ለወራት በመቀለብ በውፍረት ውድድር አዲስ ዓመቱን የሚያከብረው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ

የተቀለቡት ወንዶች በጭፈራ ወቅት አርፈው

የፎቶው ባለመብት, Tigabu Gorogi

የምስሉ መግለጫ, ተቀላቢዎቹ ለወራት ደም እና ወተት ብቻ እየጠጡ መቆየታቸው የሚያስከትለውን ውጤት ለማወቅ ጥናት እንደሚያስፈልግ የሥነ ምግብ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል

እርስዎ ውፍረትዎ አሳስበዎት ጠዋት ማታ ስፖርት ይሠሩ ይሆናል ወይ ደግሞ የሚመገቧቸውን ምግቦች እየመረጡ፣ የዕለት የአመጋገብ መርሃ ግብር እያወጡ ሊሆን ይችላል።

በደቡብ ኦሞ ዞን፣ ሰላማጎ ወረዳ የሚገኙት የቦዲ ማኅበረሰቦች ደግሞ አዲስ ዓመታቸውን ለማክበር እየተቀለቡ ነው።

የቦዲ ማኅበረሰቦች አዲስ ዓመታቸውን የሚያከብሩት አዳዲስ ልብሶችን በመግዛት፣ የቤት እቃቸውን በመቀየር አይደለም - ለወራት በመቀለብ እንጂ።

ቦዲዎች አዲስ ዓመታቸውን 'ከኤል' ይሉታል።ከኤል የተለየ ትርጉም የለውም። የዘመን መለወጫ ወይም ልዩ የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ማለት ነው።

ለክብረ በዓሉ የሚዘጋጁትም ከበዓሉ ሁለት ወይም ሦስት ወራት ቀደም ብለው በመቀለብ ነው።

ይህን የሚያደርጉት ወጣት እና ጎልማሳ ወንዶች ብቻ ናቸው።

በፍላጎታቸው ከማኅበረሰቡ የተውጣጡ ወንዶች ለሦስት ወር እና ከዚያ በላይ ወንዝ እና ጥላ ባለበት አካባቢ ይከትማሉ።

እዚያም ከሌላ ምግብ እና መጠጥ ርቀው የከብት ደም እና ወተት ብቻ እየጠጡ በዓሉ እስከሚከበርብት ቀን ድረስ ይቆያሉ።

በዚህ ሁኔታ ከተቀለቡ በኋላ የማኅበረሰቡ አባቶች በዓሉ እንዲከበር በቆረጡበት ቀን ከቆዩበት ሥፍራ እጅ ለእጅ ተያይዘው በመውጣት በባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ታጅበው እየጨፈሩ በዓሉን ያደምቃሉ።

እነዚህ ወንዶች ለሦስት ወራት ገደማ የሚቀለቡት በበዓሉ ቀን ለመጨፈር ብቻ አይደለም።በውፍረት ውድድር አሸናፊ ለመሆንም ጭምር ነው።

በዚህ የውፍረት ውድድር አሸናፊ የሚያደርገው የመጨረሻው ውጤት እንጂ ከቅለባው ቀድሞ የነበሩበት አካላዊ ቁመና ከግምት ውስጥ አይገባም።

በመሆኑም ወደ ቅድመ ዝግጅቱ ከመግባታቸው በፊት የሰውነት ክብደታቸውን አይመዘኑም፤ አይለኩ።

በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑትም ከተቀለቡ በኋላ በሚያስመዘግቡት የሰውነት ዙሪያ ገባ ልኬት ነው። በቅለባው ወቅትም የማኅበረሰቡ አባቶች ማን "ጥሩ ሁኔታ ላይ" እንዳለ በመለካት ሂደቱን ይከታተላሉ።

በበዓሉ ቀን በሚካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይም ከሚጨፍሩት መካከል ማን በደንብ እንደተቀለበ ለማወቅ ከአንገታቸው በታች እና ከእግራቸው በላይ ያለውን የሰውነት ክፍላቸውን ዙሪያ በገመድ በመለካት አሸናፊውን ይለያሉ።

ከዚያም የዓመቱ አሸናፊ አባል የሆነበት ጎሳ ስም ተጠርቶ 'እገሌ' ነው ብለው ያሳውቃሉ።

'እገሌ' የወፈረበት ዓመት ሲሉም ዘመኑን ያወድሳሉ።

የማኅበረሰቡን ባህል ለቢቢሲ ያጋሩ የአካባቢው ተወላጅ እና ባለሥልጣናት እንዳሉት በዚህ ውድድር የሚያሸንፈው ግለሰብ ከሚሰጠው እውቅና ውጨ የሚያገኘው ሽልማትም ሆነ ሥልጣን የለም።

የከኤል ቅድመ ዝግጅት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከኤል ከመከበሩ በፊት የተለያዩ ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች ይከናወናሉ።ከእነዚህ መካከል ዋነኛው የወጣቶች የቅለባ እና የውፍረት ሒደት ነው።

የቅለባው ሒደትም ደንብ እና ሥነ ሥርዓት አለው።

በሒደቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆኑት ወንዶች ወደ ቅለባው ከመግባታቸው በፊት በአገር በቀል መድኃኒቶች ሆዳቸውን መታከም ወይም መታጠብ ይኖርባቸዋል።

ለዚህም 'እንቆቅ' የተባለ እፅዋትን ከሌሎች እፅዋት ጋር በመቀመም ተፈልቶ እንዲጠጡ እና ሆዳቸውን እንዲያጥቡ ይደረጋል።ቢቢሲ የእነዚህን እፅዋት ጥቅምም ሆነ ጉዳት ባያረጋግጥም ማኅበረሰቡ እፅዋቶቹ በሆድ ውስጥ የሚገኙ ጥገኛ ትላትሎችን የማስወገድ አቅም እንዳላቸው ያምናል።

ከዚህ ሒደት በኋላ ነው እንግዲህ መስፈርቱን ያሟሉት ወደ ቅለባው ሒደት የሚገቡት።

በዚህ ሒደት ውስጥ ሴቶች አይሳተፉም።

የዞኑ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ካየ ለቢቢሲ እንደገለጹት ማኅበረሰቡ ሴቶች እንዲወፍሩ አይፈልግም፤ ሴቶቹም በዚህ ላይ ያላቸው አቋም ተመሳሳይ ነው።

"ሴቶቹ ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲሉ መወፈር አይፈልጉም። ምክንያቱም ከወፈሩ ከሚገጥማቸው ማንኛውም አደጋ ሮጠው ማምለጥ አይችሉም" ብለዋል ኃላፊው።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ሴቶች በውፍረት ውድድሩ የማይሳተፉት ራሳቸውን ከጥቃት ለመጠበቅ በአካል ብቁ ሆነው ለመቆየት ነው።

ሆኖም ሴቶቹ የተቀላቢዎቹን ምግብ በማቅረብ እና በመንከባከብ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል።

አቶ ታደሰ ካየ እንዳሉት ተቀላቢዎቹ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ የከብት ደም እና ወተት እየቀላቀሉ ብቻ ነው የሚጠጡት።

የአካባቢው ሽምግሌዎችም ሒደቱን በቅርበት ይከታተላሉ። የበዓሉ ቀን ደርሶ በጣም የወፈረው ግለሰብ እስከሚለይ ድረስ የተቀላቢዎቹን ሆድ፣ ጭን እና የዳሌ መጠንን እየለኩ ይቆያሉ።

በሂደቱ ህመም የሚያጋጥመው ካለም እንዲያቋርጥ ያደርጋሉ። "ብዙውን ጊዜ ግን ውድድር በመሆኑ በበቃኝ የሚወጡ አይኖሩም" ብለዋል አቶ ታደሰ።

የቦዲ ማኅበረሰቦች በከኤል ክብረ በዓል ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Tigabu Gorogi

የምስሉ መግለጫ, ፈቃደኛ የሆኑ ወጣት እና ጎልማሳ ወንዶች አዲስ ዓመታቸውን በውፍረት ውድድር ለማክበር ለወራት ይቀለባሉ

ከኤል

የማኅበረሰቡ አዲስ ዓመት የሚከበረው በየዓመቱ ሰኔ ወር ውስጥ ነው። በዓሉ የሚከበርበት ዕለት ግን በማኅበረሰቡ ሽማግሌዎች በሚቆርጡት ቀን ነው የሚወሰነው።

በማኅበራዊ ገጾቹ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን ታሪክ ከውብ ፎቶዎች ጋር በማጋራት የሚታወቀው ሰይፈገብርኤል ሽፈራው፤ የቦዲ ማኅበረሰብን በተመለከተ በገጹ ላይ ባጋራው ጽሑፍ እንደገለጸው በክብረ በዓሉ ቀን የተቀለቡት ወንዶች በተለያዩ ትርጉም ባላቸው ባህላዊ ጌጣ ጌጦች ይዋባሉ።

የቆዳ እና የብረት ቀበቶ 'ሙዳል' ይታጠቃሉ። ሙዳል የእናት መቀነት እንደ ማለት ነው።

ከየትኛው ጎሳ እንደሆኑና የየትኛው ትውልድ አባል እንደሆኑ ለማመልከትም የተለያየ ቀለም ያለው ቆዳ ጀርባቸው ላይ ያደርጋሉ። ብዙ ጊዜ የእነዚህ የቆዳ ቀለሞች ጥቁር እና ነጭ አሊያም ቡናማ እና ነጭ ነው የሚሆኑት።

ከዚያም እጅ ለእጅ ተያይዘው በመውጣት ይጨፍራሉ።ሌሎች የማኅበረሰቡ አባላትም ያጅቧቸዋል።

'ጆንዴ ሳሩኝ' [የአደባባይ እናት]

እነዚህ ወንዶች ለወራት ሲቀለቡ በመቆየታቸውና ካለ ልክ በመወፈራቸው ጭፈራውን መከወን ይሳናቸዋል።

በባህላቸው መንገድ እግራቸውን እያነሱ ሊጨፍሩ ይቅርና መራመድ ያቅታቸዋል። የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት እና በደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥጋቡ ጎረጊ ለቢቢሲ እንደገለጹት የአንዳንዶቹ መቀመጫቸው፣ ደረታቸውና ሆዳቸው ይሰነጠቃል።

በዚህ ጊዜ በቅለባው ወቅት ሲንከባከቧቸው የነበሩትና በጭፈራው የሚያጅቧቸው ሴት የቤተሰብ አባሎቻቸው አመድ ይዘው እየተከተሉ በተሰነጠቀው የሰውነታቸው ክፍል ላይ ይነሰንሳሉ።

ላባቸውን በመጥረግ፣ የጨሌ ስጦታ በማበርከት እና የላም ወተት በማቅረብም ለእነሱ ያላቸውን ፍቅር ያሳያሉ።

ሰይፈገብርኤል በጽሑፉ ላይ እንዳሰፈረው እነዚህ ሴቶች በቦዲ ቋንቋ 'ጆንዴ ሳሩኝ' ይባላሉ። የአደባባይ እናት እንደ ማለት ነው።

አርብቶ አደር የሆኑት እነዚህ ማኅበረሰቦች በዚህ መልኩ አዲስ ዓመታቸውን የሚያከብሩት ያለፈው ዓመት ጥሩ ምርት ያለበት ወይም ችግር ያልነበረበት መሆኑን ለማሳየት እንዲሁም መጪው ዓመትም በተመሳሳይ መልካም እንዲሆን ምኞታቸውን ለመግለፅ እንደሆነ አቶ ጥጋቡ አስረድተዋል።

የሃብት መጠናቸውን ለማሳየትም ይጠቀሙበታል።

በመቀለብ ሂደቱ ላይ የሚሳተፉት ወጣቶች እና ጎልማሶች ብዙ ከብት ያላቸው ናቸው። የሚቀለቡትም በራሳቸው ሃብት ነው። ብዙ ከብቶች የሌላቸው እና ለመቀለብ አስፈላጊውን ወተት እንዲሁም ደም ማቅረብ የማይችሉት ይህንን ማድረግ አይችሉም።

ከዚህም ባሻገር በዓሉን ሳያከብሩ ካለፉ በበሽታ ይመታሉ የሚል ባህላዊ እምነት አለ።

ለዚህም ነው በባህላቸው መሠረት ለወራት ዝግጅት በማድረግ አዲስ ዓመታቸውን የሚያከብሩት።

የተቀለቡት ወንዶች በበዓሉ ዕለት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲጨፍሩ

የፎቶው ባለመብት, Seifegebreil Shifferaw

የምስሉ መግለጫ, ሴቶች "ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል አቋማቸውን ጠብቀው መቆየት" ስላለባቸው በውድድሩ አይሳተፉም

"ፈንድቶ የሞተ እንዳለ ይነገራል"

የአካባቢው ባለሥልጣናት እንዳሉት ዝግጅቱ በአካባቢው ሽማግሌዎች ክትትል ስለሚደረግለት በተደጋጋሚ ያጋጠመ ችግር የለም።

የተቀለቡት ወንዶች ከክብረ በዓሉ በኋላ ወደ ቀድሞው የአመጋገብ ሥርዓታቸው እና የአኗኗር ዘይቤያቸው ስለሚመለሱ ውፍረታቸው እየቀነሰ ይሄዳል።

ሆኖም ከአምስት ዓመታት በፊት አንድ ተቀላቢ ከተቀመጠበት ለመነሳት ሲሞክር 'ሆዱ ፈንድቶ' መሞቱን አቶ ታደሰ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለመሆኑ ለወራት ደም እና ወተት ብቻ ብንመገብ በሰውነት ላይ ምን ይከሰታል?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ምግብ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ቃለአብ ባዩ፣ እነዚህ ወንዶች በቅለባው ወቅት የሚያገኙት በአመዛኙ ገንቢ [ፕሮቲን] እና ስብ ነው ይላሉ።

ምንም እንኳን በደም እና በወተት ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮችን የሚያገኙ ቢሆንም ከኃይል ሰጪ፣ ከአትክልት እና ከፍራፍሬዎች እንዲሁም አሰር ካላቸው (ፋይበር) ምግቦች የሚገኙ ንጥረ ነገሮችን ያጣሉ።

ሆኖም ለወራት ውስን ምግቦችን እየተመገቡ በመቆየታቸው ሊከተል የሚችለው ውጤት ጥናት እና ምርምር የሚያሻው ነው ይላሉ።

በዚህ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ ከመስጠት በፊትም የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ እና የቀደመ የአመጋገብ ሥርዓት ማጥናት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

"ሥነ ምግብ ከዘር፣ ከአኗኗር ዘይቤ፣ ከእንቅስቃሴ መጠን፣ አመጋገባችን በአንድ ነገር ላይ ተወስኖ ከሚዘልቅበት ጊዜ፣ ከምንኖርበት አካባቢ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ጋር ይያያዛል" የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ተቀላቢዎቹ ለወራት ተመሳሳይ እና ውስን ዓይነት ምግብ ብቻ በመመገባቸው የሚያጡት ንጥረ ነገር መኖሩ እንደማይቀር ይገልጻሉ።

ሆኖም እነዚህን ምግቦች የሚመገቡት ዘላቂ ለሆነ ጊዜ ባለመሆኑ በጣም የመጎዳት ስሜት ይኖራቸዋል ብለው ባይጠብቁም፤ ግለሰቦቹ ወተት እና ደም ብቻ በመጠጣት የሚቆዩበት ጊዜ እንደ ቀላል የሚታይ እንዳልሆነ ፕሮፌሰር ቃለአብ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሆድ አካባቢ የሚከማች ውፍረት እና ስብ ጥሩ የጤና ምልክት እንዳልሆነ ይገልጻሉ። "ይህም እንደ ስኳር እና የደም ግፊት ላሉ ስር የሰደዱ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልን ሊጨምር ይችላል" ብለዋል።

ነገር ግን በጥናት ካልሆነ በስተቀር ቅለባው በሰውነታቸው ላይ የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ ድምዳሜ ላይ መድረስ አስቸጋሪ እንደሆነ አስረድተዋል።

በግምት ከ20 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት የሚነገርለት የቦዲ ማኅበረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል አከባበር ከትውልድ ትውልድ እየተወራረሰ የመጣ ነው።

የበዓሉ ዝግጅት እና የአከባበር ሥነ ሥርዓትም በአካባቢው ባሉ የመንግሥት ተቋማት ድጋፍ ይደረግለታል። ተቋማቱ ተቀላቢዎች የሚጨፍሩበትን ቦታ በማዘጋጀት እንዲሁም በሌሎች ክንውኖች ላይ ይሳተፋሉ።

ይህ ባህል ቀደም ብሎ እንደ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ይቆጠር እንደነበር የገለጹት አቶ ታደሰ፣ "ማኅበረሰቡ ባህሉ እንደሆነ በማመኑ" አሁን ላይ ባህሉ ጎጂ እንዳይሆን ግንዛቤ በመፍጠር በአደባባይ እንዲከበር ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቀደም ብሎ ማኅበረሰቡ "ባህሉ እንዳይበረዝ" በሚል የመንግሥት አካላትን ጨምሮ ፈቃድ ያላገኘ አካል በበዓሉ ላይ እንዳይሳተፉ ይከለክል እንደነበርም ኃላፊው አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ግን ለውጦች በመኖራቸው ይህን ባህላዊ ክብረ በዓል እንደ ሌሎች ባህላዊ ክንውኖች ለማስመዝገብ እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመትም የዘመን መለወጫ በዓሉ ይከበራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ቀን አልተቆረጠለትም።