በአሜሪካ የአሳማን ኩላሊት ወደ ሰው ለማስተላለፍ የተደረገው ሙከራ ተስፋ ሰጪ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች በተሳካ ሁኔታ የአሳማ ኩላሊት ወደ ሰው ልጅ ማስተላለፍ ችለዋል። ንቅለ ተከላው በኩላሊት ሕክምና ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ስኬት ተብሏል።
በመላው ዓለም ኩላሊት ለጋሽ ያጡ ወይም የኩላሊት ንቅለ ተከላ እስኪያገኙ ወረፋ የሚጠባበቁ በርካታ ናቸው። የአሜሪካ የሕክምና ባለሙያዎች የአሳማን ኩላሊት ወደ ሰው ልጅ ማሸጋገር መቻላቸው ለሕሙማን ተስፋ ነው።
የአሳማ ኩላሊት የተሰጠው ግለሰብ በሰው ሠራሽ ነፍስ ማቆያ መሣሪያ እየተደገፈ የነበረ አንጎሉ መሥራት ያቆመ (ብሬን-ዴድ) ነው።
ኩላሊቱ የተሰጠው ሰው ሕሊናውን ከመሳቱ በፊት የሰውነት ክፍሎቹን ለመለገስ ይፈልግ ነበር። ቀዶ ሕክምናው የተደረገውም በቤተሰቦቹ ፈቃድ ነው።
ኩላሊቱ የተወሰደው አሳማ ዘረ መል ላይ መሻሻል ስለተደረገበት ኩላሊቱ ወደ ግለሰቡ ሲተላለፍ ሰውነቱ እንዲቀበለው ማድረግ ተችሏል።
ይህ ንቅለ ተከላ ገና በሌሎች ባለሙያዎች አልተገመገመም። በሳይንስ መጽሔቶችም ገና አልታተመም። ባለሙያዎቹ ሥራቸውን ለግምገማ ያቀርባሉ ተብሎ ግን ይጠበቃል።
እስካሁን ድረስ እንደዚህ አይነት ሙከራዎች የተደረጉት በእንስሳት ላይ ነው። ይህ ሙከራ በሰው ልጅ ላይ ሲደረግ የመጀመሪያው ነው ማለት ነው።
የአሳማ የሰውነት ክፍሎችን ለሰዎች ግልጋሎት ለንቅለ ተከላ የማዋል ሙከራ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደም የአሳማ የልብ ትቦዎችን ወስዶ ለሰው ልጆች መትከል ተችሏል።
የአሳማ የሰውነት ክፍሎች ከመጠን አንጻር ለሰው ልጅ ሰውነት ተስማሚ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, NYU Langone
የአሳማን ኩላሊት ወደ ሰው የማሻገር ቀዶ ሕክምናው የተካሄደው በኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ ላንጎን የጤና ማዕከል ነው።
ሐኪሞቹ የአሳማውን ኩላሊት ከግለሰቡ የደም ትቦ ጋር አገናኝተው፤ የግለሰቡ ሰውነት ኩላሊቱን ይቀበል እንደሆነ ፈትሸዋል።
ለሁለት ቀናት ተኩል ኩላሊቱ ላይ የሚታይ ለውጥ ካለ በቅርብ ተከታትለዋል።
ዋና ተመራማሪው ዶ/ር ሮበርት ሞንትግጎምሪ "የአሳማው ኩላሊት የሰው ልጅ ኩላሊት ማከናወን የሚችላቸውን ተግባሮች ሲያከናውን ነበር" ሲሉ ስለ ምርምሩ ገልጸዋል።
የአሳማው ኩላሊት ከሰው ሰውነት ጋር ሲገናኝ መደበኛ ሥራውን እንደቀጠለም አክለዋል።
ከአሳማው ኩላሊት በተጨማሪ የታይመስ እጢውም ወደ ግለሰቡ ተላልፏል። ይህ እጢ የሰው ሰውነት የአሳማ ኩላሊትን አልቀበልም እንዳይል የሚያግዝ ነው።
ዶ/ር ሮበርት የልብ ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው የጤና ባለሙያ ናቸው። ይህ ምርምራቸው አነጋጋሪ ሊሆን እንደሚችልም ያውቃሉ። ሆኖም ግን በርካታ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ስላሉ ምርምሩ ጠቃሚ እንደሆነ ይናገራሉ።
"አንድ ሰው እንዲኖር ሲባል ሌላ ሰው መሞት የለበትም። ኩላሊት ከሚጠብቁ ሕሙማን መካከል 40 በመቶው ኩላሊት ሳያገኙ ይሞታሉ። አሳማን ለምግብነት እና ለመድኃኒትነት እንደምናውለው ለንቅለ ተከላም ማዋል እንችላለን" ይላሉ።
ሙከራው በተግባር ከመዋሉ አስቀድሞ ተጨማሪ ጥናቶች መካሄድ አለባቸው። አሁን ያሉበት ደረጃ ወደ ቀጣዩ የምርምር ደረጃ ለመሄድ የሚያበረታታ መሆኑን ሐኪሙ ያስረዳሉ።
የአሜሪካ የመድኃኒት ተቆጣጣሪ ተቋም (ኤፍዲኤ) የዘረ መል ማሻሻያ የተደረገላቸው አሳማዎች የሰውነት አካል ለምርምር እንዲውል ፈቅዷል።
ሐኪሙ እንደሚሉት፤ በቀጣይ 10 ዓመታት የአሳማ ልብ፣ ኩላሊት እና ሳምባ ለሰዎች በተሳካ ሁኔታ መስጠት ይቻላል ተብሎ ይታመናል።
በእንግሊዝ ብሔራዊ ጤና ተቋም የሚሠሩት ዶ/ር ሜርያም ኮስራቭ የኩላሊት ሕክምና ባለሙያ ናቸው። ሙከራውን በተመለከተም "የእንስሳትን የሰውነት ክፍሎች ወደ ሰዎች ማሸጋገርን ለዓመታት አጥንተናል። የአሜሪካው የምርምር ቡድን ይህንን ጥናት አንድ እርምጃ ወደፊት ወስዶታል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የአሳማ የሰውነት ክፍልን ወደ ሰው ልጆች ማስተላለፍ ላይ ከሥነ ምግባር አንጻር ጥያቄ የሚያነሱ አሉ።
ለሰው ልጆች የእንስሳትን ሰውነት ማስተላለፍ እውን የሚሆንበት ቀን እስኪመጣ ድረስ የሰውነት ክፍላቸውን ለመለገስ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ላይ ማተኮር የግድ ይሆናል።












