አትሌት ድርቤ ወልተጂ ከአበረታች መድኃኒት ጋር በተያያዘ ለሁለት ዓመት ታገደች

የመካከለኛ ርቀት ተወዳዳሪዋ አትሌት ድርቤ ወልተጂ

የፎቶው ባለመብት, WORLD ATHLETICS

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የመካከለኛ ርቀት ተወዳዳሪዋ አትሌት ድርቤ ወልተጂ እአአ የካቲት 2025 የአበረታች መድኃኒት ምርመራ ናሙና ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኗ በስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት ለሁለት ዓመት ከማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር ታገደች።

አትሌቷ ናሙና ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆነችበት ጊዜ ወዲህ ያስመዘገበችው ውጤት እንዲሰረዝ ሲልም ወሳኔ አስተላልፏል።

ድርቤ እአአ መጋቢት 2025 ላይ በናንጂንግ ቻይና በተካሄደው የዓለመው የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ያገኘችበት ውድድር በዚህ ውሳኔ ምክንያት ከሚሰረዙት መካከል ሆኗል።

የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች መድኃኒት ተቋም ምንም ዓይነት ጥፋት አላጠፋችም ሲል አትሌቷን ቢከላከልም የዓለም አትሌቲክስ በበኩሉ ለአራት ዓመት ትታገድ ሲል የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤትን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቀው ድርቤ ለሁለት ዓመታት ከማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር ታግዳለች።

"አትሌቷ እአአ ከየካቲት 25 ቀን 2025 ጀምሮ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን እስካስተላለፈበት ቀን ድረስ ያስመዘገበቻቸው ሁሉም ውጤቶች ውድቅ ይደረጋሉ" ሲል ፍር ቤቱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

በፍርድ ቤቱ የተሾሙት ብቸኛ ዳኛ ድርቤ "ለናሙና ለመስጠት አለመቅረቧን በተመለከተ አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ እንዳልቻለች" ቢያረጋግጥም ግን "ይህ ሆን ተብሎ እንዳልተፈጸመ አረጋግጧል" ብሏል።

አትሌቷ ላይ የተጣለው እገዳ የሚጀምረው እአአ ሐምሌ 8 ቀን 2025 ሲሆን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2027 እንደሚቆይ ሲል ስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት አስታውቋል።

ድርቤ ወልተጂ እገዳው በሚያበቃበት ወቅት 25 ዓመት የሚሞላት ሲሆን የ2027ቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመስከረም 11 ጀምሮ በቤጂንግ መካሄድ ይጀምራል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።።