ለአንድ ትውልድ የዘለቀና በድል የተጠናቀቀው ከካንሰር ጋር የተደረገ ትግል

ወይዘሮ የአይኔ አበባ ብርሃን

የፎቶው ባለመብት, Yayene Abeba

ወይዘሮ የአይኔ አበባ ብርሃን በካንሰር የታመመችው ከሃያ ዓመታት በፊት ነበር። በእርግጥ ከህመሟ ብትድንም ከካንሰር ጋር የምታደርገው ትግል ግን አንድ ትውልድ አልፎ ዛሬም አላበቃም።

አሁኑ የአይኔ አበባ የ70 ዓመት አዛውንት ናት። ሰው ሁሉ ስለሚቀርባትና ስለሚያደንቃት ግን “ማንም አንቱ ብሎኝ አያውቅም” ስላለችን እኛም አንቺ ማለቱን መርጠናል።

ትምህርት፣ ሥራ፣ ትዳር

የአይኔ አበባ ብርሃን የተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው።

በቤታቸው ከእህት እና ከወንድሞቿ በተጨማሪ የትምህርት ዕድል ለማግኘት ከክፍለ ሃገር የመጡ የወንድምና የእህት ልጆችም የቤተሰቡ አባላት ናቸው።

ቤታቸው በሰው የተሞላ ነው። “ጥሩ ግንኙነት ነበረኝ። ሰላማዊ እና የፍቅር ሕይወት ነበረን” በማለት ልጅነቷን ታስታውሳለች።

እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ የተማረችው ኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ነው።

ክረምት ይሁን በጋ መቀመጥ ስለማትወድ በትምህርት ቤቱ ውስጥ እንደ ቀይ መስቀል ባሉ ክበቦች ውስጥ መሳተፍ ወይም አጫጭር ኮርሶችን መውሰድ ትመርጣለች።

አሥራ ሁለተኛ ክፍልን እንደ ጨረሰች ‘በአገር ውስጥ ገቢዎች ቢሮ’ በሒሳብ ሠራተኛነት ተቀጠረች። ጡረታ እስክትወጣ ድረስም እዚህ መስሪያ ቤት ብቻ የሰራችው የአይኔ አበባ ከሥራዋ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማታው ትምህርት ክፍል አካውንቲንግ ተምራለች።

ልክ እንደ ተማርኩበት ትምህርት ቤት እና እንደ ሰራሁበት ተቋም ሁሉ “የፍቅር ግንኙነትም ከአንድ ሰው ጋር ብቻ ነው የነበረኝ” ትላለች። ስለ ባለቤቷ አቶ ተስፋዬ አበራ ስትናገር።

ሰፈራቸው ብዙም አይራራቅም። ጓደኞቹ ጓደኞቿ ናቸው። የተማሩትም አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። ቤተሰቦቻቸውም ስለሚተዋወቁ የአይኔ አበባ እና ተስፋዬ ከመቀራረብና ከመላመድ አልፈው ፍቅር ውስጥ ገቡ።

ከስምንት ዓመት ጓደኝነት በኋላ በተክሊል ተጋብተው አዲስ ምዕራፍ ጀመሩ።

ወልዶ የመሳም ጉጉት

ትዳር ውስጥ አለመግባባትና አለመስማማት ይኖራል። ግን “ሁለታችንም መካከል ምንም ነገር አይገባም። እንነጋገራለን፤ እንተወዋለን። አንዳችን ተሸናፊ እንሆናለን” ስትል ለአንድ ቀንም እንኳ ተለያይተው እንዳላደሩ የአይኔ አበባ ትገልጻለች።

ነገር ግን ያልተፈተነ ትዳር አልነበረም። ልጅ የማግኘት ህልማቸውን እየከሸፈ ብዙ ውጣ ውረድን አሳልፈዋል።

በተደጋጋሚ ህክምና ሄደዋል።

አንዳንዶቹ ሐኪሞች “አሁን ትወልጃለሽ፣ ደህና ነሽ” ይሏታል። ሌሎቹ ደግሞ “ተኚ” ወይም ይህን “መድኃኒት” ውሰጂ ብለው ይመክሯታል። የተባለችውን ስታደርግ ግን ለውጥ አላገኘችም።

ለምን እንደ ከሸፈ ስትጠይቅ በወጉ ምላሽ አታገኝም። “እነሱም አያውቁትም። ስለዚህ ታከተኝና ተውኩት” በማለት የልጅ ህልሟን ተስፋ ቆረጠችበት።

ቢሆንም ግን አልተረበሸችም።

“ተፈጥሮዬ እንደሱ ነው፤ ለምንም ነገር አልረበሽም። በምን አምናለሁ መሰለህ? ማንኛውም ነገር ከሆነ ሆነ ነው። መቀበል ነው በቃ። ከመጣ ወዲህ ምን ማድረግ ይቻላል?” በማለት ከጭንቀት ጋር እንደማይተዋወቁ ትገልጻለች።

ከስምንት ዓመታት በኋላ የአይኔ አበባ አረገዘች። ወንድ ልጅ አቅፈው ለመሳም በቁ። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በሴት ልጅ ተባረኩ።

የጡት ካንሰር

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ስለካንሰር በወሬ ከምትሰማው የዘለለ ግንዛቤ አልነበራትም። ሰዎች ታመሙ፣ “ጡታቻው ተቆረጠ” ሲባል ትሰማለች።

አንድ ቀን ገላዋን ስትታጠብ ጡቷን ዳበስ ዳበስ አደረገች።

የሆነ እብጠት ተሰማት። ጡት ላይ የሚኖር የመጠን ወይ የቅርፅ ለውጥና እብጠት የቱንም ያህል ትንሽዬ ቢሆን እንኳ የካንሰር ምልክት ሊሆኑ እንደሚችሉ ሐኪሞች ይጠቁማሉ።

“ለሰው አይታይም እኔ ግን ስዳስሰው ይሰማኝ ነበር” ትላለች የአይኔ አበባ።

ለምርመራ ከባለቤቷ ከአቶ ተስፋዬ ጋር ወደ ሆስፒታል ሄዱ። ማሞግራፊ [የጡት ካንሰር ምርመራ] አደረገች። ጡቷ ላይ ምንም ችግር እንደሌለ ተነገራት።

ያኔ የህክምናው ጥበብ እንዳሁኑ ዘመናዊ አልነበረም የምትለው የአይኔ አበባ ከባለቤቷ ጋር የተለያየ ህክምና ቢሞክሩም ችግሩን ለይቶ የሚነግራት ሐኪም አልተገኘም።

ካንሰር የታመሙ ሰዎች መናገር ስለማይፈልጉና ህመማቸውን ስለሚደብቁ በቂ መረጃ ለማግኘት ተቸገረች። ያገኘቻቸውን ጥቂት ጽሁፎች ስታነብ ግን ጥርጣሬዋ አየለ።

መጨረሻ ላይ አንድ ዶክተር ከጡቷ ላይ ናሙና በመውሰድ ምርመራ ካደረገላት በኋላ “በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ያለ” ካንሰር እንደሆነ ተረጋገጠ።

የአይኔ አበባ ካንሰር እንደ ታመመች ሲነገራት “እኔ ብዙም አልተሰማኝም” ትላለች።

ከዚህ በፊት ያጋጠማትን የመውለድ ችግር ያለፈችው ስለችግሩ መጨነቅን ስለማትፈልግ እንደሆነ የምትናገረው የአይኔ አበባ “እሱ ጠቅሞኛል” ስትል ብዙ ያልደነገጠችበትን ምክንያት ታስረዳለች።

ባለቤቷ ግን በአንጻሩ “በጣም ደነገጠ፤ ተርበተበተ” ስትል የተፈጠረባትን ስሜት ትገልጻለች። “እና እኔ እንዳውም እሱን አጽናናሁት። ‘ተው አትጨናነቅ በቃ። የሚሆነው ይሆናል” አለችው።

የዚያን ወቅት ሐኪሞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ድንገት በልብ ህመም መሞታቸው በሰፊው እየተወራ ስለነበር “ለስንት ሰው የሚበቁ ሰዎች እንዲሁ እየሞቱ ነው። እኔ ማነኝ? ብሞትም ምንም ማለት አይደለም” ብላ ልታጽናናው ሞከረች።

የመረመራት ሐኪም በአስቸኳይ ከአገር ወጥታ መታከም እና መድኃኒትም በ15 ቀን ውስጥ መጀመር እንዳለባት አስጠንቅቋታል።

ይህንን ለማድረግ ደግሞ የባለቤቷ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር። በአገር ውስጥ እና በውጭ ከሚገኙ ጓደኞቹ ጋር ተነጋግሮ ደቡብ እፍሪካ ድረስ ሄዳ በአስቸኳይ እንድትታከም አድርጓል።

የአይኔ አበባ በሽታውን ከሰው የመደበቅ ፍላጎት አልነበራትም። እንደዚያም በመሆኑ ወንድሞቿ፣ ቤተሰቦቿና ወዳጆቿ የሕክምናው ጉዞ እንዲሳካ የተቻላቸውን ያህል ተረባርበዋል። በተጨማሪም መኪናቸውን እና መሬታቸውን እንደተሸጡ ትናገራለች።

እርግጥ ነው ባህላዊ ህክምና እንድትሞክር የገፋፉ የቤተሰብ አባላትም ነበሩ።

“ቤተሰቡ በጣም ስለተረበሸ አልሄድም ማለትም ይከብዳል” ትላለች።

“እኔ [ባህላዊ ህክምና] ውስጤ የለም ግን እነሱ ደስ እንዲላቸው፣ ቅር እንዳይላቸው. . . ካንሰር መሆኑን ካወቅኩ በኋላ እና ለህክምና ወደ ውጪ እስከምሄድ ድረስ . . .ዘመዶቼ ሁለት ቦታ ወስደውኛል።

“ስሄድ ግን ‘ቀላል ነው፤ እንደዚህ ይደረግና ይፈነዳል’ ይሉሃል። እኔ እሱ እስከሚፈነዳ እዚህ ምን አስቀመጠኝ?” ብላ ዝግጅቷን ስታጠናቅቅ ተነስታ ሄደች።

የአይኔ አበባ ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጓዘችው ብቻዋን ነው። ባለቤቷ አቶ ተስፋዬ የሁለት ልጆቻቸውን ኃላፊነት ተረክቦ ቤት ቀረ።

ልጆቹ እድሜያቸውን ገና አስር ዓመትም ስላልሞላ መጀመሪያ እናታቸው እንደታመመች አልተነገራቸውም። የዘጠኝ ዓመቱ የበኩር ልጇ ግን ጥርጣሬ አድሮበት ነበር።

ወይዘሮ የአይኔ አበባ ብርሃን እና ልጆቻቸው

የፎቶው ባለመብት, Yayene Abeba

የምስሉ መግለጫ, ወይዘሮ የአይኔ አበባ ብርሃን እና ልጆቻቸው

የደቡብ አፍሪካው ህክምና

ደቡብ አፍሪካ እንደደረሰች የባለቤቷ ጓደኛ ዘመዶች “ወደቤታቸው ወሰዱኝ። እንደቤቴ ነው የተሰማኝ” ስትል እንግዳ ተቀባይነታቸው የፈጠረባትን ስሜት ታስታውሳለች።

በማግስቱ ሦስት ቀናት የፈጀ ምርመራ ጀመረች።

“የመጀመሪያ ደስታቸው የፈለጉትን መድኃኒት ለመስጠት ውስጤ ንጹህ ነው” ስትል የመጀመሪያውን በጎ አጋጣሚ እንደነበር ትገልጻለች።

የካንሰር ህክምና ከመጀመሩ በፊት እንደ ሳንባ፣ ልብ፣ ጉበት፣ ኩላሊትና የመሳሰሉት የሰውነት ክፍሎች ላይ ምርመራ ማካሄድ ለካንሰር ህክምናው ብቁ መሆናቸውንና ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆኑ ለመወሰን እንደሚያግዝ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከሦስት ቀን በኋላ በፈሳሽ መልክ የሚሰጥ ህክምና በየ21 ቀኑ ለስድስት ጊዜ እንድትወስድ ታዘዘላት። እንደ ባለሙያዎች አገላለጽ ይህ ህክምና ሴሎችን በመግደል ወይም በመከፋፈል የካንሰር ሕዋሳትን እድገት ለማስቆምና ከቀዶ ህክማና ወይም ከጨረር ሕክምና በፊት ዕጢን ለመቀነስ ይረዳል።

የመጀመሪያውን ህክምና ወስዳ ከ21 ቀናት በኋላ ስትመለስ ያበጠው ዕጢ እንደቀነሰና ለውጥ እንዳለ ሲነገሯት ብርታት አገኘች።

የኬሞቴራፒ [የካንሰር ህክምና] የፀጉር መርገፍ፣ የቆዳ ለውጥና ሌሎች የተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል ገና ከኢትዮጵያ ሳትወጣ ሰምታ ነበር።

እናም “[ፀጉሬን] ከዚሁ አሳጥሬው ሄድኩኝ” ትላለች።

የመጀመሪያውን ኬሞ እንደወሰደች ግን ፀጉሯ ሙሉ በሙሉ ረግፎ ተመለጠች፤ ጣቶቿ በተለይ ጫፎቻቸው ጠቆሩ።

የኬሞቴራፒ ህክምና ስትጨርስ ቀጣዩ ጡትን ለማንሳት የሚደረግ ቀዶ ጥገና እና ሬድዮቴራፒ ይኖራል።

ይሁን እንጂ የኬሞቴራፒ ውጤት አበረታች ስለነበር ሐኪሙ በቀጥታ ሬድዮቴራፒ ለመጀመር ትፈልግ እንደሆን ጠየቃት።

ካንሰሩ “መቶ በመቶ ጠፍቷል?” ብላ ስትጠይቀው አንድ ወይም ሁለት በመቶ ሊኖር ስለሚችል ከቤተሰብ ጋር እንድትማከር ነገራት።

“እኔ ምን አማከረኝ? በሰው አገር እኮ ነው ያለሁት። ከዚህ ወዲህ አልወልድም፤ አላጠባም። ስለዚህ ይነሳ አልኩት።”

ከአንድ ሳምንት በኋላ ቀዶ ጥገና ተደርጎላት ጡቷ ተነሳ። “ከዚያ በኋላ እሱ ሲደርቅልኝ ደግሞ ሬድዮቴራፒ 25 ሬይ ወሰድኩ” ትላለች።

በህክምናው ሂደት የአይኔ አበባ ስለልጆቿ እንጂ ስለራሷ አልተጨነቀችም።

“የእኛ ትወልድ በመኢሶን፣ በኢህአፓ ምናምን እየተባለ የረገፈ ትውልድ ነው። የባከነ ትውልድ ነው” የምትለው የአይኔአበባ እሱን አልፋ ብዙ ነገር ለማየት መብቃቷ ቀላል እንዳልሆነና ከዚያ ወዲያ ብዙም የሚያስጨንቃት ነገር እንደሌለ ታወሳለች።

አንዳንዱ እንደወጣ ሲቀር፣ ሌላው የከፈተውን እንኳ ሳይከድንና ሳይናዘዝ እንደሚሞት ስለምታውቅ እሷ ታማ ብትሞት “ጸጋ” እንደሆነ ታምናለች።

“ግን እስካለሁ ድረስ ልኑር፣ እስካለሁ ድረስ በጎ ነገር ላድርግ፣ እስካለሁ ድረስ አምላኬን ላምልክ፣ እስካለሁ ድረስ መሆን ያለበትን ላድርግ እንጂ እኔ ስለመሞት አልጨነቅም። ምንም አይረብሸኝም።”

“በርግጥ” ትላለች የአይኔ አበባ “የልጆቼ ነገር ያሳስበኛል። እኔ ስላጣኋቸው፣ እኔ ስላላሳደግኳቸው እጨነቃለሁ እንጂ አባታቸው አለ፤ ቤተሰቦች አሉ። ስለዚህ ምንም እንደማይሆኑ አውቃለሁ” በማለት ብትሞት መጨረሻቸውን አለማየቷ ብቻ እንደሚያሳስባት ትናገራለች።”

“ትቻቸው የምሄድ ከሆነ ልጆች አትስጠኝ” ብላ ትጸልይ የነበረው ምኞቷ የልጆቿን ወግና ማዕረግ ማየት ስለሆነ ነው።

እናም ፈጣሪ ለልጆቿ ብሎ “እንደሚያድነኝ እርግጠኛ ነበርኩ” ትላለች።

ወይዘሮ የአይኔ አበባ ብርሃን

የፎቶው ባለመብት, Yayene Abeba

ጥረት ሌሎችን ለመርዳት

በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች በጡት ካንሰር የሚያዙ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከልም መቶ ሺዎች በሰበቡ ለሞት ይዳረጋሉ።

በየትኛውም የእድሜ ክልል ያሉ ሴቶች ለጡት ካንሰር በሽታ ተጋላጭ ናቸው። ቁጥሩ ኢምንት የሚባል ይሁን እንጂ ወንዶችም ቢሆኑ በጡት ካንሰር ይያዛሉ።

ስለዚህ የበሽታውን ምልክቶች፣ ቅድመ ጥንቃቄ እና ሕክምናውን ማወቅ አስፈላጊ ነው። ስለጡት ካንሰር ትክክለኛውን መረጃ ትክክል ካልሆነው መለየት እና ማወቅ ደግሞ ከስጋት ያድናል።

ወይዘሮ የአይኔ አበባ ስለ ካንሰር ለማወቅ በፈለገችበት ሰዓት መረጃ አለማግኘቷና የካንሰር ታማሚዎች ስለህመሙ መናገር አለመፈለጋቸው ያሳስባት ነበር።

ሰዎች መረዳዳት እንዳለባቸው ስለምታምን በህክምና ወቅት ከተዋወቀቻቸው ሌሎች አራት የካንሰር ታማሚዎች ጋር አንድ የካንሰር ድጋፍ ሰጪ ቡድን መስርተዋል።

ሐኪሞችን፣ ቤተሰቦቻቸውንና የቅርብ ጓደኞቻቸውን እያሳመኑ የአባላቱ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የኢትዮጵያ የካንሰር ማኅበርን አቋቋሙ።

በመጀመሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በመስጠት የጀመረው ይሄ ማኅበር አገልግሎቱን በማስፋት በአንድ ጊዜ 16 ከተለያዩ የክልል ከተሞች የመጡ ሴቶችን ተቀብሎ የሚያስተናግድ የካንሰር ታማሚዎች እንክብካቤ መስጫ ማዕከል ከፈተ።

በአሁኑ ጊዜ ማዕከሉ ለታማሚዎች ማረፊያ፣ እንክብካቤ፣ የጽዳት እና የምግብ አዘጋጅ ሠራተኞችን ከማቅረብ በተጨማሪ የትራንስፖርትና የግንዛቤ ማስጨበጫ አገልግሎቶችንም ይሰጣል።

ነገር ግን የታማሚው ቁጥርና የማኅበሩ አቅም ሊመጣጠን ባለመቻሉ ከመንግሥት ቦታ ተቀብሎ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት በዝግጅት ላይ ነው።

በአሁን ወቅት የአይኔ አበባ ያለምንም ደሞዝና ያለምንም ጥቅማጥቅም ማኅበሩን ከሚያገለግሉ የቦርድ አባላት መካከል አንዷ ናት።

እናም ከሃያ ዓመት በፊት የጀመረችው የካንሰር ትግል በሕይወት እስካለች ድረስ እንደምትቀጥልበት ጠንካራ እምነት አላት።

ባለቤቷን ከዓመት በፊት በሞት ያጣችው የአይኔ አበባ ከሐዘኗ ገና ያላገገመች ቢሆንም፣ ከጡት ካንሰር ድና ልጆቿ አድገው ለወግ ማዕረግ ሲበቁ ለመመለከት መቻሏ የስደስታታል።

አሁን ወንዱ ልጇ በሲቪል ኢንጅነሪንግ፣ ሴቷ ደግሞ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። ሴት ልጇም በቅርቡ ታገባለች።

ካንሰር መታመማቸውን ዛሬ ያወቁ ሰዎችን ብታገኚ ምን ትያቸዋለሽ ?

“አንደኛ ህመሙን ተቀበሉ ነው። . . . ህክምናውን አሁኑኑ ጀምሩ እላቸዋለሁ።”