በወር አበባ ጊዜ ከትምህርታቸው ለሚስተጓጎሉ የንጽህና መጠበቂያ የምታቀርበው ኢትዮጵያዊት

ዶ/ር ደራርቱ ነጋሽ

የፎቶው ባለመብት, Dr Deraretu

ዶ/ር ደራርቱ ነጋሽ በሰላሌ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ትምህርት ክፍል መምህርት ስትሆን በሰላሌ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደግሞ አጠቃላይ ሐኪም ናት።

ባለፈው ዓመት በምትሰራበት እና በምታስተምርበት አካባቢ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ያደረገችው ጉብኝት አሁን ለምታከናውነው ሥራ ምክንያት ሆኗታል።

“አምና የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን ለመጎብኘት ችዬ ነበር። ሴት ተማሪዎች ከትምህርታቸው ይቀራሉ” ትላለች ዶ/ር ደራርቱ።

በተለይም በገጠር አካባቢ ሴት ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት የሚያስቀሩ በርካታ ምክንያቶች አሉ።

ዶ/ር ደራርቱ በትምህርት ቤቶቹ ጉብኝት ከማድረጓ በፊት ሴት ተማሪዎች በወር አበባ ጊዜ ንጽህና መጠበቂያ ባለማግኘታቸው የተነሳ ከትምህርት ገበታቸው ይስተጓጎላሉ ብላ አስባ አታውቅም።

“በተዟዟርኩባቸው ትምህርት ቤቶች ሴት ተማሪዎችን አናግሬያለሁ። ስለ ወር አበባ በአግባቡ እንደማይማሩ ነግረውኛል። መምህራኖቹም ሸፋፍነውት ያልፋሉ እንጂ፣ ስለጉዳዩ በደንብ እንደማያስረዷቸው ተረድቻለሁ።”

በገጠር አካባቢ ሴት ተማሪዎች የወር አበባቸው ሲመጣባቸው በግልጽ ለቤተሰቦቻቸው በመናገር የንጽህና መጠበቂያ አይገዛላቸውም።

አንዱ ምክንያት አርሶ አደሮቹ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ስለሚመሩ በየወሩ ለመግዛት ስለሚቸገሩ መሆኑን ተረድታለች።

“ለሴት ተማሪዎች የወር አበባቸው ሲመጣ ምን ትጠቀማላችሁ ብዬ ጠይቂያቸው ገሚሶቹ ጨርቅ፣ ሌሎቹ ኩበት ሌሎቹ ደግሞ የወር አበባቸው ደም እንዳይታይ አመድ እንደሚጠቀሙ ነግረውኛል። ገሚሶቹ ደግሞ ሙታንታ እንኳ እንደሌላቸው ይናገራሉ። ይህንን በሰማሁ ጊዜ ነው እንግዲህ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬማሰብ የጀመርኩት።”

ተማሪዎች ውይይት እያደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Dr Deraretu

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሴት ተማሪዎች የወር አበባቸው በሚመጣበት ጊዜ የንጽህና መጠበቂያ ስለሌላቸው ብቻ፣ ቢያንስ ከአራት ቀን እስከ 10 ቀን ከትምህርት ገበታቸው እንደሚቀሩ ከመምህራኖቻቸው መረዳቷን ትናገራለች።

ይህንን የሴት ተማሪዎች ትምህርት ተሳትፎ እና ውጤት ላይ ተጽዕኖ እያደረገ ያለውን ጉዳይ ለመፍታት፣ ከምታስተምርበት ሰላሌ ዩኒቨርስቲ እና ከጓደኞቿ ጋር በመሆን መስራት ጀመረች።

“ከእኛ ዩኒቨርሰቲ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማስተባበር፣ ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ የሚቀርብበት ሁኔታ ላይ መስራት ጀመርን፤ በዚህም በሰሜን ሸዋ ውስጥ በሚገኙ 18 ትምህርት ቤቶች ለሁለት ዓመት በቂ የሆነ የንጽህና መጠበቂያ አቅርበናል” ትላለች ዶ/ር ደራርቱ።

ከሦሰት ወር በፊት ደግሞ ሰዎች የተወለዱበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ለሴት ተማሪዎች ንጽህና መጠበቂያ የሚያገለግሉ ስጦታዎችን እንዲያበረክቱ በመጠየቅ አምስት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ሴት ተማሪዎች የሚሆን እርዳታ አሰባሰበች።

“የልደት ቀኔን ምክንያት በማድረግ ስጦታ ልትሰጡኝ የምትፈልጉ ሰዎች፣ ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ መግዣ በሚሆን እንድትለውጡት እና እንድትሰጡ በማለት ጠየቅኩ። በዚሁ መሰረት ብዙ ሰዎች ከአገር ውስጥ እና ከውጪ እርዳታ አድርገውልኛል” ትላለች ዶ/ር ደራርቱ።

በዚህም መሰረት ለ467 ሴት ተማሪዎች ለሁለት ዓመት የሚያገለግል ሙታንታ እና የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ማቅረብ ችላለች።

ሴት ተማሪዎች የወር አበባቸው ሲመጣ የሚያጋጥማቸውን የአመለካከት ችግርን ለመቅረፍ እና የወር አበባ ተፈጥሯዊ ስጦታ እንጂ የሚያሳፍር አለመሆኑን ለማስተማር በየትምህርት ቤቱ በመሄድ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ታከናውናለች።

እንዲሁም በየትምህርት ቤቱ ውስጥ የሴቶች ክለብ እያቋቋመች መሆኗን ትገልጻለች።

ሴት ተማሪዎችም ራሳቸው እንዲሁ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያቸው በሚያልቅበት ሰዓት፣ ልክ እንደ ደብተር እና እስክቢርቶ ካለምንም መሸማቀቅ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ድፍረት እንዲያገኙ እያስተማረች ነው።

በሰሜን ሸዋ በ18 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ማቅረብ መቻሏ ጥሩ ስኬት በመሆኑ አሁንም ይህንን ዘመቻ አጠናክራ ለመቀጠል ፍላጎት አላት።

“አሁን ከከዚህ በፊቱ በበለጠ አስፍቼ እየሰራሁ እገኛለሁ፤ ብዙ ሰዎች ጋር በመድረስ ፍላጎታቸውን ካወቅሁ በኋላ ለመርዳት እፈልጋለሁ። በአሁኑ ጊዜም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ዘመቻ እያካሄድን እንገኛለን። ጥሩ እርዳታን በማሰባሰብ የሴት ተማሪዎች ችግር በተገቢው ሁኔታ እስኪፈታ ድረስ ቢቻል ለሁሉም ካልሆነ አብዛኞቹ ጋር ለመድረስ እየሰራን እንገኛለን።”

ዶ/ር ደራርቱ ይህንን የንጽህና መጠበቂያ ዘወትር ከሌሎች ድጋፍ በመጠየቅ ማሟላት ከባድ መሆኑን ተረድታለች።

ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት በሚልም ድጋሚ ታጥቦ ጥቅም ላይ የሚውል የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታዎች ላይ እየሰራች ነው።