"እንደምሞት አስብ ነበር"- በታሪክ የመጀመሪያው በሆነ ሕክምና ከገዳይ የደም ካንሰር የዳነችው ታዳጊ

ሕክምናው የሳይንስ ልብ ወለድ ይመስላል። በአስደናቂ ሁኔታ መፍትሄ ለሌለው የደም ካንሰር መፍትሔ ሰጥቷል።
በፍጥነት እየተስፋፋ ያለ እና ሕክምና የሌለው የደም ካንሰር ከያዛቸው ሕሙማን የተወሰኑት ላይ ለውጥ እንደታየ ዶክተሮች ገልጸዋል።
ሕክምናው የሚሰጠው በነጭ የደም ሕዋሳት ላይ የዘረ መል ምህንድስና በማድረግ ነው።
ነጭ የደም ሕዋሳት የዘረ መል ምህንድስና ከተደረገላቸው በኋላ ካንሰርን መዋጋት የሚችሉ ይሆናሉ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ሕክምናው ስለተሰጣት ሰው ቢቢሲ በአውሮፓውኑ 2022 ዘገባ ሠርቷል።
አሊሳ ታሚሊ ከሕመሙ ከዳነች በኋላ የካንሰር ተመራማሪ ሳይንቲስት ለመሆን ቆርጣ ተነስታለች።
በዚህ የደም ካንሰር ዓይነት (T-cell acute lymphoblastic leukaemia) ለተያዙ ስምንት ሕጻናት እና ሁለት አዋቂዎች ሕክምናው ተሰጥቷል።
ከታካሚዎቹ 64 በመቶ የሚሆኑት አገግመዋል።
ሰውነትን ከበሽታ የሚከላከሉት ሕዋሳት (T-cells) አደጋ እንዳይገጥም መከላከል ዋነኛ ሥራቸው ነው።
ሆኖም ሕዋሳቱ በሉኪሚያ ምክንያት ሥራቸው ይሰናከላል። በሽታውን ለማከም ኬሞቴራፒ እና የአጥንት መቅኔ ሕክምና (bone marrow transplants) ውጤት ሳያመጡ በመቅረታቸው ሙከራ ላይ ያለ ሕክምና እንደ አማራጭ ተወስዷል።
በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ማከም ባለመቻሉ ሕይወታቸው ሲያልፍ ከስቃይ ነጻ እንዲሆኑ ማገዝ ተመራጭ መንገድ ሆኗል።
በዩናይትድ ኪንግደም፣ ሌስተር የምትኖረው የ16 ዓመቷ አሊሳ ታሚሊ በዘረ መል ምህንድስና አማካኝነት ጤናዋ ተመልሷል።
"እንደምሞት አስብ ነበር። እንደ ልጅ ማድረግ ያለብኝን አድርጌ ትልቅ ሰው እሆናለሁ አላልኩም" ትላለች።
በዓለም ላይ ይህ ሕክምናው የተደረገላት የመጀመሪያዋ ሰው ናት። በግሬት ኦርሞንድ ስትሪት ሆስፒታል ከታከመች በኋላ ሕይወትን እያጣጣመች ትገኛለች።

ከሦስት ዓመት በፊት የተካሄደው ታሪክ ለዋጭ ሕክምና የቀድሞውን የሰውነቷን በሽታ የመከላከል አቅም በአዲስ ለውጧል።
ለአራት ወራት ሆስፒታል ተኝታ ስትታከም ኢንፌክሽን እንዳይዛት በሚል ወንድሟ አይጠይቃትም ነበር።
አሁን ካንሰሩ በሰውነቷ ውስጥ እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል። በየዓመቱ ጤናዋን ለመከታተል ሆስፒታል ትሄዳለች።
አሊሳ መኪና መንዳት እየተማረች ነው። በበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት ላይም ተሰማርታለች።
"ባዮሜዲካል ሳይንስ ውስጥ እንደ ጀማሪ ባለሙያ መሥራት እፈልጋለሁ። አንድ ቀን የደም ካንሰር ምርምር ውስጥ እንደምገባ ተስፋ አደርጋለሁ" ትላለች።
የተደረገላት የዘረ መል ምህንድስና 'base editing' ይባል።
ቤዝስ የሚባሉት የሰው ልጆች መሠረት ሲሆኑ አራት ዓይነት ናቸው። እነዚህም አድኒን (adenine (A))፣ ጉዋኒን (guanine (G))፣ ሲቲሲን (cytosine (C)) እና ታይሚን (thymine (T)) ናቸው።
የዘረ መል መነሻ ሲሆኑ፤ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዘረ መሎች የሰው ልጆች ሰውነት ውስጥ ይገኛሉ።
ሰውነት ያለውን ቅርጽ እና እንቅስቃሴ የሚይዘው በቤዞች አማካኝነት ነው።
እነዚህ ዘረ መሎች ላይ የሚደረግ ምህንድስና አንድ ቤዝ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ለውጥ ነው።

ጤናማ የሆኑ ነጭ የደም ሕዋሳት በሉኪሚያ የተያዙ የደም ሕዋሳትን እንዲያጠቁ የሚያስችል ሕክምና ነው።
ነጭ የደም ሕዋሳት በካንሰር የተያዙ የደም ሕዋሳትን መርጠው እንዲያጠቁ ማድረግ ቀለላ ሒደት አይደለም።
ጤናማ ነጭ የደም ሕዋስ ካለው ሰው በሚደረስ ልገሳ የደም ሕዋሳቱን አቅም ማጎልበት ይቻላል።
የመጀመሪያው የሕክምናው ደረጃ ነጭ የደም ሕዋሳቱ የታማሚዎችን ሰውነት እንዳያጠቁ ማድረግ ነው።
ሲዲ7 (CD7) የተባለ ኬሚካልን በማስወገድ ሕዋሳት ራሳቸውን ከመጉዳት እንዲታቀቡ ይደረጋል።
ሦስተኛው ደረጃ በኬሞቴራፒ መድኃኒት ሕዋሳት እንዳይሞቱ ማድረግ ሲሆን፤ አራተኛው እና የመጨረሻው የሕክምና ደረጃ የደም ሕዋሳት ሲዲ7 ያለባቸውን ፈልገው እንዲያከስሙ ማድረግ ነው።
ሕዋሳቱ እርስ በርሳቸው ሳይጎዳዱ ካንሰር ያለባቸውን ሕዋሳት ይገድላሉ።
ከሕክምናው ከአራት ሳምንታት በኋላ ታካሚዎች ሰውነት ውስጥ ካንሰር ካልተገኘ የአጥንት መቅኔ ልወጣ ይካሄዳል። ይህም የሰውነታቸውን በሽታ የመከላከል አቅም ያዳብራል።
በኪንግስ ኮሌጅ ሆስፒታል እና በግሩት ኦማንድ ስትሪት ሆስፒታል የሚሠሩት ፕሮፌሰር ዋሲም ቃሲም "ከዓመታት በፊት ይሄን ማድረግ የሚቻለው በሳይንሳዊ ልብ ወለድ ውስጥ ብቻ ነበር" ይላሉ።
"አጠቃላዩን የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም አፍርሰን ጥልቅ ሕክምና እንሰጣለን። ታካሚዎችን የሚያደክም ሕክምና ቢሆንም ውጤታማ ሲሆን አስደሳች ነው" ሲሉም ያክላሉ።
በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜድስን መጽሔት የታተመው ጥናት የ11 ታካሚዎችን ውጤት ያሳያል።
ዘጠኝ ታካሚዎች በሕክምናው አማካኝነት በሰውነታቸው ያለው ካንሰር ስለጠፋ ወደ አጥንት መቅኔ ልወጣ ተሻግረዋል።
ሕክምናው ከተደረገላቸው ከሦስት ወራት እስከ ሦስት ዓመታት ያለፋቸው ሰባት ሕሙማን ጤናቸው ተመልሷል።
የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም ደካማ በሆነት ወቅት ታካሚዎች ለኢንፌክሽን ተጋላጭ መሆናቸው አስጊ ነው።
በሁለት ታካሚዎች ላይ ካንሰር የያዛቸው ሕዋሳት ሲዲ7 ኬሚካልን በማጥፋት ሰውነት ውስጥ መደበቅ ችለዋል።
በግራንድ ኦማንድ ስትሪት ሆስፒታል የአጥንት መቅኔ ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር ሮበርት ቺሳ "ይህ የሉኪሚያ ዓይነት ከባድ ነው። ከከባድነቱም አንጻር የሕክምናው ውጤት አስደናቂ ነው። ለታካሚዎች ተስፋ መስጠት መቻላችን ያስደስተኛል" ይላሉ።
በኪንግስ ኮሌጅ ሆስፒታል የሚሠሩት ዶ/ር ዴብራ ያሎፕ በበኩላቸው "መዳን የማይችል ሉኪሚያን ጨምሮ በዚህ በሽታ ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አግኝተናል" ይላሉ።
አንቶኒ ኖለን በተባለው የስቴም ሴል ተቋም ምርምር የሚሠሩት ዶ/ር ታኒያ ዴክስተር "እነዚህ ሕሙማን ከሕክምናው በፊት ከሞት የመዳን ዕድላቸው ውስን ነበር። እንዲህ ያሉ ተስፋ ሰጪ ሕክምናቸው በስፋት ይዳረሳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ይላሉ።















