"ከእናቴ አልዛይመርስ ተላልፎብኝ ይሆን?"

የጄኒንግስ ቤተሰብ

የፎቶው ባለመብት, Jennings family

የጆን ጄኒንግስ እና ኤሚሊ ጄኒንግስ እናት የአልዛይመርስ (የመርሳት ሕመም) ምልክት ያሳዩት በ50 ዓመታቸው ነበር።

ጆን እና ኤሚሊ እናታቸው ሲታመሙ እነሱም የበሽታው ተጋላጭነታቸው 50 በ50 መሆኑ ታወቃቸው።

ጆን እንደሚለው ዕቃ አዘውትሮ የሚገዛ ሰው አይደለም። አንድ ጫማ ወይም ላፕቶፕ ዘለግ ላለ ጊዜ መጠቀም ይመርጣል።

የሚኖረው በኤዲንበርግ ከተማ ከባለቤቱ ማት ጋር ነው።

የእናቱን ዘረ መል መውረስ ወይም አለመውረሱን እርግጠኛ አይደለም።

ዘረ መሉ ተላልፎበት ከሆነ ለመርሳት ሕመም ተጋላጭነቱ ይጨምራል።

“የሚያስደስተኝ የሚወዱኝ ሰዎች አጠገብ መሆን ነው” ይላል።

ከሰዎች ጋር ሆኖ የሚሰማውን ደስታ አልዛይመርስ እንዳያሳጣው ይፈራል።

ልክ እንደ እናቱ 50 ዓመት ሲሆነው ተጋላጭ እንደሚሆን ይሰጋል።

“ብዙ ቋንቋዎች ለመማር እየሞከርኩ ነው። በጣም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እሠራለሁ። በሕመሙ የመያዝ ዕድሌን እንደሚቀንሰው አምናለሁ” ይላል።

ብዙዎች ለበሽታው የሚጋለጡት በዕድሜ መጨመር ምክንያት ነው።

ከአንድ በመቶ ያነሱ ሰዎች ለበሽታው የሚጋለጡት በዘረ መል ምክንያት ነው።

በ1980ዎቹ የቤተሰብ ተጋላጭነት በሕመሙ የመያዝ ዕድልን እንደሚያሰፋው አይታወቅም ነበር።

የጆን አያት እና አራት ቤተሰቦቻቸው የመርሳት ሕመም አለባቸው። ሁሉም ሕመሙ የተገኘባቸው በ50ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ነው።

ቢቢሲ ቱ በቅርብ የሠራው ዘጋቢ ፊልም ላይ ካሮል የተባሉ የጆን እናት እንዴት ስለ ሕመሙ ያለውን አመለካከት እንደለወጡ ያሳያል።

ለነገሮች መፍትሔ መስጠት ይወዱ እንደነበር ያስታውሳል።

የጄኒንግስ ቤተሰብ

የፎቶው ባለመብት, Jennings family

እአአ በ1986 ለኮሌጅ ኦፍ ለንደን ዩኒቨርስቲ ደብዳቤ ጻፉ።

በቤተሰባቸው ዘረ መል ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት፣ ዘረ መሉን ቤተሰቡ እንደሚጋራ በ1991 ተደረሰበት።

ለሕመሙ የመጋለጥ 50% ዕድልን ለልጃቸው ጆን አውርሰዋል። ሌላዋ ልጃቸው ኤሚሊ የመጋለጥ ዕድል ደግሞ 42% ነው።

የነርቭ ህመም ባለሙያዋ ዶ/ር ካት ሙመሪ “አንድ ሰው ዘረ መሉ በሰውነቱ ካለ የቤተሰብ አባሉ በሕመሙ በተያዘበት ዕድሜ አካባቢ በሕመሙ የመያዝ ዕድል ይኖረዋል” ሲሉ ያስረዳሉ።

በተለይ ወደዚያ ዕድሜ ሲደርሱ ሕመሙ ሊኖርብኝ ይችላል የሚለው ፍርሃታቸው ይጨምራል።

የደም ምርመራ ይደረግላቸውና ምን ያህል ተጋላጭ እንደሆኑ ይጣራል።

የጄኒንግስ ቤተሰብ

የፎቶው ባለመብት, Jennings family

የጆን እናት ምርመራ ላለማድረግ ወስነው ነበር። ትርፉ ጭንቅ ነው ብለው ነው ያሰቡት።

ጆን ግን “ቀድመን አውቀን ቢሆን ኖሮ እንዘጋጅ ነበር” ሲል ውሳኔውን ይቃረናል።

እሱ 21 ዓመት ሲሞላው በእናቱ ላይ ቅድመ ምልክት ታየ።

ሕመሙ እየበረታ ሲሄድ ያየውን ሲገልጸው “ቀስ በቀስ እየከሰሙ የመሄድ ያህል ነው” ሲል ነው።

እናቱ ሲሞቱ አንጎላቸው ለሳይንሳዊ ምርምር እንዲውል ተናዘዋል።

ጆን የደም ምርመራውን ማድረግ ይፈልጋል። እህቱ ኤሚሊም ዕድሜዋ ሲቃረብ እንድትመረመር ይሻል።

አንዳቸው ሌላቸውን ተከትለው መመርመራቸው ስለማይቀር “የጋራ ውሳኔ ነው” ሲል ይገልጸዋል።

ለመርሳት ሕመም የሚደረግ ሕክምና መሻሻል ተስፋ ይሰጠዋል። የሰውነትን በሽታውን የመከላከል አቅም የሚያዳብሩ መደኃኒቶች እየተሠሩ ነው።

በዘረ መል የሚተላለፍ አልዛይመርስ ከሌሎች የሕመሙ ዓይነቶች የተለየ ቢሆንም የሚያመሳስሉት ባህሪዎችም አሉ።

በዘረ መል ለሚተላለፈው የሕመሙ ዓይነት መድኃኒት ከተገኘ ለሌሎችም ዝርያዎች ማግኘት እንደሚቻል የሕክምና ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

በሳይንስ መድኃኒት እስከሚገኝ ድረስ ጆን ራሱን እያጽናና ነው።

ከሌሎች ለሕመሙ ተጋላጭነት ያላቸው ሰዎች ጋር የመደጋገፊያ ቡድን አላቸው።

ልክ እንደ እናቱ ሁሉ በመርሳት ሕመም ጥናት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል።

“ሕመሙን ማዳን የሚችል ሕክምና ጫፍ ላይ ደርሷል። ዕድሜ ሰጥቶኝ ስኬቱን ባይ እመኛለሁ” ይላል።