ተመራማሪዎች ለጡት ካንሰር ክትባት ለማግኘት ምን ያህል ተቃርበዋል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የካንሰር ሐኪሟ ዶ/ር ኖራ ድሪስ "የምንጠብቀውን ውጤት ለማግኘት ጫፍ ላይ ደርሰናል" ይላሉ።
ለ30 ዓመታት በሙያው ቆይተዋል። ለጡት ካንሰር ክትባት ለማግኘትም ተቃርበዋል።
በቀጣይ አሥር ዓመት ክትባት የካንሰር ሕክምና ውስጥ ይካተታል ብለው ዶ/ር ኖራ ያምናሉ።
በዩኒቨርስቲ ኦፍ ዋሽንግተን የሕክምና እና ክትባት ክፍል ኃላፊ ናቸው።
የጡት ካንሰር ሴቶችን በግንባር ቀደምትነት ከሚገድሉ ሕመሞች አንዱ ነው። ዓለም አቀፉ የካንሰር ምርምር ተቋም እንደሚለው፤ በመላው ዓለም ከ20 ሴቶች አንዷ በጡት ካንሰር ትያዛለች።
አሁን ላይ ከ50 በላይ የጡት ካንሰር ክትባቶች ላይ ሙከራ እየተደረገ ነው። ይህም ተስፋ ሰጪ ነው።
ከክትባቶቹ አምስቱ ምርምራቸው ወደ መገባደዱ ተቃርቧል።
በተለይ ባለፉት 18 ወራት የክትባት ምርምሮች ውጤታቸው አበረታች ሆኗል።
ለዚህ ምክንያቱ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም በመጠቀም ሕመምን ለመዋጋት የሚውለው መንገድ (immunotherapy) ከመቼውም በተሻለ መዘመኑ ነው።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካይነት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ናሙናዎችን መመርመር ተችሏል። በዚህም ሙከራ የሚደረግበት ፍጥነት ጨምሯል።
ተናዋይቷ ቪክቶሪያ ኤንኮዬ በ30ዎቹ ዕድሜ ላይ ነው የጡት ካንሰር እንዳለባት የታወቀው።
ምርምር ከሚደረግባቸው ክትባቶች አንዱ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, Michael Shelford
"ካንሰር በሕይወት፣ በሥራ፣ በማኅበራዊ ሕይወትና በቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና ነው የሚያሳድረው። ኑሮን ያመሰቃቅላል። በክትባት ሕመሙን መግታት ከቻልኩ ደስተኛ እሆናለሁ" ትላለች።
ተዋናይቷ የደም መርጋትም አለባት። ቀዶ ሕክምና የሚደረግላት ደም እየተሰጣት ነው።
ሕመሟ ቀድሞ ቢታወቅላት ኖሮ ለማከም ይቀል ነበር።
የካንሰር ክትባት እንዴት ይሠራል?
ሳይንቲስቶች ለዓመታት ካንሰርን ለማከም ክትባቶች ላይ ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል። እምብዛም ውጤታማ አልሆኑም።
የኩፍኝ እና ማጅራት ገትር ክትባቶች ሰውነት ራሱን የሚከላከልበትን አቅም እንዲያጎለበት ያደርጋሉ።
ሰውነት ራሱን ከቫይረስና ባክቴሪያ የሚከላከለው በክትባት ዕገዛ ነው።
ካንሰርን በዚህ መንገድ ማከም ቀላል አይደለም። ምክንያቱም ካንሰር የሚመነጨው ከሰውነትን ሕዋሳት ነው።
የካንሰር ክትባት ሲሠራ ለእያንዳንዱ ታካሚ በሚሆን መንገድ መዘጋጀት ይኖርበታል።
የሰዎችን ዘረ መል በመከተል ክትባቱ እንደሚሠራ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ክትባቱ ሰውነት ፕሮቲን እና ፀረ ቫይረስ/ባክቴሪያ እንዲያመርት ያስችላል። በካንሰር የተያዙ የሰውነት ሕዋሳትን ለይቶ እንዲያጠቃም ያደርጋሉ።

የፎቶው ባለመብት, Kiran Dhillon/UW Medicine Cancer Vaccine Institute
ዶ/ር ኖራ ከካንሰር ቫክሲን ኮአሊሽን ጋር በትብብር ይሠራሉ።
ይህ የአሜሪካ ተቋም ተስፋ ሰጪ ክትባቶች በብዛት እንዲመረቱ ያመቻቻል።
ዶ/ር ኖራ፤ የጡት ካንሰር በፍጥነት እንዲያድግ የሚያደርገውን ኸር 2 ፕሮቲን (HER 2 protein) ዒላማ የሚያደርግ ክትባት (UW's WOKVAC) ላይ ጥናት ሠርተዋል።
ክትባቱ ከኬሞቴራፒ ጎን ለጎን ይሰጣል።
ሕክምናው የሚሰጠው ዕጢውን ከሰውነት ለማውጣት ቀዶ ሕክምና ከመደረጉ አስቀድሞ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Diana Innes
"የካንሰር ክትባት የመጨረሻውን የሙከራ ደረጃ አልፎ ፈቃድ የሚያገኝነት ደረጃ ላይ ደርሰናል" ይላሉ ዶ/ር ኖራ።
አኒክሳ ባዮሳይንስ የተባለው መድኃኒት አምራች እና ክሊቭላንድ ክሊኒክ ባለፈው ነሐሴ ላይ የመጀመሪያ ዙር ሙከራ አድርገዋል።
የጡት ወተት ፕሮቲን (alpha lactalbumin) ላይ ያነጣጠረ ክትባት ነው። ከጡት ካንሰር ዓይነቶች ከባዱ ይህኛው ነው።
በአኒክሳ ባዮሳይንስ የሚሠሩት ዶ/ር አኒል ኩመር "ከጡት ካንሰር ጋር የሚመሳሰል ፕሮቲን ወደ ሰውነት በማስገባት ሰውነት ሕመም ያለበትን ሕዋስ እንዲያጠቃ እናለማምዳለን" ይላሉ።
ክትባቱ የዕጢ መጠንን መቀነስ ከቻለ ቀዶ ሕክምናው ቀላል ሊሆን ወይም ላያስፈልግም ይችላል።
ክትባቱ ከካንሰር ያገገሙ እንዲሁም ለካንሰር ተጋላጭነታቸው ከፍ ባለ ሴቶች ላይ ይሞከራል።
ጥናቱ እንደሚጠቁመው፤ከ70 በመቶ ሴቶች በክትባቱ አማካይነት ሰውነታቸው በካንሰር የተያዘውን ሕዋስ ማጥቃት ችሏል።
በክሊቭላንድ ክሊኒክ ውስጥ በሚገኘው የካንሰር ማዕከል የሚሠሩት ዶ/ር ጂ ቶማስ ባድ፤ ክትባቱ አነስተኛ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ይናገራሉ።
የምርምሩ ሁለተኛ ክፍል በ2026 መባቻ ይጀመራል።
ከጥናቱ ተሳታፊዎች ግማሹ ክትባቱ ተሰጥቷቸው የተቀሩት ደግሞ ክትባቱን ሳያገኙ ያለው ልዩነት ይፈተሻል።
ባለሙያው እንደሚሉት፤ ካንሰር የሌለባቸው ሴቶችና ወንዶችም ክትባቱን ወስደው በሽታውን የሚከላከሉበት ቀን መምጣቱ አይቀርም።
ሦስተኛው የምርምር ደረጃ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕሙማን ላይ ይካሄዳል።
ከዚያ በኋላ ክትባቱ ፈቃድ እስከሚያገኝ ዓመታት ሊወስድ ይችላል።
የአሜሪካው መድኃኒት ተቆጣጣሪ ተቋም ፈቃድ ለማግኘት የሚወስደውን ጊዜ ለማሳጠር ዕቅድ ይዟል።
ዲያና ኢንስ የካንሰር ክትባት ወስዳለች። ከካንሰር ካገገመች ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል።
"ሎቶሪ የማሸነፍ ያህል ነው" ትላለች።
በ39 ዓመቷ የሁለት ዓመት ልጇን ታቅፋ ሳለ ነበር ጡቷን የጎረበጣት።
ሦስተኛ ደረጃ የጡት ካንሰር እንዳለባት ተነገራት። Triple Negative Breast Cancer ወይም TNBC የተባለው ካንሰር ነበር የተገኘባት።
ቀዶ ሕክምና፣ የጨረር ሕክምና እንዲሁም 16 ዙር ኬሞቴራፒ ተደርጎላታል።
ለካንሰር ክትባት ሙከራ ብቁ መሆኗ ሲነገራት መጀመሪያ ላይ መጠራጠሯ አልቀረም።
ሙሉ መረጃውን ካገኘች በኋላ ተስማማች።
"በሳይንት ትልቁ ግኝት ነው የሚሆነው" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, CVC
ክትባቱ ለማን ይሰጣል?
ለእያንዳዱ ታማሚ የሚሆን ክትባት ማዘጋጀት ተስፋ የተጣለበት የሳይንስ ዘርፍ ነው።
ሆኖም ግን ለማምረት ቀላል አይደለም።
በሃብታም አገራት በካንሰር ከሚያዙ ሴቶች 83 በመቶ የመትረፍ ዕድላቸው ሰፊ ነው።
በአንጻሩ በደቡባዊ አፍሪካ በካንሰር ከሚያዙ ሴቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ይሞታሉ።
የክትባት ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ላይ ጥያቄ ያላቸው ባለሙያዎች አሉ።
የቀዶ ሕክምና፣ የጨረር ሕክምና እንዲሁም የሌሎችም መሠረታዊ የካንሰር ሕክምናዎች ተደራሽነት አሁንም ውስን ነው።
ዶ/ር ኢዛቤል ሶርጅማትን "ለእያንዳንዱ ታማሚ ተብለው የሚሠሩ ክትባቶችን ማግኘት ከዚህም በላይ ፈታኝ ነው" ይላሉ።
መድኃኒት አምራች ተቋማት የረዥም ጊዜ ዕቅዳቸው በመድኃኒት መደብር የሚሸጥ ክትባት ማምረት ነው። በዚህ መንገድ ሰፊውን ማኅበረሰብ ለመድረስ አስበዋል።
ከካንሰር የማገገም ዕድል ከአገራት ምጣኔ ሃብት ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው።
በ2050 በዓለም አቀፍ ደረጃ የካንሰር ስርጭት 68% እንደሚደርስ ይታመናል።
የካንሰር ተመራማሪ ዶ/ር ጆአን ኪም "በየደቂቃው አራት ሴቶች የጡት ካንሰር ይገኝባቸዋል። አንድ ሴት በሕመሙ ትሞታለች። ከዚህም በላይ እየተባባሰም ይሄዳል" ይላሉ።
ተዋናይቷ ቪክቶሪያ በተለይም በጥቁር ሴቶች ዘንድ የክትባት ተደራሽነት ላይ የግንዛቤ መስጫ ንቅናቄ ታደርጋለች።
"ስለ ጡት ካንሰር ምንም የማይወራባቸው ማኅበረሰቦች አሉ። ሴቶች ሃፍረትና የጥፋተኛነት ስሜት ይሰማቸዋል" ትላለች።
ዲያና በድጋሚ ካንሰሩ እንደማይመለስባት ተስፋ አላት።
"የካንሰር ክትባት ሁለተኛ ደረጃ ምርምር ላይ ደርሷል። ለውጤታማኑም ሕያው ምስክር ነኝ" ትላለች።















