ሶማሊላንድ ለአሜሪካ ማዕድናት እና የጦር ሰፈር ለመስጠት ፍቃደኛ መሆኗን ገለጸች

የሶማሊላንድ ሰንደቅ ዓላማ የያዙ ታዳጊ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ራሷን ከሶማሊያ የተለየች ነጻ አገር መሆኗን ያወጀችው ሶማሊላንድ አሜሪካ በግዛቷ ውስጥ ማዕድናትን እንድታወጣ እና ወታደራዊ ሠፈር እንዲኖራት እንደምትፈቅድ አስታወቀች።

በቅርቡ ከእስራኤል ባገኘችው የመጀመሪያ የአገርነት ዕውቅና ምክንያት ከፍተኛ ተቃውሞ እና ውዝግብ የተፈጠረባት ሶማሊላንድ ከተጨማሪ አገራት ዕውቅናን ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ውስጥ ነው ለአሜሪካ ያላትን ፈቃደኝነት የገለጸችው።

የሶማሊላንድ መንግሥት ሚኒስትር የሆኑት ኻዳር ሄሴን አብዲ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደተናገሩት፣ አሜሪካ ማዕድናትን ለማውጣት እና የጦር ሠፈር እንድትመሠርት አገራቸው ፈቃደኛ መሆኗን ገልጸዋል።

"ዩናይትድ ስቴትስ ማዕድናትን እድታወጣ የተለየ ፈቃድ ለመስጠት ፈቃደኞች ነን። በተጨማሪም የጦር ሠፈር እንዲኖራት በራችን ክፍት ነው" በማለት ሶማሊላንድ ያላትን ፍላጎት በግልጽ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ኻዳር አክለውም "ከአሜሪካ ጋር በአንዳንድ ነገሮች ላይ ከስምምነት ላይ እንደርሳለን ብለን እናምናለን" ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የእስራኤል የቅርብ ወዳጅ የሆነችው አሜሪካ አስካሁን ለሶማሊላንድ ዕውቅና ለመስጠት ውሳኔ ላይ አልደረሰችም። ነገር ግን በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት ዕውቅና እንዲሰጥ ግፊት እያደረጉ ነው።

አሜሪካ እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠቷ የራሷ መብት መሆኑን የገለጸች ሲሆን፣ ምንም እንኳን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፓርቲያቸው ሪፐብሊካን አንዳንድ አባላት ግፊት ቢደረግባቸውም ተመሳሳይ እርምጃ እንደማይወስዱ መግለጻቸው ይታወሳል።

የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ በቅርቡ እስራኤል በአገራቸው የማዕድን ሀብትን በማውጣት ውስጥ እንድትሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምንም እንኳን በገለልተኛ ጥናት የተረጋገጠ ባይሆንም ሶማሊላንድ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ተፈላጊ ከሆኑት መካከል በሊቲየም፣ በኮልተን እና በሌሎች ማዕድናት የበለጸገች መሆኗን ባለሥልጣናቷ ይናገራሉ።

በተመሳሳይ ሚኒስትር ኻዳር ሁሴን አብዲ እስራኤልም በሶማሊላንድ ውስጥ ወደታራዊ ሠፈር የምትመሠርትበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።

እስራኤል ባለፈው ታኅሣሥ ለሶማሊላንድ የመጀመሪያውን የአገርነት ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ ሶማሊያ ቁጣዋን ገልለጻች።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት በተደጋጋሚ በሶማሊላንድ እና በእስራኤል መካከል የጦር ሠፈር የመክፈት ስምምነት መደረሱን በመግለጽ ሲከስሱ ነበር።

ሶማሊላንድ በእስራኤል ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በሚሰነዘሩት የሁቲ ታጣቂዎች ከሚቆጣጠሯት የመን ባሻገር በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የምትገኝ ስትሆን፣ ለአሜሪካ እና ለእስራኤል ወታደራዊ እንቅስቃሴ ቁልፍ ናት።

ሚኒስትሩ በተጨማሪም ከሶማሊያ ጋር መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ትብብር እያደረገች ያለችውን ቱርክ በማንሳት የሚጠበቅበትን የሚያከናውን መንግሥት የላትም ከሚሏት "ከሶማሊያ ይልቅ ከእኛ ጋር መነጋገር አለባቸው" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከ30 ዓመታት በላይ በማንም ዕውቅና ያላገኘ ነጻ መንግሥት የመሠረተችውን ሶማሊላንድን እንደ ግዛቷ አካል የምትቆጥራት ሶማሊያ የእስራኤልን ዕውቅና ተከትሎ ጠንካራ ተቃውሞዋን በተለያዩ መድረኮች አሰምታለች።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ እስራኤል የሰጠችው ዕውና "በሶማሊያ ሉዓላዊነት ላይ የተፈጸመ ከባድ ጥሰት ነው" በማለት አውግዘው፤ ውሳኔው "ለዓለም እና ለቀጣናው ደኅንነት እና መረጋጋት አደጋ ነው" ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት፣ የተበባሩት መንግሥታት እንዲሁም አገራት እና ቀጣናዊ ድርጅቶች የሶማሊላንድን ዕውቅና ተቃውመው ከሶማሊያ መንግሥት መቆማቸው ይታወሳል።