ልባቸው በቀኝ ለሚገኝ ሰዎች የሚደረገው ውስብስብ ቀዶ ሕክምና

ልቧ በቀኝ በኩል ሆኖ ቀዶ ሕክምና ያስፈለጋት ው ሰዎች አንዷ መሆኗን ሞናራኒ

የፎቶው ባለመብት, MANIPAL HOSPITAL BROADWAY

የምስሉ መግለጫ, ልቧ በቀኝ በኩል ሆኖ ቀዶ ሕክምና ያስፈለጋት ው ሰዎች አንዷ መሆኗን ሞናራኒ

በኢትዮጵያ ባለፈው ግንቦት ላይ የሰውነት ክፍሎቹ በተቃራኒው ለነበረው የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ውስብስብ እና የተሳካ የልብ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለት እንደነበር ይታወሳል።

በኢትዮ-ኢስታንቡል አጠቃላይ ሆስፒታል ቀዶ ሕክምናውን የመሩት የሕጻናት እና የአዋቂዎች የልብ ሐኪም ዶ/ር ሺቢቆም ታምራት ሲሆኑ፣ ቀዶ ሕክምና የተደረገለት ታዳጊ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ቡርጂ ዞን፣ ሶያማ ከተማ የተወለደው ሂዶ ጂማ ሂዶ ነው።

በወቅቱ ዶ/ር ሺቢቆም ቀዶ ሕክምናውን “ከባድ፣ በጣም ጥንቃቄ የሚጠይቅ እና ውስብስብ” በማለት ነበር ለቢቢሲ የገለጹት።

ሞናራኒ ዳስም ተመሳሳይ ተፈጥሮ እንዳላት እንዲታወቅ ምክንያት የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት ደረቷን በቀኝ በኩል ማመም ከጀመራት በኋላ ነው።

የአሲድ መጠን ከፍ ማለት ለህመሟ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ቤተሰቦቿ ገመቱ።

ሆኖም የ52 ዓመቷ ሞናራኒ ህመም ከአሲድ ጋር የተገናኘ አይደለም። ሕክምና ለማግኘት ከአገሯ ባንግላዴሽ መውጣት ነበረባት።

“ቀኝ ደረቴን ያመኝ ነበር። መተንፈስም ይቸግረኛል” ስትል ታስታውሳለች።

ብዙም ሳይቆይ ልብ ድካም ጀመራት። ሕክምና ሲደረግላት ግን ሐኪሞች ስለ ልቧ አዲስ መረጃ አገኙ።

“ሐኪሞቹ ልቤ በቀኝ በኩል እንዳለ አወቁ” ትላለች።

ምሥል

ልብ በግራ በኩል መሆን እያለበት በቀኝ ደረት በኩል የሚገኝበት ሁኔታ (dextrocardia) ከሚገጥማቸው ሰዎች አንዷ መሆኗን ሞናራኒ አወቀች።

የእሷን ሁኔታ የተለየ የሚያደርገው ሌሎች ዋነኛ የሰውነት ክፍሎቿም በተቃራኒ የሰውነት ክፍል መገኘታቸው ነው። ይህ ሁኔታ በእንግሊዘኛው ሳይተስ ኢንቨርሰስ (situs inversus) በሚል ይታወቃል።

ኩላሊቷ፣ ሳንባዋ፣ ሆድ ዕቃዋ ከተለመደው አቀማመጥ በተቃራኒው የሚገኙ ናቸው።

ይህ ሁኔታ የሚገጥመው ከ12,000 እርግዝናዎች መካከል በአንደኛው እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።

ሞናራኒም የገጠማት ተመሳሳይ ችግር ነበር። ቤተሰቦቿ በምሥራቃዊ ሕንድ፣ ኮላካታ ወደሚገኝ የልብ ሐኪም ወሰዷት።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የባንግላዴሽ ዜጎች ለሕክምና ወደ ሕንድ ይሄዳሉ። ሕንድ የተሻለ ሕክምና እንደሚገኝ ያምናሉ።

ዶ/ር ሲደርታ ሙኬኸርጂ ከተባሉ ሐኪም ጋር ተገናኘች። ቀዶ ሕክምናም አደረጉላት።

“ልባቸው በቀኝ ላለ ሰዎች ቀዶ ሕክምና ማድረግ ፈታኝ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሐኪሞች የምንሠራው በቀኝ እጅ ነው። የለመድነውም በታካሚው ቀኝ በኩል መሥራት ነው። በታካሚው ግራ የሰውነት ክፍል ሆኖ መሥራት ይፈትናል” ይላሉ ሐኪሙ።

“በታካሚዋ ግራ የሰውነት ክፍል ሆነን ቀዶ ሕክምናውን ማከናወን ነበረብን። ይህን ያልተለመደ ሁኔታ ለመልመድ መሞከር ነበረብን” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።

ቀዶ ሕክምናው በስኬት እንደተጠናቀቀ እና ታካሚዋ ወደ ባንግላዴሽ መመለሷን አክለዋል።

ረዛኡል ካሪም

የፎቶው ባለመብት, MEDICA SUPERSPECIALITY HOSPITAL

የምስሉ መግለጫ, ረዛኡል ካሪም

ልብን ማከም

በሕንድ የተለየ የልብ አቀማመጥ ከገጠማቸው አንዱ የ66 ዓመቱ ረዛኡል ካሪም ናቸው።

ልባቸው በግራ በኩል ሆኖ ቢወለዱም ለረዥም ጊዜ በቆየ ሳል ምክንያት አቅጣጫውን መቀየር ጀመረ።

ከልጅነታቸው ጀምሮ የመተንፈስ ችግር ነበረባቸው።

“ለ25 ዓመታት ፖለቲካ ውስጥ ስለነበርኩ ከቦታ ቦታ እሯሯጥ ነበር። ሐኪም ጋር ሄጄ የተሰጠኝን መድኃኒትም እወስድ ነበር” ይላሉ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ግን ይደክማቸው ጀመር። ልጃቸው በዚህ ስጋት ስለገባት ወደ ሜዲካል ሱፐር ስፔሻሊቲ ሆስፒታል ወሰደቻቸው።

“መተንፈስ አልችልም ነበር። ለመቆም ይከብደኝ ነበር። ለፀሎት ተንበርክኬ መነሳት አልችልም” ይላሉ።

በልጅነታቸው ሳምባ ነቀርሳ ካመማቸው በኋላ ልባቸው ወደ ቀኝ መንሸራተቱን ሐኪሞች ደረሱበት።

ያለፈው ሰኔ ላይ በአፋጣኝ ቀዶ ሕክምና እንዲያደርጉ ተነገራቸው።

የልባቸውን ምትና ትንፋሻቸውን የሚቆጣጠር ፔስሜከር እንዲገጠምላቸው ተደረገ።

የልብ ቀዶ ሕክምና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የልብ ቀዶ ሕክምና

ፔስሜከር ልብ በጣም ዝግ ብሎ እንዳይመታ ይረዳል። ለheሙማን አደገኛ ሊሆን የሚችልበትም መንገድም አለ።

ቀዶ ሕክምናውን ያደረጉት ዶ/ር ዲሊፕ ኩማር እንደሚሉት፣ ፔስሜከር በአብዛኛው የሚገጠመው በህሙማን ግራ ደረት በኩል ስለሆነ ለረዛኡል የተደረገው ሕክምና ውስብስብ ነበር።

በቀኝ ደረት በኩል በሚገኝ ልብ ላይ ከዚህ ቀደም ተደርጎ የማይታወቅ ሲኤስፒ (CSP) የተባለውን የቀዶ ሕክምና ሂደት መከተላቸውን ሐኪሙ ይናገራሉ።

ይህ ሕክምና ፔስሜከርን በመጠቀም ልብ በተስተካከለ ሁኔታ እንዲሠራ የሚያደርግ ነው።

ከቀዶ ሕክምናው በኋላ አሁን የ66 ዓመቱ ረዛኡል በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

የጤናቸውን መሻሻል ለመለካት በቅርቡ ምርመራ ይደረግላቸዋል።

ሐኪሞቻቸው እንደሚሉት ለመተንፈስ ይገጥማቸው የነበረው ችግር ቆሟል። ራሳቸውን ሳይስቱ ተንበርክከው ጸሎት ማድረስም ይችላሉ።