለት ሶማሊያ ተቃውማ መግለጫ አውጥታለች።

    የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሚኒስትሩን ጉዞ "የሶማሊያን የግዛት ሉዓላዊነት እና አንድነትን የሚጥስ ነው" በማለት በተባበሩት መንግሥተት አባል አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው ሲል ጉብኝቱን ተቃውሟል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ጉብኝት የተደረገው ከሳምንት በፊት እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና ሰጥታ ተቃውሞ እና ውዝግብ ከተከሰተ በኋላ ነው።

    የእስራኤልን ውሳኔ ሶማሊያ እና የተለያዩ አገራት እንዲሁም ድርጀቶች ተቃውመውታል። ጉዳዩም በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በተጠራ ስብሰባ ውይይት ተደርጎበታል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳአር

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳአር
  12. የአሜሪካ እርምጃ "ዓለም አቀፍ ሕግን" የሚጥስ ነው" የተመድ ኮሚሽን

    የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ማዱሮ በአሜሪካ የጸጥታ ኃይሎች ታይዘው ሲራመዱ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን አሜሪካ ቬንዙዌላ ውስጥ የፈጸመችው ጥቃት "የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆችን የሚጥስ ነው" አለ።

    የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ ጄኔቭ ውስጥ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ "በማንኛውም አገር የግዛት እንድነት ወይም ፖለቲካዊ ነጻነት ላይ ኃይል መጠቀምም ሆነ ማስፈራራት አይገባም" ብለዋል።

    ይህ የመንግሥታቱ ድርጅት አካል ተቃውሞ የተሰማው ሰኞ ዕለት በተካሄደው የድርጅቱ ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የአሜሪካ አጋሮች ሳይቀሩ የትራምፕ ወታደራዊ እርምጃን መቃወማቸውን ተከትሎ ነው።

    ከእነዚህም መካከል የፈረንሳይ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ የማዱሮ በአሜሪካ መያዝ "አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት መርኅ እና ኃይል ካለመጠቀም መርኅ ጋር የሚቃረን ነው" በማለት ጠንከር ያለ ተቃውሞ አሰምተዋል።

    ባለፉት ሦስት ቀናት የአሜሪካንን እርምጃ በተከታታይ ስታወግዝ የነበረችው ቻይና ዛሬም የትራምፕን ውሳኔ "ግድየለሽ" በማለት ተቃውማዋለች።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አገራቸው "ከቀጣናው አገራት ጋር በጋራ የአካባቢውን ሰላም እና መረጋጋት ለመጠበቅ" እንደምትሠራ ተናግረዋል።

    ባለፈው ቅዳሜ ከመኖሪያቸው ከሚስተቻው ጋር ተይዘው ሰኞ ዕለት አሜሪካ ፍርድ ቤት የቀረቡት የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ የቻይና ወዳጅ ናቸው።

  13. የአሜሪካ መንግሥት በቬንዙዌላ ነዳጅ ላይ ከኩባንያዎች ጋር ንግግር ጀመረ

    የነዳጅ ማውቻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን በቬንዙዌላ የነዳጅ ጉዳይ ላይ ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ንግግር እየተካሄደ መሆኑን ለቱርክ የዜና ወኪል፣ አናዶሉ ተናገሩ።

    የአሜሪካ መንግሥትን በመወከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ እና የኤነርጂ ሚኒስትሩ ክሪስ ራይት ውይይቱን እየመሩት መሆናቸውን የገለጹት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት ባለሥልጣን፤ ነገር ግን የትኞቹ ኩባንያዎች ተሳተፊ እንደሆኑ ከመናገር ተቆጥበዋል።

    “ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቬንዙዌላ ውስጥ ስላሉት አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ከአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች ጋር ለመነጋገር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል" በማለት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

    የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ አሜሪካ አገሪቱን እንደምትመራ እና የነዳጅ ተቋማቷን በመጠገን ሥራቸውን እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።

    “በዓለም ላይ የትም ቦታ ላይ የሌሉ የአሜሪካ ግዙፍ ነዳጅ አምራች ኩባንያዎች ወደ ቬጀንዙዌላ ገብተው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በማውጣት በከፍተኛ ደረጃ የተበላሹትን የአገሪቱን የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ይጠግናሉ” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

  14. የኢትዮጵያ ወታደራዊ መኮንኖች ይዘውት በታየው ካርታ ላይ የኤርትራ ተቃውሞ

    የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ባለፈው ሳምንት ማብቂያ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ይዘውት በታየው ካርታ ምክንያት ኤርትራ ኢትዮጵያ ላይ ተቃውሞዋን አሰማች።

    የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል የወጣውን ካርታ ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ አሰብ እና አካባቢውን ወደ ኢትዮጵያ የሚያካትተው ካርታ "ትኩረት ለመሳብ" የሚደረግ ከመሆኑ በተጨማሪ "ጠብ ጫሪነት ነው" ብለዋል።

    ስለ ፎቶው የተጠየቁት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን “መውጣት አልነበረበትም” ሲሉ በስህተት የተለጠፈ መሆኑን እንደገለጹ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

    “ፎቶው የተቋሙ አይደለም፤ በተቋም የተሰጠ አቅጣጫ” እንዳልሆነ የተናገሩት ሜጀር ጄነራል እንዳልካቸው፤ በግለሰቦች “ተነሳሽነት” የተፈጸመ እንደሆነ አስረድተዋል።

    ዕሁድ ዕለት በተካሄደ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ምረቃ ላይ ከፍተኛ መኮንኖች ይዘውት የታየው እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተሠራጭቶ የነበረው ምሥል እንዲነሳ ተደርጓል።

    ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከ30 ዓመታት በፊት አገሪቱ ያጣችውን የባሕር በር መልሳ ማግኘት አለባት የሚል አቋም በስፋት እያራመዱ በሚገኙበት ጊዜ ነው ካርታው በወታደራዊ ምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የታየው።

    የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር ለዚህ በሰጡት ምላሽ "የኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት በ2026 አዲስ ዓመት ጅማሬ ግድየለሽ ጠብ ጫሪነት እና በጦርነት አጀንዳ ተጠምደዋል" ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

    ኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የራሷ የሆነ የባሕር በር የማግኘት አጀንዳን በማንሳት በተለያዩ መልኮች ጥረት እያደረገች መሆኗን አሳውቃለች። ባለሥልጣናቱም አገሪቱ ያላግባብ አጣችው ያሉትን የባሕር በር መልሳ እንደምታገኝ በእርግጠኝነት እየተናገሩ ነው።

    አቶ የማነ ይህንን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ፍላጎትን "ግድየለሽ እና አደገኛ" በማለት ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ሐሰተኛ መረጃን በማሠራጨት ከስሰዋል።

    ኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች የይገባናል ጥያቄ እያነሳችበት ያለው የአሰብ ወደብ ኤርትራ ነጻ አገር አስከ ሆነችበት ጊዜ ለኢትዮጵያ ዋነኛው የባሕር በር አገልግሎት ይሰጥ ነበር።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ወደብ ለማግኘት ብላ በኤርትራ ላይ ጦርነት የመክፈት ዕቅድ የሌላት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ነገር ግን በቀይ ባሕር በኩል የባሕር በር ማግኘት ግን "የኅልውና ጉዳይ ነው" ማለታቸው ይታወቃል።

  15. የካናዳ የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራቸውን ለቅቀው ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪን ሊያማክሩ ነው

    የካናዳ የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክርስቲያ ፍሪላንድ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የካናዳ የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክርስቲያ ፍሪላንድ የምክር ቤት አባልነታቸውን ለቅቀው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አማካሪ ልሆን ነው አሉ።

    ፍሪላንድ የኢኮኖሚ ልማት አማካሪ ሆነው የሚረከቡት ኃላፊነት ያለደሞዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

    በአውሮፓውያኑ 2013 የተመረጡት ክርስቲያ ፍሪላንድ በቀድሞው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱርዶ ስር የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትርን ጨምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ሠርተዋል።

    “ዩክሬን ዛሬ ለዓለም ዲሞክራሲ በሚደረገው ፍልሚያ ግንባር ላይ ናት። እናም ያለክፍያ [ለዜሌንስኪ] የኢኮኖሚ አማካሪ መሆኔን በደስታ እቀበላለሁ” ሲሉ በኤክስ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

    በሚቀጥሉት ሣምንታት የምክር ቤት መቀመጫቸውን እንደሚለቁ ያሳወቁት ፍሪላንድ፤ የዩክሬን መልሶ ግንባታ የካናዳ ልዩ ወኪልነታቸውንም እንደሚያስረክቡ አስታውቀዋል።

    ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የአዲስ አማካሪያቸውን መሾም አረጋግጠዋል።

  16. "እኔ የጦር እስረኛ ነኝ" - በድራማ የተሞላው የማዱሮ የችሎት ውሎ

    ማዱሮ ፍረድ ቤት ቆመው የሚያሳይ የእጅ ስዕል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሰማያዊ እና ብርቱካንማ ቀለም ያለው ካናቴራ እንዲሁም ካኪ ሱሪ ለብሰው ፍርድ ቤት የተገኙት ጥንዶቹ አስተርጓሚያቸውን ለመስማት እንዲያስችላቸው የጆሮ ማዳመጫ አድርገዋል። ጠበቃቸው መሐከላቸው ተቀምጧል።

    ማዱሮ በቢጫ ማስታወሻ ደብተር ላይ የሚሰሙትና የሚያዩት በአንክሮ ይፅፋሉ። ችሎቱ ሲጠናቀቅ ደብተሩን ይዘው መሔድ ይፈቅድላቸው እንደሆን ዳኛውን ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል።

    ማዱሮ ወደ ችሎቱ ከዘለቁ በኋላ አዳራሹን ለሞላው ታዳሚ ሰላምታ ሰጥተዋል። ፊታቸው ላይ ምንም ዓይነት ስሜት ማንበብ አይቻልም። እርጋታ ተላብሰዋል። ችሎቱ ሲጠናቀቅ ከታዳሚዎች መካከል አንዱ ብድግ ብሎ "ለወንጀልህ ዋጋ ትከፍላለህ ብሎ ሲጮህ እንኳ" በእርጋታ ነው የተመለከቱት።

    "እኔ ፕሬዝደንት ነኝ። የጦር እስረኛ ነኝ" ሲሉ በስፓኒሽ ለግለሰቡ ምላሽ ሰጡ። እንባ የተናነቀው ግለሰብ ከእስር ቤቱ እንዲወጣ ተደረገ።

  17. የማዱሮ ምክትል የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ሆነው ቃለ-መሐላ ፈፀሙ

    ማዱሮ እና ጊዜያዊ መሪዋ ዴልሲ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters/Getty Images

    የቬንዙዌላ ምክትል ፕሬዝደንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ የሀገሪቱ ጊዜያዊ መሪ ሆነው በፓርላማ በተዘጋጀ ሥነ-ሥርዓት ቃለ-መሐላ ፈፅመዋል።

    የ56 ዓመቷ ዴልሲ ከ2018 ጀምሮ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን ማዱሮ እና ሚስታቸው በአሜሪካ ኃይሎች “ታፍነው” በመወሰዳቸው እጅግ ማዘናቸውን ተናግረዋል።

    ኒው ዮርክ በሚገኘው የፌዴራል ፍድ ቤት የቀረቡት ማዱሮ እና ሚስታቸው ሲሊያ ፍሎሬስ ለቀረቡባቸው ክሶች “ጥፋተኛ አይደለንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

    የተባበሩት መንግሥት የፀጥታው ምክር ቤት የአሜሪካን ድርጊት በተለመከተ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገ ሲሆን የአሜሪካው አምባሳደር “በዓለማችን ትልቁ የኃይል ሀብት ያላት ሀገር ሕጋዊ ላልሆነ መሪ ተላልፋ ልትሰጥ አይገባም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    በመንግሥታቱ ድርጅት የቬንዙዌላ አምባሳደር የሆኑት ሳሙኤል ሞንካዳ ሀገራቸው “ሕጋዊ ያልሆነ የወታደራዊ ጥቃት” ሰለባ መሆኗን ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።

    የአሜሪካው አምባሳደር ማይክ ዋልትዝ በበኩላቸው ማዱሮ “ሕጋዊ ያልሆኑ ፕሬዝደንት” ናቸው በሚል የጥቃቱን ትክክለኛነት ለማሳመን ሞክረዋል። አክለው አሜሪካው “ከሕግ ለመሸሽ እየሞከረ” ያለ ግለሰብን ይዛ ለፍርድ አቅርባለች ብለዋል።

    ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አዲሷ የቬንዙዌላ መሪ “ትክክለኛውን ነገር የማታደርግ ከሆነ ምናልባትም ከማዱሮ የላቀ ዋጋ ትከፍላለች” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ሮድሪጌዝ ቃለ-መሐላ ከፈፀሙ በኋላ ለብሔራዊ ጉባዔ ባሰሙት ንግግር የሀገራቸውን ሰላም ለማስከበር ቃል ገብተዋል።

  18. “አሁንም የቬንዙዌላ መሪ ነኝ” ያሉት ማዱሮ፤ ለፍርድ ቤት “ጥፋተኛ አይደለሁም” አሉ

    ማዱሮ በካቴና ታስረው ወደ ፍርድ ቤት ሲወሰዱ

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    በኒው ዮርክ ደቡባዊ ቀጣና ፍርድ ቤት የቀረቡት የቬንዙዌላዊው ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ የቀረበባቸውን ክስ አስተባበሉ።

    አብረዋቸው ከቬንዙዌላ ተይዘው ወደ አሜሪካ የተወሰዱት ባለቤታቸውም ለቀረቡባቸው ክሶች ጥፋተኛ አለመሆናቸውን የሚገልጽ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ማዱሮ በዕፅ ሽብርተኝነት ሴራ እና በጦር መሣሪያ እንዲሁም ሌሎች አጥፊዎች መሳሪያዎች ክስ የቀረቡባቸው ሲሆን፣ በአራቱም ክሶች “ጥፋተኛ አይደለሁም” ሲሉ አስተባብለዋል።

    የእስር ቤት ልብስ አድርገው፤ እግራቸው በካቴና ታስሮ ፍርድ ቤት የቀረቡት ማዱሮ እና ሚስታቸው የቀረቡባቸውን ክሶች ለመስማት ነው ፍርድ ቤት የተገኙት።

    ማዱሮ ለኒው ዮርክ ፍርድ ቤት አሁንም የቬንዙዌላ መሪ መሆናቸውን መናገራቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የማዱሮ ጠበቃ ከዚህ ቀደም መረጃ አሾላኪው የዊኪሊክስ መሥራች ጁሊያን አሳንጅን ወክለው የተከራከሩት ባሪ ጆዌል ፖላክ መሆናቸውን የፍርድ ቤት ሰነዶች አሳይተዋል።

    ወደ ፍርድ ቤቱ ካሜራ እንዲገባ ባይፈቀድም የቢቢሲን ጨምሮ የሌሎች መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች የሰበሰቡትን መረጃ እንዲልኩ ተፈቅዶላቸዋል።

    24 ገፆች ያሉት የማዱሮ ክስ በዕፅ እና በጦር መሳሪያ ሴራዎች ላይ ያጠነጥናል።

    ጉዳዩን የሚከታተሉት የ92 ዓመቱ ዳኛ አልቪን ሄሌርስታይን ናቸው።

    ፍርድ ቤቱ ቀጣይ ቀጠሮ ለመጋቢት 8/2018 ሰጥቶ የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቋል።

  19. “ዓለም አቀፍ ሕግ አለመከበሩ አሳሳቢ ነው” አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    ጉቴሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    በቬንዙዌላ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባስተላለፉት መልዕክት "የዓለም አቀፍ ሕግ አልተከበረም" አሉ።

    ዋና ፀሐፊው በምክትላቸው ሮዝሜሪ ዲ ካርሎ በኩል በምክር ቤቱ በተነበበው መልዕክታቸው አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ ከፈጸመችው ጥቃት ጋር ተያይዞ “ዓለም አቀፍ ሕግ አለመከበሩ በጽኑ አሳሳቢ ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    ጉቴሬዝ የአሜሪናንን እርምጃ ተከትሎ በቬንዙዌላ ውስጥ ሊከሰት የሚችለው “አለመረጋጋት፣ እንዲሁም በአካበቢው የሚያስከትለው ተጽእኖ” በጣሙን እንዳሳሰባቸው አመልክተዋል።

    በተጨማሪም የአሜሪካ እርምጃ በዓለም አገራት መካከል ወደፊት በሚኖረው ግንኙነት ውስጥ አሉታዊ ምሳሌ በመሆን ስጋት እንደሚደቅን ገልጸዋል።

  20. የስዊዝ መንግሥት የማዱሮ ንብረት እንዳይንቀሳቀስ አገደ

    ኒኮላስ ማዱሮ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የስዊትዘርላንድ መንግሥት የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ እና “የሌሎች ከእሳቸው ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች” ንብረት እንዳይንቀሳቀስ አገደ።

    የስዊዝ መንግሥት እንዳለው ይህን ያደረገው ንብረቶቹ ከስዊትዘርላንድ እንዳይወጡ ለመከላከል ሲሆን ወደፊት ሕጋዊ ባለሆነ መንገድ መያዛቸው ከታመነ ለቬንዙዌላ ሕዝብ ለመመለስ ቃል ገብቷል።

    ስዊትዘርላንድ ከአውፓውያኑ 2018 ጀምሮ ቬንዙዌላ ላይ ማዕቀብ ጥላ ቆይታለች። በዚህ ማዕቀብ 54 ግለሰቦች የንብረት እና የጉዞ ዕገዳ ተጥሎባቸዋል።

    ማዱሮ በስዊትዘርላንድ ያላቸው ንብረት ምን ያክል እንደሆነ ባይታወቅም በ2021 የስዊዝ ጋዜጣ ሾልኮ የወጣ ሰነድን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው 10 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ በባንክ አካውንቶቻቸው ይገኛል።

    የስዊዝ ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ይህ ገንዘብ ከቬንዙዌላ ተመዝብሮ የወጣ ነው።

    ስዊትዘርላንድ የጣለችው ማዕቀብ ወዲያውኑ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ማዕቀቡ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ይቆያል።