ኢንስታግራም ታዳጊዎች ራሳቸውን ለማጥፋት የሚረዱ ይዘቶችን የሚፈልጉ ከሆነ ለወላጆቻቸው ሊያሳውቅ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢንስታግራም የሕፃናት መከታተያዎችን የሚጠቀሙ ወላጆች ልጆቻቸው በመተግበሪያው ላይ ራስን ከማጥፋት ወይም ከመጉዳት ጋር የተያያዙ ቃላትን በተደጋጋሚ የሚፈልጉ ከሆነ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ሊደረግ ነው።
ኢንስታግራምን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ሜታ ወላጆች ልጆቻቸው በኢንስታግራም ላይ ጎጂ የሆኑ ይዘቶችን ሲፈልጉ ሲያሳውቅ ይህ የመጀመርያው ነው።
ከዚህ በፊት ፍለጋዎችን ማገድ እና ተጠቃሚዎችን እርዳታ እንዲያገኙ ወደ ሌሎች የመምራት እርምጃዎችን ይወስድ ነበር።
በኢንስታግራም የታዳጊዎች አካውንት ለመከታተል የተመዘገቡ በዩኬ፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ካናዳ የሚገኙ ወላጆች እና ታዳጊዎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ማስጠንቀቂያዎች ይደርሳቸዋል ተብሏል።
በሌሎች የዓለም ክፍል ያሉ ወላጆች በሂደት የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተነግሯል።
ነገር ግን ሞሊ ሮዝ ፋውንዴሽን የተባለው ድርጅት እርምጃዎቹ "ከጥቅም ይልቅ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ" በማለት ተችቷል።
"ይህ ግዴለሽነት የተሞላበት መግለጫ በአደጋ የተሞላ ነው፣ እናም ያለ ምንም ይሁንታ ጉዳዩን ይፋ ማድረግ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ብለን እንሰጋለን" ሲሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አንዲ ቡሮውስ ተናግረዋል።
ድርጅቱ የተመሠረተው እአአ በ2017 በኢንስታግራም ላይ ራስን ስለመጉዳት እና ስለማጥፋት የሚገልፁ ይዘቶችን ከተመለከተች በኋላ በ14 ዓመቷ ሕይወቷን ባጠፋችው ሞሊ ራስል ቤተሰብ ነው።
ቡሮውስ "እያንዳንዱ ወላጅ ልጁ እየተቸገረ መሆኑን ማወቅ ይፈልጋል፤ ነገር ግን እነዚህ ደካማ ማሳሰቢያዎች ወላጆችን በፍርሃት እንዲዋጡ እና ከዚያ በኋላ ለሚመጡት ስሜታዊ እና አስቸጋሪ ውይይቶች ዝግጁ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል" ብለዋል።
ሜታ በበኩሉ ልጃቸው በኢንስታግራም ላይ ራስን የማጥፋትና የመጉዳት ይዘቶችን እየፈለገ መሆኑን ለወላጆች የሚላከው ማስጠንቀቂያ አስቸጋሪ ውይይቶችን ለማካሄድ ከሚረዱ የባለሙያ እገዛዎች ጋር አብረው የሚቀርቡ ይሆናል ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ይሁን እንጂ ሞሊ ሮዝ ፋውንዴሽንን የመሠረተው የሞሊ ራስል አባት ኢያን፣ በሚሰጡት ማስጠንቀቂያዎች ላይ ጥርጣሬ አላቸው።
"በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ልጅ ወላጅ ሆነህ በሥራ ቦታ 'ልጅህ ሕይወቱን ለማጥፋት እያሰበ ነው' የሚል መልዕክት ሲደረስህ አስብ… ምን ምላሽ እንደምሰጥ አላውቅም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"እና ሜታ ለዚያ ወላጅ ድጋፍ እንደሚሰጥ ቢናገርም፣ ስለ ልጅዎ ያንን ሰምተው በድንጋጤ ውስጥ ላሉ፣ ነገሮችን ለማድረግ በጣም ምክንያታዊ የሆነ መንገድ ነው ብዬ አላስብም።"
'እውነተኛውን ጉዳይ ችላ ማለት'
የሞሊ ሮዝ ፋውንዴሽንን ጨምሮ በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሜታ ማሳሰቢያ በኢንስታግራም ላይ ልጆችን ለመጠበቅ የበለጠ ጥረት ሊደረግ እንደሚችል የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የፓፒረስ ፕሪቬንሽን ኦፍ ያንግ ሱሳይድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጌድ ፍሊን የኢንስታግራም ማስጠንቀቂያን ቢቀበሉም፣ ሜታ "ልጆችና ወጣቶች በጨለማ እና አደገኛ በሆነ የኦንላይን ዓለም ውስጥ ዘልቀው የመግባታቸውን እውነታ ችላ እያለ ነው" ብለዋል።
"ወላጆች በኦንላይን ላይ ስለሚያሳልፉ ልጆቻቸው ምን ያህል እንደሚጨነቁ ለመንገር በየቀኑ ያገኙናል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ልጆቻቸው ጎጂ ይዘቶችን ከፈለጉ በኋላ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው አይፈልጉም፤ በማያውቁት አልጎሪዝም መረጃዎች ያለ በቂ ጥንቃቄ እንዲቀርብላቸው አይፈልጉም።"
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፋይቭ ራይትስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሊያንዳ ባሪንግተን-ሊች "ሜታ የሕፃናትን ደህንነት በቁም ነገር መመልከት ከፈለገ ወደ መሠረታዊ ነገር በመመለስ ስርዓቶቹን ለዕድሜ ተስማሚ ማድረግ አለበት" ብለዋል።
ቡሮውስ በተጨማሪም ፋውንዴሽኑ ቀደም ሲል ያደረገውን ጥናት በመጥቀስ ኢንስታግራም አሁንም "ተጋላጭ ለሆኑ ወጣቶች" ስለ ድብርት፣ ራስን ማጥፋት እና ራስን መጉዳት ጎጂ ይዘቶችን "ያለ ምንም ገደብ" እንደሚያቀርብ ጠቅሰዋል።
ሜታ ባለፈው መስከረም ወር የታተመውን የድርጅቱን ግኝቶች ውድቅ አድርጎ "ወላጆችን ለመደገፍ እና ታዳጊዎችን ለመጠበቅ የምናደርገውን ጥረት በተሳሳተ መንገድ የሚያቀርብ ነው" ብሏል።
ክትትልን መጨመር
የኢንስታግራም የታዳጊዎች አካውንት ማስጠንቀቂያዎች ወላጆች በልጃቸው ባህሪ እና በመተግበሪያው ላይ በሚያደርጉት ፍለጋ ላይ ድንገተኛ ለውጥ ከተከሰተ ለማሳወቅ የተነደፉ ናቸው።
ሜታ በብሎጉ ላይ እንደገለጸው እርምጃዎቹ በኢንስታግራም ነባር የታዳጊዎች ጥበቃ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እነዚህም በመተግበሪያው ላይ ራስን ከማጥፋት ወይም ራስን ከመጉዳት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን መደበቅ እና ጎጂ ወይም አደገኛ ይዘቶችን መፈለግን ማገድን ያካትታሉ።
ሜታ ለቤተሰቦች ባለው መረጃ ላይ በመመስረት ማንቂያዎች ለወላጆች በኢሜል፣ በጽሑፍ፣ በዋትስአፕ ወይም በኢንስታግራም መተግበሪያ ይልካል።
ሜታ እንደሚለው የኢንስታግራም አዳዲስ ማንቂያዎች ከተጠቃሚ የፍለጋ ስልቶች ትንተና የመነጨ ምንም ዓይነት ስጋት በማይኖርበት ጊዜ አልፎ አልፎ ወላጆችን ሊያስጠነቅቅ ይችላል ብሏል።
የሳይበርቡሊንግ ምርምር ማዕከል ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት ሳሜር ሂንዱጃ፣ ማስጠንቀቂያው ለማንኛውም ወላጅ "በግልጽ" አስደንጋጭ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ነገር ግን ለቢቢሲ "ዋናው ነገር ማስጠንቀቂያው ብቻ ሳይሆን ወላጆች ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመምራት ወዲያውኑ የሚያገኟቸው መረጃዎች ጥራት እና ጠቃሚነት ነው" ብለዋል።
ሂንዱጃ "ለወላጅ ማሳወቂያ መስጠት እና ብቻቸውን መተው አይቻልም፣ እና ሜታ ይህንን የተረዳ ይመስላል" ብለዋል።
ኢንስታግራም በበኩሉ ታዳጊዎች በኤአይ ቻትቦት አማካኝነት ራስን ስለማጥፋት እና ስለመጉዳት ውይይት የሚያደርጉ ታዳጊዎችን በሚመለከት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያዎችን ተግባራዊ ያደርጋል። ልጆች "ድጋፍ ለማግኘት ወደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እየዞሩ ነው"።
የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች መድረኮቻቸውን ለሕፃናት ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ በዓለም ዙሪያ ካሉ መንግሥታት የሚደርስባቸውን ጫና እየጨመረ ነው።
በዚህ ዓመት መጀመርያ ላይ አውስትራሊያ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች የማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ ስታግድ ስፔን፣ ፈረንሳይ እና ዩኬ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ማጤን ጀምረዋል።















