ወባን ለመሳሰሉ በፓራሳይት ለሚመጡ በሽታዎች ክትባት ማዘጋጀት ለምን ፈታኝ ሆነ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለፓራሳይቶች ክትባቶችን የማዘጋጀት ሂደት እጅግ በጣም ፈታኝ ነው። ሳይንቲስቶች አዳዲስ ግኝቶችን ይፋ ለማድረግ ጫፍ ላይ ሊሆኑ ይችላሉ።
ባለፈው ጥር ካሜሩን የወባ መከላከያ ክትባት በመስጠት በዓለም ላይ የመጀመሪያዋ አገር በመሆኗ ብዙዎች ደስታቸውን ገልጸዋል። በየካቲት ወር ደግሞ ቡርኪናፋሶም ተግባራዊ አደረገችው።
በዓለም ጤና ድርጅት የክትባት እና ባዮሎጂካል ክፍልን የሚመሩት ኬት ኦብሪያን “ወባን መቆጣጠር በበርካታ ምክንያቶች በጥሩ አቅጣጫ እየሄደ አይደለም” ብለዋል።
የወባ ሥርጭት ከመጨመሩ ባሻገር በየዓመቱ ወደ 600 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በወባ ይሞታሉ። የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭት፣ ኮቪድ-19 በጤና ሥርዓት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ እና የወባ ትንኞች መድኃኒት መላመድ እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ።
ይህ ማለት በቤት ውስጥ የሚረጩ ፀረ-ተባይ መድኃኒቶች እና በፀረ-ተባይ መድኃኒት የተነከሩ አጎበሮች ውጤታማነታቸውን እያጡ ነው።
የጅምላ ወባ ክትባት በዚህ የመከላከል ዘዴ ላይ አንድ ተጨማሪ መሳሪያ ይሆናል። ይህም የተለየ አቀራረብ ይሆናለውል ብለዋል ኦብራይን። “በሽታን መከላከልን መሠረት ባደረገ አካሄድን መምረጥ በጣም ታሪካዊ እና ጠቃሚ መንገድ ነው” ብለዋል።
እአአ በ2019 የአርቲኤስ፣ ኤስ የወባ መከላከያ ክትባት በጋና፣ በኬንያ እና በማላዊ በሙከራ ደረጃ ተጀምሯል። በ2021 ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ለልጆችም ጥቅም ላይ እንዲውል መክሯል። በኋላም ይህ ክትባት በአር21 ክትባት ተከትሏል።
ከዚያ ወዲህ ብዙም እመርታ አልታየም። አርቲኤስ፣ ኤስ በታሪክ የመጀመሪያው የፓራሳይት በሽታ መከላከያ ክትባት ነበር። በፓራሳይት የሚመጡ በሽታዎች ብዙ እና የተለያዩ ሲሆኑ፣ በቂ ጥናት እና የፋይናንስ ድጋፍ አላገኙም።
እንደሊሽማንያሲስ እና ቻጋስ ያሉትን ጨምሮ አብዛኞቹ ችላ የተባሉት በሽታዎች በፓራሳይት የሚመጡ ናቸው ይላል የዓለም ጤና ድርጅት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የወባ ክትባቱን የመጀመሪያው የፀረ ፓራሳይት መከላከያ ክትባት ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት አልነበረም። ነገር ግን በወባ ምክንያት የሚሞቱት ሰዎች ከፍተኛ መሆን ከሌሎች የፓራሳይት በሽታዎች ይልቅ ለወባ ክትባቶችን ለማዘጋጀት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ ማድረጉ ምናልባትም ላያስደንቅ ይችላል። አሁንም ቢሆን ግን ሃብታም አገራትን እንደጎዳው እንደ ኮቪድ-19 ክትባቶችን ያህል አይደለም።
ወባ የሚያስከትለው ከፍተኛ የሞት ምጣኔ ከፓራሳይት በሽታዎች ጎልቶ እንዲታይ ያደርገዋል። በአጠቃላይ “በፓራሳይት በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር…ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው” ይላሉ ኦብሪያን።
የአካል ጉዳት የሚያስከትሉ እና ከባድ ሊሆኑ ቢችሉም ገዳይ ግን አይደለም። በዚህ ምክንያት እና የፓራሳይት በሽታዎች ብዙውን ጊዜ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች በሚገኙ በተወሰኑ ክፍሎች ላይ ብቻ የተገደቡ በመሆናቸው በክትባት ፈጣሪዎች ቅድሚያ አልተሰጣቸውም።
ፒተር ሆቴዝ በሂዩስተን በሚገኘው የቤይለር የሕክምና ኮሌጅ የቴክሳስ የሕጻናት ሆስፒታል የክትባት ማዕከልን ይመራሉ። ፕሮፌሰሩ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ዘግይተውም ቢሆን የኮቪድ-19 ክትባትን ፈጥረዋል። ይህንምም ከባለቤትነት መብት ነፃ በሆነ መልኩ ለክትባት አምራቾች አስተላልፈዋል።
ቢያንስ 100 ሚሊዮን ዶዝ ገደማ የሚሆነው የሕንዱ ኮርቤቫክስ ተሠራጭቷል። አንድ ዶዝ ዋጋ በግምት ሦስት ዶላር ገደማ ነው። የክትባት ፈጣሪዎቹ ርካሽ የሆነ የክትባት ቴክኖሎጂን መርጠዋል። ቡድኑ ከዚህ የቀሰሙትን ልምድ የተወሰኑ በፀረ ፓራሳይት ክትባቶች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፓራሳይቶች ለክትባት ፈጣሪዎች ብዙ ፈተና ይደቅናሉ
የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጉልበት እና ገንዘብ ፈሰስ ተደርጓል። እነዚህ ክትባቶች በአንፃራዊነት በፍጥነት የተገኙበት ምክንያት ይህ ብቻ አይደለም።
“ፓራሳይቶች ከቫይረሶች የበለጠ የተወሳሰቡ መሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም" የሚሉት ሆቴዝ፤ “ከኮሮናቫይረስ ክትባት ጋር ሲወዳደር … የሁክዎርም ክትባት ቀላል አይደለም” ብለዋል።
ሁክዎርም በአንጀት ውስጥ ደምን በመመገብ የደም ማነስ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ያስከትላል። “እንደ እንስሳ አስቡበት። ስለዚህ ፀረ እንስሳት ክትባት እየሠሩ ነው ማለት ነው” ይላሉ ሆቴዝ።
አሁን ያሉት ክትባቶች በባክቴሪያ እና በቫይረሶች ላይ ይሠራሉ። በዓለም ላይ በፈንገስ ላይ የሚሠራ ምንም ዓይነት ክትባት የለም። ከፓራሳይት ደግሞ ፀረ ወባ ክትባት ብቻ ነው ያለው። ብዙውን ጊዜ ፓራሳይቶች ከግለሰቦች የበሽታ የመከላከል ሥርዓት ጋር የሚለዋወጡበት የተራቀቁ መንገዶች አሏቸው።
“በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ በተለያዩ የሕይወት ደረጃዎች ውስጥ የሚገለጡ የተለያዩ ፕሮቲኖች አሏቸው። ይህ ደግሞ ክትባቱን ለመሥራት የበለጠ ከባድ ያደርገዋል” ይላሉ ኦብራያን።
ይህ የሕይወት ዑደታቸው ውስብስብነት ፓራሳይቶችን በቤተ ሙከራ ውስጥ ለመለማመድ ቀላል እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። ለምርምር ዓላማ ሲባል ብዙዎቹን በሚፈለገው ደረጃ በቀላሉ ማምረት ከባድ ሊሆን ይችላል እንደማለት በምርምር እንስሳት ወይም በቤተ ሙከራ ውስጥ ፓራሳይቶችን መፍጠር ሌሎቹ አማራጮች ናቸው።
ሚርያም ቴንድለር በሪዮ ዴ ጄኔሮ በሚገኘው ኦስዋልዶ ክሩዝ ፋውንዴሽን (ፊዮክሩዝ) የኤስኤም14 የፀረ ሄልሚዝ ክትባትን ሥራን ያስተባብራሉ።
ቡድኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 240 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን የሚያጠቃውን እና ውሱን የሕክምና አማራጭ ያለውን ስኪስቶዞምን ጨምሮ ጥገኛ ትላትሎችን ያጠናል። ስኪስቶሶም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ሥር የሰደደ በሽታን የሚያስከትል ሄልሚንትስ ዓይነት ነው።
ከፓራሳይት ጋር የመሥራት አንዱ ተግዳሮት በዘረ መላቸው ስብጥር ምክንያት አንድ ዝርያ ላይ ማነጣጠርን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ቴንድለር እና ባልደረቦቻቸው በብዙ የሄልሚንት ዝርያዎች ውስጥ የጋራ የሆነ አካልን በመለየት መፍትሄ አግኝተዋል።
ኤስኤም14 የተሰኘው ፕሮቲን በስኪስቶሶሚያሲስ ብቻ ሳይሆን በሰዎች እና በከብቶች ላይ በሽታን በሚያስከትሉ በርካታ የሄልሚንትስ ዝርያዎች ውስጥ እንደሚገኙ ደርሰውበታል።
ቴንድለር እና ባልደረቦቻቸው በስኪስቶሶሚያሲስ ላይ የሠሩት ክትባት የደረጃ 2 ክሊኒካዊ ሙከራዎችን አጠናቅቋል። ይህ ክትባት በተሠራበት ወቅት ፕሮቲኑን ቀደም ብለው ማውጣት እንደነበረባቸው ያስታውሳሉ። ነገር ግን ይህንን ዳግም የተዋሃደ ፕሮቲን ከለዩ በኋላ አሁን በብዛት ማምረት ይችላሉ።
ብዙ ዓይነት ትሎች ኤስኤም14 ፕሮቲንን ስለሚያመርቱ፣ ቡድኑ እየገነባ ያለው የስኪስቶሶማያሲስ ክትባት በተለያዩ የሄልሚንት ዝርያዎች በሚመጡ ሌሎች በሽታዎች ላይም ይሠራል ይላሉ ቴንድለር። ስለዚህ አንድ የክትባት ሕጻናትን ከስኪስቶሶሚያሲስ፣ ከብቶችን ከፋሲዮሊስስ እና ውሾችን ለመከላከል ይረዳል ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፀረ ፓራሳይት ክትባቶችን በገንዘብ መደገፍ
ቴንድለር እና ባልደረቦቻቸው የኤስኤም14 ክትባቶችን በሰው እና በእንስሳት ላይ እንዲተገበር በትይዩ እየሠሩ ሲሆን፣ ከዚህ የጋራ ምርምር የተገኙ ልምዶች አሁን ለደረሱበት የዕድገት ደረጃ እንዲበቁ ረድቷቸዋል።
ለሰው ልጅ የሚውለው የስኪስቶሶሚያሲስ ክትባት በሴኔጋል በሙከራ ላይ ነው። ቴንድለር በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለገበያ እንደሚበቃ ይጠብቃሉ። የቡድናቸውን ስኬት “ትልቅ ደስታ የፈጠረ ነው” ብለዋል።
ይህ በሰዎች እና በእንስሳት ላይ የሚደረግ ትይዩ የክትባት ፈጠራ ሥራ ሂደቱን ወደፊት ለማራመድ ረድቶ ሊሆን ይችላል። “በሰዎች ላይ በተለይም በልጆች ላይ ያለው ተጽእኖ በጣም በጣም ከፍተኛ ነው” ይላሉ ቴንድለር።
ስኪስቶሶሚሲስ እና ሌሎች በሄልሚንትስ የሚመጡ በሽታዎች በአብዛኛው በድሃ አገራት የሚኖሩ ሰዎችን የሚያጠቁ ቢሆንም፤ ሄልሚንትስ በበለጸጉ አገሮች ውስጥም ሰዎችን ይጎዳል። ይህም የገበያ ስፋትን ያሳያል።
በሄልሚንትስ ላይ ሊኖር የሚችለው የእንስሳት ክትባት የፋዮክሩዝ አካል ለሆነው ፋብፒ ለተሰኘ የግል ኩባንያ ፈቃዱ ተሰጥቶታል። ለሰው ሚውለው ክትባት በዋናነት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት በብራዚል መንግሥት ነው።
ሁለተኛው ክትባት “የሰብአዊ ክትባት” ይሆናል ሲሉ ቴንድለር አጽንኦት ሰጥተዋል። ዕቅዱ የፊዮክሩዝ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኦን ኢሚውኖባዮሎጂ በአንድ ዶዝ ከአንድ ዶላር ባነሰ ክፍያ እንዲያመርት ነው። የምርት መጠኑ ቀስ በቀስ እየጨመረ በመሄድ አንድ ቢሊዮን ዶዝ ሲደርስ ዋጋውይቀንሳል። በትርፍ ህዳጉ ላይም ገደብ ይኖረዋል።
የሁክዎርም ክትባትም ከዋነኞቹ የዓለም አቀፍ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ውጪ ሊመረት ይችላል። የብራዚል ባዮ ማንጉዊንሆስ እንዲሁም በቻይና፣ በሕንድ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በሌሎች አገራት ያሉ አምራቾችን ጨምሮ በማደግ ላይ ባሉ አገራት የክትባት አምራቾች ጥምርት እንደሚዘጋጅ ሆቴዝ ይጠበቃሉ።
“የእኛ ቴክኖሎጂ ክትባቶችን ለማምረት ከፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የሕግ ማዕቀፎቻችን በልጦ እንዲወጣ እና እንዲመረት አድርጓል” ብለዋል።
የወደፊቶቹ የፓራሳይት ክትባቶች
ፀረ ፓራሳይት ክትባቶች በጣም ቢፈለጉም እንደ ቀላል መፍትሔ መታየት የለባቸውም ይላሉ ኦብራየን። “ፍጹም የሆነ የፀረ የወባ መፍትሔ የለም። የተለያዩ የመከላከል እርምጃዎች አሉን” ብለዋል።
የኢንፌክሽን አደጋን እና አደጋን ለመቀነስ የወባ ክትባቱ ከሌሎች ጋር አንድ አማራጭ ብቻውን የሚሆን አይደለም። በአስፈላጊ ሁኔታ፣ የአርቲኤስ፣ ኤስ ክትባት ሙከራ የተደረገባቸው ማኅበረሰቦች የአልጋ አጎበሮችን መጠቀም አላቆሙም።
ተመራማሪዎች በቅርቡ የአር21 የወባ ክትባት ውጤታማነት በአማካይ 78 በመቶ መሆኑን ሪፖርት አድርገዋል፤ ይህም ከፍተኛ ውጤታማነት የሚባል ነው። ይህ አሃዝ በቡርኪናፋሶ፣ በኬንያ፣ በማሊ እና በታንዛኒያ ውስጥ ከአምስት እስከ 17 ወር ባላቸው ሕጻናት ላይ በተደረጉ ሙከራዎች ላይ የተመሠረተ ነው።
“እንደ ኩፍኝ ላሉ እና 97 በመቶ የሚከላከሉ ክትባቶች ከሕጉ አንጻር በጣም ትልቅ ስኬት ያላቸው ናቸው” ይላሉ ሆቴዝ።
“በውጤታማነቱ ላይ የምናደርገውን ያህል ቁጥሩ ላይ ትኩረት ማድረግ የለብንም” ይላሉ ኦብሪያን። ቁጥሩ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም፣ የበለጠ አስፈላጊው ተጽዕኖው ነው። ይህም በክትባት ተደራሽነት እና በበሽታው ላይ ባለው ተጽዕኖ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያምናሉ።
በወባ ክትባቶች ለተደረጉት ተከታታይ ግኝቶች አንዳንድ ሰፋ ያሉ ጥቅሞችም አሉት። በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የማይክሮባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ጄፍሪ ቤቶኒ “የዚህ ክትባት ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መጠን ያለው በሽታ አምጪ ተህዋስያንን ለሚያስከተለው ሄልሚንትስም ተመሳሳይ ተስፋን ይፈጥራል” ብለዋል።
ለኤችአይቪ እና ለኮሮና ቫይረስ ተመሳሳይ የክትባት ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ሁሉ፤ ለወባ ክትባቶች ጥቅም ላይ የሚውሉት ስልቶች ከደም መጣጭ ፓራሳይቶች ጋር በተያያዘም ጥቅም ላይ ሊውሉው ይችላሉም በማለት “እየተነሳ ያለው ማዕበል ሁሉንም ጀልባዎች ያንቀሳቅሳል” ብለዋል ቤቶኒ።
ሆቴዝ “ይህ አስደሳች የመሆኑን ያህል በጣም አስፈሪ ክፍልም አለው። ምክንያቱም ደሃ ሰዎችን የሚያጠቃውን ይህንን በሽታ ለመከላከል ፈር ቀዳጅ ሞዴል መሆኑ የሚያስደንቅ ስሜት ያለውን ያህል፤ የወደፊቱን አቅጣጫ የሚያመለክት ፍኖተ ካርታ ስለሌለው ደግሞ በጣም አስፈሪ ነው” ሲሉ ተስፋ እና ስጋታቸውን ገልጸዋል።












