ቻይና 'ተገንጣይ' የምትላትን ታይዋንን ለማስጠንቀቅ በዙሪያ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመረች

ቤጂንግ ከ2022 ጀምሮ በታይዋን ሰርጥ የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድ አጠናክራለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቤጂንግ ከ2022 ጀምሮ በታይዋን ሰርጥ የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድ አጠናክራለች

ቻይና "ተገንጣይ ኃይሎችን" ለማስጠንቀቅ እና የደሴቷን ቁልፍ አካባቢዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ወታደራዊ ልምምድ በሰርጡ አቅራቢያ እያደረገች መሆኑ ተዘገበ።

የአገሪቱ ጦር፣ ባሕር ኃይል፣ አየር ኃይል እና ሌሎችም ኃይሎች የተኩስ ልምምድን ጨምሮ ለወታደራዊ ልምምድ መሰማራታቸውን ቤይጂንግ አስታውቃለች።

"የፍትኅ ተልዕኮ 2025" የሚል የመለያ ስም የተሰጠው ልምምዱ አሜሪካ ትልቅ የተባለውን የተለያዩ የወታደራዊ መሣሪያዎችን በ11 ቢሊዮን ዶላር ለታይዋን መሸጧን ባሳወቀች በቀናት ውስጥ የሚካሄድ ነው።

የመሣሪያ ሽያጩ ከቤይጂንግ ብርቱ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፤ በአጸፋው ቻይና በአሜሪካ የመከላከያ ኩባንያ ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

ታይዋን በዚህ ዓመት የመከላከያ ኃይሏን ማጠናከሯ የምትወስዳቸው እርምጃዎች የግዛቷ አካል አድርጋ የምታያት ቻይናን አስቆጥቷል።

የታይዋን ፕሬዝዳንታዊ ጽ/ቤት የቻይናን ወታደራዊ ልምምድ ዓለም አቀፋዊ ባህልን የሚጥስ ነው በሚል ተችቷል።

የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር ሰኞ ጠዋት የቻይናን የጦር አውሮፕላኖች እና መርከቦችን በታይዋን አካባቢ መመልከቱን ገልፆ፤ የአገሪቱ ጦር እና የሚሳኤል ሥርዓት ሁኔታውን እንዲቃኝ መመደቡን አስታውቋል።

ኃይሉ ታይዋንን እና "ሕዝቦቿን ለመከላከል" "በከፍተኛ መጠንቀቅ" ላይ እንደሚገኝም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የታይዋን ሰርጥ አካባቢ ላይ የተመደበው የቻይና ምሥራቃዊ ዕዝ በዊቦ በተባለው የማኅበራዊ የትስስር ገጽ ወታደራዊውን ልምምድ "የፍትኅ ጋሻ" ሲል ጠርቶታል።

"ለመገንጠል እያሴሩ ያሉ ሁሉ ጋሻው ሲያገኛቸው ይመነጠራሉ" ሲምል አጋርቷል።

የመጀመሪያው ወታደራዊ ልምምድ መጀመሩን ያሳወቀው የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ዋናውን ልምምድ ማክሰኞ እንደሚደረግ ጠቁሟል።

ቻይና ለረጅም ዓመታት ከታይዋን ጋር "ሰላማዊ ውህደት" ስትወተውት የቆየች ሲሆን፣ የደሴቷን መገንጠል ግን "ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ" የሚያስቆምም ሕግ አላት።

ቤይጂንግ የታይዋን ፕሬዝዳንት ሊአ ቺንግ-ቲ "የታይዋንን ነፃነት" እየመሩ ነው በሚል ትከሳለች።

የታይዋን ፕሬዝዳንት ታይዋን ወትሮውኑም ሉዓላዊ አገር ናት በማለት ነፃነቷን በይፋ ማወጅ አይጠበቅባትም ባይ ናቸው።

እሁድ ዕለት ፕሬዝዳንት ሊአ በአገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተሠራጨ ቃለ ምልልስ ቻይና ወረራ እንድትፈፅም "የሚያደርጋት ደረጃ ላይ እንዳትደርስ ታይዋን የሚገጥማትን ፈተና ማለፍ አለባት" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም አስተዳደራቸው አሁናዊ ሁኔታውን ለማስቀጠል ቁርጠኛ እና ቻይናን እንደማይተናኮስ ገልጸው፤ ሰላም "በእውነተኛ ጥንካሬ" ላይ የወደቀ ነው ብለዋል።

የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚጠቁሙት አብዛኛው የታይዋን ዜጋ ሁኔታዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ የሚሻ ሲሆን፣ ይህም ማለት ከቻይና ጋር መዋሃድም ሆነ ነፃነታቸውን በይፋ ማወጅ አይፈልጉም።

ከ2022 ጀምሮ ቻይና ስጋት ብላ በምታነሳቸው ሁነቶች ምክንያት በታይዋን ሰርጥ የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድ አጠናክራለች።

ባለፈው ሚያዝያ ቻይና ያደረገችው ወታደራዊ ልምምድ በቁልፍ የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈጸም የሚያስችል ምሥለ ልምምድ እንደነበር ቤይጂንግ አስታውቃለች።

ሕዝቧን ለጥቃት ለማዘጋጀት እና ወታደራዊ አቅሟን ለቤይጂንግ ለማሳየት ታይዋንም የራሷን ወታደራዊ ልምምድ ታደርጋለች።