ለ200 ዓመት የዘለቀውን ሕክምና የለወጠው ሁሉንም ዓይነት ጉንፋን እና ሳልን የሚከላከለው ክትባት

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ማንኛውንም ዓይነት ሳል፣ ብርድ፣ ጉንፋን፣ የሳምባ ኢንፌክሽን እና አለርጂንም የሚከላከል በአፍንጫ የሚወሰድ ክትባት ማግኘታቸውን የአሜሪካ ተመራማሪዎች ይፋ አድርገዋል።

በአፍንጫ የሚወሰደው ክትባት (nasal spray vaccine) በስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ነው የተገኘው።

ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ሕመሞችን ለማስታገስ የሚውል ሁሉን አቀፍ ክትባት (universal vaccine) እስካሁን ሙከራ የተደረገበት በእንሰሳት ላይ ሲሆን፣ በቀጣይ በሰዎች ላይ ሙከራ መደረግ ይኖርበታል።

ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ላለፉት 200 ዓመታት የነበረውን የክትባት አሠራር "በጉልህ መንገድ" የለወጠ ግኝት ነው።

ክትባቱ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም "በጣም አስደናቂ" እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

አሁን ላይ ጥቅም የሚሰጡት ክትባቶች ሰውነት አንድን ዓይነት ኢንፌክሽን ብቻ እንዲከላከል ያስችላሉ። ለምሳሌ የኩፍኝ ክትባት የሚከላከለው ከኩፍኝ ብቻ ነው።

በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኤድዋርድ ጄነር ምርምር ክትባት ሰውነት በሽታን እንዲከላከል አስችሏል።

የሳይንስ መጽሔት ዘገባ እንደሚያሳየው፤ አዲሱ ክትባት ሰውነት በሽታን እንዲከላከል ከማሠልጠን ይልቅ ሕዋሳት በሽታን የሚከላከሉበትን መንገድ በማስመሰል ይሠራል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአፍንጫ የሚወሰደው ክትባት በሳምባ ውስጥ የሚገኙ ነጭ የደም ሕዋሳት (macrophages) በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ያደርጋል።

የትኛውም ዓይነት ኢንፌክሽን ወደ ሰውነት ውስጥ ለመግባት ሲሞክር ክትባቱ መከላከል ይቻላል ማለት ነው።

እንሰሳት ላይ በተሠራው ምርምር መሠረት የክትባቱ ውጤታማነት እስከ ሦስት ወራት የቆየ ነው።

አጥኚዎቹ እንዳሉት፤ ክትባቱ በሰውነት ላይ የሚፈጥረው በሽታን የመከላከል ዝግጁነት፤ ቫይረስ መጀመሪያ ላይ ወደ ሳምባ ከዚያም ወደ ሰውነት ዘልቆ እንዳይገባ የመቋቋም አቅምን ከ100 ወደ 1,000 እጥፍ ያሳድጋል።

በስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ የማይክሮባዮሎጂ እና ኢምዩኖሎጂ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባሊ ፑለንደራን "ወደ ሰውነት ተደብቀው መግባት የሚችሉትን ቫይረሶች በፍጥነት ለመከላከል የሚያስችል አቅም ሰውነት እንዲያዳብር ያስችላል" ሲሉ ስለ ክትባቱ ያስረዳሉ።

የምርምር ቡድኑ እንዳለው ክትባቱ ሁለት የባክቴሪያ ዓይነቶች (Staphylococcus aureus እና Acinetobacter baumannii የሚባሉትን) ለመከላከልም ይረዳል።

ፕሮፌሰር ባሊ "ክትባቱ ጉንፋንን፣ ኮቪድን፣ ብርድን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዓይነት ቫይረሶች መከላከል የሚችል ነው። ባክቴሪያዎች እና አለርጂ የሚቀሰቅሱ (allergens) ላይም ተሞክሯል" ይላሉ።

ክትባቱ ከዚህ ቀደም ከሚታወቁ ክትባቶች የተለየ መሆኑን "ይህ ክትባት የሚሠራበት መንገድ ከዚህ ቀደም ከምናውቃቸው ክትባቶች የተለየ ነው" በማለት ይገልጻሉ።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የክትባቶች ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳኒላ ፌሬራ በበኩላቸው "በጣም አስደናቂ ምርምር ነው" ይላሉ።

"ሰዎችን ከሳል፣ ከብርድ ወይም ከሌሎች የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽኖች የምንከላከልበትን መንገድ ይለወጣል" ሲሉም ያስረዳሉ።

እንዲህ ያሉ ክትባቶች በምን መንገድ ሊሠሩ እንደሚችሉ ማሳየቱ "የጥናቱ ጠንካራ ጎን" መሆኑን ባለሙያዋ ይገልጻሉ።

ፕሮፌሰር ዳኒላ ጨምውም "ከፍተኛ ጫና የሚያሳድሩ ኢንፌክሽኖችን በመከላከል ረገድ ወደፊት የሚያራምደን ትልቅ ጥናት ነው" ብለዋል።

ጉንፋን የያዛት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ክትባቱን በተመለከተ አሁንም መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች አሉ።

እንሰሳት ላይ ሙከራ ሲደረግበት በአፍንጫ የሚሸተት ክትባት ተደርጎ ነው። በአፍንጫ ገብቶ ወደ ሳምባ ይደርሳል።

ሰዎች ላይ ተመሳሳይ ውጤት ስለማሳየቱ ገና እርግጥ አይደለም። ሰውነት በሽታን ለመከላከል ምን ያህል ጊዜ በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ እንደሚያደርግ በትክክል አልታወቀም።

የአይጦች እና የሰዎች በሽታን የመከላከል አቅም የተለያየ ነው። የሰው ልጆች ሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም የተቀረጸው አሥርታት ባስቆጠሩ ኢንፌክሽኖች አማካኝነት ነው።

ተመራማሪዎቹ ክትባቱን ለሰዎች በመስጠት፤ ከዚያም ሰዎችን ሆነ ብሎ ለበሽታ በማጋለጥ ነው ሙከራቸውን የሚያደርጉት። ይህም የሰዎች ሰውነት በምን መንገድ በሽታን እንደሚቋቋም መረጃ ይሰጣቸዋል።

የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ከተፈጥሯዊ ገደቡ በላይ ማሳደግ ሊፈጥር የሚችለው ቀውስ ክትባቱ ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች አንዱ ነው።

በሊቨርፑል ስኩል ኦፍ ትሮፒካል ሜድስን የሞለኪውላር ቫይሮሎጂ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆናታን ቤል እንደሚሉት ጥናቱ "አስደናቂ" ቢሆንም ጥንቃቄ ያሻል።

"ሰውነት በሽታን ለመከላከል ከመጠን በላይ እንዲዘጋጅ ማድረግ በጤናማ ሕዋስ ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ሊያደርግም ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ከመጠን በላይ ዝግጁ የሆነ ሕዋስ ያልተጠበቀ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም ያስጠነቅቃሉ።

ክትባቱ ላይ ምርምር ያደረጉት ባለሙያዎች እንደሚሉት የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም ሁሌም በተጠንቀቅ እንዲቆም መደረግ የለበትም።

አዲሱ ክትባት አሁን ያሉትን ክትባቶች የሚተካ ሳይሆን ተጨማሪ እገዛ የሚሰጥ እንዲሆን ይፈልጋሉ።

እንደዚህ ያለ ክትባት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ቢኖር ኖሮ ለቫይረሱ የሚሆን ክትባት እስከሚሠራ ድረስ የሰዎችን ሕይወት መታደግ ይቻል ነበር።

የማይክሮባዮሎጂ እና ኢምዩኖሎጂ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባሊ ክትባቱ ቢኖር ኖሮ "የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር እንዲሁም የበሽታውን ጉዳት ይቀንስ ነበር" ይላሉ።

የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም በማዳበር ሰፊ ሚና ሊኖረው ይችል እንደነበረም ያምናሉ።

ከክረምት ወቅት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የተለያዩ ሕመሞችን ለማስወገድ ጠቅለል ያለ በሽታ የመከላከል አቅም ማዳበር እንደሚቻል ያስረዳሉ።