ጠባብ የጡት ማስያዣ ማድረግ ለጡት ካንሰር ያጋልጠኝ ይሆን?

የጡት ማስያዣ ያደረገች ሴት የጡት ካንሰር ግንዛቤ መስጫ ሪበን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በ2020 (እኤአ) በዓለም 2.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶች በጡት ካንሰር የተያዙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 685 ሺህ ያህሉ መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

በዚሁ ዓመት መጨረሻ 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑ የዓለማችን ሴቶች ባለፉት አምስት ዓመታት በጡት ካንሰር መያዛቸው የታወቀ ሲሆን፣ ይህም የጡት ካንሰር በርካታ ሰዎችን በመያዝ ቀዳሚውን ተርታ እንዲይዝ አድርጎታል።

በየትኛውም የእድሜ ክልል ኣሉ ሴቶች ለጡት ካንሰር በሽታ ተጋላጭ ናቸው። ቁጥሩ ኢምንት የሚባል ይሁን እንጂ ወንዶችም ቢሆኑ በጡት ካንሰር ይያዛሉ።

ለዚህ በሽታ ያጋልጣሉ ተብለው የተለዩ ምክንያቶችን መቆጣጠር ቢቻል በአጠቃላይ ለበሽታው የመጋለጥ ዕድል በ30 በመቶ ብቻ ነው የሚቀንሱት።

ስለዚህ የበሽታውን ምልክቶች፣ ቅድመ ጥንቃቄ እና ሕክምናውን ማወቅ አስፈላጊ ነው።

ስለዚህ ጉዳይ ትክክለኛውን መረጃ ትክክል ካልሆነው መለየት እና ማወቅ ደግሞ ከስጋት ያድናል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ወሳኝ የሚባሉ መረጃዎችን ለማግኘት በመደወላቡ ዩኒቨርስቲ፣ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት እና በጡት ካንሰር ላይ ጥናት የሚያደርጉትን ዶ/ር ከበበ በቀለን አነጋግረናል።

የጡት ካንሰር ከምን እንደሚመጣ ይታወቃል?

ዶ/ር ከበበ እንደሚሉት ከሆነ የጡት ካንሰርንም ሆነ ሌሎቹን የካንሰር ዓይነቶች በተጨባጭ ምን ሊያመጣቸው እንደሚችል በጥናት የተረጋገጠ መንስዔ የለም።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የጡት ካንሰር 85 በመቶ ያህሉ ‘Epithlium of the ducts’ የሚባል ሆርሞን ሴሎች ውስጥ መብቀል ይጀምራሉ ይላል።

ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ተፈጥሯዊ ኦስትሮጀን ያላቸው በመሆኑ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ለችግሩ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

ኦስትሮጅን በብዛት ካለ ደግሞ ተጨማሪ የጡት ሕብረ ህዋሳትን የሚፈጥር ሲሆን፣ አንዳንዴ እነዚህ ያልተለመደ እድገት ከመፍጠር ባለፈ ወደ ጡት ካንሠርነት ሊያመሩ ይችላል።

ዶ/ር ከበበ እነዚህ የካንሰር ህዋሳት ከሌሎች የሰውነታችን ህዋሳት በተለየ ቶሎ ቶሎ የመብዛት እና ከቁጥጥር ውጪ በመሆን ወደ ሞት ሊያደርሱን ይችላሉ ይላሉ።

ይህንን በሽታ ምን ሊያመጣው እንደሚችል ካላወቅን ተጋላጭነታችንን ሊጨምሩ የሚችሉ ጉዳዮች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ሐኪሙን ጠይቀናል።

እድሜ

የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ በሆኑ ሴቶች ላይ በብዛት ይታይ እንጂ፣ በ20ዎቹ ውስጥ ያሉ ሴቶችንም እየያዘ መሆኑን ሐኪሙ ይናገራሉ።

“ከዚህ በፊት በተደረገ ጥናት ስምንት በ20ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች ላይ መገኘቱ ተረጋግጧል፤ ነገር ግን እድሜ በጨመረ ቁጥር ለዚህ በሽታ የመጋለጥ ዕድልም እንዲዚያው እየጨመረ ይሄዳል።”

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ይህ በሽታ አብዛኛውን ጊዜ እድሜያቸው ከ40 በላይ የሆኑ ሴቶችን ያጠቃል ቢልም፣ ዶ/ር ከበበ ግን “በአገራችን እድሜያቸው ከዚያ በታች ባሉ ሴቶች ላይ በብዛት እየታየ ነው” ይላሉ።

የጡት ካንሰር በምርመራ ወቅት

የፎቶው ባለመብት, SPL

ጾታ

ዶ/ር ከበበ ሴት መሆን በራሱ ለጡት ካንሰር ተጋላጭ ያደርጋል ይላሉ።

ይህ ማለት ግን ወንዶችን ከነጭራሹ አይዛቸውም ማለት አይደለም። ወንዶች በዚህ በሽታ የሚያዙበት መጠን በጣም አነስተኛ ነው።

ሴቶች 99 በመቶ ያህሉ ለጡት ካንሰር የሚጋለጡበትን ምክንያትም ሲያብራሩ የወር አበባ ዑደትን ያነሳሉ።

“ሴት ልጅ በወር አበባዋ ጊዜ በየወሩ ጡቷ ይጨምራል ይቀንሳል፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ኦስትሮጅን የተባለው የሴት ሆርሞን ስለሚመረት እና ለረዥም ጊዜ ለሆርሞኑ ስለምትጋለጥ፣ በየጊዜው የሚኖር ሂደትም ስለሆነ ለካንሰር ህዋሳት መብቀል ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል።”

ወንዶች ለምን በጡት ካንሠር ይያዛሉ?

የወንዶች የጡት ካንሠር መነሻ ትክክለኛው ምክንያት ባይታወቅም በዘረ መል እና የቤተሰብ የጡት ካንሠር ታሪክ፣ በሰውነት ውስጥ የኤስትሮጅን መጠን ከፍ የሚያደርጉ ነገሮች ማለትም ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት እና የጉበት ጠባሳ በአጋላጭ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም ቀደም ሲል ደረት አካባቢ የተደረገ ራዲዮቴራፒ እንደ አጋላጭ ምክንያትነት በእንግሊዙ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ተጠቅሷል።

ወንዶች በጡት ካንሰር የመጋለጥ ስጋታቸውን ለመቀነስም የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ፣ ከመጠን በላይ ወፍራም ከሆኑ ክብደት እንዲቀንሱ እና ከመጠን በላይ አልኮል ከመጠጣት እንዲቆጠቡ ይመከራል።

የጡት ካንሰር በዘር ሊተላለፍ ይችላል?

ዶ/ር ከበበ እንደሚሉት የጡት ካንሰር 20 በመቶ ያህሉ በዘር የሚተላለፍ ነው። ይህም እናት፣ እህት፣ ልጆች በዚህ በሽታ ከተያዙ የዚያ ቤተሰብ አባል የሆነች ሴት ለበሽታው የመጋለጥ ዕድሏ ሰፊ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ለዚህ በሽታ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች የሰውነት ክብደት አለአግባብ መጨመር፣ አልኮል መጠጥ አዘውትሮ መጎንጨት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ለረዥም ጊዜ ያለ እንቅስቃሴ መቀመጥ እና አንዱ ጡት ከዚህ በፊት በካንሰር ተይዞ ከሆነ ሌላኛው ጡት ለበሽታው የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።

ጡት አለማጥባትም ለዚህ በሽታ ሊያጋልጥ ከሚችሉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል።

የጡት ካንሰርን የምትፈትሽ ሴት

የፎቶው ባለመብት, SPL

“ጡቴ በጣም ትልቅ ነው ለካንሰር ያጋልጠኝ ይሆን?”

 ዶ/ር ከበበ ጡት መጠኑ ስላደገ ብቻ ለካንሰር አያጋልጥም፤ መጠኑ ስላነሰ ደግሞ ከካንሰር አይተረፍም ይላሉ።

“ጡት ከሦስት ነገሮች ነው ሚፈጠረው። የጡት ካንሰር ደግሞ የሚነሳው ወተት ከሚያመነጨው ቲሹ (ሕብረ ህዋስ) እንጂ ጡቱ በራሱ ትልቅ ስለሆነ ካንሰር ይያዛል ማለት አይደለም።”

ጠባብ ጡት ማስያዣ ማድረግ ለካንሰር ያጋልጣለ?

እስካሁን ድረስ ጠባብ የጡት ማስያዣ በማድረግ ይህ የካንሰር ዓይነት ይይዛል የሚል ተለይቶ የታወቀ ነገር እንደሌለ የሕክምና ባለሙያው ይናገራሉ።

አብዛኛውን ጊዜ ይህ በሽታ ከተፈጥሯዊ አወቃቀር (ጄኔቲክስ) ጋረ የተያያዘ ስለሆነ በውጫዊው የሰውነት ክፍላችን ላይ ከሚደረጉ ጉዳዮች ጋር አይያያዝም።

የጡት ካንሰር ሊድን ይችላል?

 በመጀመሪያ ማወቅ የሚገባን ጉዳይ የጡት ካንሰር ሊታከም እና ሊድን የሚችል በሽታ መሆኑ ነው ይላሉ ዶ/ር ከበበ። ይህ ግን የሚሆነው በሽታው ሰውነታችን ወስጥ ሳይስፋፋ በጊዜ ከተደረሰበት ብቻ ነው።

በጊዜ ተደርሶበታል የሚለውንም ሲያብራሩ “የጡት ካንሰር እስከ አራት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን የመጀሪያው ደረጃ ካንሰሩ በበቀለበት የሰውነት ክፍል የሚገኝ ነው። ካንሰሩ በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ላይ እያለ ከተደረሰበት በጊዜ ተደርሶበታል ማለት ይቻላል። ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ከሆነ ወደ ብብት እንዲሁም ወደ ሳንባ ከተንሰራፋ በኋላ የሚደረስበት ነው።”

ስለዚህ ይላሉ ዶ/ር ከበበ ሴቶች ጡታቸው ላይ ማንኛውንም የእብጠት ዓይነት ካዩ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ፣ ካንሰር መሆኑን እና አለመሆኑን በጊዜ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

የጡት ካንሰር መጀመሪያ ሲወጣ ምንም ዓይነት ህመም የማይሰማ በመሆኑ “ይህች በጣም ትንሽ ናት፤ ምንም አታደርገኝም በሚል እስከ አራት ወር ድረስ በመቆየት ብዙ ሰዎች በሽታው እንዲስፋፋ ዕድል ይሰጡታል” ሲሉ ያክላሉ።

ዶ/ር ከበበ “ሴቶች ጡታቸው ላይ እብጠት ካዩ በአስቸኳይ ወደ ሐኪም ቤት መሄድ ይኖርባቸዋል” ሲሉ ይመክራሉ።

ጡቷን የምትፈትሽ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጡት ካንሰርን በጊዜ ለማወቅ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በተለይም በጡት ላይ እብጠትን ጨምሮ ሌሎች ምልክቶችን ሊከታተሉ ይገባል።

ዶ/ር ከበበ ጡታችን ሁሉ ጊዜ የምንነካካው እና የምንደርስበት የሰውነታችን ክፍል መሆኑን ማስተዋል እንደሚገባ ይናገራሉ።

ስለሆነም ይላሉ፣ እድሜያቸው ከ45 ዓመት በታች የሆነ እና የወር አበባ እያዩ ያሉ ሴቶች “የወር አበባቸው መጥቶ እንደሄደ በየወሩ ጡታቸውን በአግባቡ በመፈተሽ፣ እብጠት መኖሩን እና አለመኖሩን ማረጋገጥ አለባቸው፤ በተለይም ትልቅ ጡት ያላቸው ሴቶች የላይኛውን ቆዳቸውን ብቻ ነካክተው ከተዉ ሊያገኙት ስለማይችሉ በአግባቡ እና ሙሉ በሙሉ መፈተሽ ይኖርባቸዋል።”

የወር አበባ እያዩ ያልሆኑ ሴቶች ደግሞ በወር ውስጥ አንድ ቀን ቆርጠው በየወሩ ጡታቸውን መፈተሽ እንደሚኖርባቸው ይመክራሉ።

“በዚህ ሂደት ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት እብጠት ካዩ፣ ባያማቸውም እንኳ የካንሰር ምልክት ሊሆን ስለሚችል ወደ ሐኪም ዘንድ መሄድ ይኖርባቸዋል።”

ከዚህ በተጨማሪ በቤታሰባቸው ውስጥ በካንሰር የተያዘ ሰው ካለ እና እድሜያቸው ከ40 በላይ ከሆነ ምንም ዓይነት ምልክት ሳያዩ ወደ ሐኪም ቤት በመሄድ መታየት ይኖርባቸዋል።

የጡት ካንሰር ብዙ ጊዜ “የእብጠት ምልክት ሳያሳይ ሰውነታችን ውስጥ ሊጠፋ አይችልም። ነገር ግን አንዳንዴ ይህ እብጠት ጡታቸንን ትቶ ብብታችን ስር ሊወጣ ስለሚችል እዚያም ስር በደንብ መፈተሽ አስፈላጊ ነው። የጡት ካንሰር መብቀል እንደ ጀመረ ህመም የሌለው ሲሆን፣ ነገር ግን አንድ ጊዜ ማመም ከጀመረ ህመሙ የወር አበባ በመጣበት ጊዜም ይሁን በሌለ ጊዜ ይቀጥላል።”

ነገር ግን ይላሉ ዶ/ር ከበበ፣ አንድ ሰው ካንሰር ይዞታል ማለት ህመም የመጀመሪያው ምልክት አይደለም።

የጡት ካንሰር ሰውነታችን ውስጥ ከተስፋፋ በኋላ ኬሞቴራፒን ጨምሮ የተለያዩ ሕክምናዎች ይሰጣሉ። በዚህም ሰዎች ሊድኑ ይችላሉ።

የካንሰሩ ደረጃ በጨመረ መጠን ግን ሰውነት ውስጥ በመስፋፋት ሕክምናውን ውስብስብ ያደርገዋል። ስለዚህ አስቀድሞ ክትትል ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን ሕክምና ባለሙያው አስረግጠው ይናገራሉ።