ኢትዮጵያ "ታይዋን የማትነጠል የቻይና ግዛት" እንደሆነች ስታረጋገጥ፤ ቤይጂንግ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይን አነሳች

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ ኢትዮጵያ የላከችው ቻይና፤ የቀጣናው አገራት "ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን" ባከበረ መልኩ "የማሪታይም ሎጂስቲክስ ትስስራቸውን ለማጠናከር" የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ አስታወቀች።

"የባሕር በር የማግኘት" ጉዳይ የማሪታይም ሎጂስቲክስ ትስስርን ለማጠናከር ከሚረዱ ተግባራት መካከል እንደሆነም ገልጻለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ "ታይዋን የማትነጠል የቻይና ግዛት አካል" እንደሆነች በመግለጽ፤ ለ"አንድ ቻይና" መርኅ ያላትን ቁርጠኝት አረጋግጣለች።

የአውሮፓውያኑ 2026 የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በአፍሪካ ያደረጉት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፤ ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ሐሙስ ታኅሣሥ 30/2018 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ገብተዋል።

ዋንግ በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር ተነጋግረዋል።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዐቢይ እና ጌዲዮን ጋር የነበራቸው ውይይት ከአገር ውስጥ ጉዳዮች ባሻገር ቀጣናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች የተነሱበት እንደሆነ ዛሬ አርብ ጥር 1 ቀን የወጣው የሁለቱ አገራት የጋራ መግለጫ ያስረዳል።

የቻይና መንግሥት በኢትዮጵያ በምታከናውነው "አገራዊ ልማት" ለተመዘገቡ "አዲስ ስኬቶች" ያለውን አድናቆት እንደገለጸ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው የጋራ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

ቻይና "የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገሪቱ ሁኔታ ጋር የሚስማማ የልማት ጎዳና ለመከተል የሚያደርገውን ጥረት በጽኑ" እንደምትደግፍ አስታውቃለች። ኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣ "የውጭ ጣልቃ ገብነትን" እንደምትቃወምም አስታውቃለች።

መግለጫው እንደሚያስረዳው ሁለቱ አገራት "የልማት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን" በተመለከተ ቅንጅታቸውን ለማጠናከር እንዲሁም "ከመንግሥት አስተዳደር" ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የሚደረጉት የልምድ ልውውጦችን "ለማበረታታት" ተስማምተዋል።

"ቻይና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ለምትጫወተው ሚና ከፍ ያለ ግምት" እንደምትሰጥ መግለጿ በጋራ መግለጫው ላይ ሰፍሯል። ኢትዮጵያ በበኩሏ "በቻይና የሰላም እና ልማት ዕቅድ በአፍሪካ ቀንድ አማካኝነት ለተመዘገቡ ውጤቶች" ያላትን አድንቆት ገልጻለች።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ተወያይተዋል

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ተወያይተዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቻይና በዚህ መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአጽንኦት እያነሳ ያለውን የባሕር በር ተጠቃሚነት ጉዳይን ከቀጣናዊ ትስስር ጋር አያይዛ ጠቅሳለች። የቀጣናው አገራት በተለያዩ መስኮች "የግንኙነት ትብብርን እና የአፍሪካ ውህደትን" ለማጠናከር የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምታበረታታ አስታውቃለች።

ግንኙነትን ለማጠናከር በሚል ከተጠቀሱት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ "የማሪታይም ሎጂስቲክስን" ማሳደግ ነው። ይህ የሚሆንበት አንዱ መንገድም "የባሕር በር ማግኘት" እንደሆነ ቻይና ጠቅሳለች።

የባሕር ሎጂስቲክስ ጉዳይ፤ "በቀጠናው ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልጽግናን" ለማስፈን ዓላማ መዋል እንዳለበት የገለጸችው ቻይና፤ "በንግግር እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ" መከናወን እንዳለበትም አንስታለች።

ከቀጣናዊ ትስስር ጋር የተያያዙት እነዚህ ተግባራት ጉዳዩ "የሚመለከታቸውን አገራትን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት" እንዲሁም "የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር እና ዓለም አቀፍ ሕግን. . . በማክበር ላይ መመሥረት" እንዳለባቸውንም አስረድታለች።

ኢትዮጵያ በአንጻሩ፤ ከሰሞኑ በድጋሚ የውጥረት ምንጭ እየሆነ ባለው የታይዋን ጉዳይ ድጋፏ ለቻይና እንደሆነ በድጋሚ አሳውቃለች።

ቻይና፤ ሉዓላዊ አገር እንደሆነች ያወጀችውን ታይዋንን የምትቆጥራት እንደ የራሷ ግዛት አካል አድርጋ ነው። ከሰሞኑም ቻይና በታይዋን አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ እያደረገች መሆኑ፤ ቤይጂንግ በደሴቷ ላይ ጦርነት ልትከፍት ትችላለች የሚል ስጋት በድጋሚ እንዲበረታ ምክንያት ሆኗል።

ይህ ውጥረት ባየለበት በአሁኑ ወቅት የወጣው የሁለቱ አገራት የጋራ መግለጫ ላይም ኢትዮጵያ "ለአንድ ቻይና መርኅ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጣለች።"

"በዓለም ላይ አንድ ቻይና ብቻ መኖሯን፣ ታይዋን የማትነጠል የቻይና ግዛት አካል መሆኗን" በመጥቀስ አቋሙን ያሳወቀው መንግሥት፤ ኢትዮጵያ "ማንኛውንም የ'ታይዋን ነጻነት' እንቅስቃሴን በጽኑ ትቃወማለች" ብሏል።

መግለጫው፤ ኢትዮጵያ "የቻይና መንግሥት አገራዊ አንድነትን ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት ሁሉ በጽኑ ትደግፋለች፤ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ 2758ን ሥልጣን በቁርጠኝነት ትከላከላለች" ይላል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ

የፎቶው ባለመብት, African Union

የምስሉ መግለጫ, የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ከተወያዩ በኋላ በወጣው የጋራ መግለጫ ላይ፤ ሕብረቱ የታይዋንን ጉዳይ በተመለከተ ከቤጂንግ ጎን እንደሚቆም አስረግጧል

ታይዋንን የተመለከተው ይህ ግልጽ እና ጠንካራ አቋም የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር እና የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተገናኙ በኋላ በወጣው የጋራ መግለጫ ላይም በተመሳሳይ ተንጸባርቋል።

ታይዋንን የተመለከተው የኅብረቱ መግለጫ ክፍልም በተመሳሳይ "ታይዋን የማትነጠል የቻይና ግዛት አካል መሆኗን" አስረግጧል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት እና የቻይና መግለጫ፤ ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ መንግሥት ከአገራቸው የተወሰዱትን የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ጉዳይ አንስቷል።

በቅርቡ በቬንዙዌላ የተፈጠረው ክስተትን በተመለከተ "ያላቸውን ስጋት" የገለጹት ቻይና እና የአፍሪካ ኅብረት "የሁሉም አገራት ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መከበር" እንዳለበት አሳስበዋል።

"የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር መሠረታዊ መርሆች እና ዓለም አቀፍ ሕጎች መከበር" አለባቸው የሚለውን አቋማቸውንም በመግለጫው አስፍረዋል።

ኢትዮጵያ እና ቻይና በመግለጫቸው ላይ የቬንዙዌላን ጉዳይ በግልጽ ባይጠቅሱም፤ ሁለቱ አገራት "በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ኃይልን መጠቀምን ወይም በኃይል ለመጠቀም መዛትን" እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ቻይና እና ኢትዮጵያ በአዲሱ የአውሮፓውያን 2026 "በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮቻቸው መካከል አዲስ የፖለቲካ ምክክር ለማካሄድ" እንደተስማሙ መግለጫው ያስረዳል።