ፊቼ ጨምበላላ፦ የሲዳማ ሕዝብ አዲስ ዓመት

ገንዘብ ያበደረ እንዲመለስለት የማይጠይቅበት፣ ከብት የማይታረድበት፣ ዛፍ የማይቆረጥበት፣ ያጠፉ ይቅር የሚባሉበት ዕለት ነው- ጨምበላላ።
የሲዳማ ሕዝብ የጨረቃና ከዋክብትን አቀማመጥ በማጥናት አዲስ ዓመት ያከብራል። በዓሉም ፊቼ ጨምበላላ ይባላል። ይህ በዓል መከበር ከጀመረ ከ1800 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን የአገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ።
የባህል አጥኚው አቶ ብርሃኑ ሃንካራ ደግሞ ''የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሲዳማ ሕዝብ ማንነቱን ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ ሲከበር የቆየ ነው'' ይላሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በቅርስነት የመዘገበው ይህ በዓል ዛሬ መከበር ጀምሯል።
ፊቼ ጨምበላላ በዓል የሚከበርበት ቋሚ ቀን የለውም። በአያንቱዎች ጥቆማ መሰረት በዓሉ የሚከበርበት ቀን ይቆረጣል። ከዚያም ለበዓሉ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ይጀመራል።
ከዋዜማው አንስቶ በዓሉ መከበር ይጀምራል። ጎረቤት ተሰብስቦም ከእንሰት የሚዘጋጀውን ቦርሻሜ ተብሎ የሚጠራውን ምግብ በወተት ይመገባሉ።

ለበዓሉ ከሚበሉ ባህላዊ ምግቦችና ከሚከናወኑ ጭፈራዎች በተጨማሪ የተለያዩ ባህላዊ ሁነቶችም ይካሄዳሉ። ቄጠላ፣ ኛፋሮና የመሳሰሉ ሙዚቃዎችም በበዓሉ ይከወናሉ።
ቄጠላ በተባለው ባህላዊ ሙዚቃ፤ አገር፣ ዘመን፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች እየተወደሱ ይጨፈራል።

''የፊቼ ጨምበላላ ዋነኛ ትርጉም ሰላም ነው'' የሚሉት አቶ ብርሃኑ ሃንካራ፤ አንድነትና ፍቅር የበዓሉ መለያ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የተጣሉ ሰዎች በፊቼ ጨምበላላ በዓል ላይ ይታረቃሉ። ሃዘን ላይ የነበሩ ሰዎችም የሃዘን ልብሳቸውን ይቀይራሉ።
ፊቼ ጨምበላላ ዘንድሮ ያገባች ሴት ሙሽርነቷን ጨርሳ ከሌሎች ሴቶች ጋር የምትቀላቀልበት በዓል ነው።
በተለያዩ ምክንያቶች ከቀዬው ርቆ የነበረ ሰው ለፊቼ ጨምበላላ ወደቀዬው ይመለሳል።

ለዚህ በዓል ተብሎ እርድ አይፈጸምም፤ ስጋም አይበላም። ክብቶችን መምታትም ክልክል ነው። ላሞች ሳር የበዛበት መስክ ላይ ይሰማራሉ።
በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ በፊቼ ጨምበላላ በዓል ወቅት ማረስ ነውር ነው። ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሲዳማ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮም ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው።ፊቼ የአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ ሲሆን፤ ጨምበላላ ደግሞ የአዲስ ዓመት መጀመሪያው ቀን ነው።

ሲዳማ ከአንድ ዓመት ወደሌላው የሚሸጋገርበት ሂደት ሁሉቃ ይባላል። ሁሉቃ ማለት ከሸምበቆና ከአርጥብ ቅጠል ተሠርቶ የሚቆም ነገር ነው።
ሁሉቃ በቤተሰብና በማኅበረሰብ ደረጃ የሚሠራ ሲሆን፤ አዲስ ዓመት ሲገባ ሰዎችና ከብቶች ይተላለፉበታል። የሲዳማ ሕዝብ አዲስ ዓመትን ሲቀበሉ፤ ዓመቱ የብልጽግና እንዲሆንላቸው 'ፊቼ ጄጂ' ይላሉ።












