"ቲክቶክ በአፍሪካ ሕጻናትን በሚያካትቱ ወሲባዊ ቀጥታ ሥርጭቶች ትርፍ እያገኘ ነው"

የሞባይል ስልክ

ቲክቶክ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች በሚከናወኑ የወሲባዊ ይዘቶች የቀጥታ ሥርጭቶች ትርፍ እያገኘ መሆኑን ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በኬንያ የሚኖሩ ሦስት ሴቶች፤ ይህን ተግባር የጀመሩት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ መሆኑን ይገልጻሉ።

ሴቶቹ በሌሎች የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች ለሚልኳቸው ወጣ ያሉ ይዘቶች ክፍያ ለመደራደር ቲክቶክን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

ቲክቶክ እንዲህ ዓይነቱን ይዘት ቢከለክልም እንደሚፈጸም እንደሚያውቅ የቲክቶክ ቀጥታ ሥርጭት ተቆጣጣሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቲክቶክ ከሁሉም የቀጥታ ሥርጭቶች ላይ ከሚመነጭ ገቢ 70 በመቶ ያህል እንደሚወስድ ቢቢሲ ከዚህ ቀደም ዘግቧል።

ቲክቶክ ለቢቢሲ "ለብዝበዛ ምንም ትዕግስት የለኝም" ብሏል።

ከኬንያ የሚካሄዱ የቀጥታ ሥርጭቶች በቲክቶክ ዝናቸው የናኘ ነው። በዓለም ዙሪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእያንዳንዱ ምሽት፣ በደርዘን የሚቆጠሩ የኬንያ ሴቶች ሲጨፍሩ በቀጥታ በመተግበሪያው ላይ ይመለከታሉ።

ናይሮቢ ውስጥ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ነው። ሕይወት በቲክቶክ መተግበሪያ ላይ ደረቷል።

ሙዚቃው ይጮኻል፥ ተጠቃሚዎች እርስ በርስ ይጨዋወታሉ። አንዲት ሴት ስሜት ቀስቃሽ የዳንስ ትርዒት ልታሳይ ካሜራዋን አብርታላች። በተለምዶ ኢሞጂ የሚባሉት ስሜት ገላጭ ምሥሎች በስጦታ መልክ እየጎረፉ ስክሪኑን ሞልተውታል።

የዳንስ ትርዒት የምታሳየው ሴት በተደጋጋሚ "ታፕ ታፕ አድርጉ 'ለኪኔምቤ' በውስጥ መልዕክት ላኩልኝ" ስትል ትሰማለች።

'ታፕ ታፕ' የሚለው ሐረግ በብዛት በቲክቶክ ላይ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ ተመልካቾች የቀጥታ ሥርጭቱን "ላይክ" እንዲያደርጉ የሚደረግ ጥሪ ነው።

"ኪነምቤ" በስዋሂሊ ቂንጥር ማለት ነው። "መልዕክት ላኩልኝ" የሚለው ሐረግ ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ድርጊቶች መመልከት ለሚፈልጉ ተመልካቾች በቲክቶክ ላይ በግል መልዕክት እንዲልኩ የሚቀርብ ጥሪ ነው።

ከቲክቶክ የቀጥታ ሥርጭት የተወሰደ ምሥል
የምስሉ መግለጫ, ከቲክቶክ የቀጥታ ሥርጭት የተወሰደ ምሥል

ባየናቸው አንዳንድ የቀጥታ ሥርጭቶች ላይ ወሲባዊ አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ ምሥጢራዊ የወሲብ ቃላቶች ጥቅም ላይ ውለዋል።

የኢሞጂ ስጦታዎች ለቲክቶክ የቀጥታ ሥርጭቶች ክፍያ ሆነው ያገለግላሉ። ቲክቶክ ግልጽ የሆኑ ወሲባዊ ድርጊቶችን እና እርቃንን ስለሚያስወግድ - እነዚህ ይዘቶች በሌሎች መተግበሪያዎች ይላካሉ። ስጦታዎች ወደ ገንዘብ ሊለወጡ ይችላሉ።

ቲክቶክ በዓለም ዙሪያ ቀጥሯቸው ከነበሩ 400 ሺህ የቀጥታ ሥርጭት ተቆጣጣሪዎች መካከል ጆ እያልን የምንጠራው ኬንያዊ አንዱ ነው።

ጆ "ወሲባዊ ይዘቶችን መገደብ የቲክቶክ ፍላጎት አይደለም፤ ብዙ ሰዎች በቀጥታ ሥርጭት ላይ ስጦታዎች ሲሰጡ ለቲክቶክ ከፍ ያለ ገቢ ነው" ይላል።

ቲክቶክ አሁንም ከቀጥታ ሥርጭት ስጦታዎች 70 በመቶ ያህል እየወሰደ መሆኑን ደርሰንበታል። ኩባንያው ይህን ያህል ትልቅ ኮሚሽን ይወስዳል መባሉን አስተባብሏል።

ባለፈው ዓመት በአሜሪካ የዩታ ግዛት በቲክቶክ ላይ ባቀረበው ክስ መሠረት፤ ኩባንያው በ2022 ባካሄደው የውስጥ ምርመራ በቀጥታ ሥርጭቱ ውስጥ የሕፃናት ብዝበዛ እንደሚካሄድ ቢያውቅም "ከፍተኛ ትርፍ" ስለሚያገኝ ጉዳዩን ችላ ብሎታል።

ቲክቶክ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ ያለው ክስ ደኅንነትን ለማሻሻል ያደረጋቸውን "ቅድመ እርምጃዎች" ችላ ያለ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

'ቻይልድ ፈንድ ኬንያ' የተሰኘው በጎ አድራጎት ድርጅት ብዙ ወጣቶች ያሉበት የአገሪቱ የሥነ ሕዝብ አወቃቀር እና ሰፊ የኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር ተደምሮ ኬንያ ለዚህ ብዝበዛ ተጋላጭ ነች ይላል።

በአጠቃላይ የአፍሪካ አህጉር ከምዕራባውያን አገራት ጋር ሲነጻጸር ደካማ የበይነ መረብ ሽፋን አለው ሲል በጎ አድራጎት ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።

የይዘት ቁጥጥር ለማድረግ ከቲክ ቶክ ጋር ውል ላሰረው ቴሌ ፐርፎርማንስ የሠራው ጆ፣ ተቆጣጣሪዎች የተከለከሉ ወሲባዊ ቃላት ወይም ድርጊቶች ማጣቀሻ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል ብሏል።

ነገር ግን ይህ መመሪያ ገዳቢ ነው የሚለው ጆ፣ ምሥጢራዊ ቃላትን ወይም ሌሎች ቀስቃሽ ምልክቶችን ግምት ውስጥ አያስገባም።

"[ለምሳሌ] ካሜራው ደረታቸው እና ጭናቸው ላይ እንዲያተኩር ሲያደርጉት ወሲባዊ ቅስቀሳ እያደረጉ እንደሆነ ማየት ትችላላችሁ። ምንም ላይናገሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን ወደ [የማኅበራዊ ትስስር] አካውንታቸው እየመሩ እንደሆነ ማየት ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ምንም ማድረግ የምችለው ነገር የለም።"

ሌላው ኬልቪን የምንለው የቴሌ ፐርፎርማንስ የይዘት ተቆጣጣሪ፣ ቁጥጥሩ በቲኪቶክ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ላይ ያለው ጥገኛነት የተገደበ ነው፤ አካባቢያዊ እና ምስጢራዊ የሆኑ ወሲባዊ ቃላትን መለየት አይችልም ይላል።

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የቲክ ቶክ ይዘት ተቆጣጣሪ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጆ እና ኬልቪን ስጋታቸውን ከነገሩን ሰባት የአሁን እና የቀድሞ የይዘት ተቆጣጣሪዎች መካካል ናቸው።

ጆ በይዘት ተቆጣጣሪዎች ገጽ ውስጥ የተጠቆሙት የቀጥታ ሥርጭት 80 በመቶ ያህሉ ወሲባዊ ወይም ወሲባዊ አገልግሎቶች የማስታወቂያ እንደሆኑ ተናግሯል፤ እናም ቲክቶክ የጉዳዩን ስፋት ያውቃል።

ቻይልድ ፈንድ ኬንያ እና ሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በእነዚህ ተግባራት እስከ ዘጠኝ ዓመት ያሉ ሕጻናት እየተሳተፉ ነው።

በቀን እስከ ስድስት ወይም ሰባት ሰዓታት በዚህ ድርጊት ላይ እንደሚያሳልፉ እና በአማካኝ ለሳምንት ምግብ እና ትራንስፖርት የሚሆን 30 ፖውንድ እንደሚያገኙ የሚናገሩ ታዳጊ እና ወጣት ሴቶችን ቢቢሲ አነጋግሯል።

ኤስተር እያለን የምንጠራት የ17 ዓመት ወጣት "ራሴን በቲክቶክ እሸጣለሁ። ራቁቴን እጨፍራለሁ። ያንን የማደርገው ራሴን የማስተዳድርበትን ገንዘብ የማገኘው በዚህ መንገድ ስለሆነ ነው" ስትል ተናግራለች።

የምትኖረው 3,000 ነዋሪዎች የመጸዳጃ ቤት መገልገያዎችን በሚጋሩበት ሰፈር ውስጥ ነው።

ገንዘቡ ለልጇ ምግብ እንድትገዛ እና የኤስተር አባት ከሞተ ጀምሮ የቤት ኪራይ ለመክፈል ስትቸገር የነበረችውን እናቷን ለመደገፍ እንደረዳት ተናግራለች።

በጓደኛዋ ከቲክቶክ የቀጥታ ሥርጭት ጋር ስትተዋወቅ 15 ዓመቷ ነበር።

በእርግጥ በቲክቶክ የቀጥታ ሥርጭት ለመጠቀም የሚችሉት ዕድሜያቸው ከ18 በላይ የሆኑ ብቻ ናቸው።

ተጠቃሚዎች የቀጥታ ሥርጭት ለማድረግ ቢያንስ 1,000 ተከታዮች ያስፈልጋቸዋል።

ስለዚህ ብዙ ተከታይ ያላቸው የቲክቶክ ተጠቃሚዎች እንደ ዲጂታል አገናኞች (pimps) ይሆናሉ።

ወሲባዊ ይዘትን የሚሸጡ የቀጥታ ሥርጭቶችን ማስተናገድ ይችላሉ። አንዳንዶቹ የመጠባበቂያ የቲክቶክ አካውንት አላቸው፣ ይህም ከዚህ ቀደም በቲክቶክ እንደታገዱ ያመለክታል።

አንድ አገናኝ "ስትደንሺ ከካሜራው ራቂ ካለበለዚያ ትታገጃለሽ" እያለ በስክሪኑ ላይ ስትደንስ በምትታየው ሴት ላይ ይጮኻል።

በቀጥታ ሥርጭቱ ላስተናገዳት አገናኝ ከምታገኘው ገንዘብ ላይ ማካፈል አለባት።

ኤስተር ግንኙነቱ በፍጥነት ወደ ብዝበዛ ሊለወጥ ይችላል ትላለች። የእርሷ ዲጂታል አገናኝ (pimp) ከ18 ዓመት በታች እንደነበረች እንደሚያውቅ ተናግራለች፤ እናም "ወጣት ልጃገረዶችን መጠቀም ይወዳል።"

ብዙ ገንዘብ እንድታመጣ ጫና እንዳደረገባት ትናገራለች፤ ይህ ማለት ቶሎ ቶሎ በቀጥታ ሥርጭት መግባት አለባት። ከምታገኘው ገንዘብ ከጠበቅችው በላይ እንደወሰደባትም ትናገራለች።

"ለምሳሌ 35 ሺህ ሽልንግ የሚገመት ኢሞጂ በስጦታ መልክ ከተላከ 20 ሺህ ይወስዳል፤ ስለዚህ የማገኘው 15 ሺህ ሽልንግ ብቻ ይሆናል።"

በስጦታ መልክ የሚቀርቡት የቲክቶክ ኢሞጂዎች
የምስሉ መግለጫ, በስጦታ መልክ የሚቀርቡት የቲክቶክ ኢሞጂዎች

ለእርሱ መሥራት "በካቴና" እንደመታሰር ነበር ትላለች። "ትልቁን ድርሻ ስለሚያገኝ መጠቀሚያ የሆንኩትም የምጎዳውም እኔ ነኝ።"

በቲክ ቶክ የቀጥታ ሥርጭት በጀመረችበት ወቅት እሷም 15 ዓመቷ እንደሆነ የምትናገው ሶፊ (እውነተኛ ስሟ አይደለም)፣ በአውሮፓ ካሉ ወንዶች በሦስተኛ ወገን መተግበሪያዎች ላይ አገልግሎት እንድትሰጣቸው ጥያቄ እንዳቀረበላት ተናግራለች።

አንዱ የጀርመን ተጠቃሚ ለገንዘብ ስትል ጡቶቿን እና ብልቷን እንድትዳብስ እንደጠየቃት ትገልጻለች።

አሁን 18 ዓመት የሆናት ሶፊ በበይነ መረብ የወሲብ ሥራዋ ተፀፅታለች። በሌሎች መድረኮች ለተጠቃሚዎች የላከቻቸው አንዳንድ ቪዲዮዎች ያለፈቃዷ በሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተጭነዋል ስትል ተናግራለች።

ጎረቤቶቿ ይህን በማወቃቸው ሌሎች የአካባቢው ታዳጊዎች ከእርሷ ጋር እንዳይገናኙ ያስጠነቅቋቸዋል ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

"የጠፋ በግ ብለው ፈርጀውኛል፣ እና ወጣቶች እንደማሳስታቸው ተነገሯቸዋል። ብዙ ጊዜ ብቸኛ ነኝ።"

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንዳንድ ልጃገረዶች እና ሴቶች የቲክቶክ ተጠቃሚዎችን በአካል ለወሲብ ለመገናኘት ክፍያ እንደተከፈላቸው ወይም ከአገናኞቻቸው (pimp) ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ግፊት እንደተደረገባቸው ተናግረዋል።

ቲክቶክ በአፍሪካ ገበያዎች ውስጥ እግሩን ለማስገባት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ይዘቱን በብቃት ለመከታተል በቂ ሠራተኞችን እየቀጠረ አይደለም ሲሉ በኬንያ ያሉ የይዘት ተቆጣጣሪዎች ይናገራሉ።

የኬንያ መንግሥት ለጉዳዩ እውቅና የመስጠት ምልክቶችን አሳይቷል። በአውሮፓውያኑ 2023 ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከቲክቶክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሾው ዚ ቼው ጋር በመድረኩ ላይ የተሻለ የይዘት ልውውጥ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

ኩባንያው በኬንያ ከሚገኘው የቲክቶክ ቢሮ ጋር በመተባባር ቁጥጥር ለማድረግ መስማማቱን መንግሥት ገልጿል።

ነገር ግን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተቆጣጣሪዎች ከ18 ወራት በኋላ አንዳቸውም ተፈጻሚ አልሆኑም ብለዋል።

ቴሌ ፐርፎርማንስ የይዘት ተቆጣጣሪዎቹ "በማኅበረሰብ ደረጃዎች እና የደንበኛ መመሪያዎች ላይ ተመሥርተው በተጠቃሚ የመነጨ ይዘትን ለመሰየም እና ለመጠቆም በትጋት እንደሚሰሩ" እና የደንበኞች ሥርዓቱ ቴሌ ፐርፎርማንስ የሚያስከፋ ይዘትን እንዲያስወግድ ወይም ለሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት እንዲያሳውቅ ተደርጎ እንዳልተዘጋጀ ገልጿል።

የማኅበራኢ ሚዲያው ቃል አቀባይ "ቲክቶክ ለብዝበዛ ምንም ትዕግስት የለውም። ጠንካራ የይዘት ቁጥጥር ደንቦችን፣ ስዋሂሊንን ጨምሮ በ70 ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጥብቅ የደኅንነት ጥበቃ ፖሊሲዎችን እናስፈጽማለን። አካሄዳችንን በቀጣይነት ለማጠናከር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ የደኅንነት አማካሪዎች ምክር ቤት ጋር በአጋርነት እንሰራለን" ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።