አልዛይመርስ የሚከሰተው እንዴት ነው? ሕክምናውስ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፉት አራት ዓመታት አልዛይመርስ ወይም የመርሳት ሕመም ላለባቸው ሰዎች የተሻሉ የሕክምና አማራጮች ታይተዋል።
ከእነዚህ አማራጮች መካከል አዲስ መድኃኒት፣ የደም ምርመራ እና ሕመም ያለባቸው ሰዎች የሚያርፉበት መንደር ይጠቀሳሉ።
ይህ ከእድሜ እና ከተለያዩ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ የሚከሰተው የጤና ችግር በመላው ዓለም እየተስፋፋ ብዙዎችን እያሳሰበ ነው።
ተመራማሪዎችን እና የሕክምና ባለሙያዎችም ለዚህ የአልዛይመር ችግር መፍትሔ የሚሆኑ አመራጮችን ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ዓመታትን አስቆጥረዋል። ከምን ላይ ደርሰው ይሆን?
አልዛይመርስ ምንድን ነው?
አልዛይመርስ ዕድሜያቸው ከፍ ባሉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ሕመም ነው።
ከ55 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያጠቃ ሕመም ሲሆን፣ መጠሪያ ስሙን ያገኘው በዶ/ር አልዮስ አልዛይመር አማካይነት ነበር።
እአአ በ1906 አንዲት ሴት የመዘንጋት ችግር ገጥሟት፣ ቋንቋዋን ማስታወስ አቅቷትም ነበር። ይህች ሴት ሕይወቷ ካለፈ በኋላ ዶ/ር አልዮስ የአእምሮ ሕዋሷን መረመሩ።
በዚህ መንገድ ነበር አልዛይመርስ ያለበት ሰው አእምሮ ምን እንደሚመስል የታወቀው።
በዩናይትድ ኪንግደም የአልዛይመርስ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሳራ ኢማሪሲዮ እንደሚሉት በዓመታት ሂደት ሕመሙ የሚለይበት፣ የሚታከምበት እንዲሁም መከላከል የሚቻልበት መንገድም እየተሻሻለ መጥቷል።
ስለ ሕመሙ ከተደረጉ ጥናቶች ጉልህ የሆኑትን እንመልከት።
1. የዘረ መል ምርምር
ዘንድሮ በተሠራ ጥናት መሠረት፣ 42 ተጨማሪ ከሕመሙ ጋር የተገናኙ ዘረ መሎች ተገኝተዋል።
ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያን ጨምሮ በስምንት አገራት ያሉ ተመራማሪዎች የ111,000 ሰዎችን ዘረ መል አጥንተው ነው እዚህ ግኝት ላይ የደረሱት።
ለበሽታው ተጋላጭነታቸው የጨመረ 75 ዘረ መሎች የተገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 42ቱ ከዚህ ቀደም የሚታወቁ አልነበሩም።
'ኔቸር ጄነቲክስ' በተባለው መጽሔት በታተመው ጥናታቸው መሠረት፤ ለአልዛይመርስ የሚጋልጡ የተለያዩ ሁኔታዎች አሉ።
ይህ ጥናት ሕመሙን ለመረዳት ከፍተኛ እገዛ ያደረገ እንደሆነ ዋና አጥኚው ፕሮፌሰር ጁሊ ዊልያምስ ተናግረዋል።
ሕመሙ ሰው ላይ ሳይከሰት እንዲዘገይ በማድረግ እና በመፈወስም ረገድ ሁነኛ ግኝት እንደሆነ አክለዋል።
“አልዛይመርስ ውስብስብ ሕመም ነው። ብዙ ነገሮች ሕመሙን ሊያስከትሉ ይችላሉ። በእድገቱ የሚካተቱ የተለያዩ የሕዋስ ዓይነቶችም አሉ” ሲሉ አስረድተዋል።
ሲጋራ ማጨስ እንዲሁም የተዛባ አመጋገብ ለበሽታው ተጋላጭ ሊያደርግ እንደሚችል ከዚህ ቀደም የተሠሩ ጥናቶች ቢጠቁሙም፣ ለበሽታው መከሰት ከፍተኛ ድርሻ የሚወስደው ዘረ መል ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
2. ለሕሙማን የተዘጋጀው መንደር
ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች የባለሙያዎች ክትትል እየተደረገላቸው መደበኛ ሕይወታቸውን የሚገፉበት መንደር ተዘጋጅቷል።
በዘርፉ በጉልህ ከሚጠቀሱ ፈጠራዎች አንዱ ነው።
የኔዘርላንድስን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ፈረንሳይ ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር ይህንን መንደር የገነባቸው።
ይህንን መንደር ያዋቀረው መሃንዲስ እንዳለው፣ መንደሩ የተቀረው አገሪቱን የሚመስል ማኅበራዊ እና ባህላዊ ገጽታ ተላብሷል።
ኑሯቸውን እዚህ መንደር ካደረጉ ቀዳሚ ሰዎች መካከል የ82 ዓመቷ ማድሊን ሊሳልዴ ይገኙበታል።
“እዚህ መንደር ልዩ እንክብካቤ ይደረግልናል” ይላሉ።
የልጅ ልጃቸው አውሮሬ እንደምትለው፣ አያቷ ወደ መንደሩ ከገቡ በኋላ የመዘንጋት ሁኔታቸው መሻሻል አሳይቷል።
“ደስተኛ ሆናለች። የሕይወትን ትርጉም እንደ አዲስ አግኝታለች” ትላለች አውሮሬ።
በዚህ መንደር ውስጥ ሕመሙ ያለባቸው ተሞክሯቸውን ይለዋወጣሉ።
ይህ መንደር ከተከፈተ በኋላ ከበሽታው ጋር የሚኖሩ ሰዎች ይደርስባቸው የነበረው መገለል እንደቀነሰ ዘንድሮ የወጣ ጥናት ጠቁሟል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
3. ፈቃድ ያገኘው የአልዛይመርስ መድኃኒት
አምና ሰኔ ላይ የመጀመሪያው የአልዛይመርስ መድኃኒት በአሜሪካ ፈቃድ አግኝቷል። ይህ እውን ለመሆን 20 ዓመታት ነው የፈጀበት።
መድኃኒቱ Aducanumab የሚባል ሲሆን፣ ሕመሙን ከሥር ከመሠረቱ ለማከም የሚውል ነው።
በ2019 መድኃኒቱ በ3,000 ሕሙማን ላይ እየተሞከረ ሳለ እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር።
መድኃኒቱ በወቅቱ የማስታወስ ችሎታን ለማበረታታት እያገዘ እንዳልሆነ ታስቦ ነበር የተቋረጠው።
ኋላ ላይ ግን ባዮጀን የተባለው የአሜሪካ መድኃኒት አምራች የዳበረ መረጃ ከሰበሰበ በኋላ መድኃኒቱ በከፍተኛ መጠን እስከተሰጠ ድረስ ጥቅም እንዳለው ደረሰበት።
አምና የአውሮፓ የመድኃኒቶች ኤጀንሲ መድኃኒቱን አልፈቀደም ነበር።
አሜሪካ ያሉ አጥኚዎችም በቂ ሙከራ እንዳልተደረገ ገልጸዋል።
አሁን መድኃኒቱ ቢፈቀድም በምን ያህል አገራት ጥቅም ላይ ይውላል የሚለው ገና አልታወቀም።
4. የደም ምርመራ
በ2019 ሳይንቲስቶች ለአልዛይመር ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች የበሽታውን ምልክት ከማሳየታቸው በፊት ማወቅ የሚችሉበት መንገድ እንዳዳበሩ ገልጸዋል።
ይህም መድኃኒት ለመሥራት ያግዛል ተብሎ ይታመናል።
አሚሎይድ የተባለው ፕሮቲን መጠን ከፍ ሲል አእምሮ ውስጥ የሚፈጠረውን ለውጥ ለመረዳት ያስችላል።
ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ 158 አዋቂዎች ላይ በአሜሪካ፣ ሚዙሪ ውስጥ ምርምር ተካሂዷል።
በደማቸው ያለው የፕሮቲን መጠን የተለያየ እንደሆነም ታውቋል።
አጥኚዎቹ እንደሚሉት፤ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆነና APOE4 የተባለ ዘረ መል ያላቸው ሰዎች ምርመራ ሲደረግ ግን በተቃራኒው የ94 በመቶ መመሳሰል አሳይቷል።
በዚህ መሠረት በደም ምርመራ አልዛይመርስ ሊታወቅ ይችላል ተብሎም ተስፋ ተጥሏል።
በእርግጥ ሙሉ በሙሉ በደም ምርመራ መተማመን እንደማይቻል የጤና ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
የበሽታው ምልክቶች መኖር አለመኖራቸው የሚታወቀው በሕክምና ባለሙያዎች ምርመራ እንደሆነም ያሰምሩበታል።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የአልዛይመርስ ጥናት ማዕከል ኃላፊት ዶ/ር ሳራ ኢማሪሶ እንደሚሉት፣ በቀጣይ ዓመታት መድኃኒቶች ውጤታማ ሲሆኑ፣ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ ሲቀየርና ሌሎችም መሻሻሎች ሲታዩ ለውጥ ይመጣል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












