"ባረፍንበት ሆቴል ክፍል በተደበቀ ካሜራ ተቀርጸን እራሳችንን የልቅ ወሲብ ድረ ገጽ ላይ አገኘነው"

- ፀሐፊ, ዋንኪንግ ዣንግ
- የሥራ ድርሻ, ከቢቢሲ ቻይና እና የምርመራ ቡድን
- የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ አስጸያፊ አገላለጾች ይዟል።
በአውሮፓውያኑ በ2023 አንድ ምሽት ላይ ኤሪክ ማኅበራዊ ሚዲያ እየተመለከተ ነበር። ልቅ ወሲብ ከሚታይባቸው ድረ ገጾች በአንዱ ላይ ፈጽሞ ያልጠበቀው ነገር አየ።
ጥንዶች ወደ ሆቴል ክፍል ገብተው ሻንጣቸውን ያስቀምጣሉ። ከዚያም ወሲብ ሲፈጽሙ ይታያል። እነዚህ ጥንዶች እራሱ ኤሪክ እና የፍቅር አጋሩ ነበሩ።
ቪድዮውን ከመመልከቱ ከሳምንት በፊት በደቡባዊ ቻይና፣ ሸንዘን በሚገኝ ሆቴል ውስጥ አንድ ምሽት አሳልፈዋል።
ክፍሉ ውስጥ ብቻቸውን እንደሆኑ ነበር ያመኑት። ነገር ግን በድብቅ ካሜራ ሲቀረጹ ነበር።
ኤሪክን ጨምሮ በርካቶች ልቅ ወሲብ በሚመለከቱበት ድረ ገጽ ላይ ቪድዮው ተለቋል።
ኤሪክ እና ፍቅረኛው በቆዩበት የሆቴል ክፍል ውስጥ የተገጠመው ድብቅ ካሜራ እንቅስቃሴያቸውን እየተከተለ ሲቀርጻቸው ነበር።
የዚህ ድብቅ ካሜራ ሰለባ ኤሪክ (ስሙ ተለውጧል) እና ፍቅረኛው ብቻ አይደሉም።
በድብቅ ካሜራ የተቀረጸ ልቅ የወሲብ ቪድዮ (spy-cam porn) በቻይና ቢያንስ ለአሥርታት ሲሠራጭ ቆይቷል።
በአገሪቱ ልቅ ወሲብ መቅረጽ ወይም ማሠራጨት ሕገ ወጥ ነው።
ሴቶች ሆቴል ውስጥ ሲገቡ ድብቅ ካሜራ ተገጥሞ ከሆነ ማወቅ የሚችሉባቸውን መንገዶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጥቆማ የሚሰጡ ሰዎች የተበራከቱት ያለ ምክንያት አይደለም።
በጣም ትናንሽ እና የተለያየ ቅርጽ ያላቸው ድብቅ ካሜራዎች በስውር ቦታዎች ላይ ተቀምጠው የሰዎችን እንቅስቃሴ ይቀርጻሉ።
ከወራት በፊት የወጣ ድንጋጌ የሆቴል ባለቤቶች በመኝታ ክፍሎች ውስጥ ካሜራ ተደብቆ ከሆነ ፍተሻ ማድረግ እንዳለባቸው ያስገድዳል።
ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ በተለያዩ የልቅ ወሲብ ድረ ገጾች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ በድብቅ ካሜራ ሆቴል ውስጥ የተቀረጹ ቪድዮዎች አግኝቷል።
አብዛኞቹ ቪድዮዎች የሚተዋወቁት ቴሌግራም ላይ ነው። የቢቢሲ ዘጋቢ በ18 ወራት ውስጥ ቴሌግራም ላይ የሚተዋወቁ ስድስት የተለያዩ ድረ ገጾች አግኝታለች።
በእነዚህ ድረ ገጾች ከሚቀርቡት የወሲብ ቪድዮዎች መካከል በ180 የሆቴል ክፍሎች የተቀረጹ ይገኙበታል።
እነዚህ ቪድዮዎች በቀጥታ የሚተላለፉ ጭምርም ናቸው።
የቢቢሲ ዘጋቢ ለሰባት ወራት ክትትል ያደረገችበት ድረ ገጽ በ54 ካሜራዎች የተቀረጹ ቪድዮዎች ተገኝቶበታል። ቢያንስ ግማሽ ያህሉ ካሜራዎች በአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ይውላሉ።
በእነዚህ ወራት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የሆቴል እንግዶች ቪድዮ ተቀርጸዋል ማለት ነው። በርካቶቹ ቪድዮ እየተቀረጹ መሆኑን አያውቁም።
የሆንግ ኮንጉ ኤሪክ ወጣት ሳለ በድብቅ ይቀረጹ የነበሩ የወሲብ ቪድዮዎችን ይመለከት ነበር።
"ሰዎች እየተቀረጹ እንደሆነ አለማወቃቸው ይስበኝ ነበር። ለቀረጻ ተብሎ የተዘጋጀ ልቅ ወሲብ ተውኔታዊ ነው" ይላል።

ኤሪክ አሁን በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ይገኛል። በድብቅ መቀረጽ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጥር ተረድቷል። አሁን በድብቅ የተቀረጸ የወሲብ ቪድዮ መመልከት አንዳችም ደስታ አይሰጠውም።
ፍቅረኛው ኤሚሊ (ስሟ ተቀይሯል) በድብቅ ቪድዮ መቀረጻቸውን ሲነግራት እየቀለደ ነበር የመሰላት።
የሆቴል ቆይታቸው ወደ አንድ ሰዓት ቪድዮ ወርዶ በድረ ገጽ መለቀቁን ስታውቅ የሥራ ባልደረቦቿ እና ቤተሰቦቿ ቢያዩት ምን እንደሚፈጠር በማሰብ ትጨነቅ ጀመር።
ጥንዶቹ ለሳምንታት ማውራት ተሳናቸው።
ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ መሠረት በድብቅ ካሜራ ልቅ ወሲብ ከሚያስተላልፉ ኤጀንቶች አንዱ 'AKA' (ለኤኬኤ) ይባላል።
የቢቢሲ ዘጋቢ ድረ ገጹን እንደሚከታተል ደንበኛ ራሷን ስታቀርብ በየወሩ 47 ዶላር እንድትከፍል ተጠይቃለች።
አምስት የድብቅ ካሜራ ቪድዮ አማራጮች በድረ ገጹ ይገኛሉ። እንግዶች ሆቴል ክፍላቸው ከገቡ ጀምሮ ቀረጻው ይጀምራል።
ቪድዮዎቹን ከመጀመሪያው አንስቶ መመልከት፣ ከመሃል መጀመር ወይም በስልክ/ኮምፒውተር ላይ መጫን ይቻላል።
ኤኬኤ የተባለው ኤጀንት በቴሌግራም ይዘቱን ያስተዋውቃል። አንደኛው የቴሌግራም ገጽ 10 ሺህ ተከታዮች አሉት።
በቴሌግራም ገጹ ላይ በክፍያ የልቅ ወሲብ ቪድዮዎች ማግኘት ይቻላል። እንደ አውሮፓውያኑ ከ2017 ጀምሮ የተለቀቁ ከ6,000 በላይ ቪድዮዎች ይገኛሉ።
በቴሌግራም ገጹ ላይ የሚታዩት ጥንዶችን ተክለ ሰውነት እና የወሲብ ክህሎትን በተመለከተ የሚነጋገሩ ሰዎች ይታያሉ።
ሴቶችን ጸያፊ እና አዋራጅ በሆነ መንገድ "ሸርሙጣ" እያሉ የሚሳደቡም አሉ። ጥንዶች መብራት ሲያጠፉ የሚቆጡ ተመልካቾችም በቴሌግራም ገጹ ይገኛሉ።
ድብቅ ካሜራ ከሚገኝባቸው ሆቴሎች አንዱን ቢቢሲ በማዕከላዊ ቻይና፣ ዠንግዙ ግዛት ውስጥ ደርሶበታል።
ድብቅ ካሜራዎቹ የሚቀመጡት ያለ ማስጠንቀቂያ ነው። የቢቢሲ መርማሪ ቡድን ድብቅ ካሜራውን ሲያነሳ ቴሌግራም ገጹ ላይ ያሉ ተከታታዮች ወዲያው ነበር ቅሬታ ያቀረቡት።
"ያ የሆቴል ክፍል በጥሩ ሁኔታ ድምጽ ይቀርጽ ነበር። ካሜራው መነሳቱ ያሳዝናል" ሲሉ ለኤኬኤ ጽፈዋል።
ኤኬኤ ብዙም ሳይቆይ በሌላ ሆቴል ክፍል ውስጥ ሌላ ድብቅ ካሜራ ሲገጥም ተከታታዮቹ ደስታቸውን ገልጸዋል።
"በምን ያህል ፍጥነት አዲስ ካሜራ እንደምንገጥም አያችሁ አይደል? አስደናቂ አይደለን?" ሲል ኤኬኤ በቴሌግራም ገጹ ጽፏል።
ቢቢሲ በ18 ወራት ምርመራው እንደ ኤኬኤ ያሉ በርካታ ኤጀንቶችን አግኝቷል።
ከደንበኞቻቸው ጋር ከሚያደርጉት ንግግር በመነሳት ለሌሎች ተቀጥረው እንደሚሠሩ ለማወቅ ተችሏል።
እነዚህ አካላት "የካሜራ ባለቤቶች" የሚባሉ ሰዎች ድብቅ ካሜራዎች በሆቴሎች በማስገጠም የቪድዮ ሥርጭቱን ይቆጣጠራሉ።

የቢቢሲ ዘጋቢ ማንነቷን ሳትገልጽ ከኤኬኤ ጋር ባደረገችው ንግግር ላይ "የካሜራ ባለቤት" የሚባልን ሰው ማንነት በድንገት አጋልጦላታል።
ወንድም ቻን (ብራዘር ቻን) የተባለ ሰውን ማንነት ያጋለጠበትን የጽሑፍ መልዕክት ወዲያው አጥፍቷል።
'ብራዘር ቻን' የተባለው ግለሰብ ግን እንደ ኤኬኤ ኤጀንት እንደሆነ እና ከእሱ በላይ ላሉ ቀጣሪዎች እንደሚሠራ ከመግለጽ የዘለለ መረጃ አልሰጠም።
ኤኬኤ ከሚያዝያ ወዲህ ባሉት ወራት ብቻ ቢያንስ 22,000 ዶላር እንዳገኘ ይገመታል።
የቻይና ስታትስቲክስ ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው አምና በአገሪቱ አማካይ ገቢ ተብሎ የተመዘገበው ገቢ 6,200 ዶላር ነው።
በቻይና ለድብቅ ቀረጻ የሚውል ካሜራ መግዛትን የሚከለክል ድንጋጌ ቢኖርም በአንድ ገበያ ውስጥ በቀላሉ መሸመት እንደሚቻል ቢቢሲ ደርሶበታል።
በሆንግ ኮንግ የሚገኘው እና በድብቅ የተቀረጹ የወሲብ ቪድዮዎችን በማጥፋት ተጎጂዎችን የሚረዳው 'ሬይንሊሊስ' የተባለው የተራድኦ ድርጅት እንደሚለው፤ ቪድዮዎችን መሰረዝ ቀላል አይደለም።
ቪድዮዎችን ከገጹ እንዲያጠፋ ለቴሌግራም የሚላከው መልዕክት ምላሽ እንደማያገኝ ተቋሙ ይገልጻል።
"የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ትልቁን ኃላፊነት ይሸከማሉ። ይዘቶች የሚሠራጩት እነሱ ያወጡትን ፖሊሲ በመከተል ነው" ሲልም ለቢቢሲ አስታውቋል።
ቢቢሲ ስለ ኤኬኤ እና ብራዘር ቻን ድርጊት ለቴሌግራም ቢያሳውቅም ኩባንያው እርምጃ አልወሰደም።
ሆኖም ግን ቢቢሲ መረጃውን ለቴሌግራም ከሰጠ ከ10 ቀናት በኋላ ኩባንያው "ያለ ፈቃድ የወሲብ ይዘት ማስተላለፍ በቴሌግራም ፖሊሲ መሠረት የተከለከለ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎጂ ይዘቶችን እንድናጠፋ ጥቆማዎች ይደርሱናል" ሲል አስተያየት ሰጥቷል።
ቢቢሲ በድብቅ ካሜራ በሚደረግ ቀረጻ የሆቴል እንግዶች ላይ ብዝበዛ እየተፈጸመ እንደሆነ ለኤኬኤ እና ብራዘን ቻን ቢገልጽም ምላሽ አልሰጡም።
ከቀናት በኋላ ቪድዮዎችን ለማስተዋወቅ የሚጠቀሙባቸውን የቴሌግራም አካውንቶች አጥፍተዋል።
ኤሪክ እና ኤሚሊ በደረሰባቸው ነገር ከገጠማቸው ድንጋጤ አልወጡም።
ሆቴል ውስጥ ማረፍ አቁመዋል። ሰዎች አይተዋቸው ማንነታቸውን እንዳይለዩ በሚል ኮፍያ አድርገው መንቀሳቀስ ጀምረዋል።
የወሲብ ቪድዮዋቸው በድጋሚ ተለቅቆ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት ኤሪክ ቴሌግራምን አልፎ አልፎ ያስሳል።
ቴሌግራም ላይ የወሲብ ቪድዮ መመልከት ግን ማቆሙን ይናገራል።















