በሠው ሰራሽ አስተውሎት የሚታገዝ ስቴትስኮፕ በሰከንዶች ውስጥ ዋና ዋና የልብ ችግሮችን መለየት ይችላል ተባለ

በኤአይ በታገዘ ስቴትስኮፕ የልብ ምቷን የምታዳምጥ ዶክተር እና ታካሚ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

በሠው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የሚታገዙ ስቴትስኮፖች በሴኮንዶች ውስጥ ሦስት የተለያዩ የልብ በሽታዎችን ለመለየት ይረዳሉ ሲሉ ተመራማሪዎች ተናገሩ።

የመጀመርያው ስቴትስኮፕ እአአ በ1816 የተፈለሰፈ ሲሆን ዶክተሮች የታካሚውን ውስጣዊ አካል ድምፆች እንዲያዳምጡ ያስችላቸዋል።

ዘመናዊ ስሪትን በመጠቀም ምርምር ያካሄደው የብሪታንያ የሕክምና ቡድን፤ የልብ ድካም፣ የልብ ቫልቭ በሽታ እና ያልተለመዱ የልብ ምቶችን በቅጽበት እንደሚለይ አረጋግጠዋል።

ተመራማሪዎቹ ይህ መሳሪያ ሕሙማን በፍጥነት የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ በመርዳት ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል።

በምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ ለንደን በሚገኙ 205 የቀዶ ሕክምና ክሊኒኮች ሙከራ ከተካሄደ በኋላ በመላው ዩናይትድ ኪንግደም ጥቅም ላይ ለማዋል ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚታገዘው ይህ መሳሪያ የተለመደውን የልብ ምት ማዳመጫ የመጫወቻ ካርድ መጠን ባለው አዲስ መሳሪያ ይተካዋል ተብሏል።

ይህ መሳሪያ የሰው ጆሮ ሊያዳምጠው የማይችለውን የልብ ምት እና የደም ፍሰት ልዩነትን አዳምጦ ለመተንተን ማይክራፎን ይጠቀማል።

እንዲሁም ኢሲጂ (ኤሌክትሮካርዲዮግራም) ይወስዳል፤ ከልብ የሚመጡ የኤሌትሪክ ምልክቶችን ይመዘግባል፤ በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ ታማሚዎች መረጃ ሰብስቦ ለመተንተን ወደሰለጠነ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የዳታ ማዕከል ይልካል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ እና ኢምፔሪያል ኮሌጅ ሄልዝኬር ኤን ኤች ኤስ ትረስት የተደረገው ጥናት በአሜሪካ ኩባንያ ኤኮ ሄልዝ በተመረተ በኤአይ ስቴቶስኮፕከ የተመረመሩ1ከ2,000 በላይ ታካሚዎች እንዲሁም 96 የቀዶ ሕክምና ክሊኒኮችን አሳትፏል።

ከዚያም ውጤቱ ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ ያልዋለባቸው 109 ቀዶ ሕክምና የተደረገላቸው ታካሚዎች ጋር ተነጻጽሯል።

ተመራማሪዎቹ የልብ ድካም ያለባቸው ሰዎች በ12 ወራት ውስጥ በአይ ስቴቶስኮፕ ሲመረመሩ በ2.33 እጥፍ የመታወቅ ዕድሉ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ምንም ምልክት የሌላቸው ያልተለመዱ የልብ ምቶች ነገር ግን ስትሮክ የማስከተል አቅም ያላቸው ደግሞ በኤአይ ስቴቶስኮፕ በ3.5 እጥፍ የበለጠ መለየት ተችለዋል። የልብ ቫልቭ በሽታ ደግሞ በ 1.9 እጥፍ የበለጠ መለየት መቻሉን ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።

በብሪቲሽ ሀርት ፋውንዴሽን (ቢኤችኤፍ) ክሊኒካል ዳይሬክተር እና አማካሪ የልብ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሶንያ ባቡ ናራያን "ይህ ከ 200 ዓመታት በፊት የተፈጠረውን ምርጡን ስቴቶስኮፕ ለ 21 ኛው ክፍለዘመን እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው" ብለዋል።

እንዲህ ያሉ ፈጠራዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው ካሉ በኋላ "ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ይህ ሁኔታ የሚታወቀው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ታካሚዎች በድንገተኛ አደጋ ሆስፒታል ሲገቡ ብቻ ነው" ብለዋል።

"አስቀድሞ በሚደረግ ምርመራ ሰዎች ለረጅም ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እንዲኖሩ ለመርዳት የሚያስፈልጋቸውን ሕክምና ማግኘት ይችላሉ" በማለት አስረድተዋል።

ግኝቶቹ በዓለም የአውሮፓ የልብ ሕክምና ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዶክተሮች ቀርበዋል።

አዲሱን ስቴቶስኮፕ በደቡብ ለንደን፣ሱሴክስ እና ዌልስ ለአጠቃላይ ሕክምና ዶክተሮች ለማስተዋወቅ ዕቅድ ተይዟል።