የዓለማችን የዘመን አቆጣጠር ለምን የተለያየ ሆነ? ዋነኞቹ የዘመን አቆጣጠሮች የትኞቹ ናቸው?

የግድግዳ ሰዓቶችን እየሰቀለ ያለ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዓለም ዙሪያ የተለያዩ የጊዜ ቀጣናዎች እንዳሉ ሁሉ የዘመን አቆጣጠሮችም በርካታ ናቸው

ምንም እኳን ብዙ አገራት አማራጭ የቀን መቁጠሪያ እና የጊዜ ቀመር ሥርዓት ቢኖራቸውም ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ከሌሎች የዘመን መቁጠሪያዎች ጎን ለጎን የጎርጎሪዮሳዊው የቀን መቁጠሪያን በዕለት ተዕለት ኑሮው ውስጥ ባሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይጠቀማል።

ከታሪክ፣ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ እና ከባህል ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ እጅግ በርካታ እና የተለያዩ የዘመናት አቆጣጠሮች አሉ።

በተለይ የእምነት መሠረት ያላቸው የዘመን አቆጣጠሮች በአገራት እና በመንግሥታት ተቀባይነት አግኝተው በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

ቢሆንም ግን የጎርጎሪዮሳውያኑ (የአውሮፓውያን) የዘመን አቆጣጠር በዓለም ዙሪያ ጥቅም ላይ የማይውልበት ስፍራ የለም ማለት ይቻላል።

ይህ በምዕራቡ ዓለም በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው የዘመን አቆጣጠር ከቅኝ ግዛት እና ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ሰፊ ተቀባይነትን አግኝቷል።

ኮምፒውተር እና ሞባይል ስልኮች ደግሞ ይህንን የዘመን አቆጣጠር ወደ እያንዳንዳችን ቤት እና እጅ አስገብተውታል።

በዚህም ሳቢያ የጎርጎሪዮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር የዓለማችን ማዕከላዊው ዋነኛው በመሆኑ ወደድንም ጠላንም የዘመን አቆጣጠሩን እናውቀዋለን ወይም እንጠቀምበታለን።

የራሳቸው የዘመን አቆጣጠር ባላቸው አገራት ውስጥም ሳይቀር ካላቸው የዘመን ቀመር ጋር ጎን ለጎን ይህ የጎርጎሪዮሳውያኑ አቆጣጠር ጥቅም ላይ ይውላል ወይም ለይፋዊ አገልግሎት አገልግሎት ይሰጣል።

በትራንስፖርት እና በኢንተርኔት መስፋፋት በእጅጉ እየተሳሰረች ባለችው ዓለማችን ላይ የአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር አጠቃቀም እየተጠናከረ እና ሰፊ ቦታን እየሸፈነ ይገኛል።

የአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ምንም እንኳን ከሁሉ የላቀ ተቀባይነት እና ተጠቃሚ ቢኖረውም፤ አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዓለም ሕዝብ የሚጠቀማቸው ዋነኛ የዘመን አቆጣጠሮች በሥራ ላይ ይገኛሉ።

የጁሊየስ ቄሳር ሃውልት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከጎርጎሪዮሳዊው የዘመን አቆጣጠር ቀደም ብሎ የነበረው የጁሊያን ካሌንደር ጀማሪ የጁሊየስ ቄሳር ሃውልት

ሌሎች ዋነኛ የዘመን አቆጠጣጠሮች

ከእነዚህ መካከልም የጎርጎሪዮሳውያኑን የዘመን አቆጣጠር ተከትሎ ዋነኛ የሚባሉት መሠረታቸው ሃይማኖት የሆኑ የዘመን አቆጣጠሮች ናቸው። እነሱም፡

* እስላማዊ የዘመን አቆጣጠር፡ ይህ ብዙኃን የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚኖሩባቸው አገራት ውስጥ በዋናነት ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

*የሂብሩው ዘመን አቆጣጠር፡ ዋነኛዋ የአይሁድ እምነት ተከታዮች መኖሪያ በሆነችው እስራኤል ውስጥ ለሃይማኖታዊ አገልግሎት ጥቅም ይሰጣል።

*የቡዲስቶች የዘመን አቆጣጠር፡ የቡድሃ እምነት ተከታዮች በስፋት በሚገኙባቸው በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

*የቻይና የዘመን አቆጣጠር፡ ከዓለም በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ በሆነችው ቻይና እና በውጭ አገራት በሚኖሩ ቻይናውያን ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ በዋናነት ለባህላዊ ሥርዓቶች ይገለገሉበታል።

ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሌሎችም ለየት ያሉ የዘመን አቆጣጠርን የሚከተሉ አገራት ሲኖሩ ኢትዮጵያም ከእነዚህ ውስጥ ተከተታለች።

በርማ፣ ኢትዮጵያ፣ ጃፓን፣ ባንግላዲሽ፣ ኢራን፣ ሕንድ፣ ቡታን፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ታይዋን የራሳቸው የሆነ የተለየ የዘመን አቆጣጠር ካላቸው የሚጠቀሱ ናቸው።

የጎርጎሪዮሳውያኑን ዘመን አቆጣጠርን ጨምሮ ሌሎቹም የራሳቸው የጊዜ ቀመሮች፣ የአዲስ ዓመት ጅማሬ እና ሌሎችም ልዩነቶች ስላላቸው ልዩነታቸው ጠባብ አይደለም።

የፖፕ ግሪጎሪ 13ኛ ሥዕል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ በስፋት ጥቅም ላይ የሚገኘውን የዘመን አቆጣጠር ተግባራዊ ያደረጉት ፖፕ ግሪጎሪ 13ኛ

የጎርጎሪዮሳውያን የዘመን አቆጣጠር

የጎርጎሪዮሳውያኑ (የአውሮፓውያን) የዘመን አቆጣጠር መሠረቱ ሃይማኖት ቢሆንም እምነት ሳይለይ በዚህ ወቅት በዓለም ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለ የዘመን ቀመር ነው።

ይህ የዘመን አቆጣጠር ተግባራዊ የሆነው ፖፕ ግሪጎሪ (ጎርጎሪዮስ) 13ኛ ለረጅም ዘመናት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረውን የጁሊያን የዘመን አቆጣጠርን በ1582 በቀየሩበት ጊዜ ነው።

ይህ የጎርጎሪዮሳውያን የዘመን አቆጣጠር በዋናነት በአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት መስፋፋት፣ በንግድ እና በሌሎች ተጽእኖዎች አማካኝነት ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ለመስፋፋት ችሏል።

በዘመኑ የአውሮፓ ኃያላን አገራት የነበሩት ስፔን፣ ፖርቱጋል፣ ፈረንሳይ እና ብሪታኒያም የዘመን አቆጣጠሩን በቅኝ ግዛቶቻቸው ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረጋቸው በዓለም የመስፋፋት ዕድልን ፈጥረዋል።

የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑ አገራት አዲሱን የዘመን አቆጣጠር በፍጥነት ሲቀበሉት፣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሚበዛባቸው አገራት ደግሞ ቀስ በቀስ ተቀብለው መጠቀም ጀምረዋል።

በዘመናት ሂደትም ዓለም አቀፍ ንግድ እና ግንኙነት በመስፋፋቱ ለሁሉም የሚያገለግል ወጥ የዘመን መቁጠሪያ አስፈላጊነት በመጨመሩ ከሌሎቹ በተለየ በበርካታ አገራት ተቀባይነት ያገኘው ይህ የግርጎሪዮሳውያን የዘመን መቁጠሪያ ትኩረትን አግኝቷል።

ይህ የዘመን መቁጠሪያ የፀሐይ ዑደትን በመከተል በኩል አለው በተባለው ትክክለኝነት የተነሳ የበለጠ ተመራጭ እንዲሆን እንዳደረገው ይነገራል።