
የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ የኢራን ልዑካን ቡድን ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ ከአሜሪካ እንዲወጣ ማዘዛቸውን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን እና የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለሲቢኤስ ኒውስ ገለጹ።
በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ሩቢዮ የልዑካን ቡድኑ እንዲወጣ ያዘዙት
በሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት መካከል ከተደረጉ ቴክኒካዊ ውይይቶች በኋላ ሰኞ ዕለት መሆኑን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የሚመሩት ልዑክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመካፈል ባለፈው ሳምንት ወደ ኒውዮርክ የሄደ ሲሆን፣ የሆርሙዝ ባህር
ወሽመጥን ዳግም ለመክፈት ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።
አራግቺ ከዚህ ቀደም ለሲቢኤስ ኒውስ እንደገለጹት ከአሜሪካ ማክሰኞ ዕለት ለመውጣት አቅደው ነበር።
ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ንግግር ካደረጉ በኋላ በሚቀጥለው ቀን ከኒው ዮርክ ቢወጡም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ግን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ስለመክፈት እና ግጭቱን በዘላቂነት
በማስቆም ዙሪያ በሚደረጉ ቀጥተኛ ያልሆኑ ውይይቶች ላይ ለመሳተፍ በዚያው ቆይተው ነበር።
አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የተመደቡትንና በግዛቷ ውስጥ የሚገኙትን የኢራን ዲፕሎማቶች በሙሉ ከአገር እንዲወጡ አላደረገችም።
በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮን ትዕዛዝ
ተከትሎ ሰኞ ዕለት ምሽት አራግቺ እና ልዑካን ቡድናቸው ኒው ዮርክን “ወዲያውኑ” ለቅቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን አክሲዮስ ዘግቧል።
ኢፒ በበኩሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ፣ የልዑካን ቡድኑ “ከተፈቀደለት ጊዜ
በላይ ቆይቷል” እንዲሁም “የመንግሥታቱ ድርጀት ጉባዔ አብቅቷል፤ ስለዚህ ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው” መባሉን ዘግቧል።
የኢራን የልዑካን ቡድን ማክሰኞ ዕለት ከኒው ዮርክ ወደ ዶሃ ጉዞውን ጀምሯል።
እንደዘገባው ከሆነ፣ ዋይት ሐውስ ሰኞ ጠዋት ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ የተወሰነ መሻሻል ይኖራል ብሎ ጠብቃ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ከሰዓት በኋላ ድርድሩ ለውጥ
አለመሳየቱን ግልጽ ሆኗል።
የኳታር አደራዳሪዎች ከሁለቱም አገራት ተወካዮች ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ሊደረስበት
በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በተናጠል እየተወያዩ ናቸው።
እስራኤል እና አሜሪካ በጋራ በመሆን የካቲት 28 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ
ጦርነት የከፈቱ ሲሆን በምላሹም ኢራን ወደ ባህረ ሰላጤው አገራት ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን አስወንጭፋለች።
በመካከለኛው ምሥራቅ ኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ የዓለም አንድ አምስተኛ
የነዳጅ የሚጓጓዝበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም ነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ተስተውሏል።