ካንሰር፡ የንብ ሰንኮፍ የያዘው መርዝ "የተወሰኑ የጡት ካንሰር ሴሎችን ይገድላል"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውስትራሊያውያን ተመራማሪዎች የንብ ሰንኮፍ አደገኛ የሆነ የጡት ካንሰር ሴልን እንደሚያጠፋ በላብራቶሪ ሙከራ ወቅት ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል።
በንብ ሰንኮፍ ውስጥ ያለው መርዝ ሜልቲን የተባለ ውህድ የያዘ ሲሆን ይህም ሁለት ለማከም አስቸጋሪ የሆኑ የካንሰር ዓይነቶች ለማከም ምርምር ተደርጓል።
እነዚህ የካንሰር አይነቶች ትሪፕል ኔጋቲቭ እና HER2 የተባሉ ናቸው።
የምርምር ውጤቱ በሳይንቲስቶቹ "አስደናቂ" በሚል የተገለፀ ሲሆን ነገር ግን ተጨማሪ ምርመር መደረግ እንዳለበት ተገልጿል።
በዓለማችን ላይ ሴቶችን ከሚያጠቁት የካንሰር አይነቶች መካከል የጡት ካንሰር አንዱ ነው።
በቤተ ሙከራ ውስጥ የካንሰር ሴሎችን ለመዋጋት በሺዎች የሚቆጠሩ ኬሚካሎች ቢኖሩም ለሰው ልጅ ህክምና ጥቅም ላይ የሚውሉት ግን ጥቂቶቹ ናቸው።
ከዚህ ቀደም የንብ ሰንኮፍ የያዘው መርዝ ሜላኖማ ለሚሰኝ የካንሰር ዓይነት ፀረ ካንሰር የሆነ ንጥረ ነገር መያዙ ይታወቅ ነበር።
ጥናቱ እየተሰራ ያለው በምእራብ አውስትራሊያ በሚገኘው በሃሪ ፐርኪንስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ሜዲካል ሪሰርች ሲሆን፣ የጥናቱ ውጤት የታተመው ደግሞ በዘርፉ ባለሙያዎች አርትኦትና ግምገማ በሚሰራለት ኔቸር ፕሪሲሽን ኦንኮሎጂ መጽሔት ላይ ነው።
በጥናቱ የተገኘው ምንድን ነው?
ከ300 ከሚበልጡ እና ከሁለት አይነት የንብ ዝርያዎች የተወሰደው መርዝ ላይ ሙከራ ተደርጓል።
የንቦቹ አይነት የማር ንብ እና 'በምብል ቢ' የሚባሉት ናቸው።
ከማር ንብ የተወሰደው መርዝ "በጣም ኃይለኛ" መሆኑን ለሶስተኛ ዲግሪዋ ምርምሯን እየሰራች የምትገኘው እና ጥናቱን የምትመራው የ25 ዓመቷ ሲያራ ዱፊ ተናግራለች።
በንቦቹ ሰንኮፍ ውስጥ ያለው መርዝ ሌሎች ሴሎች ላይ አነስተኛ ጉዳት በማድርስ፣ የካንሰር ሴሎችን በአንድ ሰዓት ውስጥ ይገላል ስትል የጥናቷን ግኝት ታስረዳለች።

የፎቶው ባለመብት, HARRY PERKINS INSTITUTE
ተመራማሪዎቹ ጨምረው ያገኙት ነገር ሜሊቲን የተሰኘው ውህድ በራሱ የካንሰር ሴል እድገትን በማስተጓጎል አልያም "በማቋረጥ" ረገድ ውጤታማ መሆኑን ነው።
ሜሊቲን በማር ንብ ሰንኮፍ መርዝ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በፋብሪካም ሊመረት ይችላል።
ከጡት ካንሰሮች ሁሉ አደገኛ የሆነው ትሪፕል ኔጋቲቭ በቀዶ ህክምና፣ ራዲዮቴራፒ እና ኬሞቴራፒ ነበር የሚታከመው። በዚህ የካንሰር ዓይነት የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ከአጠቃላይ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ከ10 እስከ 15 በመቶ ያህል ያለውን ይይዛሉ።
ወደ ፊት ልንገለገልበት እንችላለን?
ረብዑ እለት፣ የምዕራብ አውስትራሊያ ተመራማሪዎች ኃላፊ ውጤቱን "እጅጉን አስደናቂ" ሲሉ ገልፀውታል።
"በተጨባጭ ሜሊቲን እንዴት የጡት ካንሰር ሴሎችን እድገትና መራባት እንደሚያቋርጥ አሳይቷል" ያሉት ፕሮፌሰር ፒተር ክሊንከን ናቸው።
"ይሀ የተፈጥሮ ውህዶች የሰውን ልጅ በሽታ ለማከም እንዴት እንደሚውሉ የሚያሳይ ሌላ ድንቅ ምሳሌ ነው"
ነገር ግን ተመራማሪዎቹ የንብ ሰንኮፍ የያዘው መርዝ መድሃኒቶች ካንሰርን በሚዋጉበት ልክ መዋጋት ይችላል የሚለው ላይ ሌላ ምርመር እንደሚቀረው አስጠንቅቀዋል።
ከሲድኒ በጋርቫና ኢንስቲትዩት ኦፍ ሜሪካል ሪሰርች የሚሰሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር አሌክስ ስዋርብሪክ በበኩላቸው የንብ ሰንኮፍ የያዘው መርዝ የካንሰር መድሃኒት ነው ብሎ ለመደምደም " ጊዜው ገና ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
















