አሜሪካ አዲሱን የታይዋን መሪ ‘እንኳን ደስ አልዎ’ ማለቷ ‘ትልቅ ስህተት ነው’ ስትል ቻይና ወቀሰች

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂን ፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂን ፒንግ

ከቅዳሜው የታይዋን ምርጫ ውጤት በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ለአገሪቱ ነፃነት ለሚታገሉ ሰዎች “በጣም የተሳሳተ መልዕክት” አስተላልፋለች ስትል ቻይና ወቀሰች።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ውጤቱን ተከትሎ ለተመራጩ የታይዋን ፕሬዝዳንት ዊልያም ላይ የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክት ልከዋል።

መልዕክቱን ዋሽንግተን ከታይዋን ጋር ያላትን ግንኙነት ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ብቻ ለማስቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት የሚጥስ ነው በማለት ቤይጂንግ ገልጻለች።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ላይ ታይዋንን ከጊዜ ወደ ጊዜ “ጨቋኝ እየሆነች ከመጣችው ቻይና” ለመጠበቅ ቃል ገብተዋል።

ታይዋንን እንደ ግዛቷ ምትመለከታት ቻይና፣ ከዚህ የተለየ ሐሳብ ያለውን ማንኛውንም መንግሥት አጥብቃ ትቃወማለች።

በታይፔ እና በዋሽንግተን መካከል ያለውን አጋርነት አፅንኦት የሰጡትን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብሊንከንን ጨምሮ ከምርጫው በኋላ ለአዲሱ ታይዋን ፕሬዝዳንት በርካታ አገራት የእንኳን ደስ አልዎ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

“የጋራ ጥቅማችንን እና እሴቶቻችንን ለማስቀጠል ከዶክተር ላይ እና ከታይዋን መሪዎች ጋር ለመሥራት እንጠባበቃለን” ሲሉ በመግለጫቸው ተናግረዋል።

ብሊንከን አክለውም ከታይዋን ታላላቅ አጋሮች አንዷ የሆነችው አሜሪካ በአካባቢው “ሠላም እና መረጋጋት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆኗን” አፅንኦት ሰጥተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩናይትድ ስቴትሱ ከፍተኛ ዲፕሎማት አክለውም እንዲህ ዓይነቱ ትብብር “የእኛን የቆየ ይፋዊ ያልሆነ ግንኙነታችንን የሚያጠናክር እና ከአሜሪካ የአንድ ቻይና ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም መሆን አለበት” ብለዋል።

በፖሊሲው መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ ከታይዋን ደሴት ይልቅ ከቻይና ጋር መደበኛ ግንኙነት እንዳላት ነው። ቤይጂንግ በበኩሏ ታይዋንን የምትመለከተው አንድ ቀን እንደምትዋሃዳት የተገነጠለች ግዛቷ ነው።

የብሊንከን መልዕክት ከቤይጂንግ የሰላ ትችት አስተናግዷል። ለታይዋን የሚሰጥን ማንኛውንም የድጋፍ መግለጫ አገሪቱን ወደ ነፃ እና ሉዓላዊ አገርነት ለመቀየር ተስፋ ላለው ዕጩ እና የፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊነትን እንደመስጠት ትቆጥረዋለች።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም፣ የብሊንከን እንኳን ደስ አልዎት መልዕክት ዋሽንግተን ከታይዋን ጋር “በባህል፣ በንግድ እና በሌሎች ይፋዊ ባልሆኑ ግንኙነቶችን ብቻ” እንደሚወሰን የገባችውን ቃል የሚጻረር ነው።

የታይዋን ጥያቄ “በቻይና እና በአሜሪካ ግንኙነት ውስጥ መታለፍ የሌለበት የመጀመሪያው ቀይ መስመር” መሆኑን አፅንኦት ሰጥቶ ዲፕሎማሲያዊ ቅሬታ መቅረቡንም ገልጿል።

“ዩናይትድ ስቴትስ ከታይዋን ጋር ያላትን ማንኛውንም ዓይነት ይፋዊ ግንኙነት እና በታይዋን ጉዳዮች በማንኛውም መንገድ ወይም በማናቸውም ምክንያት ጣልቃ መግባቷን ቻይና አጥብቃ ትቃወማለች።”

የቤይጂንግ መግለጫ ታይዋን አዲሱን መሪ ከመረጠች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የቀድሞ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ያቀፈ ልዑክ በታይዋን ውስጥ ካሉ ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎች ጋር እንዲወያይ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ለላከችው ዋሽንግተን ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይችላል ትበሏል።

የምርጫውን ውጤት በተቀበሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተሠማራው የልዑካን ቡድኑ የቀድሞውን የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እና የቀድሞ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አካቷል።

ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመንን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ለአዲሱ መሪ የእንኳን ደስ አልዎ መልዕክት አስተላልፈዋል።