በፍሎሪዳ ወደሚገኘው የትራምፕ መኖሪያ ቤት መሳሪያ ይዞ የገባ ግለሰብ መገደሉን የደህንነት መሥሪያ ቤቱ አስታወቀ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የማርአ-ላጎ መኖሪያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የማርአ-ላጎ መኖሪያ ቤት
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አንድ የታጠቀ ሰው በፍሎሪዳ ወደሚገኘው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የማርአ-ላጎ መኖሪያ ቤት ከገባ በኋላ በጥይት ተመትቶ መሞቱን የአገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት አስታወቀ።

ባለሥልጣናቱ ግለሰቡ በደህንነት አባላት እንዲቆም ተደርጎ ሲተኮስበት ሽጉጥ እና የነዳጅ ቆርቆሮ ይዞ ነበር ብለዋል።

ጉዳዩ የተከሰተው እሁድ ማለዳ ሲሆን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዋሽንግተን ዲሲ ነበሩ ተብሏል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ተጠርጣሪው ግለሰብ ኦስቲን ቲ ማርቲን የሚባል መሆኑን እና በሰሜን ካሮላይና በምትገኘው ካሜሮን መወለዱን ዘግቧል።

በሰሜን ካሮላይና የሚኖሩ ቤተሰቦቹ እሁድ ጠዋት ላይ እንደጠፉ ለፖሊስ አስታውቀው እንደነበር የሙር ካውንቲ ፖሊስ ለቢቢሲ ገልጿል።

የጠፉ ሰዎች መረጃ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለፌዴራል ባለሥልጣናት ተላልፎ መሰጠቱን ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ ማርቲንን በተመለከተ ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት መረጃ እንዳልነበረው የገለፀ ሲሆን በፍሎሪዳ እየተካሄደ ባለው ምርመራ ውስጥም እንዳልተሳተፈ አስታውቋል።

ባለሥልጣናት ሽጉጡን ከኖርዝ ካሮላይና ወደ ፍሎሪዳ በሚመጣበት ወቅት ገዝቶት እንደሆን እያጣሩ መሆኑን ሲቢኤስ ዘግቧል።

የደህንነት ሠራተኞች "ዛሬ ጠዋት በማር-አ-ላጎ ጥበቃ በሚደረግለት ስፍራ ውስጥ ያለ ፈቃድ የገባ ግለሰብ ከተመለከቱ በኋላ ተኩሰውበታል" ሲሉ የኤጀንሲው ቃል አቀባይ አንቶኒ ጉግሊኤልሚ በኤክስ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

ተጠርጣሪው "በማር-አ-ላጎ ሰሜናዊ በር አጠገብ ሽጉጥና የነዳጅ ቆርቆሮ ይዞ ታይቷል" ሲል ኤጀንሲው በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቋል።

የፓልም ቢች ካውንቲ ፖሊስ ሪክ ብራድሻው እንደተናገሩት ግለሰቡ ትዕዛዝ አልቀበልም በማለቱ ተተኩሶበት ተገድሏል።

"እኛ ያልነው 'እቃዎቹን ጣል' ብቻ ነው፤ ይህም ማለት የነዳጅ ቆርቆሮውን እና ሽጉጡን ማለት ነው" ሲሉ ብራድሻው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"በዚህ ጊዜ የነዳጅ ቆርቆሮውን ካስቀመጠ በኋላ፣ ሽጉጡን ለመተኮስ አነጣጠረው" ብለዋል።

በዚያን ጊዜ የደህንነት ባልደረቦች "ስጋቱን ለማስወገድ" ተኩሰዋል ሲሉ ሁኔታውን አብራርተዋል።

ተጠርጣሪው መጥፋቱን ቤተሰቦቹ ለፖሊስ ማመልከታቸውን ሲቢኤስ ዘግቧል

የፎቶው ባለመብት, Facebook

የምስሉ መግለጫ, ተጠርጣሪው መጥፋቱን ቤተሰቦቹ ለፖሊስ ማመልከታቸውን ሲቢኤስ ዘግቧል

ፖሊሶቹ ካሜራ በልብሳቸው ለላይ መገጠሙን እና ምንም ዓይነት ጉዳት የደረሰበት የሕግ አስከባሪ አንደሌለ ጨምረው ተናግረዋል።

ብራድሻው የተጠርጣሪው ሽጉጥ ተቀባብሎ እንደሆነ እንደማያውቁ እና ይህም የምርመራ አካል እንደሚሆን ተናግረዋል።

የአሜሪካ የደህንነት መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር ሺን ኩራን እሁድ ዕለት "ከድርጊት በኋላ" ወደ ፍሎሪዳ መጓዛቸውን ኤጀንሲው በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

በማር-አ-ላጎ የሚገኘው የጸጥታ ሁኔታ እጅግ በጣም ጥብቅ ሲሆን የአካባቢው የፓልም ቢች ፖሊሶች ከውጭ የደህንነት ሰራተኞች ደግሞ የመኖርያ ግቢውን ከውስጥ ይጠብቃሉ።

ጎብኚዎች እንዲሁም መኪኖቻቸው እና ቦርሳዎቻቸው በአነፍናፊ ውሾች እና በኤክስሪይ ማሽን የታገዘ ፍተሻ ይደረግላቸዋል።

ትራምፕ ከዚህ በፊትም በርካታ የግድያ ሴራዎች ወይም ሙከራዎች ዒላማ ሆነዋል።