ወጣቶች በተለይ ደግሞ ሴቶች የልብ ጤናቸውን መከታተል ያለባቸው ለምንድን ነው?

 የ24ዓመቷ ኬይትሊን ላውረንስ
የምስሉ መግለጫ, ኬይትሊን ላውረንስ

"በጣም የማይበገር እንደሆንኩ አስቤ ነበር... እና በድንገት በአንድ የስፖርት አዳራሽ ውስጥ ወደቅኩ እና ችግሬ ምን እንደሆነ ማንም አላወቀም ነበር።" ትላለች።

የኬይትሊን ላውረንስ ሕይወት የተለወጠው በ22 ዓመቷ ኔትቦል ስትጫወት ካጋጠማት የልብ ሕመም በኋላ ነው።

ጤናማና ጠንካራ ስፖርተኛ በመሆኗ በልቧ ላይ ችግር ሊገጥማት እንደሚችል አስባ አታውቅም ነበር።

ይህ የተለመደ ጉዳይ ነው።የልብና የደም ቧንቧ በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለወንዶችም ለሴቶችም ዋነኛ የሞት መንስኤ ነው። ነገር ግን ባለሙያዎች ሴቶች ብዙውን ጊዜ አደጋ ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ አይገነዘቡም።

ኬይትሊን እአአ ጥቅምት 2023 ራሷን ስታ ስትወድቅ በቀሪው ሕይወቷ ላይ ሁሉ ጉልህ አሻራውን ያሳረፈ መሆኑን ትናገራለች። ለኔትቦል ግጥሚያዋ ሰውነቷን ስታሟሙቅ እንደነበር አታስታውስም፤ ትንሽ የማቅለሽለሽ ስሜት እንደተሰማት ግን ትዝ ይላታል።

የ24 ዓመቷ ኬይትሊን "የሚቀጥለው የማስታውሰው ነገር ፊቴ ላይ የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያ እንደነበር ነው" ብላለች።

ራሷን ስታ ከወደቀች በኋላ ለስድስት ደቂቃዎች አልነቃችም። "ምን ችግር እንዳለብኝ በትክክል አያውቁም ነበር" ብላለች።

በሆስፒታል የተደረገላት ምርመራ የልቧ ምት መዛባቱን በማሳየቱ የልብ ምቷን የሚከታተል መሣሪያ ተገጠመላት። ከዚያም ቀስ በቀስ እንደገና ወደ ምትወደው ስፖርት ተመለሰች።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ፣ በአንድ ሞቃታማ በሆነ የሳምንት መጨረሻ ላይ ከኔትቦል ጨዋታ በኋላ፣ ዶክተሯ የልብ ምቷ ጤነኛ አለመሆኑን ስላስተዋለ ክትትል ከምታደርግበት ሆስፒታል ስልክ ተደወለላት።

የልብ ምቷን ለመከታተል የተገጠመው መሣሪያ ከፍተኛ የሆነ የልብ ምት መዝግቧል።ያ ደግሞ ያልተለመደ ነው።

የኬይትሊን ልብ ለ11 ሰከንዶች ያህል በደቂቃ 294 ጊዜ ይመታ ነበር። ይህም በዕድሜ እኩዮቿ የሆኑ ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ከሚጠበቀው ከ100-170 የበለጠ ነው።

ዶክተሮች ይህ ሊገድላት እንደሚችል ነግረዋታል።

አሪትሞጄኒክ ካርዲዮሞፓቲ (arrhythmogenic cardiomyopathy) በሚባል አልፎ አልፎ የሚከሰት የልብ ሕመም እንዳለባት ታወቀ።

ይህ ማለት የጡንቻዎቿ ህዋሳት በሚፈለገው መንገድ አልዳበሩም ማለት ነው።

ኬይትሊን ቤተሰቧ በዚህ በሽታ እንደሚጠቃ ምንም የምታውቀው ነገር አልነበረም። ሕክምና ክትትል የሚያደርጉላት ባለሙያዎች ዳግም ኔትቦልን በክለቦች ውስጥ መጫወት እንደማትችል ነግረዋታል።

"ከሰማሁት ሁሉ የከፋው ይህ ነበር" ትላለች።

"በእድሜ የገፉ ሰዎች ሕመም አይደለም"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዓለም የልብ ሕመም ፌዴሬሽን (ደብሊውኤችኤፍ) እንደሚለው በሴቶች ላይ የሚከሰተው የልብና የደም ቧንቧ በሽታ በቂ ምርመራ እና ሕክምና ያልተደረገለት ነው። ይህ የሆነው በታካሚዎችም ሆነ በዶክተሮች መካከል ባለው የተሳሳተ ግንዛቤ እና የግንዛቤ እጥረት ምክንያት መሆኑን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

"በየቀኑ የልብና የደም ቧንቧ ችግር እንዳለባቸው የማያውቁ ሴቶች ያጋጥሙናል" ይላሉ የፌዴሬሽኑ ዋና ኦፕሬሽን ኦፊሰር ቦርጃና ፔርቫን።

የልብ ድካም ምልክቶች፣ ብዙውን ጊዜ ስር የሰደደ በሽታ የመጀመሪያ ምልክት ሊሆን የሚችል በመሆኑ፣ ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ ለመለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

በጣም የተለመደው የልብ ድካም ምልክት የሆነው የደረት ሕመም ሁልጊዜ በሴቶች ላይ የሚታይ አይደለም።

በምትኩ፣ ሕመሙ በትከሻዎች፣ በአንገት፣ በመንጋጋ፣ በክንድ፣ በሆድ እና በጀርባ የበለጠ ሊሰራጭ ይችላል።

ሴቶችም ያልተነገረ ጭንቀት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማዞር፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የልብ ምት እና ቀዝቃዛ ላብ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ምልክቶቹ ቀደም ብሎ ያላጋጠመ ድካም ተከትለው ሊመጡ ይችላሉ።

የጤና ባለሙያዎችም ቢሆኑ ምልክቶቹን ሊያስተውሏቸው ይችላሉ። ፐርቫን እንዳሉት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ክስተቶች አጋጥሟቸዋል።

ከእነዚህም መካከል በቅርቡ የወለደች እና ምልክቶቹ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የመንፈስ ጭንቀት እንደሆኑ በስህተት የተነገራት የ27 ዓመት ታካሚ ትገኝበታለች።

"ሴቶች ምልክቶቹ ቢያጋጥማቸውም ወደ ሆስፒታል የመሄድ ዕድላቸው አነስተኛ ነው" ብለዋል።

"ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር ፈጣን እና በቂ ሕክምና የማግኘት ዕድላቸው አነስተኛ ነው እና ወደ ሆስፒታል ከመጡ በኋላ እንኳን የመትረፍ ዕድላቸው አነስተኛ ነው።"

የዓለም የልብ ሕመም ፌዴሬሽን የልብና የደም ቧንቧ በሽታ በሴቶች ላይ ሞት ከሚያስከትሉ ሕመሞች 30 በመቶውን ይይዛሉ።

እንደ ብሪታኒያ የልብ ፋውንዴሽን እአአ በ2021 የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በዚያ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሴቶች በበሽታው ሞተዋል፤ ይህም ከስዊትዘርላንድ ሕዝብ ቁጥር ይበልጣል።

ፐርቫን "ይህ የአረጋውያን በሽታ አይደለም። እንደዚያ ብሎ ማሰብ በጣም አደገኛ ስህተት ነው" ይላሉ።

የልብ ሕመምን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ኬይትሊን ኳስ ይዛ በሜዳ ውስጥ ቆማ ትታያላች
የምስሉ መግለጫ, ኬይትሊን የኔትቦል ተጫዋቾች ወደ መጫወቻ ሜዳ ከመግባታቸው በፊት የልብ ጤንነታቸውን እንዲከታተሉ ትቀሰቅሳለች

እንደ ኬይትሊን ያሉ በዘር የሚመጣ የልብ ጤና ችግሮች የሚያጋጥማቸው ሰዎች ያለጊዜያቸው ከሚሞቱት ሰዎች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑትን ይሸፍናሉ ሲሉ ፐርቫን ተናግረዋል።

በልብ ሕመም ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት አደጋውን ሊያባብሰው እንደሚችል የሚናገሩት ባለሙያዋ፤ ስለዚህ ሰዎች ከእነዚህ በሽታዎች ጋር በተያያዘ ሌላ የቤተሰብ አባል ታምሞ ወይንም ተመርምሮ እንደሆነ ማወቅ አስፈላጊ ነው።

የቀሩት 80 በመቶ የሚሆኑት ያለጊዜው የሚከሰቱ ሞቶችን የአመጋገብ ስርዓትን በማሻሻል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በመጨመር፣ የአልኮል መጠጥን በመገደብ እና ባለማጨስ መከላከል ይቻላል።

"ነገር ግን በማኅበረሰቡ እና በሥርዓቱ ውስጥ የሚያጋጥሙ ነገሮችም ትልቅ ድርሻ አላቸው፤ ግለሰቡ ምን እንደሚበላና ምን እንደሚገዛ በሚመርጠው ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም" ይላሉ ፐርቫን ።

በሴቶች ላይ የሚደረጉ ምርምሮች እና ሙከራዎች አለመኖር፣ ደካማ የትምህርት ደረጃ እና የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት ውስንነት ሁሉም አደጋዎችን ያባብሳሉ።

የዓለም የጤና ድርጅት 80 በመቶ የሚሆነው የልብ እና የደም በንቧ በሽታዎች ሞት የሚከሰተው በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ ሲሆን፣ ይህም በከፊል የቅድመ ምርመራ ፕሮግራሞች እጥረት በመኖሩ ነው ብሏል።

ምንም እንኳን በአብዛኛዎቹ የዓለማችን አካባቢዎች ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በልብና የደም ሥር (cardiovascular) በሽታዎች ቢሞቱም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሰሜን አፍሪካ እና ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ክፍሎች እንደ ኳታር፣ ማሊ እና ኮንጎ ባሉ አገራት ሴቶች ከፍተኛ የሞት መጠን ያጋጥማቸዋል።

"በሕይወት እንድንቆይ የሚያደርገው ጡንቻው ነው"

ኬይትሊን አሁን ልቧን የሚከታተል ውስጣዊ የልብና የደም ሥር (cardioverter defibrillator) ተገጥሞላታል። ሌላ ለሕይወት አስጊ የሆነ የልብ ምት ካገኘ፣ ይህ ልቧን ወደ መደበኛ ሁኔታው ​​ይመልሰዋል ማለት ነው።

በሕይወቷ ውስጥ በጣም መጥፎውን ቀን ካሳለፍች በኋላ ሌሎች የኔትቦል ተጫዋቾች ተመሳሳይ አደጋ እንዳያጋጥማቸው ለመከላከል ቆርጣ ተነስታለች።

ከኔትቦል ተጫዋቾች ማኅበር እና ካርዲያክ ሪስክ ኢን ዘ ያንግ ከተባለ ማኅበር ጋር በመተባበር ዘመቻ ካካሄደች በኋላ የዩናይትድ ኪንግደም የኔትቦል ሱፐር ሊግ ለአትሌቶቹ የልብ ምርመራ ለማድረግ ተስማምቷል።

ኬይትሊን ከተሞክሮዋ በመነሳት "በበቂ ስላልተነገረ ብቻ ነው" እንጂ ወጣቶች የልብ ጤንነታቸውን ማወቅ አለባቸው ትላለች።

አንድ ሰው ከተለመደው የተለየ የልብ ምት ከተሰማው፣ ልቡ ደረቱን ጥላ ለመውጣት እየታገለች እንደሆነ ከተሰማው፣ ሊገልፀው በማይችለው ምክንያት ራሱን ከሳተ፣ መመርመር ያለበት የመጀመሪያው ነገር ልቡ ነው ትላለች።

"ሕያው የሚያደርገን ጡንቻው ነው፣ ስለዚህ መመርመር አለብን" ስትል አክላለች።