የጅማ ዩኒቨርስቲ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ወደ ውጪ የሚደረገውን ጉዞ ያስቀር ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Jimma University
የሰበታ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አሕመድ አባዲ የሦስት ዓመት ልጃቸው በጭንቅላት ካንሰር በመታመሙ ከሰባት ወራት በፊት ታይላንድ ባንግኮክ ከተማ ወስደው አሳክመዋል።
“ከዚያ ተመልሰን በሦስተኛው ወር ስናስመረምረው በአከርካሪ አጥንቱ ላይ ካንሰር ተገኘበት” ይላሉ አቶ አሕመድ።
የልጃቸው የጤና በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበር የሚናገሩት አቶ አህመድ፣ “መቀመጥ፣ መሄድ፣ መተኛት እና ምግብ መዋጥም አይችልም ነበር” ይላሉ።
በዚህ ሰዓት ነበር አቶ አሕመድ ልጃቸውን እና ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ጅማ ከተማ የሄዱት።
ወደ ጅማ ያቀኑት በጅማ ዩኒቨርስቲ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ልጃቸውን ለማሳየት እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለካንሰር ሕክምና ወደ ጅማ ያቀኑት አቶ አሕመድ ብቻ አይደሉም።
የባቱ ከተማ ነዋሪው አቶ ሙላቱም ጅማ ድረስ ያመጣቸው ሕክምናውን በመፈለግ ነው።
ከዚህ ቀደም በካንሰር እንደታመሙ የሄዱት ወደ ሐዋሳ ነበር።
በሐዋሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለካንሰር የሚያስፈልገውን የኬሞቴራፒ ሕክምና ከወሰዱ በኋላ ለጨረር ሕክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልከው ነበር።
በጥቁር አንባሳ ለጨረር ሕክምና ተመዝግበው ወረፋ እስኪደርሳቸው እየጠበቁ እነደነበር የሚናገሩት አቶ ሙላቱ “በጥቁር አንባሳ ሰው ይበዛል፣ ለጨረር ሕክምና ከተመዘገብኩ ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር በኋላ በቀደም’ለታ ጠሩኝ” ይላሉ።
ለ4500 ሰዎች የካንሰር ሕክምና . . .
ዶ/ር አብዩ ለገሰ በጅማ ዩኒቨርስቲ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ስፔሻሊስት እና ኃላፊ ናቸው።
“አገልግሎቱን ከጀመረ ወደ አራት ዓመት ይሆናል። ስንጀምር በመርፌ የሚሰጠውን ወይንም የካንሰር ሜዲካል አንኮሎጂ በመስጠት ነበር። በእርሱ ጀምረን ከተጠናከረ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ የጨረር ሕክምና ማሽን አስመርቀን አገልግሎቱን መስጠት ጀመርን” ይላሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ የካንሰር ጨረር ሕክምና (ራዲዮ ቴራፒ) የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ነበር።
የጅማ ዩኒቨርስቲ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ይህንን አገልግሎት የሚሰጥ ሁለተኛው ማዕከል ነው።
“እኛ የምንሰጠው አገልግሎት ለጅማ አካባቢ ማኀበረሰብ ብቻ ሳይሆን ከመላው አገሪቱ ለሚመጡ ታካሚዎች ነው” ይላሉ ዶ/ር አብዩ።
ከዚህ በፊት ወደ ውጭ አገራት በመሄድ ሕክምና ያገኙ የነበሩ ታማሚዎች በአሁኑ ጊዜ ወደ ማዕከሉ በመምጣት አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የሚገልጹት ኃላፊው፣ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥም 4500 ለሚሆኑ ታካሚዎች የካንሰር ሕክምና መስጠታቸውን ይናገራሉ።
አገልግሎት መሰጠት ከጀመረ ሰባት ወር የሆነው የሆስፒታሉ የጨረር ሕክምና (ራዲየሸን) ደግሞ 725 የሚሆኑ ታካሚዎችን አስተናግዷል።
የውጭ አገር ጉዞዎች
የካንሰር ሕክምና አገልግሎት ካለመስፋፋቱ ጋር በተያያዘ የካንሰር ሕሙማን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለወራት የሕክምና ቀጠሮን ይጠብቃሉ።
በተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙት ደግሞ እንደ ቱርክ፣ ሕንድ እና ታይላንድ ወዳሉ አገራት በመጓዝ ሕክምና ያገኛሉ።
የሰበታ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አሕመድ አባዲ፣ ልጃቸው የጭንቅላት ካንሰር መያዙን በተነገራቸወ ወቅት ታይላንድ ወስደው ነበር ያሳከሙት።
ይሁን እንጂ ወደ አገር ቤት ተመልሰው የተወሰኑ ወራት ከቆዩ በኋላ በአከርካሪ አጥንቱ ላይ ካንሰር በመገኘቱ ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ይዘውት መጥተዋል።
የልጃቸው የጤና ሁኔታ በአስጊ ሁኔታ ላይ ደርሶ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አህመድ፣ “አርብ እነርሱ ጋር ሄጄ፣ በልዩ ሁኔታ ካዩት በኋላ በሦስተኛው ቀን ማክሰኞ ዕለት የጨረር ሕክምና እንዲያገኝ አደረጉልኝ” ይላሉ።
“15 የጨረር ሕክምና ነው የታዘዘለት። ከዚያም መካከል እስካሁን ሰባቱን ወስዷል። በእነዚሁ በወሰዳቸው ሰባቱ ሕክምና አስገራሚ ውጤት ነው ያየነው። አንደኛ በእግሩ እና በመቀመጫው ላይ የነበረው ችግር ተፈትቷል” በማለት ስለልጃቸው ጤንነት መሻሻል ይናገራሉ።
ለሕክምና ከአገር መውጣት ኪስንም ስነ ልቦናንም እንደሚፈታተን አቶ አህመድ አልሸሸጉም።
“አንደኛ የአውሮፕላን ቲኬት ራሱ በጣም ውድ ነው። ሌላው ደግሞ ከእኛ አገር ባህል ወጥተህ በሌላ አገር ውስጥ ትቸገራለህ። ክፍያውን የምትፈጽመው በውጭ ምንዛሪ ነው። ከህክምናው ውጪ ለሌሎች ወጪዎች የሚሆን የውጪ ምንዛሪ ማግኘት አስቸጋሪ ነው።”
እንደ ቱርክ፣ ሕንድ እና ታይላንድ ባሉ የውጭ አገራት የሚሰጡ ሕክምናዎች ውድ መሆናቸውን የሚናገሩት የካንሰር ስፔሻሊስቱ ዶ/ር አብዩ፣ ማዕከላቸው ከፍተኛ ደረጃ ያለው ሕክምና እየሰጠ መሆኑን ያስረዳሉ።
ይህም ዜጎች ወደ ውጭ አገር በመሄድ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚደርስባቸውን እንግልት የሚያስቀር መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
በተጨማሪም የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያብራራሉ።
የረዥም ቀጠሮ ሁኔታ
ከዚህ በፊት ከመላው አገሪቱ ለሚመጡት ታካሚዎች የካንሰር ሕክምናን ሲሰጥ የነበረው የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ከታካሚዎች ቁጥር መብዛት የተነሳ ለጨረር ሕክምና የረዥም ጊዜ ቀጠሮ እንዲጠብቁ ይደረግ ነበር።
ዶ/ር አብዩ ይህንን ሲገልፁ፣ ቢያንስ አንድ ዓመት ያህል የሚወስድ ቀጠሮ እንደሚሰጥ ያስረዳሉ። በዚህም የቀጠሮ ጊዜያቸው ሳይደርስ እና ህክምናውን ሳያገኙ፣ ሕይወታቸው የሚያልፍ ነበሩ።
በአሁኑ ወቅት በጅማ ዩኒቨርስቲ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ታካሚዎች የጨረር ሕክምናን ለማግኘት ከሦስት እስከ አራት ወር ድረስ ብቻ ቀጠሮ ሊሰጣቸው እንደሚችል ኃላፊው ይናገራሉ።
ይህም ሊሆን የቻለው፣ ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚመጡ ታካሚዎች ወደ ጅማ ለሕክምና በመሄዳቸው የተነሳ መሆኑን ይናገራሉ።
በተቻለን መጠን እስከ አንድ ዓመት ቀጠሮ የሚያዝላቸው ህሙማን እንዳይኖሩ ጥረት እያደረግን ነው የሚሉት ዶ/ር አብዩ፣ የካንሰር ታማማዎችም ቢሆኑ የበሽታው ምልክቶች እንደታየባቸው ወዲያውኑ ሕክምና መጀመር አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።
ስለ ማዕከሉ
የካንሰር ህመምን ለማከም የሚሰጡት ሕክምናዎች ዋና ዋናዎቹ ሦስት መሆናቸውን ባለሙያው ይናገራሉ።
እነርሱም ቀዶ ሕክምና፣ በመርፌ የሚሰጥ መድኃኒት እና የጨረር ሕክምና ናቸው።።
የጅማ ዩኒቨርስቲ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ከእነዚህ መካከል ሁለቱን፣ ማለትም በመርፌ የሚሰጠውን ሕክምና እና የጨረር ሕክምና (ራዲዮቴራፒ) አገልግሎቶችን ይሰጣል።
በማዕከሉ ለጨረር ሕክምናው የሚሆነው መሳርያ በጅማ እና በዙሪያዋ ለሚገኙ 20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ ነው የተደራጀው።
“አንድ ማሽን ነው ያለን። የማሽን እና እቃዎች ጉድለት አለብን” የሚሉት ዶ/ር አብዩ፣ በአሁኑ ሰዓትም ተጨማሪ ማሽን ለመግጠም የሚያስችል ተስማሚ ቦታ እንዳላቸው ይናገራሉ።
ማዕከሉ ሁለት የካንሰር ስፔሻሊስቶች፣ የጨረር ማሽን ባለሙያ፣ አንድ ሜዲካል ፊዚስት፣ እንዲሁም ነርሶች እና የሬዲዮ ቴራፒ ባለሙያዎች ጋር የተደራጀ ነው።
ዶ/ር አብዩ ወደ ማዕከላቸው በብዛት የሚመጡ የካንሰር ታማሚዎችን ሲያስረዱ፣ የማህፅን ጫፍ፣ የጡት እና የአንጀት ካንሰር ታማሚዎች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ይናገራሉ።
ከእነዚህም በተጨማሪ የጡንቻ፣ የአጥንት እንዲሁም የደም ካንሰር ቀጥሎ በብዛት የሚስተዋሉ መሆናቸውን ስፔሻሊስቱ ይናገራሉ።












