የኤችፒቪ ክትባት፡ የማህፀን ካንሰን መከላከያ ክትባትን ማን መውሰድ አለበት? ምን ያህልስ አስተማማኝ ነው?

የኤችፒቪ ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንድ አዲስ ጥናት የኤችፒቪ ክትባትን የወሰዱ ሴቶች በማህፀን ካንሰር የመያዝ ዕድላቸውን በ90 በመቶ እንደሚቀንስ አመለከተ።

የማህፀን ካንሰር ሴቶችን ከሚገጥሟቸው ዋነኛ የጤና ችግሮች መካከል አራተኛ ደረጃን ይይዛል። በየዓመቱ ከ300,000 በላይ ሴቶች በማህፀን ካንሰር ሳቢያ ይሞታሉ።

የኤችፒቪ ክትባት ከማፀን ካንሰር የሚከላከለው እንዴት ነው?

የኤችፒቪ ክትባት የተለያዩ አይነት የኤችፒቪ በሽታዎችን ይከላከላል። ይህም የማህጸን ካንሰር፣ የመቀመጫ ካንሰር፣ የመራቢያ አካላት ካንሰር እና የአንገት ካንሰርን ይጨምራል።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ክትባቱ ቢያንስ ለ10 ዓመታት በኤችፒቪ ላለመያዝ ይከላከላል። ክትባቱ ከ10 ዓመታት በላይም በሽታውን ሊከላከል እንደሚችልም ባለሙያዎች ያምናሉ።

አንድ በከፍተኛ ደረጃ የተሠራ ጥናት እንደሚለው፤ ይህ ክባት የማህፀን ካንሰርን 90 በመቶ በሆነ መጠን ይቀንሳል።

የኤችፒቪ ክትባት እአአ ከ2008 ወዲህ በእንግሊዝ ለታዳጊ ሴቶች መሰጠት የጀመረ ሲሆን፤ ጥናቱ የተካሄደውም ከእንግሊዝ በተሰበሰበ መረጃ ነው።

ክትባቱን መውሰድ ያለበት ማነው?

ታዳጊ ሴት እና ወንድ ታዳጊዎች ለኤችፒቪ ከመጋለጣቸው በፊት ክትባቱን እንዲወስዱ ይመከራል። ስለዚህም ወጣቶች ወሲብ መፈጸም ከመጀመራቸው አስቀድሞ የኤችፒቪ ክትባትን መውሰድ አለባቸው ማለት ነው።

ክትባቱ የሚሠራው ሰዎች ለቫይረሱ ከመጋለጣቸው በፊት ብቻ ነው። በቫይረሱ የተያዘ ሰውን መፈወስ ግን አይችልም።

ኤችፒቪ ወይም ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ከ100 በላይ የቫይረስ አይነቶች ያሉት ዝርያ ነው።

በቫይረሱ የተያዘ ሰው በአብዛኛው ምልክት አያሳይም። አንዳንዴ ግን እጅ፣ እግር፣ መራቢያ አካል ወይም አፍ ውስጥ እብጠት ሊከሰት ይችላል።

አብዛኛው ሰው በቫይረሱ እንደተያዘ ሳይታወቅ ሰውነት ቫይረሱን ያስወግዳል።

ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለው የኤችፒቪ ቫይረስ አይነት የሕዋስ እድገት ላይ ጉዳት ከማስከተሉም በላይ ለካንሰር ያጋልጣል።

ኤችፒቪ በወሲብ ይተላለፋል?

ሰዎች ለቫይረሱ የሚጋለጡት በቀላሉ ነው። ከሰው ወደ ሰው በቆዳ ንክኪ ይተላለፋል።

ወደ 80 በመቶ የሚጠጉ ሰዎች ለቫይረሱ የሚጋለጡት በ25 ዓመታቸው ገደማ ነው።

በወሲብ ወቅት በሚፈጠሩ ፈሳሾች አማካይነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ባለመሆኑ በወሲብ ከሚተላለፉ በሽታዎች አንዱ ነው ለማለት ያስቸግራል።

ሆኖም ግን በዋነኛነት የሚተላለፈው በወሲብ ነው። በመነካካትም ይተላለፋል።

የኤችፒቪ ክትባት ምን ያህል ተደራሽ ነው?

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ በአብዛኛው በማህፀን ካንሰር የሚሞቱት አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው።

በእነዚህ አገሮች የማህፀን ካንሰር የተባባሰ ደረጃ እስከሚደርስ ድረስ አይታወቅም።

የዓለም ጤና ድርጅት እስከ 2030 ድረስ የኤችፒቪ ክትባትን በመላው ዓለም በማዳረስ ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ የማስወገድ እቅድ እንዳለው አምና አስታውቆ ነበር።

ወደ 100 በሚጠጉ አገሮች ውስጥ የኤችፒቪ ክትባት ማግኘት ይቻላል።

እስከ 2020 በተሰበሰበ መረጃ መሠረት 85 በመቶ የሚሆኑ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ክትባቱን ሲያቀርቡ፣ ቁጥሩ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ ግን ይቀንሳል።

25 በመቶ የሚሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች እና 30 በመቶ የሚሆኑ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ብቻ ናቸው ክትባቱ ያላቸው።

አፍሪካ ውስጥ የማህፀን ካንሰር ሴቶች ላይ በከፍተኛ መጠን ከሚከሰቱ በሽታዎች መካከል ሁለተኛውን ደረጃ ይዟል። ይህ በሽታ በአህጉሪቱ ውስጥ ገዳይም ነው።

በበቂ ሁኔታ የማህፀን ካንሰር ቅድመ ምርመራ አለመደረጉ ለበሽታው መስፋፋት ቀዳሚው ምክንያት ነው።

ሕክምና ለማግኘት አስቸጋሪ ከመሆኑ ባሻገር የኤችፒቪ ክትባት ለመውሰድ አለመፍቀድም ይስተዋላል።

ጃፓን ውስጥ ክትባቱን መውሰድ ካለባቸው መካከል 0.1 በመቶው ብቻ ናቸው የሚከተቡት።

ሩዋንዳ 2011 ላይ ታዳጊ ሴቶች የኤችፒቪ ክትባት እንዲከተቡ እና የካንሰር ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ አገር አቀፍ ንቅናቄ በማድረግ ከመጀመሪያዎቹ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ሆናለች።

ንቅናቄው በተጀመረ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ10 ሴቶች ዘጠኙን መከተብ ተችሎ ነበር። ሩዋንዳ ለሌሎች አገራት ተምሳሌት ተደርጋም ትወሰዳለች።

በአንዳንድ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ክትባቱ 'መሀን ያደርጋል' የሚል የተዛባ አመለካከት መኖሩም እንቅፋት ሆኗል።