‘ሲጨንቀን ከሐኪም የማይጠበቅ ምክር እንሰጣለን' - በዓይደር ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Ayeder Hospital
ተክለመድኅን ተክለሃይማኖት የ14 ዓመት ልጅ ነው፤ ከስድስት ወር በፊት ሆዱ አብጦ፣ ከባድ ሙቀት፣ የክብደት መቀነስ እና የአፍንጫ መድማት ምልክቶች ሲያሳይ ወላጆቹ ከተንቤን ወደ መቀለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ይዘውት ሄዱ።
የሕክምና ባለሙያዎቹ ምርመራቸውን አደረጉ፤ የደም ካንሰር (lukimea) እንዳለበትም ለቤተሰብ አሳወቁ።
በወቅቱ የመጀመርያው ደረጃ የኬሞቴራፒ (የጨረር) ህክምና ተደርጎለት መጠነኛ የጤና መሻሻል ማሳየቱን የጤና ባለሞያዎቹ ይናገራሉ።
ሁለተኛው የኬሞቴራፒ ህክምና እንዲደረግለትም ከሁለት ሳምንታት በኋላ እንዲመለስ ተነግሮት ከሆስፒታሉ ቢወጡም፣ ወላጆቹ ግን ለስድስት ወራት በዚያው ጠፉ።
በዚህ ሁኔታ መቆየት ከሚገባበት በላይ ዘግይቶ እንደገና ወደ ሆስፒታሉ ሲመለስ ግን ከዚህ ቀደም የታዩት ምልክቶች ተባባሱ።
"ለደም ምርመራ እና መድኃኒት መግዣ የሚሆን ገንዘብ ስለሌለን ነው የጠፋነው" ይላሉ ወላጆቹ።
በዚህ ምክንያት፣ ልጁ የሚያሳያቸው ምልክቶች ከቀን ወደ ቀን መሻሻል ያሳዩ ይሆናል በሚል ተስፋ ቤት ይዘውት መቀመጣቸውን ይናገራሉ።
ሆኖም ግን በዚህ ወቅት በሽታው በመባባሱ ሆስፒታል ተኝቶ ህክምና ማግኘት እንዳለበት ተነገራቸው።
የዓይደር ሆስፒታል ሠራተኞች ግን፣ ሆስፒታሉ ባጋጠመው የመድኃኒት እና ሌሎች ቁሳቁሶች እጥረት ምክንያት፣ ህጻናት እና አዋቂዎች የካንሰር ህሙማን የሚያክሙበት አቅም እየተሟጠጠ መምጣቱን ይናገራሉ።
አክለውም 'ተስፋ መቁረጥ ደረጃ ላይ ነን' ብለዋል።
አብዛኛው በክልሉ ህጻናት ላይ የሚታየው ካንሰር የደም ካንሰር መሆኑን የሚገልጸው የካንሰር ሐኪም እና ጥናት [ኦንኮሎጂ] ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ክብሮም ሕሉፍ፣ ህጻናት ላይ የሚታዩ የካንሰር አይነቶች በቀላሉ መታከም የሚችሉ ናቸው ይላል።
ሆኖም "አሁን ህክምና የለም፤ በህይወት እንዲቆዩ ብቻ የመጠቀሚያ ቀን ያለፈባቸው መድኃኒቶች እየሰጠናቸው ነው። ምናልባት እድለኞች ከሆኑ፤ ከጊዜ በኋላ ምን ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ግን ማወቅ አንችልም" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።
በክልሉ የካንሰር ህሙማን ልጆች ያሉዋቸው ቤተሰቦች ገንዘብ የሚያገኙበት አማራጭ በመቋረጡ ምክንያት ልጆቻቸውን ከክልሉ ውጪም ቢሆን ለማሳከም ለትራንስፖርት እና ሌሎች ወጪዎች ገንዘብ ለማግኘት መቸገራቸው ይናገራሉ።
የካንሰር ህክምና ከባድ ወጪ እና ረጅም ጊዜ የሚፈልግ ነው። በዚህ ምክንያት፣ እንደ ኬሞቴራፒ ያሉ ለካንሰር ህሙማን የሚሰጡ የህክምና አይነቶች ባለማግኘታቸው በርካታ ህጻናት ቤት ውስጥ እየሞቱ ነው የሚል ስጋት ከሕክምና ባለሙያዎቹ ይሰማል።
ከአምስት ዓመት በፊት በ1999 ዓ.ም በዓይደር ሆስፒታል የህጻናት የካንሰር ህክምና ክፍል ሲከፍት መሰል ችግሮችን ለማቃለል እና ሰዎች በአቅራቢያቸው አገልግሎት እንዲያገኙ ለማገዝ በሚል መንግሥት የኬሞቴራፒ ወጪውን ግማሽ ክፍያ ሲሸፍን፣ ቀሪውን ክፍያ ደግሞ ቤተሰቦች በብድር መልክ እንዲከፍሉ በማድረግ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
ባለፉት ሦስት ዓመታትም ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች፣ የተወሰኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች፣ ከአፋር እንዲሁም ከኤርትራ የሚመጡ የካንሰር ሕሙማን በሆስፒታሉ አገልግሎት ሲያገኙ እንደነበረ እና የአዲስ ተካሚዎች ቁጥር ከ72 ወደ 110 ከፍ ብሎ እንደነበር ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በጦርነቱ ምክንያት እና ከዚያ በኋላ በቀጠለው የማኅበራዊ አገልግሎቶች መቋረጥ ምክንያት ግን ይሄንን ቁጥር በግማሽ መቀነሱ ይጠቀሳል።

የፎቶው ባለመብት, Ayeder Hospital
ትልቁ የዓይደር ሆስፒታል ፈተና
ለ17 ወራት በቀጠለው ጦርነት ምክንያት በክልሉ የሚገኙ የካንሰር ህሙማን በከባድ ችግር ላይ ወድቀው ከሚገኙ ታካሚዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ባሉ ጊዜያት 1643 አዋቂዎች እና 126 ህጻናት የካንሰር ታካሚዎች ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸው የሚያሳየው የሆስፒታሉ ሪፖርት፣ አብዛኛዎቹ ግን በትራንስፖርት ችግር፣ በገንዘብ ማጣት እና የስልክ አገልግሎት ባለመኖሩ ምክንያት መጥተው ህክምና ማግኘት አልቻሉም ሲል የሆስፒታሉ አስተዳደር ያስረዳል።
"70 በመቶ የካንሰር ታካሚዎቻችን ሴቶች ናቸው። ከእነዚህ 30 በመቶ የጡት ካንሰር አለባቸው። የማህጸን በር ካንሰር ያለባቸው 126 ሴቶች ሲኖሩ ከእነዚህ 15 ብቻ ናቸው የመጀመሪያው ደረጃ ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው። ቀሪዎቹ 111 ግን የኬሞቴራፒ ህክምና ባለመኖሩ ምንም አማራጭ ስለሌለ ወደ ቤታቸው ልከናቸዋል" ይላል ሆስፒታሉ።
ባለፈው ወር የሆስፒታሉ ባለሙያዎች፣ ከላባራቶሪ እስከ የኬሞቴራፒ መድኃኒት ድረስ እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት ከ1700 በላይ የካንሰር ህሙማን ለሞት አደጋ ተጋልጠዋል ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ከጦርነቱ በፊት፣ ሆስፒታሉ ከ60 እስከ 70 በመቶ የኬሞቴራፒ አገልግሎት በመስጠት ከ45 በላይ የካንሰር መድኃኒቶች በሆስፒታሉ እንደነበሩት ይገለጻል።
በአሁኑ ወቅት ያለው የኬሞቴራፒ አገልግሎት ከ10 በመቶ በታች ሲሆን፣ ሦስት የመድኃኒት አይነቶች ብቻ እንዳሉትም የካንሰር ሕክምና ክፍል መጋቢት ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
በዚህ ምክንያት የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችም እያለቁ ናቸው ሲል ዶክተር ክብሮም ያስረዳል።
"አሁን ላይ ኬሞቴራፒ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል። የካንሰር መድኃኒቶች እጅግ ከባድ ናቸው። ለምሳሌ ኬሞቴራፒ የሚወስድ ታካሚ ወደ ላይ የማለት ችግር ሊኖረው ስለሚችል ለዚህ የሚሰጥ መድኃኒት ነበር፤ አሁን እሱም ነው የሌለን። በግሉኮስ መልክ የሚሰጡ መድኃኒቶች የሉም። አብዛኛዎቹ ታካሚዎች ህክምና የለም እያልን ነው የምንመልሳቸው፤ የማጽናናት ሥራ እንጂ የህክምና ሥራም እየሰራን አይደለም" ይላል።
የአንጀት ካንሰር ታካሚዎች ህክምናቸው ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል የሚለው ኃላፊው፣ ሁሉም የካንሰር ታካሚዎች ከባድ ችግር ላይ ናቸው ሲል ይናገራል።
"የተለያዩ መድኃኒቶችን ነበር የሚወስዱት፤ ካጋጠመን እጥረት አንጻር አራት ለሚወስዱት አንድ ስንሰጣቸው ነበር፤ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ጭምር። አሁን ግን እሱም ተቋረጠ" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Ayder Hospital
'ሲጨንቀን ከሐኪም የማይጠበቀውን እንላለን'
የካቲት ወር አጋማሽ ላይ የዓለም የጤና ድርጅት በስድስት ወራት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አንቲባዮቲክስ፣ የወባ እና የስኳር እንዲሁም የከባድ የምግብ እጥረት መድኃኒቶች የያዙ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ትግራይ እንዲያስገባ ፈቃድ አግኝቶ ነበር።
ሆኖም ክልሉ ውስጥ ባለው የነዳጅ እጥረት ምክንያት ወደ ሚፈለገው ቦታ ማድረስ አልተቻለም ሲል የገጠመውን ተግዳሮት ገልጾ ነበር።
ባለፈው መጋቢት ወር፣ የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ለሰብዓዊነት በሚል ግጭት ለማቆም ከወሰኑ በኋላ፣ በተለያዩ ጊዜያት ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የቀይ መስቀል መኪኖች መቀለ መድረሳቸው ተነግሯል።
አብዛኛው ወደ ክልሉ የገባው መድኃኒት አጣዳፊ ለሆኑ ወይም በኢንፌክሽን ለሚመጡ በሽታዎች መከላከያ የሚሆን እንጂ፣ እንደ ካንሰር ያሉ በሽታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገቡ አይደሉም የሚለው ዶክተር ክብሮም፣ "በዚህ ሳቢያ በቅርቡ በርካታ ታካሚዎቻችን አጥተናል፤ ልናጣቸው ጫፍ የደረሱም አሉ" በማለት ስጋቱን ይገልጻል።
"500 ተከታታይ ኬሞቴራፒ ማግኘት ያለባቸው፣ 300 የሚጠጉ ደግሞ ፈጣን የጨረር ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች አሉ። ችግሩ በዚህ ከቀጠለ እነዚህንም እናጣቸዋለን ማለት ነው። ስልክም ስለሌለ መድኃኒት የለም ብለን ወደ ቤታቸው የመለስናቸው ታካሚዎች ምን እንደገጠማቸው አናውቅም" ብሏል።
በተለይ ከመቀለ ውጪ የሚኖሩ የካንሰር ህሙማን በገንዘብ እጥረት እና በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ወደ ሆስፒታሉ መምጣት ማቆማቸውን ባለሙያው ይናገራል።
"ካንሰር ከባድ በሽታ ነው፤ ሞት ደረጃ የሚያደርስ እና ህክምናውም ከባድ የሆነ በሽታ ነው። ከአሁን በፊት ህክምና እየሰጠን ተስፋ አላችሁ እንላቸው ነበር። አሁን ግን 'በሽታህ ይህ ነው፣ መድኃኒት ግን የለም፤ ምንም ማድረግ አልችልም' ማለት ለእኔ የሞት ፍርድ መንገር ነው። ሲጨንቀን ከሐኪም የማይጠበቀውን እንላለን፤ እስቲ ፀበል ሞክሩ ብለን ነው የምንሸኛቸው" ሲል ያስረዳል።
ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል አሁን ያጋጠሙት ችግሮች መፍትሄ ካላገኙ ሆስፒታሉ ለህጻናት እና ለአዋቂዎች የካንሰር ህሙማን ህክምና መስጠት የማይችልበት ደረጃ ደርሶ "መፍረስ" ላይ ነው የሚገኘው በማለት የጤና ሚኒቴር እና ሌሎች ተቋማት ትኩረት እንዲሰጡት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ይማጸናሉ።
"ማስታገሻ ሳይቀር እኮ ነው ያጣነው፤ አንድ ሰው እባክህ ወደ ላይ እያለኝ ነው ብሎን መድኃኒት መስጠት አልቻልንም። ሆስፒታሉ የሚዘጋበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ይህ ማለት ህክምና በማጣት ምክንያት ትውልድ ማጣት ነው። የእኔ ትልቅ ስጋት ይህ ነው" ይላል ዶክተር ክብሮም።
















