"በኢትዮጵያ በየዓመቱ ቢያንስ 5 ሺህ ሴቶች በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ሳቢያ ይሞታሉ"

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ቢያንስ 5000 ሴቶች በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ሳቢያ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ በጤና ሚንስትር የእናቶችና የህጻናት ጤና እንዲሁም የሥርአተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይዴክተር ዶ/ር መሠረት ዘላለም ገለጹ።

በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር የሚያዙ ሴቶች ቁጥርን በተመለከተ የተሟላ መረጃ ባይኖርም፤ በየዓመቱ እስከ 7ሺህ የሚደርሱ ሴቶች በበሽታው እንደሚያዙ ተናግረዋል።

በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ አማካይነት የሚከሰተውን የማህጸን በር ጫር ካንሰር ለመከላከል ከጥር 17 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ. ም. አገር አቀፍ የክትባት ዘመቻ እየተካሄደ ነው።

ዶ/ር መሠረት እንዳሉት፤ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ እየተካሄደ ባለው የክትባት ዘመቻ 14 ዓመት የሞላቸው ሴቶች እንዲከተቡ እየተደረገ ነው።

ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ሁለተኛው አስጊ የሆነውን የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በክትባት መከላከል ይቻላል።

"የግብረ ስጋ ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት ክትባቱን መውሰድ ስላለባቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ሴቶች ክተባቱን እየሰጠን ነው። ክትባት ቅድመ መከላከል ይሰጣል" ሲሉ አስረድተዋል።

የሚሰጠው ሁለት ጠብታ ክትባት ሲሆን የመጀመሪያው ከተሰጠ ከስድስት ወር በኋላ ሁለተኛው ይሰጣል።

"ሴቶች ይህንን ክትባት ሁለት ጠብታ ከወሰዱ በኋላ በድጋሚ መውሰድ አያስፈልግም። ነገር ግን ኤችአይቪ ላለባቸው ክትባቱ በድጋሚ ሊሰጥ ይችላል" ይላሉ ዶ/ር መሠረት።

ከዚህ በፊት በነበሩት ሦስት ዓመታት ከትምህርት ሚንስትር ጋር በመሆን 14 ዓመት ለሞላቸው ሴቶች ክትባቱ መሰጠቱን ይናገራሉ።

"በየዓመቱ 1. 2 ሚሊዮን ልጃገረዶች እንደርሳለን ብለን እናስባለን" የሚሉት ዶ/ር መሠረት ዘንድሮም በየትምህርት ቤቱና በጤና ጣቢዎች አማካይነት ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አምና የመጀመሪያው የክትባት ጠብታ ከተሰጠ በኋላ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሁለተኛውን ዙር ማዳረስ ባለመቻሉ፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ክትባት ከሚወስዱ ጋር አንድ ላይ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ዘንድሮ የመጀመሪያውን የክትባት ጠብታ የሚወስዱ ታዳጊ ሴቶች ሐምሌ ላይ ወይም በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት አካባቢ ሁለተኛውን ጠብታ ይወስዳሉ።

ትግራይ ክልል ውስጥ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ክትባቱን መስጠት እንደማይቻል፤ የገለጹት ዶ/ር መሠረት ክትባቱን ማዳረስ ላልተቻለባቸው አካባቢዎች ቀጣይ እቅድ እንደሚወጣ ተናግረዋል።

በትምህርት ሚኒስትር በኩል ትምህርት ቤት የገቡ ታዳጊ ሴቶችን እንደሚያገኙና በተለያየ ምክንያት ትምህርት ላይ ያልሆኑትን ደግሞ በጤና ተቋሞች እንዲሁም ቤት ለቤት በመዘዋወርም ክትባቱን እንደሚሰጡ አስረድተዋል።

ዶ/ር መሠረት "የማህጸን በር ጫፍ ካንሰርን በተመለከተ ሴቶች ክትባቱን እንዲወስዱ በመገናኛ ብዙሀንም እንቀሰቅሳለን። አንደኛ ዙር ክትባት የወሰዱ ሁለተኛውንም ዙር እንዲወስዱም ቅስቀሳ እናደርጋለን" ብለዋል።

በኢትዮጵይ ላለፉት በርካታ ዓመታት ኩፍኝን ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል አገር አቀፍ የክትባት ዘመቻዎች ተካሂደዋል።