ከአልዛይመርስ በሕክምና መዳን የሚቻልበት መንገድ ይገኝ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, James Gallagher
አዛይመርስ ያለባቸው ሰዎች ከሕመሙ እንዲድኑ ማድረግ ይቻላል? ይህ ዓመታትን የተሻገረ ጥያቄ ነው።
ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ቀዶ ሕክምና እንዲከታተል የቢቢሲ ዘጋቢ ተጋብዟል።
ቀዶ ሕክምናው የሚከናወነው በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኤደንብራ ሮያል ኢንፊርማሪ ሆስፒታል ነው።
ቀዶ ሕክምናውን ለመከታተል ብዙዎች ተገኝተዋል። ታካሚው ማደንዘዣ ተሰጥቶታል።
በቀዶ ሕክምናው ክፍል በሚገኝ ስክሪን የታካሚው አንጎል ኤምአርአይ ይታያል። አንጎሉ ላይ ደማቅ ነጭ የሆነ እብጠት (ዕጢ) መመልከት ይቻላል።
ካንሰሩ የጀመረው ከታካሚው ትልቁ አንጀት ሲሆን ቀስ በቀስ ወደ አንጎሉ ተስፋፍቷል።
የአንጎል ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ፕሮፌሰር ፖል በርናን "ዕጢው ያለው በአንጎል የላይኛው ክፍል አይደለም። ስለዚህ በኮርቴክ (cortex) ላይ ቀዳዳ ማበጀት አለብን" ይላሉ።
ይህ ቀዳዳ በተቻለው መጠን አነስተኛ ሲሆን፤ ወደ ዕጢው ለመድረስ እንደ መንገድ ያገለግላል።
ኮርቴክስ የላይኛው የአንጎል ክፍል ሲሆን፤ ቋንቋ፣ ትውስታ እና ሐሳብ የሚፈጠርበት ቦታ ነው።
የአንጎል የውስጠኛው ክፍሎች ለስላሳ ቢሆኑም ወደ እነዚህ ክፍሎች ለመድረስ ኮርቴክስ ተሰንጥቆ መታለፍ አለበት።

የፎቶው ባለመብት, James Gallagher
ፕሮፌሰር ፓል የውስጠኛው አንጎል ጋር ሲደርሱ ከልብ ምት ጋር በተመጣጣኝ ሁኔታ የሚመታ፣ ሮዝ ቀለም ያለው ክፍል ይታያል።
በቀዶ ሕክምና ክፍሉ በኤደንብራ ዩኒቨርስቲ የአልዛይመርስ ተመራማሪ ዶ/ር ክሌር ዳረንትም ይገኛሉ።
አንጎልን እና አከርካሪ አጥንትን ከሚሸፍነው ፈሳሽ ጋር የሚመሳሰል ሰው ሠራሽ ፈሳሽ (artificial cerebrospinal fluid) ይዘዋል።
በአብዛኞቹ ቀዶ ሕክምናዎች ከአንጎል ላይ የሚቆረጠው ኮርቴክስ ይጣላል።
የኢደንብራው ማዕከል ውስጥ ግን ይህ የአንጎል ክፍል ጠቀሜታ አለው። በዓለም ላይ ኮርቴክስን ለጥናት ከሚሰበስቡ ተቋማት አንዱ ነው።
ታካሚዎች ፈቃድ ከሰጡ በኋላ በቀዶ ሕክምናው የተቆረጠው ኮንቴክስ ለምርምር ይቀመጣል።

የፎቶው ባለመብት, James Gallagher
በቀዶ ሕክምና የሚወገደው የኮርቴክስ ክፍል በፍጥነት ወደተዘጋጀለት ማስቀመጫ ይገባል። ባለበት ሁኔታ እንዲቆይ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ይደረግለታል።
የኮርቴክስ ክፍሉ ከቀዶ ሕክምና ማዕከሉ ወደ ዩኒቨርስቲው ለምርምር ተወስዷል።
ይህ የአንጎል ክፍል በአንድ ወቅት ሐሳብ፣ ፍርሃት እና ሌሎችም ስሜቶች የሚመነጩበት ነው።
"ይህ የሰውነት ክፍል ሲሰጠን እንደ ትልቅ ስጦታ ነው የምንወስደው። ሰዎች በሕይወታቸው ከባዱ በሆነው ቀን ላይ ነው ይሄንን የአንጎል ክፍል ለመለገስ የሚፈቅዱት" ይላሉ ዶ/ር ክሌር።
በሕይወት ያለ ሰው አንጎል ላይ ከዕድሜ ጋር ስለሚከሰተው የመርሳት ችግር ዲሜንሺያ (dementia) ምርምር ከሚደረግባቸው ማዕከሎች አንዱ የዶ/ር ክሌር ነው።
ዲሜንሺያ መዘንጋት እና የማሰላሰል ብቃት መድከምን ያመለክታል። አልዛይመርስ ከ60 አስከ 80 በመቶ ለዲሜንሺያ የሚዳርግ ሲሆን፤ ቀስ በቀስ የሚስፋፋ የአንጎል ሕዋስ ሕመም ነው።
"እጅግ አስከፊ ከሆነ በሽታ ዓለም የሚድንበትን መንገድ እናገኛለን ብለን እናስባለን" ይላሉ ባለሙያዋ ዶ/ር ክሌር።
ዶ/ር ክሌር የሚሠሩት ጥናት ከአልዛይመርስ በሕክምና መዳን የሚቻልበት መንገድ ይገኝ ይሆን? ለሚለው ጥያቄ መልስ እየፈለገ ነው።
የአልዛይመርስን ተፈጥሯዊ ውቅር በመገንዘብ መፍትሔ ለማግኘት ምርመራቸውን ቀጥለዋል።

የፎቶው ባለመብት, James Gallagher
አሁንም ገና በሕክምና ምርምር መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች አሉ።
ሲናፕሲስ (synapses) የሚባለው የኒውሮን ዓይነቶች መካከል ያለው ትስስር አልዛይመርስ ባለባቸው ሰዎች ላይ ለምን እንደማይታይ እስካሁን ድረስ አይታወቅም።
የፎርሙላ 1 የመኪና እሽቅድምድም ኮከብ የነበሩት የ86 ዓመቱ አዛውንት ጃኪ ስቲዋርት 'ሬስ አጌንስት ዲሜንሺያ' በሚባለው የተራድኦ ድርጅታቸው አማካኝነት ለአልዛይመርስ ምርምር ገንዘብ ለግሰዋል።
በምርምሩ የሚሳተፉት አራት ሳይንቲስቶች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በፍጥነት ነው።
መጀመሪያ ላይ የአንጎል ሕዋሱ ጄል ውስጥ ይቀመጥና ከ10 እስከ 20 ይቆራረጣል።
የአንጎል ሕዋሳቱ በሕይወት እንዲቀጥሉ ልዩ ማቆያ ውስጥ ይቀመጣሉ።
አልዛይመርስ ያለባቸው ሰዎች አንጎል ውስጥ በብዛት የሚገኙት መርዛማ ፕሮቲኖች (amyloid እና tau) ይባላሉ።
እነዚህ መርዛማ ፕሮቲኖች የአንጎል ቁርጥራጮቹ ላይ ይጨመራሉ።
ሲናፕሲስ የሚባለው የኒውሮን ዓይነት በመርዛማ ፕሮቲኖች ምክንያት ከጥቅም ውጪ ሲሆን የሚመለከቱት ሳይንቲስቶች ጉዳቱን ማስቆም የሚቻልበት መንገድ ካለ ይመራመራሉ።
አልዛይመርስን በፍጹም ማከም አይቻልም ብሎ መደምደም እንደማይቻል ዶ/ር ክሌር በጥናታቸው ተገንዝበዋል።
"ከዚህ ቀደም ያለው ተሞክሯችን በሽታዎችን ማከም እንደሚቻል ያሳያል። አልዛይመርስ ሰው የመሆን አንድ ገጽታ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ አንድ ቀን እናቀርብ ይሆናል። አሁን ግን ጊዜው አልደረሰም" ሲሉ የዶ/ር ክሌር ባልደረባ ይናገራሉ።
"በምሠራው የአልዛይመርስ ጥናት አሁን ብዙም ተስፋ አላየሁም። በእኔ የዕድሜ ዘመን ትርጉም የሚሰጥ መሻሻል እናያለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉም አክለዋል።
ባለሙያዎቹ ተስፋ የጣሉት በሁለት መድኃኒቶች ላይ ነው። lecanemab እና donanemab የተባሉት መድኃኒቶች አልዛይመርስ የሚስፋፋበት ፍጥነት ያዘገያሉ።
መድኃኒቶቹ በሕሙማን ጤና ላይ የሚያሳዩት መሻሻል ላይ አሁንም ተጨባጭ መረጃ አለ ለማለት ግን ያስቸግራል።
በኤደንብራ ዩኒቨርስቲ የአንጎል ሳይንስ ክፍል ኃላፊ ፕሮፌሰር ታራ ስፓየርስ-ጆንስ እንደሚሉት እነዚህ መድኃኒቶች ለአልዛይመርስ ጥናት መሻሻል አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
የኮከብ ቅርጽ ያላቸው ሰውነትን ከበሽታ የሚከላከሉ ሕዋሳት (astrocytes) በአልዛይመርስ ያላቸው ሚና ላይ ጥናት ያደርጋሉ።
ከላይ የተጠቀሱት ሁለት መድኃኒቶች መርዛማ ፕሮቲን (amyloid) ላይ አነጣጥረው ይሠራሉ።
ሌላኛው መርዛማ ፕሮቲን (tau) ላይ ደግሞ የሕክምና ምርምሮች እየተደረጉ ነው።
አልዛይመርስን በሕክምና ለማዳን በተለያየ አቅጣጫ የሚደረጉ ምርምሮች አካል ነው።
አልዛይመርስን በጥልቅ ለመረዳት የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም፣ የደም ሕዋስ እና የከባቢ አየር ሁኔታን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ተመራማሪዎች ተስፋ የሚያደርጉት በመጀመሪያ ደረጃ በሽታው የሚስፋፋበትን ፍጥነት ማዘግየት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ዲሜሺያ እንዳይከሰት ማድረግ ይፈልጋሉ። ሦስተኛው ግን ደግሞ የአልዛይመርስ ምልክት እያሳዩ ያሉ ሰዎችን ማከም ነው።
ከአምስት እስከ 10 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ "ሕይወት የሚለውጥ" ሕክምና እንደሚገኝ ባለሙያዋ ተስፋ ያደርጋሉ።
"በሽታው ሳይባባስ በመድረስ መደበኛ ሕይወትን ለመግፋት የሚያስችልበት መንገድ ይዘረጋል" ይላሉ።
"የሰው ልጅ አንጎል እጅግ ውስብስብ ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር ታራ።
አልዛይመርስን ለማከም ተስፋ ቢኖርም አሁንም ጥናቶች እና የሕክምና ሙከራዎችም መቀጠል አለባቸው።















