‘ከበሽታው ይልቅ ጭንቀቱ ሕመሜን አባሰው’

- የማህጸን በር ካንሰር በኢትዮጵያ ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሆኑ የካንሰር ዓይነቶች መካከል ሁለተኛው ነው።
- የሕክምና ባለሙያዎች አብዛኞቹ ታማሚዎች ወደ ሕክምና ተቋም የሚመጡት ህመማቸው ከተባባሰ በኋላ ነው ይላሉ።
- ሂውመን ፓፒሎማ ቫይረስ ለማህጸን በር ካንሰር ዋነኛው አጋላጭ ቫይረስ ነው።
- ቫይረሱ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ነው።
- ማንኛዋም ግንኙነት የጀመረች ሴት በማህጸን በር ካንሰር ልትያዝ ትችላለች።
- የማህጸን በር ካንሰርን የሂዩመን ፓፒሎማ ቫይረስ ክትባት በወቅቱ በመውሰድ መከላከል ይቻላል።
- የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም ሴቶች አስራ አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ክትባቱን እንዲውስዱ ይመክራል።
የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ገነት ኤልያስ ነዋሪነታቸው ሐዋሳ ከተማ ነው።
ልጆቻቸውን ብቻቸውን እንዳሳደጉ የሚናገሩት ወ/ሮ ገነት ሁለት የልጅ ልጆቻቸውም አብረዋቸው ይኖራሉ።
“ከባለቤቴ ጋር ከተለየሁ ቆይቻለሁ። ልጆቼን የማሳድገው ብቻዬን ነው” የሚሉት ወ/ሮ ገነት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ እንደሚመሩ ይናገራሉ።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ተስፋ የሚያደርጉት ልጆቻቸው ለወግ ማዕረግ በቅተው ማየት ነው።
ወ/ሮ ገነት የጤናዬ ጉዳይ እምብዛም ነው ይላሉ። ምንም እንኳ እድሜያቸው ያልገፋ ቢሆንም በ2005 የወር አበባ ማየት እንዳቆሙም ያስታውሳሉ።
በ2007 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕክምና ቡድን መጥቶ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ ሲያደርግ ወ/ሮ ገነትም ተመርምረዋል።
“ነጻ ነበርኩ፤ ከአምስት ዓመት በኋላ ነይ ተባልኩ” ይላሉ።
በ2009 ዓ.ም ላይ ግን የወገብ ሕመም እና ከማህጸን የሚወጣ ፈሳሽ አጋጠማቸው። በአቅራቢያቸው ወደ ሚገኘው የጤና ተቋም ጎራ ብለው የተፈጠረውን ሁኔታ አስረዱ።
በሽታቸው ነው ለተባለው ጉዳይ መድኃኒት ተሰጥቷቸው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
በዚያው ዓመት ሌላ ሕክምና ቡድን ወደ ሐዋሳ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ ለማድረግ መጣ።
ያኔ ወ/ሮ ገነት የተሰጣቸውን የቀጠሮ ካርድ ይዘው ቀረቡ።
የሕክምና ቡድኑ ከማህጸናቸው ከሚወጣው ፈሳሽ ናሙና ወስዶ፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ በተገኘው ውጤት መሠረት ወደ ጥቁር አንበሳ ሪፈር ተጻፈላቸው።
‘የምሞት መስሎኝ ተስፋ ቆርጬ ነበር’
ወ/ሮ ገነት ከማህጸናቸው መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ ይፈስስ እንደነበር ይናገራሉ።
የምርመራው ውጤት ደግሞ ካንሰር የሚለውን ቃል ይዞ መምጣቱ ዙሪያቸው እንዲጨልም አደረገ። ቤታቸው በጭንቀት እና በልቅሶ ተሞላ።
ባለሙያዎች “ከዚህ በፊት ምርመራ ተደርጎ ነጻ ነሽ ብለውኝ ስለነበር እንዴት በአጭር ዓመት ውስጥ ሊገኝ ቻለ” ብለው ግራ ተጋብተዋል ይላሉ ሁኔታውን ሲያስታውሱ።
ልጆቻቸው በፍርሃት ራዱ። እርሳቸው ተስፋ በመቁረጥ ክፉ በትር ተመትቱ።
በዚያ ላይ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ለሚኖር ምንዱባን አዲስ አበባ ሩቅ የተሰቀለ ዳቦ ነው። የትራንስፖርት ወጪው ብቻ ሲታሰብ ጉልበት ያዝላል።
“አይደለም ጥቁር አንበሳ እዚያው ጤና ጣቢያ እንኳ ለመታከም አቅም ያጥረኛል። በጣም አዘንኩ። በቃ መሞቴ ነው ብዬ ከፋኝ፝።”
የምርመራ ውጤታቸውን የሰሙ ዘመዶች፣ ጎረቤቶች ምክር ያሉትን ሁሉ ይዘው ወደ እርሳቸው ቤት ይጎርፋሉ።
“ብዙ ደምጽ ነበር የምሰማው” ይላሉ ሁኔታውን ሲያስታውሱ።
“በዙሪያዬ ያሉ ሁሉ ፀበል እንድሄድ፣ ማህጸኔን እንዳስወጣ ይመክሩኛል” ያሉት ወ/ሮ ገነት አንድም ሰው መሃረቡን ፈትቶ፣ ከጥሪቱን አውጥቶ በዚህ ታከሚ ያላቸው አልነበረም።
“ከመጠን በላይ ያዘነው ትልቁ ልጄ ነው” የሚሉት ወ/ሮ ገነት፣ ሌላኛዋ ልጃቸውም እናቷን ለመደገፍ በማሰብ ወደ አረብ አገር ጓዟን ጠቅልላ ሄደች።
ይህ ግን ስምንት ወር ብቻ ነው የቆየው፤ ወድያው ተመለሰች።
“ካንሰር መሆኑን ሲያውቁ ልጆቼ ተስፋ ቆርጠዋል። አንደኛዋ ልጄ ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ነበር የደረሳት ውጤቴን ከሰማሁ በኋላ አልማርም ብላ ልትቀር ነበር። በወቅቱ ለህክምና ገንዘብ ማውጣት፣ ልጅ ማስተማር የሚለውን ማሰብ አእምሮዋን ረበሸው፣ ነገር ግን የኔ ሕክምና ይቀራል እንጂ አንቺ ትምህርትሽን አታቋርጪም ብዬ ላኳት” ይላሉ።
አክለውም “እንዴት እንዳሳደግኳቸው ያውቃሉ። በጣም ተስፋ ቆርጠው ነበር። የሚያኖር ፈጣሪ ነው፣ እስከ አሁን ድረስ ኖሬላቸዋለሁ” እላሉ።
በካንሰር የተያዘ ሰው መጨረሻው ሞት እንደሆነ ሲሲሙ የቆዩት ወ/ሮ ገነት ተረብሸው ነበር። በዚህ ላይ የመታከሚያ ገንዘብ አጥተው ቤት ውስጥ በተኙበት አልጋ ላይ የቀሩ ሰዎች ማወቃቸው ደግሞ ፍርሃታቸውን ከፍ አደረገው። አዲስ አበባ ሄደው የሚያርፉበት፣ ለሕክምና የሚያስፈልጋቸው ወጪን ሲያስቡ ህመማቸው በረታ።
“እርሱን እርሱን ሳስታውስ ልቤ በፍርሃት ራደ። ጭንቀቱ በሽታ ጨመረብኝ። ለአስራ አምስት ቀን ያህል ታመምኩ።”
እስቲ ለማንኛውም ወደ አዲስ አበባ ሄጄ ምን እንደሚሉኝ ልስማ ብለው ሲወስኑ፣ በሐዋሳ ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታል የሚገኙ ነርሶች ወ/ሮ ገነት አዲስ አበባ ሄደው መታከም የሚችሉበትን ሁኔታ ማፈላለግ ጀመሩ።
በዚህ መካከል ማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ አቅም የሌላቸው የካንሰር ታማሚዎችን እንደሚደግፍ በመስማታቸው ከድርጅቱ ጋር አገናኟቸው።
ጓደኞቻቸው ለትራንስፖርት የሚሆናቸው ገንዘብ አዋጥተው ወደ አዲስ አበባ ላኳቸው።
ማቴዎስ ወንዱ ለታማሚዎች እንክብክካቤ ማቅረብ እንዲሁም ስለበሽታው ግንዛቤ መፍጠርን ግብ አድርጎ እየሰራ የሚገኝ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።
ከተቋቋመ ሁለት አስርታትን ያስቆጠረው ድርጅቱ እስካሁን ድረስ 1860 በላይ ለሚሆኑ ሕጻናትና ሴት የካንሰር ሕሙማን ድጋፍ ያደርጋል።
ተቋሙ የማህጸን ጫፍ እና የጡት ካንሰር እንዲሁም የትምባሆ ቁጥጥር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም ያከናውናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሕክምናው ተጀመረ
ወ/ሮ ገነት ወደ አዲስ አበባ የመጡት በ2009 ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ መሆኑን ያስታውሳሉ። በተከታታይም የተለያዩ ምርመራዎች እና ሕክምናዎችን ማድረግ ጀመሩ። ከዚያም ለወራት የሚያስፈልገውን ሕክምናውን ሲከታተሉ ቆይተው ግንቦት 2010 ወደ ሐዋሳ ተመለሱ፥
ወደ ሐዋሳ ሲመለሱም ጤናቸው ተስተካክሎ የበፊት ስጋታቸው እንደ ጠዋት ጤዛ ጠፍቶ ነበር።
በየስድስት ወሩም ለሕክምና ክትትል ወደ አዲስ አበባ ይመላለሳሉ።
ይህ ግን እስከ 2013 ዓ.ም ብቻ የቆየ ነበር። ከማህጸናቸው ዳግም መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ ይፈስ ጀመር።
ጉዳዩን ለባለሙያዎች ሲያስረዱም “ብዙ መድኃኒት ስለወሰድሽ ይሆናል” የሚል ምላሽ አግኝተው በስድስት ወራቸው የቀጠሯቸውን ቀን ጠብቀው እንዲመለሱ ተነገራቸው።
በቀጠሯቸው ተመልሰው ሐኪም ጋር ሲቀርቡ፣ ቀደም ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ የካንሰር ሕክምና ሲጀምሩ የተደረገላቸው ምርመራ በሙሉ አንደ አዲስ ተሰራላቸው።
“ውጤቱም ተመሳሳይ ነበር” ይላሉ ወ/ሮ ገነት። “መጀመሪያ ላይ ስመረመርም ካንሰሩ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ነበር የተባልኩት። አሁንም ሦስተኛ ደረጃ ላይ ያለ ካንሰር መሆኑን ነገሩኝ።”
ስለዚህ ዳግም ሕክምናውን እንደ አዲስ መጀመር አስፈላጊ ሆነ።
ልጆቻቸው ዳግም ካንሰሩ ማገርሸቱን ሲሰሙ የበለጠ ተረበሹ። “ከመጀመሪያው የበለጠ ደነገጡ። ከበፊቱ ይበልጥ አዘኑ። እህቶቼን እና ወንድሞቼን አስጨነቋቸው” ይላሉ።
“እንደ ቤተሰብ ብዙ መከራ አሳልፈናል፤ ደክመናል። በሕይወት መኖሬ ነው የእነርሱ መጽናናት። በልጆቼ ፀሎት ኃይል እና በህክምና እርዳታ ነው እስካሁን ያለሁት።”
የካንሰር ሕክምና እና ወጪው
ወ/ሮ ገነት የሚከታተሉትን የካንሰር ሕክምና የሚደግፋቸው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባይኖር የሚታሰብ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
ለምርመራ እና ለመድኃኒት የሚወጣው ወጪ እንኳን የዕለት ጉርስ ለማግኘት ለሚባትል እንደ እርሳቸው ያለ ሰው ቀርቶ፣ ወርሃዊ ደመወዝ አለኝ ለሚል እንኳ የሚታሰብ አይደለም።
“ሕክምናው ሲደረግ የተለያዩ መድኃኒቶች ነው የምንገዛው፤ በየ15 ቀኑ ለእኔ ሕክምና ብቻ ድርጅቱ እስከ ስድስት ሺህ ብር ድረስ ያወጣል” ይላሉ።
ወ/ሮ ገነት የጤና መድህን ያላቸው መሆኑን ገልፀው፣ ነገር ግን በጤና መድህኑ መድኃኒት መግዛት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
“ይህ ድርጅት ባይኖር ኖሮ እስካሁን ሞቼ ነበር” የሚሉት ወ/ሮ ገነት፣ በየቤታቸው የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን አቅቷቸው ቀናቸውን የሚቆጥሩ በርካቶች መሆናቸውን ይናገራሉ።
አሁን ጤናዬ ደህና ነው በማለትም “መጨረሻውን ፈጣሪ ነው የሚያውቀው እንደ ገና ምርመራ መደረጉ አይቀርም” ብለዋል።












