አሜሪካን እንዳያስቆጣ የተሰጋው ደቡብ አፍሪካ ከቻይና፣ ኢራን እና ሩሲያ ጋር የምታደርገው ወታደራዊ ልምምድ

የደቡብ አፍሪካ እና የቻይና ባሕር ኃይል ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, SA National Defence Force

በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው ወታደራዊ ልምምድ ላይ ከቻይና፣ ከኢራን እና ከሩሲያ የተውጣጡ የጦር መርከቦች መሳተፋቸው አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ሊያሻክረው ይችላል።

ደቡብ አፍሪካ በወታደራዊ ልምምዱ ላይ ኢራን ንቁ ተሳታፊ ከምትሆን ይልቅ ታዛቢ እንድትሆን ለማሳመን ጥረት እያደረገች መሆኑን የሚጠቁሙ ዘገባዎች ወጥተዋል።

በቅርብ ቀናት ውስጥ የቻይና፣ የኢራን እና የሩሲያ ባንዲራዎችን የሚያውለበልቡ መርከቦች በኬፕ ባህረሰላጤ የሲሞንስ ከተማ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ዋና የባህር ኃይል ጣቢያ ሲቀዝፉ ይታያሉ።

ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ልምምድ አርብ ዕለት ተጀምሯል። በቻይና የሚመራው ይህ ልምምድ እአአ በ2006 የተመሰረተው እና ብሪክ (Bric) በመባል የሚታወቀውን ዋና ዋና ታዳጊ አገሮች ጥምረት የተውጣጡ ሌሎች አባላትን ያካትታል።

ምህጻረ ቃሉን የወሰደው ከብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና የእንግሊዘኛ ስሞች የመጀመርያ ፊደላት ነው። ደቡብ አፍሪካ ከአራት ዓመታት በኋላ ቡድኑን ስትቀላቀል "s" የሚለው የስሟ ፊደል የቡድኑ መጠሪያ ላይ ተጨመሮ ብሪክስ ተባለ።

በቅርቡ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (UAE) በመጨመራቸው፣ ጥምረቱ አሁን ብሪክስ+ ተብሎ ይጠራል።

የቡድኑ ዓላማ የበለጸጉ የምዕራባውያን አገሮችን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ኃይል መገዳደር ነው።

አርብ ዕለት በሲሞን ከተማ የታየው የኢራን መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አርብ ዕለት በሲሞን ከተማ የታየው የኢራን መርከብ

የደቡብ አፍሪካ መከላከያ እንዳስታወቀው የባሕር ኃይል አባላት "ለጋራ የባህር ደህንነት ሥራዎች፣ ለተቀናጀ የተግባር ልምምድ እና የባህር ላይ ጥበቃ ተከታታይ ፕሮግራሞች" የተሰባሰቡ ናቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የትኞቹ አገራት እንደሚሳተፉ ባይናገሩም የስልጠናው ዓላማ "የመርከብ እና የባህር ላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ደህንነት ማረጋገጥ" ብቻ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የብሪክስ+ አባላት ለምን አንድ ላይ ወታደራዊ ልምምዶችን እያደረጉ እንደሚገኙ ይጠይቃሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ቡድኑ የኢኮኖሚ ጥምረት መሆኑ ላይ ነው።

"የብሪክስ+ አባላት በፖለቲካዊ መልኩ እርስ በርስ የሚቃረኑ እና በመካከላቸውም የጋለ የድንበር ግጭት የሚፈጥሩ አሉ" ሲሉ የመከላከያ ተንታኝ ዲን ዊንግሪን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪካ ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር የባሕር ኃይል ልምምድ ስታደርግ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። የመጀመሪያው "ሞሲ" ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጉሙም በደቡብ አፍሪካ የስዋና ቋንቋ "ጭስ" ማለት ነው።

ይህ ወታደራዊ ልምምድ የተደረገው እአአ በ2019 ሲሆን ብዙም ትኩረት አልሳበም።

ነገር ግን እአአ በ2023 ሁለተኛው ዙር ሞሲ ሲካሄድ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ በሙሉ ወረራ ፈጽማ የነበረ በመሆኑ ልምምዱ ለማካሄድ የተመረጠበት ወቅት በጣም ተተችቷል ።

"ሩሲያ ወረራውን በፈጸመች በዓመቱ ነበር ልምምዱ የተደረገው" ይላሉ ዊንግሪን። "ስለዚህ በጊዜው ሁሉም በልምምዱ ዙሪያ ጥያቄ እንዲያነሳ አድርጓል።"

የአሁኑ ልምምድ መጀመሪያ ላይ ኅዳር ወር ላይ እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረ ሲሆን ሞሲ ሳልሳዊ ተብሎ ሊጠራ ነበር።

ነገር ግን ደቡብ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀችው የቡድን 20 መሪዎች ጉባኤ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

እናም የስም ለውጥ ተደርጎበት በርከት ያሉ አገራት እነዲሳተፉበት ተደርጓል።

"ባለፈው ዓመት አጋማሽ አካባቢ፣ ሞሲ III ተብሎ እንደማይጠራ፣ ነገር ግን አሁን 'ዊል ፎር ፒስ' የሚባል የብሪክስ+ የባህር ላይ ልምምድ እንደሚሆን መስማት ጀመርን" ይላሉ ዊንግሪን።

ነገር ግን አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ የተሳተፉ አገራት ደቡብ አፍሪካን ከዋና የንግድ አጋሮቿ አንዷ ከሆነችው ከአሜሪካ የበለጠ ሊያርቃት ይችላል።

በጆሃንስበርግ በሚገኘው የዊትዋተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዊሊያም ጉሜዴ "የትራምፕ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ ደቡብ አፍሪካ ጫና ውስጥ ነች። ከዚያ በፊትም ቢሆን ዴሞክራቶች ሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ደቡብ አፍሪካን እንደ ፀረ አሜሪካዊ አድርገው ይመለከቷት ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን ከጥቃት መከላከል አልቻለችም በማለት ይከስሳሉ።

ይህንንም ተከትሎ ለነጭ ደቡብ አፍሪካውያን የስደተኝነት መብት ሰጥተዋል።

ከዚያም ከፍተኛ ታሪፍ በመጣል ለደቡብ አፍሪካ የሚሰጠውን እርዳታ አገዱ።

የትራምፕ ንዴትን በከፊል ያባሰው ፕሪቶሪያ በእስራኤል ላይ በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት (ICJ) በማቅረብ ረገድ ባላት ሚና ነው።

የአሜሪካ አጋር የሆነችው እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል "መሠረተ ቢስ" በማለት ውድቅ አድርጋዋለች።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ወደ ዋይት ሐውስ ያደረጉት ጉዞ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ሊጠግን አልቻለም።

ጉሜዴ ለዓመታት ፈተና ውስጥ የቆየው የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ወደ አሜሪካ ገበያ መግባት እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።

"አሜሪካን ማራቅ አንችልም። የአሜሪካ መንግሥት፣ የአሜሪካ የግል ዘርፍ እና የአሜሪካ ሲቪል ማኅበረሰብ አስተዋጽኦ በደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ ብንጨምር ከቻይና ኢኮኖሚ በጣም ከፍ ያለ ነው" ብለዋል።

"በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የአሜሪካ ኩባንያዎች ብቻ ከ500,000 በላይ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራሉ። በደቡብ አፍሪካ ያሉትን ሁሉንም የቻይና ኩባንያዎች ብታዩ፣ 10,000 የሥራ ዕድሎችን ወይም 20,000 የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥሩ መናገር ለጋስ ግምት ይሆናል።"

ይህ እአአ በ2024 መንግሥት ቻይና በደቡብ አፍሪካ ወደ 400,000 የሚጠጉ የሥራ እድሎችን ፈጥራለች ከሚለው የተለየ ነው።

"አሜሪካ ከቻይና ይልቅ ለእኛ በጣም ስትራቴጂካዊ ነች ብዬ አስባለሁ" ይላሉ ጉሜዴ።

ባለፈው ዓመት የደቡብ አፍሪካ ማዕከላዊ ባንክ አሜሪካ በአገሪቱ ላይ የጣለችው የ30 በመቶ ታሪፍ ወደ 100,000 የሚጠጉ ሰዎችን ሥራ ሊያሳጣ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በዚህም ክፉና የተጎዱት የግብርና እና የመኪና አምራች ዘርፎች ናቸው።

ጉሜዴ እአአ በ1994 ደቡብ አፍሪካን ነፃ ያወጣው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ቻይናን እንደ ርዕዮተ ዓለም አጋር አድርጎ ይመለከታታል ይላሉ። ሩሲያም ኤኤንሲ የአፓርታይድ አገዛዝን ለማስወገድ ያደረገውን ትግል በመደገፍ ላበረከተችው ሚና ከፍተኛ ግምት ይሰጣታል።

ነገር ግን ኤኤንሲ በ2024 የፓርላማ አብላጫ ድምጽ ካጣ በኋላ የመሰረተውን አዲሱን የጥምረት አጋሮቹን ለማካተት የውጭ ፖሊሲውን ማዘመን አልቻለም ሲሉ ይኮንኑታል።

"አብላጫ ፓርቲ በነበረበት ጊዜ ቻይና ለኤኤንሲ መንግሥት ስትራቴጂካዊ አጋር ነበረች። አሁን ግን በብሔራዊ አንድነት መንግሥት ውስጥ ነን፣ ስለዚህ እንደ አገርም ሆነ እንደ መንግሥት ማድረግ የነበረብን የኤኤንሲን አጋሮች የሚያካትት አዲስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማውጣት ነው፣ ምክንያቱም ኤኤንሲ ከእንግዲህ አብላጫ ድምጽ ያለው ፓርቲ ስላልሆነ።"

የደቡብ አፍሪካ ወታደራዊ አዛዦች

የፎቶው ባለመብት, SA National Defence Force

የምስሉ መግለጫ, የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት የወታደራዊ ልምምዱ የጦሩን ሞራል በመገንባት ረገድ ጠቃሚ መሆኑን ይናገራሉ

በአገሪቱ ውስጥ ሁለተኛው ትልቁ ፓርቲ የሆነው ዲኤ፣ የባህር ኃይል ልምምዱን በእጅጉ ተችቷል።

ይሁን እንጂ ዊንግሪን ደቡብ አፍሪካ ወታደራዊ ልምምዱን ከእነዚህ አገራት ጋር በጋራ ለማካሄድ የወሰነችበት ፖለቲካዊ ምክንያት ሊኖራት ይችላል ይላሉ።

"ደቡብ አፍሪካ መከላከያዋ ለዓመታት በበጀት እጥረት እየተፈተነ ነው" ሲሉ ምክንያት ይሆናል ያሉትን ይናገራሉ።

"ወደ ሌላ አገር ሄደው ልምምድ ማድረግ የሚችሉ ጀልባዎች የሉንም። ስለዚህ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመምጣት ፈቃደኛ ከሆኑ አገራት ጋር በራሳችን ባሕር ላይ ልምምድ ማድረግ አማራች ነው።"

የደቡብ አፍሪካ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ባንቱ ሆሎሚሳም ትችቱን ችላ ብለው የአገሪቱ የመከላከያ ኃይሎች "በወታደራዊ ዘርፍ በሚገባ ከታጠቁ አገሮች ጋር ልምምድ ማድረግ" ክብር እንደሆነ እና ይህም የወታደሮችን ሞራል እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ዊንግሪን ችግር ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። "ይህ ልምምድ ከሌላ አገር የሚመጣ ማንኛውንም ወታደራዊ እርምጃ ያስከትላል ብዬ አላምንም።

"ነገር ግን የደቡብ አፍሪካን የንግድ ድርድር ከተወሰኑ አገሮች ጋር የበለጠ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል።"

ይህንን ሃሳብ እንደ ጉሜዴ ያሉ ሌሎች ተንታኞችም ይጋሩታል። "ይህ በእርግጠኝነት የትራምፕ አስተዳደርን እንደ መተንኮሳ ተደርጎ ይታያል።"

"ይህ ለደቡብ አፍሪካ አሁን ካለው የጂኦፖለቲካ አንጻር ጥሩ ገጽታ አይደለም። ፕሬዝዳንት ራማፎሳ እነዚህን የጋራ የባህር ኃይል ልምምዶች ቢሰርዙ የተሻለ ነበር ብዬ አስባለሁ።"

የሩሲያ ጦር መርከብ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ ባሕር ኃይል በደቡብ አፍሪካ ውሃ ላይ በተገኘበት ወቅት ከዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ትችት አስከትሎ ነበር

የፖለቲካ ተንታኙ ሳንዲሌ ስዋና ደግሞ "የልምምዱ ዓላማ ባህሮችን ለዓለም አቀፍ ንግድ ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ፣ የባህር ላይ ውንብድናን መዋጋት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር አካባቢ መፍጠር ነው። በማንኛውም መስፈርት ማንም ሰው የሚቀበለው ይመስለኛል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሜሪካ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ከዚህ የከፋ ሊሆን እንደማይችልም አክለዋል።

"ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር ላይ እንቅስቃሴዎች ጥሪ በማንኛውም ሰው ሊገታ የሚገባው ለምን እንደሆነ ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት አይታየኝም። ትራምፕ ከባድ ማስፈራሪያዎችን ሲያወጡ እና ልክ እንዳደረገው ሁሉ ጀርባቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል።"

"ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር ላይ እንቅስቃሴዎች ጥሪ በማንኛውም ሰው ሊገታ የሚገባው ለምን እንደሆነ ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት አይታየኝም። ትራምፕ ከባድ ማስፈራሪያዎችን ሲያወጡ ጀርባቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል።"

ለጉሜዴ ግን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የአለመግባባቱ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ ነው።

"አደጋ ላይ ነን፤ የውጭ ፖሊሲያችንን ከአሜሪካ ጋር የበለጠ እርቅ ወይም ተራማጅ ካላደረግነው፣ በአሜሪካ እና በቻይና፣ በአሜሪካ እና በኢራን እንዲሁም በአሜሪካ እና በሩሲያ መካከል በሚደረጉ ግጭቶች መካከል እንወድቃለን።"

"እናም ደቡብ አፍሪካ ትልቋ ተሸናፊ ትሆናለች።"