የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ከኢፕስቴን ወንጀል ጋር በተያያዘ ቃላቸውን ሰጡ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን በኮንግረስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ከወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኢፕስቲን ጋር በተያያዘ "ምንም ያየሁት ነገር የለም" እንዲሁም "ምንም ስህተት አልሠራሁም" ሲሉ ተናገሩ።

ቢል ክሊንተን ሙሉ ቀን በፈጀው እና በዝግ በተካሄደው የምስክርነት ቃላቸውን የመቀበል ሂደት ጄፍሪ ኢፕስቲንን በሚመለከት በቅርቡ ይፋ የሆኑ ሰነዶች ላይ ስለተጠቀሱ ጉዳዮች ተጠይቀዋል።

በእነዚህ ዶሴዎች ውስጥ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙቅ የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ማንነቱ ይፋ ካልሆነ ሰው ጋር ሲዋኙ ይታያል።

ቢል ክሊንተን ምስክርነታቸውን የሰጡት ባለቤታቸው የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን ለኮሚቴው "ስለ ኢፕስቲን ወንጀሎች ምንም አላውቅም" ብለው ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

በኢፕስቲን ዶሴዎች ውስጥ ስማቸው መጠቀሱ ወይንም ፎቶዎቻቸው መገኘቱ በወንጀል ውስጥ ተሳትፈዋል ማለት አይደለም።

እስካሁን ድረስ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተንም ሆኑ ባለቤታቸው ሂላሪ ክሊንተን በኢፕስቲን ጥቃት በተፈጸመባቸው ሰዎች አልተወነጀሉም።

ክሊንተን "ምን እያደረገ እንዳለ ግንዛቤ ቢኖረኝ ኖሮ" ከኢፕስቲን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያቋርጡ እንደነበር አንዲሁም በአውሮፕላኑ እንደማይበርሩ ተናግረዋል።

"እኔ ራሴ አጋልጠው ነበር" ሲሉ ክሊንተን ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ ገልጸዋል።

ክሊንተን በኒው ዮርክ ምስክርነታቸውን ከሰጡ በኋላ የመክፈቻ ንግግራቸውን ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

"ምንም ያህል ፎቶዬ ቢታይም" የኢፕስቲንን ወንጀሎች አላውቅም ሲሉ ተናግረዋል።

"ዛሬ የምስክርነት ቪዲዮዬ ሲለቀቅ፣ ሁሉም ሰው የሚያውቀውን በኮንግረሱ ፊት ቀርቦ እንዲናገር እንደሚያነሳሳው ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ ክሊንተን ተናግረዋል።

"ይህ የፍትሕ ቢሮን ሁሉንም ሰነዶች እንዲለቅ እና ይህ እንደገና እንዳይከሰት እንደሚያበረታታ ተስፋ አደርጋለሁ። ከጥቃቱ የተረፉት ሰዎች ይህ ይገባቸዋል።"

ቢል ክሊንተን እና ባለቤታቸው የቁጥጥር ኮሚቴው ፊት ቀርበው ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት የቀረበላቸውን የምስክርነት ጥሪ የፖለቲካ ዓላማ አለው በሚል ውድቅ አድርገው ነበር።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሙቅ ገንዳ ውስጥ አብራቸው ስትዋኝ የምትታየውን እና ማንነቷን ያልተገለጸችዋን ሴት በተመለከተ ሲጠየቁ እንደማያውቋት ገልጸዋል።

ከሴትየዋ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽመዋል ወይ ተብለው ሲጠየቁም አለመፈጸማቸውን ተናግረዋል ሲል አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ቢል ክሊንተን ከባለቤታቸው በተለየ የምስክርነት ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ አልሰጡም።

ቢል ክሊንተን በሙቅ ገንዳ ውስጥ ዘና ብለው ሲዋኙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ክሊንተን ለኮንግረስ የምስክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ በሙቅ ገንዳ ውስጥ ስለነበረው ሁኔታ መጠየቃቸውን ምንጮቸ ለቢቢሲ ተናግረዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኮንግረሱ የቁጥጥር ኮሚቴው ሊቀመንበር የሆኑት ሪፐብሊካኑ ጄምስ ኮመር ለሰዓታት የዘለቀውን ምስክርነት "በጣም ውጤታማ የሆነ መግለጫ" ሲሉ ጠርተውታል።

"ፕሬዝዳንት ክሊንተን እያንዳንዱን ጥያቄ መልሰዋል ወይም እያንዳንዱን ጥያቄ ለመመለስ ሞክረዋል" ሲሉ የሰጡትን ምስክርነት ቪዲዮ እና ሙሉ ቅጂው በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የክሊንተንን ምስክርነት "ታሪካዊ" ሲሉ የጠሩት ሊቀመንበሩ፤ ከሥልጣን ከለቀቁ በኋላ በኮንግረስ ፊት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ጄራልድ ፎርድ በአውሮፓውያኑ 1974 በፈቃደኝነት በኮንግረስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰንን ይቅርታ ለምን እንዳደረጉላቸው አስረድተዋል።

ኮመር "ይህ ከባድ ምርመራ ነው" ካሉ በኋላ "እውነቱን ለአሜሪካ ሕዝብ እና ለተጎጂዎች ፍትሕ ለማግኘት መሞከራችንን እንቀጥላለን።"

ቢል ክሊንተን በሰጡት ምስክርነት ወቅት ከተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢፕስቲን ጋር የነበራቸው ግንኙነት ይገኝበታል።

ዴሞክራቶች ክሊንተን የሰጡት ምስክርነት ስለ ትራምፕ "ተጨማሪ መረጃ" እንዳስገኘ እና የአሁኑን ፕሬዝዳንት ለጥያቄ ለማቅረብ አዲስ ጥሪ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በኮሚቴው የቁጥጥር ኮሚቴ ውስጥ አባል የሆኑት ዴሞክራቱ ሮበርት ጋርሲያ፣ ክሊንተን "ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ስለተደረጉ አንዳንድ ውይይቶች ተጨማሪ መረጃ" ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ጋርሲያ ልክ እንደሌሎች ዴሞክራቶች ሁሉ ትራምፕ በኮሚቴው ፊት ቀርበው ምስክርነት እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርበዋል።

በኮንግረሱ መዝገብ መሠረት፣ ስድስት ፕሬዝዳንቶች እና የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች በኮንግረሱ ኮሚቴዎች ፊት ቀርበው ምስክርነት ሰጥተዋል። ክሊንተን ሰባተኛው ናቸው።

ኮመር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ በምስክርነቱ ወቅት ክሊንተን ትራምፕ በኮሚቴው ፊት ለመመስከር መጠራት አለባቸው ወይ የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።

ኮመር እንዳሉት ክሊንተን "እርሱን የምትወስኑት እናንተ ናችሁ" ብለው መልሰዋል።

የቀድሞው ክሊንተን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢፕስቲን ወንጀሎች ውስጥ ስለመሳተፋቸው ምንም ዓይነት እውቀት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ኮመር፣ ክሊንተን የሰጡት ማንኛውም አዲስ መረጃ ትራምፕ ከጥፋተኝነት ነፃ ናቸው የሚለውን እምነታቸውን እንዳልቀየረው ጨምረው ተናግረዋል።

"ለረጅም ጊዜ ከዚህ ክስ ነፃ ሆኖ ቆይቷል" ብለዋል።

ትራምፕ አርብ ዕለት ስለ ክሊንተን ምስክርነት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ "ለምስክርነት ቀርበው ማየት አልፈልግም" ብለዋል።